ረቂቅ አዋጁ ዜጎች ባላቸው ችሎታና አቅም በውጭ ሀገራት ሠርተው ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚያስችል ነው

– አቶ ተስፋዬ ንዋይ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ምክትል ሰብሳቢ ሆነው ተሾሙ

አዲስ አበባ፦ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዜጎች መብት፣ ክብር፣ ደህንነትና ጥቅምን በተሻለ መልኩ ሊያስጠብቅ ይችላል ተብሎ የታመነበትን የኢትዮጵያ የውጭ ሀገር ሥራ ስምሪት አዲስ ረቂቅ አዋጅን ለሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ መራ።አቶ ተስፋዬ ንዋይ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ምክትል ሰብሳቢ ሆነው ተሾሙ።

ምክር ቤቱ ትናንት ባካሄደው 6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 36ኛ መደበኛ ስብሰባው፤ የውጭ ሀገር ሥራ ስምሪት አዲስ ረቂቅ አዋጅ ላይ ተወያይቷል።አዋጁ ወደ ውጭ ሀገር በመጓዝ ለመሥራት ፍላጎት ያላቸውና ብቁ የሆኑ ኢትዮጵያውያን መብታቸው፣ ደህንነታቸውና ክብራቸው ተጠብቆ ባላቸው ችሎታና አቅም ሠርተው ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚያስችል መሆኑ ተጠቁሟል።

የኢትዮጵያ የውጭ ሀገር ሥራ ስምሪት ረቂቅ አዋጅ የመንግሥት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር)፤ ረቂቅ አዋጁ ስለሥራ ስምሪት አገልግሎት፣ ስለሥራ ሁኔታዎች መያዙን ተናግረዋል።

በኤጀንሲ ስለሚሰጡ የሥራ ስምሪት አገልግሎትና የኤጀንሲዎች ደረጃ፣ በኤጀንሲዎች የሚፈጸም ጥፋት እና የሚወሰዱ ርምጃዎችን እና ስለማህበራዊ ደህንነት የተመለከቱ ድንጋጌዎችን ማካተቱን ተስፋዬ በልጅጌ(ዶ/ር) አብራርተዋል።

ተስፋዬ(ዶ/ር) በማብራሪያቸው እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያውያን መብታቸው፣ ደህንነታቸውና ክብ ራቸው ተጠብቆ ባላቸው ችሎታና አቅም በውጭ ሀገራት ሠርተው ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማስቻል የቀድሞውን አዋጅ ማሻሻል አስፈላጊ ሆኗል።

በሀገር ውስጥ ምቹ የሥራ እድሎች የሚስፋፋበትን ሁኔታ ለመፍጠር መንግሥት የሚያደርገው ጥረት ተጠናክሮ መቀጠሉንም አስታውሰዋል።

የኢትዮጵያ የውጭ ሀገር ሥራ ስምሪት ቀደም ሲል ሲሠራበት የነበረው አዋጅ ቁጥር 923/2008 እንዲሁም ማሻሻያው አዋጅ ቁጥር 1246/2013 የተወሰኑ ጉዳዮችን ብቻ በማሻሻሉ ሕጎቹ የነበረባቸውን የሕግ፣ የአሠራርና የአደረጃጀት ክፍተት ተለይቶ በረቂቁ መመልከቱንም አንስተዋል።

ምክር ቤቱ የበኩሉን ሃሳብ አክሎበት ረቂቅ አዋጁ ለዝርዝር እይታ ወደሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ ተመርቶ ሪፖርትና የውሳኔ ሃሳብ እንዲቀርብበትም ጠይቀዋል።

የምክር ቤት አባላት በበኩላቸው፤ ረቂቁ የሚመ ራለት ቋሚ ኮሚቴ ዜጎች ለሥራ ስምሪት ወደ ውጭ ሀገር ሲሠማሩ የዓለምን የሥራ እድል ፈጠራ ታሳቢ ያደረገ የቴክኖሎጂ እና ስለሚሄዱበት ሀገር ግንዛቤ እንዲኖራቸው ማድረግ እንደሚገባ አሳስበዋል።

በውጭ ሀገር የሥራ ስምሪትን በተመለከተ በየሀገሩ ያሉ የኢትዮጵያ ኤምባሲዎች የዜጎች ክብር እና ጥቅም ተጠብቆ እንዲሠሩ የሚያደርግ ኃላፊነት በአዋጁ በግልጽ ሊቀመጥ እንደሚገባ ተናግረዋል።

ምክር ቤቱም አስተያየቶቹን ካደመጠ በኋላ ረቂቁን ለሰው ሀብት ልማት፣ ሥራ ስምሪት እና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ለዝርዝር ዕይታ በሙሉ ድምጽ መርቶታል፡፡

በተመሳሳይ ምክር ቤቱ የእፅዋት ጥበቃና ኳራንታይን ረቂቅ አዋጅን ለግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በሙሉ ድምጽ የመራ ሲሆን፤ በእዚህም የምክር ቤቱ አባል ደሳለኝ ጫኔ (ዶ/ር)፤ ረቂቅ አዋጁ የሚመራለት ቋሚ ኮሚቴ እንደ እምቦጭ ያሉ ወራሪ ተክሎች ወደ ሀገር ውስጥ እንዳይገቡ ከለላ በሚያደርግ መልኩ አዋጁን ሊያዘጋጅ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡

የረቂቁን ማብራሪያ የመንግሥት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ረቂቁ የዘመናዊ የእፅዋት ጥበቃ እና ኳራንታይን ለማዘመን፣ መጤ እና ወራሪ ተባዮችን ለመከላከል፣ በዘርፉ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ረቂቁ ትልቅ ፋይዳ እንዳለው አብራርተዋል፡፡

በሌላ በኩል ምክር ቤቱ አቶ ተስፋዬ ንዋይን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ምክትል ሰብሳቢ፣ አቶ ተክሊት ይመስል እና ወይዘሮ ነሲም አሊን የቦርዱ አመራሮች እንዲሆኑ ሾሟል።

ተሿሚዎቹ የቀጣይ ሀገራዊ ምርጫ ብዝሃነትና ታአማኒነት ባለው መልኩ ለማከናወን እንደሚሠሩ በምክር ቤቱ ፊት ቀርበው ቃለ-መሃላ ፈጽመዋል።ምክር ቤቱም ሹመቱን በሁለት ድምጸ- ተዓቅቦ እና በአብላጫ ድምጽ አጽድቆታል፡፡

በሳሙኤል ወንደሰን

አዲስ ዘመን ዓርብ ሰኔ 6 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You