ጫና፣ ጭቆና እና ቅኝ ግዛትን አሻፈረኝ በማለት በፈጸመችው ታላቅ ገድል የነፃነት ተምሳሌት የሆነችው ኢትዮጵያ፤ ይሄን ነፃነቷን በሙላት ከፍ አድርጋ ሁለንተናዊ ነፃነቷን እውን ከማድረግ አኳያ የኢኮኖሚ ነፃነቷን ማስጠበቅ በእጅጉ ያስፈልጋታል ፡፡
ሉዓላዊ ነፃነቷ ሙሉ ነው የሚባለው፤ ፖለቲካዊ ነፃነቷም እውን የሚሆነው፤ በኢኮኖሚው ረገድ ያላት አቅም ሲፈጥርላት ብቻ ነው፡፡ ይህ ካልሆነ ግን የኢኮኖሚው ጥገኝነት ከቴክኖሎጂው ጥገኝነት ጋር ተዳምሮ ነፃነት የሚለውን ትርጉም ጎዶሎ ያደርገዋል፡፡
ኢትዮጵያ ይሄን ከፍ ያለ የተጋድሎ የነፃነት ገጿን ወደላቀ የነፃነት ሰገነት ለማሸጋገር፤ ባለፉት ዓመታት ዘርፈ ብዙ ሥራዎችን አከናውናለች፡፡ በተለይ እንደ አገር የኢኮኖሚ እድገትን በማምጣት እና የቴክኖሎጂ አቅምን በመገንባት ረገድ ቀላል የማይባል ሥራ ሠርታለች ፡፡
የአስር ዓመት የኢኮኖሚ ልማት ፍኖተ ካርታ ተዘጋጅቶ ወደ ትግበራ ተገብቷል፤ የልማት ጉዞውን ሊደግፉ የሚችሉ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሥራዎችንም ተሰናስለው በመሠራት ላይ ናቸው፡፡ በግብርናው ዘርፍ እየተመዘገበ ያለው እመርታም ሆነ፤ በማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪው ዘርፍ እየታየ ያለው መነቃቃት የዚህ እውነታ አመላካቾች ናቸው፡፡
ይህ ውጤት ደግሞ ዝም ብሎ የተገኘ አይደለም፤ ይልቁንም የኢትዮጵያን ብልጽግና እውን ከማድረግ አኳያ ኢትዮጵያ በሁሉም ዘርፍ ከፍ ወዳለ የምርታማነት ደረጃ እንድትሸጋገር በእቅድ ተይዞ በመተግበሩ ነው ፡፡
ለአብነት የግብርናውን ዘርፍ በተመለከተ በአስር ዓመቱ የኢኮኖሚ ልማት እቅድ ላይ እንደተገለጸው፤ የግብርናው ዘርፍ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ በዘላቂነት ለማሳደግ ድርብርብ ሚና መጫወት ይጠበቅበታል።
በእቅድ ዘመኑ ዓመታትም የሀገሪቱን ሕዝብ የመመገብ፣ በመካከለኛ ጊዜ የሚያስፈልገውን የውጭ ምንዛሪ የማስገኘት፣ የመዋቅራዊ ሽግግርን እውን የማድረግ፣ ለኢንዱስትሪውና መሰል ዘርፎች በቂ ግብዓት የማቅረብን የመሳሰለ ኃላፊነት አለበት። ይሄን እውን ከማድረግ አኳያም የመስኖ አቅምን በማጎልበት የግብርናውን ዘርፍ ከዝናብ ጥገኝነት ማላቀቅ እና ሜካናይዜሽን አገልግሎትን ማስፋፋት ላይ በትኩረት ተሰርቷል፤
በዚህም በአንድ በኩል፣ ቆላማ በሆኑ አካባቢዎች ያለውን ሰፊ መሬት እና የውሃ ሃብት በመጠቀም፤ በሌላ በኩል በኩታ ገጠም ግብርና ላይ የተመሠረተ የሜካናይዜሽን ሥራን በማካሄድ ኢትዮጵያ እንደ ሀገር በስንዴ ልማት ዘርፍ ዓለማቀፍ ተሞክሮ የሚቀመርበት ውጤታማ ተግባር ማከናወን ችላለች፤ ስንዴን ከውጭ ማስገባቷ ቀርቶ ወደ ውጪ ለመላክ የቻለችበትን እድልም ፈጥሮላታል፡፡
ለዚህ ውጤት መገኘት የመንግሥት ከፍ ያለ ቁርጠኝነት ጉልህ ሚና ያለው ሲሆን፤ አርሶ አደሩ ከፍ ያለ መነሳሳት እንዲይዝ በማድረግ፤ ባለሃብቱ በዘርፉ ጉልህ ተሳትፎ እንዲኖረው በመደገፍ፤ የግብርና ግብዓቶች፣ የግብርና ቴክኖሎጂዎች፣ ማሽነሪዎችና ለግብርናው ዘርፍ እድገት ከፍ ያለ አበርክቶ ያላቸው ማናቸውም ነገሮች ከቀረጥና መሰል ጫናዎች ነፃ ሆነው ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገቡ የተደረገበት አሠራር የማይተካ ድርሻ ተወጥቷል፡፡
ይሄ ደግሞ “የሰጡትን ነው የሚሰጠው” ለሚባለው ግብርና በተሰጠው ልክ እንዲሰጥ እና ኢትዮጵያ የራሷን ፍላጎት ከመሸፈን አልፋ ትርፍ አምራች ሆና በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ ስንዴን ለውጪ ገበያ ለማቅረብ አስችሏታል፡፡ ለገበያ ብቻ ሳይሆን፤ በአሁኑ ወቅት በችግር ውስጥ ላሉት የሱዳን ሕዝቦች በኢትዮጵያን ኤይድ ዓርማ ኢትዮጵያ የሰብዓዊ ድጋፍ እነሆ የምትልበትን አቅም አደርጅቶላታል፡፡
በዚህ መልኩ በግብርናው ዘርፍ ያከናወነችው ተግባር እና የተገኘው ውጤት በማሳያነት ይነሳ እንጂ፤ ኢትዮጵያ የነፃነቷ እና የብልጽግናዋ ምሉዕነት ማረጋገጫ የሆነው የኢኮኖሚ ልማቷን እውን ከማድረግ አኳያ “ኢትዮጵያ ታምርት” በሚል መርሕ በአምራች ኢንዱስትሪውም መስክ ምርትና ምርታማነትን የማሳደግ ተግባራዊ ጉዞ ከተጀመረ አንድ ዓመት ተቆጥሯል፡፡
ይህን ተከትሎም በአምራች ዘርፉ ላይ ውጤቶች መታየት ጀምረዋል፡፡ በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ እየተከናወነ ያለውን ተግባር እና እየተገኘ ያለው ውጤት ከግብርናው ውጤታማነት ጋር ተሰናስሎ በሰሞኑ ሀገር አቀፍ ባዛር ላይ ዓለም በስፋት እንዲገነዘበው ማድረግ ተችሏል፡፡
ይሄ ደግሞ እንደ ሀገር ያለውን አቅም መለየት፣ አቅምን አመጋግቦ መጠቀም፣ የጎደለን ለይቶ መደመር እና ቁርጠኛ ሆኖ በኃላፊነት መሥራት ከተቻለ የኢትዮጵያ ልማትና ብልጽግና እውን መሆኑ እንደማይቀር አመላካች ነው፡፡
ለዚህ ደግሞ በግብርናው፣ በኢንዱስትሪው፣ በማዕድኑ፣ በቱሪዝሙ፣ በሳይንስና ቴክኖሎጂ የሚጠበቀው እድገት እንዲፋጠን ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ ይገባል ፤ ለኢኮኖሚ ልማቱ ግብ መሳካትም በሁሉም ዘርፎች ኢትዮጵያ ልታመርት የግድ ይላል!
አዲስ ዘመን ግንቦት 3/2015