መንግሥት በለውጡ ማግስት ዜጎች የተሻለ አገር ባለቤት እንዲሆኑ የጀመረው አገርን የማበልጸግ የልማት ውጥን ተጨባጭ እንዲሆን የአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ ስትራቴጂክ አቅም ነው። ዘርፉን ቀጣይነት ባለው ሁለንተናዊ መልኩ ማሳደግ ደግሞ ለነገ የማይባል ትልቁ አገራዊ የቤት ሥራ እንደሆነ ይታመናል።
የአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ አገራዊ ምርታማነትን ለማሳደግ፣ የሥራ ዕድል ለመፍጠር እና የቴክኖሎጂና የእውቀት ሽግግር ለማድረግ የሚኖረው አስተዋጽኦ የላቀ ከመሆኑ አንጻር፣ አሁን ላይ አገሪቱን እንደአገር እየተፈታተኗት ካሉ መልከ ብዙ ተግዳሮቶች / ፈተናዎች ሰፊው መውጫ መንገድ ሊሆን የሚችልም ነው።
እንደ አገር ዘርፉን ለማሳደግ ከ1950ዎቹ አ.ም ጀምሮ በአገር አቀፍ ደረጃ የታዩ መነሳሳቶች ቢኖሩም፤ በየወቅቱ የነበሩ መንግሥታቶች ሲከተሏቸው ከነበሩ የፖለቲካ እና ኢኮኖሚያዊ አስተሳሰቦች አኳያ የተጠበቀውን ያህል ውጤታማ መሆን አልተቻለም።
እንደ አገር አሁን ላይ ካለን ሰፊ የተፈጥሮ ሀብትና ብዛት ያለው አምራች የሰው ኃይል፤ በየዓለም አቀፉ የውጪ ኢንቨስትመንት ትኩረት እየሆንን ከመምጣታችን አንጻር፤ ሁሉንም ዕድሎች አቀናጅቶ በመጠቀም ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት ማምጣት እንደሚቻል ይታመናል።
ይህንን ተጨባጭ እውነታ ታሳቢ በማድረግም መንግሥት ለዘርፉ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ መንቀሳቀስ ከጀመረ ውሎ አድሯል፣ ለዚህም አንዱ ማሳያ የአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ የሚያስፈልገውን ሀብት በብድር የሚያገኝበትን ሁኔታ ለማመቻቸት እያደረገ ያለው ጥረት ነው።
መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፣ ዛሬ ላይ መንግሥታዊው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ከሚሰጣቸው ብድሮች መካከል 70 ከመቶ የሚሆነውን የሚሰጠው ለአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ ነው። በዚህ ተግባሩም እስከ ተያዘው በጀት ዓመት መጨረሻ ከ40 ቢሊዮን ብር በላይ ብድር ለመስጠት አቅዶ እስከ መጋቢት ወር ድረስ 21 ቢሊዮን ብር ሰጥቷል።
በእርግጥ ይህ በሌሎች ባንኮች በኩል ለዘርፉ እየተደረገ ያለውን ድጋፍ የሚገልፅ አይደለም፤ በአጠቃላይም አገሪቱ በዘርፉ ከሚያስፈልጋት ሀብት አንጻር ተጋንኖ የሚታይም አይሆንም፤ ነገር ግን አገር ትናንትና እና ዛሬ ላይ ካለችበት ተግዳሮት አንጻር መንግሥት ለዘርፉ የሰጠውን ትኩረት በተጨባጭ አመላካች ነው።
በጦርነት ኢኮኖሚ ውስጥ በምንገኝበት በዚህ ወቅት ይህንን ያህል ሀብት በዘርፉ የማፍሰሱ እውነታ፤ ጠባሳ ፈጥኖ በማከም ወደ አዲስ የታሪክ ምዕራፍ ለመግባት አንዱ ዕድል ቢሆንም፤ ሀብቱ በተፈለገለት ሁኔታ ሥራ ላይ ስለመዋሉ ግን ሰፊና ጠንካራ ክትትል የሚፈልግ ነው።
ከቀደሙት ተሞክሯችን ለመረዳት እንደምንችለው፤ መንግሥት በብድር በሚያቀርበው ፋይናንስ ዙሪያ ገና ብዙ ያልተሻገርናቸው ተግዳሮቶች ስለመኖራቸው ለጥያቄ የሚቀርብ አይደለም። ችግሮቹ የቱን ያህል ዋጋ እንዳስከፈሉንም የሚረሳ አይደለም።
ምክንያቱም ከለውጡ ቀድሞ ባለው አሠራር የሕዝብ ሀብት ባለቤትና ጠያቂ አጥቶ ፣ በአደባባይ ለከፋ ዘረፋ የተዳረገበትና ተጠያቂነት ትርጉም አልባ የነበረበት ሁኔታ ተፈጥሮ አገርና ሕዝብ ላልተገባ ኪሳራ ተዳርገዋል። በወቅቱ ብዙ ተስፋ የተጣለበት እና የትኩረት አቅጣጫ የነበረው የግብርናው ዘርፍም በዜሮ ድምር መቅረቱ ይታወሳል።
ይህ የትናንት የዜሮ ድምር የኪሳራ/የጥፋት መንገድ እንዳይደገም ከሁሉም በላይ መንግሥት ለዘርፉ በብድር እንዲቀርብ ያዘጋጀውን ሀብት የሚያስተዳድረው የልማት ባንክ የተሰጠውን ትልቅ ትውልድ ተሻጋሪ አገራዊ ኃላፊነት በስኬት መወጣት የሚያስችል ሁለንተናዊ ዝግጁነት መፍጠር ይጠበቅበታል።
በዘርፉ ለመሰማራት የሚፈልጉ ባለሀብቶችም ቢሆኑ የቀደሙት የአየር ባየር አስተሳሰቦች ከወለዷቸው የጥፋት አስተሳሰቦች ወጥተው ዘርፉ ከነሱ አልፎ አገርን ማበልጸግ የሚያስችል አቅም እንዳለው በአግባቡ ተረድተው ለራሳቸው ከዚያም አልፈው ለአገር ባለውለታ ለሚያደርጋቸው ለዚህ ትልቅ ኃላፊነት /አገራዊ ሸክም ራሳቸውን ማዘጋጀት ይኖርባቸዋል!።
አዲስ ዘመን ግንቦት 2/2015