ፍራንኮ ቫሉታ /Franco- Valuta/ ሕጋዊ ከሆነ ምንጭ የሚገኝ የውጭ ምንዛሬ ሲሆን የባንክ ቤት ፈቃድ(Bank Permit) ሳያስፈልገው ከውጭ አገር ዕቃ ለማስገባት የሚያስችል ፈቃድ ነው። የፍራንኮ ቫሉታ መብት ያላቸው አስመጪዎች ወደ አገር ውስጥ ለሚያስገቧቸው ምርቶች የውጭ ምንዛሬን በተመለከተ በብሔራዊ ባንክ የወጡ እና በንግድ ባንኮች የሚተገበሩ ጥብቅ መመሪያዎችን የማለፍ ግዴታ የለባቸውም። ይህም ማለት የውጭ ምንዛሬ ለማግኘት የባንክ ቤቶች ፍቃድ ሳያስፈልገው በፍራንኮ ቫሉታ የሚገቡ ምርቶችን ወደ አገር ውስጥ የማስገባት መብት ያገኛል ማለት ነው።
በኢትዮጵያ ያለምንም የውጭ ምንዛሬ ፈቃድ ምርቶችን ማስገባት በተለይ የገቢ ንግድን ለማሻሻል እና ለማረጋጋት በተለያዩ ጊዜያት ሲፈቀድ ተመልሶም ሲከለከል ቆይቷል:: ፍራንኮ ቫሉታ በአግባቡ ተግባራዊ ማድረግ ከተቻለ በተለይ የአገር ኢኮኖሚ ሲንገጫገጭና ግሽበት ሲከሰት ዋጋን ከማረጋጋት አንፃር ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ አለው::
ፍራንኮ ቫሉታ የዋጋ ግሽበትን ለመቀነስና የምርት አቅርቦትን ለመጨመር ይረዳል:: የአገር ውስጥ ፍላጎትና አቅርቦትም አለመመጣጠን በማስተካከል፤ የዋጋ ንረትን ለማረጋጋትና የምርት እጥረትን ለመቅረፍ ጊዜያዊም ቢሆን ጥሩ መፍትሄ ተደርጎ የሚታይ ነው::
የገንዘብ ሚኒስቴር ባሳለፍነው አመት እየተስተዋለ ያለውን የዋጋ ንረት ማረጋጋት እንዲቻልና መሠረታዊ የምግብ ሸቀጦች የሆኑት ዘይት፣ ስንዴ፣ ስኳር፣ የሕፃናት ወተት እና ሩዝ ያለምንም የውጭ ምንዛሬ ፍቃድ (በፍራንኮ ቫሉታ) በጉምሩክ ኮሚሽን በኩል በቀጥታ እንዲገቡ መወሰኑን ማሳወቁ ይታወሳል::
ውሳኔውም በርካታ የውጭ አገር የመኖሪያ ፈቃድ ያላቸው ኢትዮጵያውያን የዋጋ ንረት ለማረጋጋት የራሳቸውን ሚና መጫወት እንዲችሉ የፍራንኮ ቫሉታ በተፋጠነ ሁኔታ እንዲፈቀድላቸው ጥያቄ ማቅረባቸውን ተከትሎ የተላለፈ መሆኑ ታውቋል::
ቀረጥና ታክስን በሚመለከት በገንዘብ ሚኒስቴር በ22/3/2013 ዓ.ም በቁጥር ማአ.30/7/51 በተጻፈው ደብዳቤ መሠረት እንዲፈጸም ፤ አፈጻጸሙን በተመለከተ ጉዳዩ በሚመለከታቸው አካላት በኩል ጥብቅ ክትትልና ቁጥጥር እንዲደረግበትም አቅጣጫ ተሰጥቷል::
መንግሥት በከፍተኛ ወጪ በመግዛት በዝቅተኛ ዋጋ ለኅብረተሰቡ ከሚያቀርባቸው መሠረታዊ የምግብ ሸቀጦች በተጨማሪ በሌሎች አካላት የሚገባውን በማከል አቅርቦቱ በከፍተኛ ደረጃ ይጨምር ዘንድ ያለውጭ ምንዛሪ ሸቀጦችን የማስገባት አሠራር መፈቀዱ በአገሪቱ የሚስተዋለው የዋጋ ንረት ከዚህም በከፋ መልኩ እንዳይሰቀል ትልቅ አቅም መፍጠሩም የሚካድ አይደለም::
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከወር በፊት ለምክር ቤት በሰጡት ማብራሪያ ካነሷቸው ዋና ዋና ነጥቦች መካከልም ፍራንኮ ቫሉታ ጉዳይ አንደኛው ነው:: በወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትሩ መንግሥት እየተስተዋለ ያለውን የዋጋ ንረት ለማረጋጋት እንዲቻል በወሰነው ፍራንኮ ቫሉታ ከ10 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ማግኘት እየቻለ ማጣቱን ጠቁመዋል:: አንድ መታወቅ ያለበት ነገር ቢኖር መንግሥት ፍራንኮ ቫሉታን ባይተገብር በተለይ የዋጋ ግሽበት ከዚህም በላይ በመጨመር፣ መሠረታዊ የምግብ ሸቀጦች ዋጋ የማይቀመስ ደረጃ መድረሱ አያጠያይቅም::
ይሁንና ከፋይዳው ባሻገር የፍራንኮ ቫሉታው ውሳኔ ያላግባብ ጥቅም ላይ እንዳይውል መጠንቀቅ ያስፈልጋል:: የፈቃዱን ዓላማ ለማሳካት ሳይሆን የራሳቸውን ጥቅም ለማዳበር የሚፈልጉ ግለሰቦች ያላግባብ እንዳይጠቀሙበት ሂደቱ በጥብቅ ሥነ ምግባር ሊመራ ይገባል:: በፍራንኮ ቫሉታው ትግበራ ከሁሉ በላይ ጠንካራ ቁጥጥር እጅግ ወሳኝ ነው::
ምክንያቱ ደግሞ ፍራንኮ ቫሉታ አማራጭ መፍትሄ ከመሆኑ ባሻገር የራሱ የሆኑ ፈተናዎችን ይዞ የሚመጣ በመሆኑ ነው:: በትግበራ ወቅት ከቁጥጥር ጋር በተያያዘ በሚስተዋሉ ድክመቶችና በሚፈፀሙ ሕገ ወጥ ተግባራት አገር የሚያስፈልጋትና ወደ አገር የሚገባው የተለያየ ሊሆን ይችላል:: ተጠቃሚዎቹ እንጂ አገር የምትፈልገው ላይገባም የሚችልበት ዕድል ከፍተኛ ነው::
ተጠቃሚዎቹ ትርፍን ብቻ ታሳቢ በማድረግ የሚፈልጉትን ምርት ወደ አገር ውስጥ አስገቡ ማለት ደግሞ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የአገርን ኢኮኖሚ ይጎዳል:: ገበያ ላይ ያሉ በተለይ በአገር ውስጥ መመረት የሚችሉት ሳይቀር በዝቅተኛ ዋጋ የሚገቡ ከሆነ ደግሞ የአገር ውስጥ አምራቾችን ያደቃል:: በማደግ ላይ ያሉ ፋብሪካዎችን ያቀጭጫል::
ፍራንኮ ቫሉታ፣ በተለይ በተለይ የጥቁር ገበያን በማስፋፋት ረገድ ከባድ ተፅእኖ እንዳለውም እሙን ነው:: ከሁሉ በላይ በወንጀል የተገኘ ገንዘብንም በእግረ መንገድ ሕጋዊ ለማድረግ ዕድል ይሰጣል:: አሠራሩ ጥንቃቄ ካልተደረገበት ግለሰቦች በትይዩ ገበያ ገዝተው ያስቀመጡትን ወይም ያጠራቀሙትን የውጭ ምንዛሪ የሚያጥቡበት ወይም ሕጋዊ የሚያደርጉበት ሁኔታን ሊያመቻች ይችላል::
በፍራንኮ ቫሉታው ተጠቃሚ የሚሆኑ ግለሰቦች የውጭ ምንዛሪ ምንጭን ማሳወቅ እንደ ግዴታ መቀመጡ ተገቢ ቢሆንም፤ ብሔራዊ ባንክ ምንጩን የማረጋገጥ ግዴታ ተከታትሎ የማስፈጸም አቅሙ ደካማ ከሆነ መመሪያው አደገኛ መሣሪያ የመሆን ዕድል እንደሚኖረው እሙን ነው::
ከሁሉም በላይ መሠረታዊ የምግብ ሸቀጦች ያለ ውጭ ምንዛሪ ፈቃድ በቀጥታ እየተፈቀደ ወደ አገር ውስጥ እንዲገቡ በመወሰኑ ውጤቱ ታይቷል? ገበያውስ ተረጋግቷል? የሚለው መሠረታዊ ጥያቄ በየጊዜው መቃኘት የግድ ይላል:: አፈፃፀሙንም በየጊዜው በመከታተል የተፈለገውን ውጤት አምጥቷል፣ አላመጣም፣ የሚለውን መገምገም ያስፈልጋል:: ከዚህም ከፍ ሲል ውጤቱ እየታየ ማሻሻያዎች ካስፈለግ ተግባራዊ ማድረግ የግድ ይላል::
ከዚህ ባሻገር ወደ አገር ውስጥ የሚገቡት ምርቶች መንግሥት ፈቃድ የሰጣቸው ናቸው? አይደሉም የሚለውን ይበልጥ መከታተል ያስፈልጋል:: ይህን ኃላፊነትም የጉምሩክ ኮሚሽን ብሎም የንግድ ሚኒስቴርና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት በከፍተኛ ኃላፊነት መወጣት ይኖርባቸዋል::
ከሁሉ በላይ ፍራንኮ ቫሉታ በተወሰነ ጊዜ የተወሰነ ችግር እንዲፈታ እንጂ ለረጅም ጊዜ የሚሆን መፍትሄ አለመሆኑ፣ ጊዜያዊና ችግሮቹ ይበልጥ እንዳይባባሱ ማድረግን ታሳቢ ያደረገና ለአጭር ጊዜ የሚሆን ማስተንፈሻ መሆኑ ሊታወቅ ይገባል:: በተለይ የዋጋ ንረቱን ለማረጋጋት በአጭር ጊዜ እንጂ በዘላቂነት መፍትሄ አያመጣም::
በተለይ ከዕለት ዕለት እየተባባሰ የመጣውን ዋጋ ግሽበት ፈር ለማስያዝ ዘላቂው መፍትሄ የአገሪቱን መዋቅራቂ ኢኮኖሚ ኡደት ማስተካከል ነው:: በተለይ ፍላጎትና አቅርቦት ምጥጥን ልዩነቱን ለማስተካከል አገር ውስጥ በተሻለ ማምረት የሚችልበትን መንገድ መቀየስና ለዚህ ተግባራዊነትም ሌት ተቀን መትጋት የግድ ይላል::
በተለይም ከሰላም እና ጸጥታ ጋር ተያይዞ የሚነሱት ችግሮች ፈጣን እልባት መስጠት፣ ሎጂስቲክስና ሌሎች ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርጎ መሥራት፣ በቋሚነት የውጭ ምንዛሬ ግኝትን ማሳደግና ከውስጥ ፍላጎት አልፎም የውጭ ምንዛሬ ማስገባት የሚያስችሉ ዋና ዋና ምርቶችን በስፋት በአገር ውስጥ ማምረት ብሎም ለውጭ ገበያ ማቅረብ ታሳቢ ማድረግ ይገባል::
ታምራት ተስፋዬ
አዲስ ዘመን ግንቦት 2/2015