ከአዝናኝነት ባለፈ የአዕምሮ ማሰላሰልን ከሚጠይቁ ስፖርቶች መካከል አንዱ ቼስ ነው። ሰዎች በአብዛኛው ቼስን በዕለት ተዕለት በሚያደርጉት እንቅስቃሴ ጊዜያቸውን ለማሳለፍ ይጠቀሙበታል። በጨዋታው ውስጥ ያለው ሕግና ሂደት በሰው ልጅ ታሪክና የዕለት እንቅስቃሴ የተቃኘ በመሆኑ እጅጉን መሳጭ ነው። በተጫዋቾች መካከል የመፎካከርንና የአልሸነፍ ባይነትን ስሜት ያሰርጻል። በዚህም ምክንያት ቼስ ወደ ስፖርት ደረጃ ተሸጋግሮ በዓለም ዙርያ በመዘውተር ላይ ይገኛል።
የኢትዮጵያ ቼስ ፌዴሬሽንም ይህንኑ የስፖርቱን መልካም አጋጣሚ ለስዕብና ግንባታ በመጠቀም አርአያ መሆን ችሏል። ስፖርቱ ከስፖርትነቱ ባለፈ ኅብረተሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግም ከትምህርት ሚኒስቴር፣ ከክልሎችና ከተማ መስተዳድሮች ጋር በመቀናጀት ሥልጠናዎችን በማዘጋጀት እየሰጠ ይገኛል። በቅርቡም ስፖርቱን ለማስፋፋት እና ማህበረሰብ ተኮር ለማድረግ በትልልቅ ስፖርተኞች ላይ ብቻ ሳይገደብ በማህበራዊ ተቋማት ላይ አትኩሮ ለመሥራት እቅድ ይዟል። በዚህም መሠረት ከፌዴራል ማረሚያ ቤቶች ጋር በመቀናጀት ሥልጠና ለመስጠት ዝግጅት አጠናቋል።
በዓለም አቀፉ ወረርሽኝ ኮቪድ 19 ምክንያት ከመቋረጡ በፊትም በተመረጡ ትምህርት ቤቶች ባለሙያ በመመደብ ከትምህርት ሰዓት ውጪ ሥልጠና ለመስጠት ተሞክሯል። ለተማሪዎቹ ቼስን በማዘውተር የሚያገኙትን ጥቅም በማስረዳት ትኩረት እንዲሰጡት ለማድረግ ተሞክሯል። ቼስ የጨዋታው ሂደት በራሱ ሰላማዊ ትግልን የሚያሳይ በመሆኑ፤ ለተሰለፉበት ዓላማ እንዴት ውጤታማ መሆን ይቻላል የሚለውን መፍትሔ የሚያመጣም ጭምር ነው።
በኢትዮጵያ የቼስ ፌዴሬሽን ባለሙያ የሆኑት ወይዘሮ የዝና ሙኔ፤ የቼዝ ስፖርት ለስዕብና ግንባታ ጉልህ ሚናን ስለሚጫወት ቢሠራበት ጠቃሚ መሆኑን ያስረዳሉ። ኅብረተሰቡ ቼስን እንደ መዝናኛ እና የትርፍ ጊዜ ሥራ ሳይሆን እንደ ስፖርት ለምዶት ቀለል ባለ ሁኔታ እንዲያዘወትረው የማስተዋወቅና የማስረጽ ሥራዎች ተከናውነዋል። የቼስ ስፖርት ሥልጠና ለወጣት ታራሚዎችም በመስጠት ላይ ሲሆን፤ በቀጣይም ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል። ሥልጠናውን ያገኙትም ታዳጊ ታራሚዎችም የስብዕና ለውጥ ማሳየት ችለዋል። በጎዳና ሕይወት ለሚኖሩና በተለያዩ ሱሶች ተጠምደው ለሚገኙ ወጣቶችም በተሰጠው ሥልጠና ከፍተኛ ለውጥ በመገኘቱ በስብዕና ግንባታ ያለው ሚና ከፍተኛ ሆኖ ተገኝቷል። በዚህም መሠረት በስብዕና ግንባታ ላይ በመሥራት አገር ተረካቢ የሆኑትን ወጣቶች በማነጽ ረገድ የኢትዮጵያ ቼስ ስፖርት ፌዴሬሽን የድርሻውን እንደተወጣ ያስረዳሉ።
የቼዝ ስፖርት ፈጣንና ቅጽበታዊ የጨዋታ ዓይነቶች ሲኖሩት፤ እነሱንም ለማህበረሰቡ በማስተዋወቅ እንዲሁም ውድድር ተዘጋጅቶ ብዙዎችን ተሳታፊ ባደረገ መልኩ ማካሄድ ችሏል። በዘንድሮ ዓመትም የ‹‹ራፒድ እና ቢሊቲዝ›› የሚባሉ ፈጣን የቼስ ቻምፒዮናዎች ተካሂደዋል። በቀጣይም የማስተዋወቁ ሥራ ተጠናክሮ የሚቀጥል ሲሆን፤ ክለቦችን እና ቡድኖችን ለማበረታታት ውድድር የሚዘጋጅ ይሆናል።
ፌዴሬሽኑ ከአገር አቀፍ ውድድሮች ባለፈ ብሔራዊ ቡድኑን በ2015 ዓ.ም መጀመሪያ በሕንድ በተዘጋጀው የቼስ ኦሊምፒያድ በማሳተፍ አበረታች ፉክክር አድርጎ መመለስ ችሏል። ዓመታዊ ቻምፒዮናዎችንም ሳያቋርጥ አካሂዷል። በዚህም መሠረት ሦስት ቻምፒዮናዎችን ጨምሮ፣ የታዳጊዎች እንዲሁም ከ20 ዓመት በታች የክልሎች ቻምፒዮናን በቅርቡ አከናውኗል። በተጨማሪም የ2015 ለሁሉም ክፍት የሆነ የግል የበላይነት ቻምፒዮናን አዘጋጅቶ በስኬት ማጠናቀቅ ችሏል። በውድድሩም በቅርቡ ለሚካሄደው ዞናል ቻምፒዮና እና ለመላው አፍሪካ የቼስ ቻምፒዮና ብሔራዊ ቡድንን የሚወክሉ ተወዳዳሪዎች ተመርጠውበታል።
ይህንኑ ሥራ አጠናክሮ ለማስቀጠልም የተለያዩ እንቅስቃሴዎች እየተደረጉ መሆኑን ባለሙያዋ ይገልጻሉ። ስፖርቱ ሰፊ ቦታን የማይፈልግ ቢሆንም፤ ሰፊ ሀብት ግን ይጠይቃል። ምክንያቱ ደግሞ ብዙ መሣሪያዎቹ አገር ውስጥ በቀላሉ ባለመመረታቸው ነው። ይኸውም ስፖርቱን ለማስፋፋት አዳጋች አድርጎታል። ስፖርት የሕዝብ እንደመሆኑ ስፖርቱን ሕዝባዊ ለማድረግ ጅምር ሥራዎች በመሠራት ላይ ናቸው። ፌዴሬሽኑ በአሁኑ ወቅት በመንግሥት በጀት እየተዳደረ የሚገኝ ሲሆን እራሱን ለመቻል በርካታ እንቅስቃሴዎችን በማድረግ ላይ ይገኛል። ድጋፍ አድራጊዎችን፣ የግል ባለሀብቶችን ዓለምአቀፍ ለጋሾችን የማስተባበር ሥራዎች እየተከናወኑም ይገኛሉ። በቀጣይም እነዚህን አጠናክሮ በመቀጠል ስፖርቱን ማስፋፋትና ለስፖርቱ አስፈላጊ የሆኑ ቁሳቁሶችን በሀገር ውስጥ እንዲመረቱ ለማስቻል መታሰቡንም ባለሙያዋ ጠቁመዋል።
አለማየሁ ግዛው
አዲስ ዘመን ግንቦት 1/2015