ፍሬ አልባው የዋሊያዎቹ የአፍሪካ ዋንጫ የማጣሪያ ጉዞ

በሞሮኮ አስተናጋጅነት ከዓመት በኋላ ታህሳስ ወር ላይ ለሚካሄደው 35ኛ የአፍሪካ ዋንጫ 48 ሀገራት በ12 ምድቦች ተከፍለው የማጣሪያ ውድድራቸውን ሲያደርጉ ቆይተዋል:: ለ2025 የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታዎች ተጠናቀው 24ቱ ተሳታፊ ሀገራት ተለይተዋል:: ኢትዮጵያም ካደረገቻቸው አምስት የማጣሪያ ጨዋታዎች በኋላ የአህጉሪቱ ትልቅ ውድድር ላይ እንደማትሳተፍ አረጋግጣለች:: ዋልያዎቹ የምድቡን ስድስተኛ ጨዋታ ከትናንት በስቲያ ቀደም ብላ ማለፏን ካረጋገጠችው ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ጋር አድርገው 2ለ1 በማሸነፍ በማጣሪያው የመጀመሪያ ድል አስመዝግበዋል::

ዋልያዎቹ በምድቡ የመጨረሻ ጨዋታ ያስመዘገቡት ድል ወደ አፍሪካ ዋንጫው ለማቅናት ምንም ጥቅም ባይኖረውም ቡድኑ ከበርካታ ጨዋታዎች በኋላ ወደ አሸናፊነት የተመለሰበት ሆኗል:: ይህም ቡድኑ በቀጣይ በሚያደርጋቸው የቻን አፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታዎች ላይ ተነሳሽነት ሊፈጥርለት ይችላል ተብሎ ይጠበቃል:: የዋሊያዎቹን የአሸናፊነት ግቦች በረከት ደስታ በ36ኛ ደቂቃና መሐመድኑር ናስር መደበኛው የጨዋታ ሰዓት ተጠናቆ በተጨመረው 93ኛ ደቂቃ ከመረብ አሳርፈዋል:: የኮንጎን ብቸኛ ግብ ደግሞ፣ ድይላን ባቱቢንሲካ አስቆጥሯል::

ኢትዮጵያ ከዲሞክራቲክ ኮንጎ፣ ታንዛኒያና ጊኒ በምድብ ስድስት ተደልድላ ውድድሯን ያካሄደች ሲሆን፤ በስድስት ጨዋታዎች አንድ አሸንፋ፣ አንድ አቻ ወጥታ በአራት ጨዋታዎች ተረታ በአራት ነጥብና በ9 የግብ እዳዎች የምድቡን ግርጌ ይዛ ተሰናብታለች:: የመጀመሪያዎቹን አራት የማጣሪያ ጨዋታዎች በአሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ የመጨረሻዎቹን ሁለት ጨዋታዎች ደግሞ በአሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ መሪነት የተጫወቱት ዋልያዎቹ ከ2021 የአፍሪካ ዋንጫ በኋላ ለተከታታይ ሁለት የአፍሪካ ዋንጫዎች ሳያልፉ ቀርተዋል::

ዋሊያዎቹ በአሰልጣኝ ገብረመድህን እየተመሩ ካካሄዱት አራት ጨዋታ በሶስቱ ሽንፈት ሲገጥማቸው በአንዱ ነጥብ ተጋርተዋል:: በነዚህ ጨዋታዎችም ከትርጉም አልባ የሜዳ ላይ ቅብብል ባሻገር ቶሎ ቶሎ ወደ ተጋጣሚ ሜዳ መድረስና የጎል እድሎችን መፍጠር ሲቸገሩም ነበር:: የተጫዋቾቹ ቴክኒክ፣ ታክቲክ፣ የአካል ብቃት፣ ስነልቦናዊ ጥንካሬ ማጣትና የሜዳ ላይ ቅንጅት መጥፋትም ብዙ ትችት ያስተናገደ ሆኗል::

ዋልያዎቹ በአሰልጣኝ ገብረመድን እየተመሩ የመጀመሪያ ጨዋታቸውን ከታንዛኒያ ጋር አድርገው ያለምንም ግብ አቻ ሲለያዩ፣ ሁለተኛውን ጨዋታ በኮንጎ 2 ለምንም ተረተዋል:: ሦስተኛና አራተኛ ጨዋታቸውን በተከታታይ ከጊኒ ብሔራዊ ቡድን ጋር አድርገውም በሁለቱ ጨዋታዎች በድምሩ 7 ጎሎችን አስተናግደው ተሸንፈዋል:: በዚህም አሰልጣኙ የኮንትራት ውላቸው በመጠናቀቁ ኃላፊነታቸውን ለአዲሱ ጊዜያዊ ዋና አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ አስረክበዋል::

የዋሊያዎቹ ወደ አፍሪካ ዋንጫ የማለፍ ተስፋ ሳይሟጠጥ ቡድኑን የተረከቡት አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ፣ ሁለት ጨዋታዎችን በመምራት የአፍሪካ ዋንጫ ጉዞው ሳይሳካላቸው ቀርቷል:: አሰልጣኙ በአስራ አንደኛው ሰዓት ብሔራዊ ቡድኑን ከነበረበት የመቀዛቀዝ ስሜት ለማውጣት ጥረት አድርገዋል:: በስነ ልቦና፣ በቴክኒክና ታክቲክ ግንዛቤ ችግርና በአካል ብቃት መውረድ ውስጥ የሚገኙ ተጫዋቾችን አነቃቅተው ለመጫወትም ሞክረዋል:: ይሁን እንጂ ከታንዛኒያ ጋር የምድቡን አምስተኛ ጨዋታ አከናውነው 2 ለምንም መሸነፋቸው በጊዜ ከአፍሪካ ዋንጫው እንዲሰናበቱ አድርጓል:: በቀናት ልዩነት ከኮንጎ ጋር የመጨረሻ ጨዋታውን አድርጎ ግን የመጀመሪያውን ሦስት ነጥብ አሳክቷል::

የአፍሪካ ዋንጫን ከመሰረቱት ሦስት ሀገራት ሁለቱ (ግብፅና ሱዳን) ወደ ትልቁ መድረክ ማለፋቸውን ሲያረጋግጡ፤ ኢትዮጵያ ዳግም አልተሳካላትም:: ግብፅ ምድቧን በበላይነት እየመራች ነው ወደ አፍሪካ ዋንጫው ማለፏን ያረጋገጠችው:: በእርስ በርስ ጦርነት እየታመሰች የምትገኘው ሱዳን በሜዳዋ አንድም ጨዋታ ሳታደርግ ከምድቧ ሁለተኛ ሆና ለአፍሪካ ዋንጫ መብቃቷ ያልተጠበቀ ነው::

ከምስራቅ አፍሪካ ሦስት ሀገራት (ሱዳን፣ ዩጋንዳ እና ታንዛኒያ) 35ኛ የሞሮኮ አፍሪካ ዋንጫ ማለፋቸውን ያረጋገጡ ሀገራት ናቸው:: ኢትዮጵያና ሱዳን በ2021 የአፍሪካ ዋንጫ ተሳታፊ የነበሩ ሲሆን፣ ሱዳን ከአንድ የአፍሪካ ዋንጫ በኋላ ስትመለስ ኢትዮጵያ ለሁለተኛ ጊዜ ሳትሳተፍ መቅረቷ ብዙዎችን አስቆጭቷል:: እግር ኳሳቸው ደካማና ብዙ ገንዘብ የማይወጣበት እንደነ ኮሞሮስ፣ ቤኒን፣ ሱዳን፣ ዚምባብዌና ታንዛኒያን የመሳሰሉ ሀገራት ለትልቁ የአህጉሪቱ መድረክ ሲበቁ ብዙ ገንዘብ የሚፈስበት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ዛሬም የቁልቁለት ጉዞ ላይ መገኘቱ የስፖርት ቤተሰቡን አሳዝኗል::

35ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ውድድር እአአ ከታህሳስ 21/2025 እስከ ጥር 18/2026 በስድስት ከተሞች በሚገኙ ስታድየሞች የሚካሄድ ይሆናል::

ዓለማየሁ ግዛው

 አዲስ ዘመን ህዳር 12/2017 ዓ.ም

 

 

Recommended For You