‹‹ኮንጎን በሜዳዋ ካሸነፍን ሌላውን የማናሸንፍበት ምክኒያት የለም››-አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን(ዋልያዎቹ) ለ2025 የሞሮኮ አፍሪካ ዋንጫ ለመሳተፍ ከምድብ ማጣሪያ መውደቁን ቀደም ብሎ ማረጋገጡ ይታወቃል። ዋልያዎቹ በምድብ ስድስት ከዲሞክራቲክ ኮንጎ፣ ጊኒና ታንዛኒያ ጋር ተደልድለው ባደረጓቸው ስድስት የማጣሪያ ጨዋታዎች በአራቱ ተሸንፈው አንዱን በማሸነፍ አንዱን ደግሞ አቻ በመለያየት ወደ አፍሪካ ዋንጫው የሚያደርጉት ጉዞ ተቋጭቷል።

ይህንንም ተከትሎ በመጨረሻዎቹ ሁለት የማጣሪያ ጨዋታዎች ጊዜያዊ ዋና አሰልጣኝ ሆነው ቡድኑን የመሩት አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ ትናንት ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡ ዋልያዎቹን ከአሰልጣኝ ገብረመድህን ሀይሌ ተረክበው ካደረጋቸው ሁለት ጨዋታዎች አንዱ አሸንፈው በአንዱ የተሸነፉት አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ፣ በምድብ ማጣሪያው ቀዳሚ ሆና ያለፈችው ኮንጎን በሜዳዋ 2ለ1 አሸንፈው በታንዛኒያ ደግሞ 2ለ0 ተሸንፈዋል፡፡

በመጨረሻው የማጣሪያ ጨዋታ ባለፈው ማክሰኞ ምሽት ጠንካራዋን ኮንጎ ቀደም ብላ ወደ አፍሪካ ዋንጫ ማለፋን ብታረጋግጥም ዋልያዎቹ ማሸነፋቸው ያልተጠበቀ ነበር፡፡ አሰልጣኝ መሳይ ይህንን ድል በተመለከተ ‹‹ይህ ድል ለእኔም ለተጫዋቾቹም ትርጉም አለውና ማስቀጠል አለብን፣ ኮንጎን ሜዳው ላይ አሸንፈን ከወጣን ሌላውን የማናሸንፍበት ምክኒያት የለም፣ ፈተናው ቀላ አይደለም፣ ያምሆኖ ነገ ከነገ ወዲያ ከሌላው ጋር ተፎካካሪና አሸናፊ የምንሆንበትን ነገር መፍጠር እንችላለን፡፡›› በማለት ተናግረዋል፡፡

አሰልጣኙ ኮንጎን ስላሸነፉበት ጨዋታ ሲያብራሩ፣ ‹‹ለተጋጣሚዎቻችን ተገቢ ያልሆነ የተጋነነ ግምት እንደምንሰጥ እረዳለሁ፡፡ ፕሮፌሽናል ናቸው፣ ከእኛ በአካል ብቃትም ይበልጣሉ ወዘተ የሚሉ ተገቢ ያልሆኑ በራስ መተማመን እንዳይኖረን የሚያደርጉ አስተሳሰቦች አሉ፡፡ ይህን ለማስቀረትና እኛ እነሱን የምንበልጥባቸው ነገሮች እንዳሉ ለማሳየት ተሞክራል፡፡ ማሸነፍ የምንችልባቸው ነገሮች ላይ ተነጋግረናል፡፡ ግቦች ከተቆጠሩብን በሀላ ሳይሆን በሙሉ የጨዋታ ጊዜ ማጥቃትና ማሸነፍ እንችላለን ብለን ወደ ሜዳ ገብተናል›› ብለዋል፡፡

የዋልያዎቹ ከጨዋታ አስቀድሞ አላስፈላጊና ልክ ያልሆነ ፍርሃት ሊቀር እንደሚገባ የገለፁት አሰልጣኝ መሳይ፣ በቴክኒክ፣ ታክቲክና አካል ብቃት ላይ በደንብ መዘጋጀት እንዲሁም ስለራሳችንና ተጋጣሚያችን ጠንቅቀን ማወቅ የሚፈጥረው የስነ-ልቦና ጥንካሬ እንዳለ ባስረዱበት መግለጫ፣  ቡድናቸው ኮንጎን ለማሸነፍ  በተጫዋቾቻቸው ላይ የነበረው ተነሳሽነት ትልቅ እንደነበረ አስታውሰዋል፡፡

የመጨረሻዎቹን ሁለት ጨዋታዎች በድል ለመወጣት ተጫዋቾች የቻሉትን እንዳደረጉ ገልፀው፣ በታንዛኒያው ጨዋታ ድል ባይቀናቸውም ኮንጎን በተለይም ከረጅም ጊዜ በኋላ ማሸነፉ ትልቅ ትርጉም እንዳለው አብራርተዋል፡፡ ‹‹ወደ አፍሪካ ዋንጫ እንደማናልፍ ቀደም ብለን ብናረጋግጥም የክብር ጉዳይ ነው፣ የወዳጅነት ጨዋታም ቢሆን በደረጃችን ላይ የሚፈጥረው ልዩነት አለ›› ሲሉም ገፀዋል፡፡

አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ በጊዜያዊ ዋና አሰልጣኝነት ዋልያዎቹን በመምራት በሀገር ውስጥ ሊጎች ብቻ የሚጫወቱ ተጫዋቾች የሚሳተፉበት የአፍሪካ ዋንጫ(ቻን) ማጣሪያ ጨዋታዎችን ያደርጋሉ፡፡  በዚህ ማጣሪያ ወደ አፍሪካ ዋንጫ ካለፈችው ከሱዳን ጋርም ይገናኛሉ፡፡ ለዚህ ጨዋታም ለዋልያዎቹ በተለይ የአካል ብቃት፣ ስነ-ልቦና እና ቪዲዮ ትንተና ባለሙያዎች አስፈላጊ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

እንደ አሰልጣኙ ገለፃ፣ በአፍሪካ ዋንጫው ማጣሪያ ጨዋታ የመረጣቸው ተጫዋቾች ቻንን ታሳቢ ባደረገ መልኩ ነው፡፡ ወጣት ተጫዋቾች ቡድኑን ተቀላቅለዋል፣ እነዚህን ልምድ ካላቸው ጋር በማጣመር ለቻን ውድድር ለማለፍም ይጫወታሉ፡፡ ለዚህም ‹‹አሁን ያለውን ሞራል ከሚመለከተው ጋር ተባብረን ማስቀጠል አለብን፡፡ ክብሩ የሀገር ነው፣ ድል የሚመጣው የብዙ ሰዎች ድምር ሲኖር ነው፡፡›› ብለዋል፡፡

በፌዴሬሽኑ በኩል ከበጀት አንፃር የተለያዩ ፈተናዎች ሊኖሩ እንደሚችሉ ስጋታቸውን የገለፁት አሰልጣኝ መሳይ፣ ያምሆኖ የአሰልጣኝ ቡድን አባላት መጠናከር አለበት ባይ ናቸው፡፡ ምንም አይነት ጥቃቅን ክፍተቶች መኖር እንደሌለባቸውና የዘመኑ እግር ካስ የሚፈልገውም ይሄንኑ እንደሆነ በመግለጫቸው ተናግረዋል፡፡

ቦጋለ አበበ

አዲስ ዘመን ዓርብ ኅዳር 13 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You