የትምህርት ሚኒስቴር በዚህ ዓመት የዩኒቨርሲቲ መውጫ ፈተና እንደሚሰጥ አስታውቋል:: መውጫ ፈተናው ተማሪዎች በሰለጠኑባቸው የሙያ ዘርፎች ብቁ መሆናቸውን ለማረጋገጥ የሚያስችል እንደሆነ ተነግሯል:: ፈተናው በኦንላይን ለሁሉም የመንግሥት ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የሚሰጥ ሲሆን፣ ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው የሚጠቀሙባቸውን እውቀት፣ ክህሎትና አመለካከት በብቃት መያዛቸውን መለኪያ መሆኑንም ሚኒስቴሩ አመልክቷል::
የመውጫ ፈተናው፣ ዩኒቨርሲቲዎች በትምህርት አሰጣጥ ላይ ያሉበትን ሁኔታ በማሳየት የትምህርት ጥራትን በማስጠበቅ እንዲሠሩ የሚያደርግ መሆኑንም ሚኒስቴሩ ጠቅሶ፤ ፈተናው በትምህርት ዘርፍ ጥራትን ለማረጋገጥና በተቋማት ግንባታ ሂደት ውስጥ ብቁና ንቁ የሰው ኃይል እንዲኖር በማድረግ የሚጫወተው ሚና የጎላ እንደሆነም አስረድቷል::
የመውጫ ፈተና መሰጠቱን በአዎንታዊ የተቀበሉ እንዳሉ የሚታወቅ ሲሆን፣ ጥቂቶች ደግሞ በተለይ ብዙ ዝግጅት እና ጥናት ሳይደረግበት ወደ ትግበራ የመጣ በመሆኑ ውጤታማነቱ እምብዛም ነው የሚሉ አልታጡም::
በዚህ ጉዳይ ሰፊ ማብራሪያ የሰጡን የፖሊሲ ጥናት አማካሪ እና በትምህርት ሚኒስቴር የከፍተኛ ትምህርት ጥራት እና ብቃት ማሻሻያ ዴስክ ኃላፊ አቶ ሰይድ መሐመድ ናቸው:: እርሳቸው እንደሚናገሩት፤ የመውጫ ፈተና በዓለም አቀፍ ደረጃም ይሁን በኢትዮጵያ የመጀመሪያ አይደለም:: ከዚህ በፊት የተለያዩ ልምዶች ያሉ ሲሆን፣ ተሞክሮውም የሚያሳየው ከጊዜ ወደ ጊዜ የተማሪዎች ውጤታማነት እየተሻሻለ፣ እያደገ እንደሚመጣ እና የትምህርት ጥራቱም እየተጠበቀ መሆኑን ነው::
የመውጫ ፈተና አላማ አድርጎ የሚሰጠው በአንድ የትምህርት መስክ የሚመረቁ ተማሪዎች ሲመረቁ ሊኖራቸው የሚገባው ብቃት ምንድን ነው የሚለውን ለመለካት ነው:: ከዚህ ጎን ለጎን ተማሪዎች በሚመረቁት የትምህርት መስክ ገበያው ምን ዓይነት ብቃት እንዲኖራቸው ይፈልጋል በሚል የገበያውን ፍላጎት መሠረት ባደረገ መልኩ ስለሚዘጋጅ ለገበያው ብቁ ናቸው ወይስ አይደሉም የሚለውንም ለመለካት የሚያስችል ነው:: ስለዚህ ከዚህ አንፃር የትምህርት ጥራት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ እንዲመጣ ያደርጋል::
እኛ አገር ባለው ልምድ በሕግ ትምህርት እና በጤና የሙያ መስክ ለሚመረቁ ተማሪዎች እየተሰጠ ያለው የመውጫ ፈተና መጀመሪያ አካባቢ እና አሁን ላይ ያለው የማለፍ ምጣኔ የተለያየ ነው የሚሉት ኃላፊው፣ ስለዚህ ከጊዜ ወደ ጊዜ ፈተናውን የሚያልፉ ተማሪዎች ቁጥር ከፍ እያለ እየመጣ እንደሆነ ያሳያል ሲሉ ይናገራሉ::
ኃላፊው እንደሚናገሩት፤ የመውጫ ፈተና ጉዳይ ድንገት የመጣ አይደለም:: የከፍተኛ ትምህርት አዋጅ ቁጥር 1152/2011 ከዛሬ አራት አምስት አመት በፊት የተዘጋጀ አዋጅ ነው:: በዚህ አዋጅ ላይ የመውጫ ፈተና በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተግባራዊ እንደሚደረግ ተቀምጧል:: በተጨማሪም ባለፈው አመት የመውጫ ፈተና መመሪያ ተብሎ መመሪያ ቁጥር 919/2014 በሚል በ2014 ዓ.ም የፀደቀ መመሪያም አለ:: ስለዚህ ይህ መመሪያ ራሱ ከአመት በፊት ፀድቆ ወደ ሥራ የገባበት ሁኔታ መኖሩ የሚዘነጋ አይደለም:: በመሆኑም ፈተናው በድንገት በዘንድሮ ተመራቂ ተማሪዎች ላይ የተከሰተ አለመሆኑ ማሳያ ነው::
በተመሳሳይ ደግሞ ሁሉም ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሚያውቁት በትምህርት ሚኒስቴር ተዘጋጅቶ የተሰራጨ ሰነድ አለ:: የ15 ወራት የትግበራ ሰነድ ከባለፈው አመት ከሚያዝያ ወር ጀምሮ እስከ ሰኔ ወር 2015 ዓ.ም ድረስ የመውጫ ፈተና ለተማሪዎች ለመስጠትና ተማሪዎችን ውጤታማ ለማድረግ ምን ምን ሥራዎች ይሠራሉ? ምን ዓይነት ውጤት ይጠበቅባቸዋል? ማን ያከናውናቸዋል? መቼ ይከናወናሉ? የሚለውን የሚያሳይ የትግበራ እቅድ ተዘጋጅቶ ለሁሉም ተቋማት ተልኳል:: ስለዚህ እነዚህን ዝግጅቶች ስናይ ለሥራው መሳካት በተጠናከረ መልኩ ስለመሠራቱ ማረጋገጫ ነው ብለዋል::
ሂደቱ እየተከናወነ ያለው ፍትሃዊና ግልፅነት የሰፈነበት እንዲሆን የፈተና አሰጣጡ የብዙ ባለድርሻ አካላት ሚና በሚኖርበት መልኩ ነው:: መመሪያው ተዘጋጅቶ የፀደቀው ከዝግጅቱ ጀምሮ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ምሁራን፣ የሙያ ማህበራት፣ የተማሪ ህብረት ተወካዮች ሁሉ እንዲወያዩበት ብሎም እንዲሳተፉበት ተደርጎ ነው:: በሌላ በኩል ለፍትሃዊነቱ በመንግሥት እና በግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ የሚማሩ ተማሪዎች ፈተናውን በተመለከተ ተመሳሳይ መረጃ እንዲኖራቸው ማድረግ እንዲሁም ሁሉም ተማሪዎች ፈተናውን ለመሥራት የሚያስችላቸውን አቅም እንዲያዳብሩ የማድረግ ሥራ መሥራት ነው:: ለዚህም እንደ ትምህርት ሚኒስቴር እየሠራን ነው፤ የግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት አመራሮችን እና ባለሀብቶችን ጨምሮ በየጊዜው በመገናኘት ተማሪዎችም የተዘጋጀው ፈተና መሠረት አድርገው እንዲያዘጋጁ ከሁሉም ተቋማት ጋር በመግባባት እየተሠራ ነው ብለዋል::
አቶ ሰይድ እንዳሉት፤ በአንድ የትምህርት መስክ የሚመረቁ ተማሪዎች የሚወስዱት ተመሳሳይ ጥያቄ ነው:: ጥያቄዎቹም የመማሪያ መስኮችን ታሳቢ ያደረጉ ናቸው:: ተመሳሳይ ብቃት ስለሚጠበቅ ተመሳሳይ ጥያቄ ነው የሚፈተኑት:: ከግል ለተመረቀ እና ከመንግሥት ለተመረቀ ተብሎ የሚለይበት ሁኔታ የለም:: በመደበኛ ትምህርት ለሚማር እና መደበኛ ባልሆነ በርቀት ለሚማር የመደበኛው ከፍ ይበል የርቀቱ ዝቅ ይበል የሚባል ነገር የለም:: ሁሉም ተማሪዎች በትንሹ ገበያው የሚፈልገውን ብቃት ያሟሉ ሆነው መውጣት አለባቸው:: ስለዚህ ከዚህ አንፃር በተለየ ውድድር እና ብቃት የሚዘጋጅበት ሁኔታ የለም:: በመሆኑም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎቻቸውን በአግባቡ የማብቃት እና የማዘጋጀት የቤት ሥራ ይኖርባቸዋል::
የተቋማት ዝግጁነትን በተመለከተ፤ አሁን ባለው ሁኔታ ብዙዎቹ ተቀብለውታል:: በሆነ ወቅት ግን የሚቃወሙ አካላት፣ ተቋማትም እንዲሁም መምህራን አካባቢ፣ ተማሪዎችም ዘንድ ይታይ ነበር:: የመቃወሙ ነገር በርግጥ አንድ አዲስ ነገር ወይም ሥራ ወደ ተግባር ሲመጣ የሚታይ ዓይነት ነውና የሚጠበቅ ነበር:: አሁን ግን ፈተናው የማይቀር መሆኑን ብዙዎቹ ተረድተው ተማሪዎች ለመውጫ ፈተና የመዘጋጀት የቤት ሥራ ላይ በትኩረት እየሠሩ ይገኛሉ:: በቅርቡ ባደረግነው የክትትል ሥራ የተቋማት ዝግጁነት ተመልክተናል ያሉት አቶ ሰይድ፣ ከዚህ አንፃር የተዘጋጀውን የማብቃት ፈተና ተማሪዎች ዘንድ እንዲደርስ እና እንዲረዱት የማድረግ ነገር ብዙዎቹ ሠርተዋል:: አንዳንዶች ደግሞ ከመውጫ ፈተና አንፃር ተማሪዎችን ሞጁል ትቶሪያል እያዘጋጁ ለፈተናው ዝግጁ የማድረግ ሥራ እየሠሩ ይገኛሉ:: በተጨማሪም የሙከራ ፈተና አዘጋጅተው ተማሪዎቻቸውን እየፈተኑ ያሉ ተቋማትም እንዳሉ ኃላፊው ይናገራሉ::
ፈተናው የሚሰጠው በበየነ መረብ ስለሆነ ዩኒቨርሲቲዎች ተማሪዎቻቸውን በጉዳዩ ግንዛቤ እንዲኖራቸው የራሳቸውን ሶፍትዌር አበልፅገው በበየነ መረብ ተማሪዎችን የሙከራ ፈተና የፈተኑ ተቋማት አሉ:: በትምህርት ሚኒስቴር በኩል በበየነ መረብ ፈተናውን ለመስጠት የሚያስችል መሠረተ ልማት በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መኖር አለመኖሩን አጣርተን ለፈተናው በቂ ዝግጅት መደረጉን አረጋግጠናል ሲሉም ይገልጻሉ::
ዘንድሮ እንደ ትምህርት ሚኒስቴር አላማ አድርገን የተነሳነው ከመውጫ ፈተና ጋር ተያይዞ ፈተናውን በተሳካ ሁኔታ እና በተገቢው ጥራት መስጠት መቻልን ነው:: ሌላው ተማሪዎችን በመውጫ ፈተና ውጤታማ የማድረግ የቤት ሥራ እንደሆነ እና ለዚህም በተገቢ ሁኔታ ሥራዎች እየተሠሩ እንደሆነ ተናግረዋል::
የትምህርት ባለሙያ እና በኮተቤ ትምህርት ዩኒቨርሲቲ መምህር የሆኑት ዶክተር አማኑኤል ኤሮሞ በበኩላቸው፤ ፈተና ማለት የመማር ማስተማር ሂደት ውጤታማነት አፈፃፀሙን የምንለካበት መሣሪያ ነው ይላሉ። በፈተና የሚገኘው ውጤት ለመማር ማስተማሩ እንደግብረ መልስ ሆኖ እንደሚያገለግልም ጠቅሰው፤ የዩኒቨርሲቲ መውጫ ፈተና መዘጋጀቱም መንግሥት አላማው አድርጎ የተነሳውን የትምህርት ጥራትን ከፍ የሚያደርገው መሆኑን ያስረዳሉ::
እርሳቸው እንደሚናገሩት፤ የመውጫ ፈተናው በመጀመሪያ ዲግሪ ተማሪዎች ትምህርታቸውን በተገቢው ሁኔታ መከታተላቸውን ማረጋገጫ ይሆናል:: በተጨማሪ በተማሪዎች ላይ የአመለካከት ለውጥ ያመጣል:: ወደ ፊት ተማሪዎች እንደዚህ ዓይነት ፈተና ከፊታቸው መኖሩን ስለሚያውቁ በደንብ ይሠራሉ:: ያጠናሉም:: ያንን መሠረት በማድረግም በሥርዓተ ትምህርቱ ላይ ያሉ ክፍተቶች ካሉ በትምህር አቀባበል ላይ ያሉ ችግሮችም ካሉ ያንን ያስተካክላል ተብሎም ይታመናል::
በእርግጥ ይላሉ ዶክተር አማኑኤል፣ በዓለም ላይ በብዙ ዩኒቨርሲቲዎች ላይ አይካሄድም፤ ምክንያቱም ዩኒቨርሲቲዎች የየራሳቸው የሆነ አካሄድ አላቸው:: ለዚህ ደግሞ ተጠቃሹ አሠራራቸው ወጥ ባለመሆኑ ነው:: በሥርዓተ ትምህርቱ ላይ የሚቀመጡ የመወዳደሪያ መስፈርቶች ማስተማሪያ ሥነ ዘዴዎች፣ መልመጃዎች ተመሳሳይ ናቸው:: ዩኒቨርሲቲ ላይ ስንመጣ ግን በዚህ መልኩ አይደለም:: እያንዳንዱ ዩኒቨርሲቲ በጥንካሬ ሆነ በድክመት የተለያየ ደረጃ አለው:: እንደ አገር የዩኒቨርሲቲ የሰው ኃይል ልዩነት ይኖረዋል::
ዶክተር አማኑኤል እንደሚሉት፤ ዋናው የትምህርት ጥራት የሚያመጣው መማር ማስተማሩ ነው:: በዚህ ሂደት ተማሪው፣ መምህሩ፣ የሚማርበት ሥርዓተ ትምህርቱ፣ የመማሪያ አካባቢው ማለትም ቤተ መጻሕፍቱ፣ ቤተ ሙከራው ሁሉ ተደማምረው የትምህርት ጥራቱን የሚያረጋግጡት ናቸው፤ በእነዚህ ነገሮች ላይም በተጠናከረ መልኩ ሊሠራ ይገባል::
በሌላ በኩል የዩኒቨርሲቲ አመራሩ ቁርጠኛ ነው ወይ? ለዚህ ጉዳይ ዝግጁ ነው ወይ? የሚለውን በደንብ ልናየው ይገባል፤ ይህንን ፈተና የግልም የመንግሥትም ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ የሚማሩ ከሁለት መቶ ሺህ በላይ የሚሆኑ ተማሪዎች ናቸው የሚወስዱት:: የግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ደግሞ ቁጥራቸው ብዙ ነው፤ ከሦስት መቶ በላይ ይደርሳል፤ የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች ደግሞ ከአርባ በላይ ናቸው:: ከዚህ አንጻር የመውጫ ፈተና ውጤት ፋይዳ እንዲኖረው ምን መሠራት አለበት የሚለውን ማጤንን ይጠይቃል::
የመውጫ ፈተናው ለተማሪው ስጋት እንዳይሆን አስቀድሞ በተማሪዎች ሥነ ልቦና ላይ መሥራት እና ዝግጁነት እንዲኖራቸው ማድረግ ወሳኝ ነው የሚሉት ዶክተር አማኑኤል፣ ፈተናው በተማሪዎች በተሻለ ሁኔታ መሠራቱ የሚሰጠው ጥቅም ዘርፈ ብዙ ነው ብለዋል:: ነገር ግን በአጠቃላይ ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ዝግጁነት ወሳኝ ነው ሲሉ አመልክተዋል።
የመጨረሻ የትምህርት ግቡ ብቁ፣ ተወዳዳሪ እና መልካም ሥነ ምግባር ያለው ዜጋ ማፍራት ነው የሚሉት ዶክተር አማኑኤል፣ ይህንን ለማድረግ ደግሞ መጀመሪያ ብቃት (competency) ሥርዓተ ትምህርት ውስጥ የሚቀመጡ ነገሮች ናቸው ይላሉ:: እነዚህ ብቃት ያልናቸው ጉዳዮች ወጥ መሆንም ይጠበቅባቸዋል ሲሉ ያስረዳሉ:: ተማሪዎችም በዚህ ውስጥ ሆነው መማር እንደሚገባቸውና መመዘንም የሚጠበቅባቸው በዚያው ልክ መሆኑን ያስረዳሉ:: ስለዚህ ውጤቱ ያማረ ይሆን ዘንድ ዩኒቨርሲቲዎቻችንም ወጥ የሆነ የመማር ማስተማር ሂደት ሊያከናውኑ እንደሚገባቸው አመልክተዋል::
ዶክተሩ እንደሚሉት፤ መማር ማስተማር አገልግሎት ላይ መሠራት አለበት:: ጥራት ያለው አገልግሎትም መስጠት ተገቢ ነው:: ቀድመን በአመለካከት ሆነ በአስተሳሰብ ዝግጁ መሆንም የግድ ይላል:: ስለዚህ የመምህሩ ብቃት የትምህርት ሥርዓቱ ብቃት፣ የምንጠቀምባቸው የማስተማር ሥነ ዘዴዎች ላይ በአግባቡ መሠራት አለበት:: በትምህርት ቤቱ ያለው መሠረተ ልማትም የተሻለ አቅም ያለው መሆን አለበት:: በጥቅሉ ዓለምአቀፍ ተወዳዳሪ የሰው ኃይል ለመፍጠር ቅድመ ሁኔታዎች መሟላት አለባቸው:: ፈተና በራሱ የማጣሪያ ነጥብ (check point) ነው።
ዶክተር አማኑኤል፣ በአገራችን በሕግ ትምህርት የመውጫ ፈተና መስጠት ከተጀመረ ቆይቷል፤ በሕግ ትምህርትስ ዓለምአቀፍ ተወዳዳሪ እና ብቁ መልካም ሥነ ምግባር ያላቸውን ሰዎች አፍርተናል ወይ? የሚለው መታየት አለበት ሲሉ ተናግረዋል::
የትምህርት ጥራትን በዋናነት ለማምጣት ከተፈለገ ግን መሠራት ያለበት ጥራት ያለው የመማር ማስተማር አገልግሎት በመስጠቱ ላይ ነው። የዩኒቨርሲቲ መሪዎች ቁርጠኝነት እንዲሁም የመንግሥት ቁርጠኝነት ያስፈልጋል:: ጥራት ለማምጣት ደግሞ ተከታታይ ማሻሻያ በማድረግ መሠራት አለበት፤ በእርግጥ ጥራት በአንድ ጊዜ የሚመጣ ነገር አይደለም:: ስለሆነም በተከታታይ መሥራትን ይጠይቃል:: ተማሪዎችን በመውጫ ፈተና ከመለየት አስቀድሞ መሠራት ባለባቸው ወሳኝ ጉዳዮች ላይ አጠንክሮ መሥራት የግድ እንደሚል ዶክተሩ ተናግረዋል::
በአጠቃላይ ያነጋገርናቸው የዘርፉ ባለሙያዎች እንዳሉት፤ አዲስ ነገር ወደትግበራ ሲገባ የማንገራገርና የመቃወም ነገር ሊስተዋልበት ይችላል፤ ይሁንና ይህ የታየው ነገር የቆየው ለትንሽ ጊዜ ነው:: በአሁኑ ወቅት አብዛኞቹ ሒደቱን በአግባቡ እየተከተሉ ይገኛሉ:: ተማሪዎቻቸውንም ለዚህ ፈተና ብቁ ለማድረግ የየበኩላቸውን በመወጣት ላይ ይገኛሉ::
በሌላ በኩል ደግሞ እንደገለጹት፤ ከሁሉም በፊት ጥራት ያለው የመማር ማስተማር እና የምርምር አገልግሎት መሰጠት አለበት:: ምክንያቱም ጥናት እና ምርምር ለዩኒቨርሲቲ ወሳኝ ነው። ጥናትን መሠረት አድርጎ ነው ሥርዓተ ትምህርቱ የሚስተካከለው:: ችግሮች የሚለዩት የዩኒቨርሲቲ ተቋማዊ ባህሉ በእጅጉ ማሻሻያ ሲደረግበትም ነው።
ክብረኣብ በላቸው
አዲስ ዘመን ግንቦት 1/2015