
– አቶ ደሳለኝ ሥዩም የሸገር ከተማ የሰላምና ፀጥታ ጽሕፈት ቤት ምክትል ኃላፊ
የዝግጅት ክፍላችን ከሸገር ከተማ አስተዳደር የሰላምና ፀጥታ ጽሕፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ ደሳለኝ ሥዩም ጋር በከተማው ስላለው ወቅታዊ ሁኔታ ቆይታ አድርጓል። በቆይታው የነዋሪውን ሰላም ከማስጠበቅ፣ በማኅበረሰብ ላይ ስጋት የሚደቅኑ የሽብር ወንጀሎችን ከመቆጣጠር፣ ውስብስብ የሆኑ እና በአደባባይ የሚፈፀሙ ስርቆቶችን ከመቆጣጠር አንፃር እየተሠሩ ስለሚገኙ ተግባራት ዝርዝር ጥያቄዎችን በማንሳት እንደሚከተለው ምላሽ አግኝቷል። አብራችሁን ቆዩ።
አዲስ ዘመን፦ በቅርቡ የተመሠረተችው የሸገር ከተማ የሰላምና ፀጥታ ሁኔታ በምን ደረጃ ላይ ይገኛል?
አቶ ደሳለኝ ሥዩም፦ የሸገር ከተማ ከተመሠረተ ሁለት ዓመት ተኩል ሆኖታል። ሲመሠረትም የራሱ ተልዕኮና ዓላማ ይዞ ነው የተመሠረተው። በተለይ በኢኮኖሚ እና በቴክኖሎጂ የበለፀገች መልካም አስተዳደር የሰፈነባት ለዜጎቿ ምቹ የሆነች ከተማ ሆና እንድትቀጥል በርካታ ሥራዎች እየተሠሩ ነው። የታላላቅ ሀገራት ከተሞች የደረሱበት ደረጃ ላይ እንድትደርስ የተገነባች ከተማ ነች። 12 ክፍለ ከተሞች እና 36 ወረዳዎች ያላት ከተማ ነች።
እነዚህ የከተማዋ ክፍሎች በጣም ሰፊ ቦታ የያዙ እንደመሆኑ መጠን የልማቱን ሥራ ለማስቀጠል መልካም አስተዳደርን ለማስፈን እና ዜጎች በሰላም ወጥተው በሰላም እንዲገቡ ለማስቻል ቅድሚያ ሰጥተን ከምንሠራቸው ሥራዎች መካከል ዋናው ሰላምና ፀጥታ ነው። ይህ ሥራ ጊዜ የሚሰጠው እና የምንዘናጋበት ሳይሆን ሁሌም በቀጣይነት የምንሠራው ነው።
ይህንንም ሥራ የፀጥታው መዋቅር ብቻ ሳይሆን መሥራት ያለበት የተለያዩ ባለድርሻ አካላት፣ የሚሳተፉበት ሥራ ነው። እኛን እንደ ከተማ ፀጥታ ምክር ቤት የፀጥታና የሰላም እቅድ በማዘጋጀት ከላይ እስከታች በተዋረድ እንዲወርድ እና እንዲተገበር በመሥራት ላይ እንገኛለን።
አዲስ ዘመን፦ በ2017 ዓ.ም የበጀት ዓመት የተሠሩ ሥራዎችን ቢገልፁልን?
አቶ ደሳለኝ ሥዩም፦ በ2017 ዓ.ም የሥራ ዘመን እቅድ አዘጋጅተን በእቅዱ ዙሪያ፣ የከተማ፤ የክፍለ ከተማ፣ የወረዳ አመራር እስከ ታች እስከ ዞን አመራር ድረስ በቅድሚያ ውይይት በማድረግ የጋራ ግንዛቤ የተያዘበት ሁኔታ ነው ያለው።
ከዚህም ባሻገር ይህ የሰላምና ፀጥታ እቅድ የሚተገበረው የሕዝቡ ተሳትፎ ካለ ብቻ ነው። የሕዝቡን ተሳትፎ ለማሳካት በሰፋፊ መድረኮች በማወያየት እያንዳንዱ ነዋሪ የራሱ አጀንዳ እንዲያደርገው የሚያስችል ሥራ አከናውነናል።
በዚህ መሠረት ግንዛቤ ማስጨበጥ ብቻ ሳይሆን ኅብረተሰቡ እራሱ በሰላምና ፀጥታ እንዲሳተፍ ስንል ከአካባቢ ጥበቃ ጀምሮ ከፀጥታ ኃይል ጋር መረጃ በመስጠት እገዛ እንዲያደርግ፣ ሌላው የፀጥታ ኃይሉን በፋይናንስ አቅም የሚያጠናክርበት መንገድ በመፍጠር ሰፋፊ ሥልጠናዎችን ስናካሂድ ነው የቆየነው።
የሚሊሻ አባላት በብዛት አሉን። እነዚህ የሚሊሻ አባላት በየጊዜው ሥልጠና እየወሰዱ እውቀት እንዲኖራቸው አድርገናል። ለዚህ ሥልጠና የሚሆን ከምግብ፣ ከአልባሳት ጀምሮ ለሚሊሻው የሚያስፈልገውን ነገር እራሱ እያዋጣ ሲሠለጥን ነበር። ይህ ተነሳሽነት የሚበረታታ እና የሰላምና የፀጥታ ጉዳይ የራሱ የኅብረተሰቡ ጉዳይ መሆኑ እየተገነዘበ ነው። ምንም ግፊት ሳይደረግበት በራሱ ተነሳሽነት በዚህ መልኩ እገዛ ማድረግ ይችላል።
ከዚህ ባሻገር ሰፊ ቁጥር ያለው የጋቸና ሲርና (የሥርዓቱ ጋሻ) የምንለውን አደረጃጀት አለን። በዚህ አደረጃጀት ውስጥም ኅብረተሰቡ መጀመሪያ በዚህ ውስጥ ማነው መሳተፍ ያለበት፤ የሚለውን ከምልመላው ጀምሮ በሕዝብ ዘንድ ተወዳጅ የሆኑ የተሰጠውን ሥራ በአግባቡ መፈፀም የሚችሉ፤ እራሳቸውም ፍላጎት ያላቸው እና ሕዝቡም የሚወዳቸው ሰዎችን መልምለው እንዲሠለጥኑ በማድረግ፣ አስፈላጊውን የቁሳቁስ እና የፋይናንስ ድጋፍ በማድረግ ሥልጠና እንዲያገኙ አድርገዋል።
ከዚያ በመለስ ራሱ ኅብረተሰቡ በፍላጐቱ ሮንድ እና በልማት ቡድን አደረጃጀት አካባቢውን የሚጠብቅበትን ሁኔታ እንዲፈጠር ተደርጓል። ይሄ በከተማችን አስፈላጊውን ጥበቃ፣ ፀጉረ ልውጥ የሆኑ ሰዎች እንኳን ሲታዩ በቶሎ ለፀጥታ መዋቅሩ ለፖሊስ መረጃን የመለየትና የማጣራት ሥራ እንዲሠራ የሚያደርጉበት ሁኔታ ነው ያለው። በአጠቃላይ ሰላም እንዲሰፍን ከፍተኛውን ተሳትፎ ኅብረተሰቡ (የከተማዋ ነዋሪ) ነው የሚያደርገው።
አዲስ ዘመን፦ የኢንቨስትመንት ዘርፉ ስኬታማ እንዲሆን ፍጹም ሰላምና ፀጥታ ይፈልጋል፤ በከተማው የሚገኙ ኢንቨስትመንት ሥራዎች እንዲቀላጠፉ ምን እየሠራችሁ ነው?
አቶ ደሳለኝ ሥዩም፦ ከኢንቨስትመንት ጋር ተያይዞ እንደ ሸገር አሁን የኢንቨስትመንት ተግባራት ተጠናክሮ እየሄደ ነው። በከተማዋ ከዚህ በፊት የነበሩ የጥፋት አጀንዳዎች አሁን በዚህ ደረጃ የሉም። ከዚህ ቀደም ለማንኛውም ባለሀብት የተለየ የሐሰት ፕሮፖጋንዳ የሚነዛበት ሁኔታ ነበር። ያንን ፕሮፖጋንዳ ለመስበር የተሠራ ሥራ አለ።
ዛሬ ባለሀብቱ በሸገር ከተማ ኢንቨስትመንት ላይ ለመሰማራት ትላልቅ ጥያቄዎችን እያቀረበ ነው ያለው። የከተማ አስተዳደሩም ይህንን ለማመቻቸት በዚህ ዙሪያ ሰፊ ሥራ እየሠራ ነው። ከፀጥታ አንፃርም ምንም አይነት ኮሽታ በዚህ ከተማ ውስጥ የለም። ይህ ኮሽታ የሌለው ሥራ ስለተሠራ ነው። እንዳነሳሁት በጥበቃ ሥራ ላይ የተሰማሩ ሰዎች ሳይቀሩ በየአካባቢያቸው የማወያየት ሥራ በመሥራት፣ እንዳይደናገጡ እና ሥራቸውን በአግባቡ እንዲሠሩ ስለተደረገ ምንም ስጋት የለም። ማንኛውም ባለሀብት አሁን በዚህ ሰዓት የመሬት ጥያቄ እያቀረበ ይገኛል። ይህንን የሚያደርገው የሰላም ችግር ያለመኖሩን ስላየ እና ስለተረዳ ነው። በመሆኑም እንደ ችግር እስካሁን የገጠመን ነገር የለም።
በየደረጃው ያሉ ሌሎች መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ መዋቅሮች የማወያየት፣ አስፈላጊውን የፀጥታ ሥራ እንዲያደርጉ የመሥራት ተግባራት ሲከናወን ቆይቷል። ሸገር እንደሚታወቀው ሰፊ ከተማ ነው። ብዙ የኢንቨስትመንት ሥራዎች ይገኛሉ። ብዙ ፋብሪካዎች አሉ። በዚህ ውስጥ ብዙ ሠራተኞች ተቀጥረው ይሠራሉ። ብዙ ኢኮኖሚውን የሚደግፉ ምርቶች በከተማዋ ይመረታሉ። በዚህ አካባቢ ጥበቃ እንዲጠናከር የማድረግ ሥራ እየተሠራ ነው።
በየአካባቢው ያሉና የራሳቸው የፋብሪካዎቹ ጥበቃዎችንና አመራሮችን የማወያየት አስፈላጊውን ሥራ እንዲያከናውኑ፣ በቴክኖሎጂ የሚደገፉበት ሁኔታ እንዲመቻች፣ የማድረግ ተግባር ሲፈፀም ቆይቷል። ከዚህ ባሻገር የአጎራባች ዞኖች እና ወረዳዎች በጥምረት ለመሥራት የጋራ እቅድ አውጥተን ስንሠራ የቆየንበት አግባብ አለ።
አዲስ ዘመን፦ የሰላምና ፀጥታ ሥራው ውጤታማ እንዲሆን ሳይንሳዊ ጥናቶች እና ዳሰሳዎችን በምን መልኩ ትሠራላችሁ፤ ምን ውጤትስ አስገኙ?
አቶ ደሳለኝ ሥዩም ፦ የሰላምና ፀጥታውን ጉዳይ አስተማማኝ ለማድረግ የሁኔታ የዳሰሳ ጥናቶች በሰፊው ሲካሄዱ ቆይተዋል። በከተማው ውስጥ የሰላምና የፀጥታ ስጋት የሆኑ ጉዳዮች ምን እንደሆኑ መለየት ተችሏል። ጥናቱንም እንደ ግብዓት የመውሰድ ሥራ ስናከናውን ቆይተናል። በተለይ ፀረ ሰላም የሆኑ ኃይሎች የተለያዩ ተልዕኮና አጀንዳ ይዘው በከተማችን ሁከት ሊፈጥሩ እና አለፍ ሲልም ሰላም የሌለ ለማስመሰል የሚሠሩ ስላሉ ይህንን በጥናት በማረጋገጥ እና እነዚህን የመሰሉ ሰዎች በመከታተል፣ በመረጃ በማስደገፍ፣ የመቆጣጠር እና ለሕግ የማቅረብ ሥራ በሰፊው ሲደረግ ቆይቷል።
ከዚህ ባሻገር የጦር መሣሪያ ዝውውር፣ የኮንት ሮባንድ እንቅስቃሴን የመከታተል የመቆጣጠር ሥራዎች በሰፊው እየተሠራ ነው። የተለያዩ የጦር መሣሪያዎች የተያዙበት፤ በኮንትሮባንድም የተለያዩ ምርቶች በቁጥጥር ስር የዋሉበት ሁኔታ አለ። ከዚሁ ጋር ተያይዞ ይህንን የኮንትሮባንድ ተግባር ለመከታተልም፤ ሕገወጥ ሥራን ለመከታተል እና ለመቆጣጠር በቅንጅት ከአዲስ አበባ ከተማ ጋር የሚሠሩ ሥራዎች አሉ።
በተለይ የኑሮ ውድነትን ለማባባስ አንዳንድ ስግብግብ ነጋዴዎች የሚፈጥሩት ችግር አለ። ይህንን በጥብቅ ቁጥጥር እንከታላለን። በመጋዘን ውስጥ ምርት ደብቀው መሸጫ መደብር አካባቢ ደግሞ ምርት እንደጠፋ በማስመሰል ዋጋው እንዲንር የሚያደርጉበትን ሁኔታ የመከታተል፣ በቁጥጥር ስር የማዋል እና ለሕግ እንዲቀርቡ የማድረግ ሥራዎችን ከአዲስ አበባ ታክስ ፎርስ ጋር እየሠራን ነው፡፡
አዲስ ዘመን፦ በዘመናዊው ዓለም ወንጀልን በብቃትና በፍጥነት ለመቆጣጠር ቴክኖሎጂ እጅጉን ወሳኝ እንደሆነ ይነገራል፤ የሸገር ከተማ ከዚህ አንፃር ምን ላይ ይገኛል?
አቶ ደሳለኝ ሥዩም፦ የተለያዩ ወንጀሎች እንዳይፈፀሙ፤ ከመፈፀማቸው በፊት በቶሎ ደርሶ ለመቆጣጠር በሰው ኃይል ብቻ የሚቻል አይደለም። ቴክኖሎጂም በዚሁ ተግባር ላይ ትልቁን ድርሻ ይወስዳል። ለምሳሌ የሸገር ከተማ አስተዳደር ባሉት 12 ክፍለ ከተሞች ያለውን የሰላምና ፀጥታ ሁኔታ
ለመከታተል በሁሉም ቦታዎች የሲሲ ቲቪ ካሜራ ተተክሎ በዋናው ጽሕፈት ቤት የመከታተያ ክፍል (ሲቹዌሽን ሩም) በማዘጋጀት ባለሙያዎች ተመድበው ይከታተላሉ።
እያንዳንዱን እንቅስቃሴም በየደረጃው ለሚመ ለከተው አካል ሪፖርት በማድረግ ወንጀሉ ባለበት አካባቢ ችግሩ ሳይፈጠር ወዲያው በቁጥጥር ስር እንዲውል ይደረጋል። ወንጀል ቢፈጠርም በፍጥነት በዚያ አካባቢ በመገኘት እና ሁኔታውን በቁጥጥር ስር በማዋል ወደ ሕግ አግባብ እንዲሄድ ይደረጋል።
አዲስ ዘመን፦ የአደባባይ በዓላት እና ሁነቶች በሰላምና በፀጥታ እንዲጠናቀቁ ምን ተግባራት ታከናውናላችሁ ?
አቶ ደሳለኝ ሥዩም፦ ከፀጥታ ሥራ ጋር ተያይዞ የአደባባይ በዓላት እና የተለያዩ ሕዝብ በብዛት የሚገኝባቸው ሁነቶች በሰላም እንዲከበሩ እና እንዲጠናቀቁ ለማድረግ ሰፋፊ ሥራዎችን እንሠራለን። በዚህም ከሕዝብ ውይይት አንስቶ በተግባር ሰፊ የሰው ኃይል በመመደብ ክትትል እስከማድረግ የሚያስችሉ ሥራዎች ተፈፅመዋል።
ለአብነት ያህልም የመስቀል ደመራ በዓል፣ የጥምቀት፣ የእሬቻ በዓል (በዓሉ ሰፊ ሕዝብ የሚገኝበት እና በተለይ በሸገር ከተማ እና በቢሾፍቱ ሲከናወን) በቂ የሰው ኃይል በመመደብ አስፈላጊውን ዝግጅት በማድረግ በሰላም እንዲከበር ለማድረግ ተችሏል። በዚህም ምንም አይነት የፀጥታ ችግር እንዳይኖር እና ምንም ኮሽታ ሳይፈጠር እንዲከበር በማድረግ ብዙ ሥራ ተከናውኖ ውጤታማ መሆን ተችሏል።
በዚህ ምክንያት ሁሉም የአደባባይ በዓላት ችግር ሳይፈጠር በሰላም እንዲከበሩ ማድረግ ተችሏል። በከተማዋና በዙሪያው በተካሄዱ ልዩ ልዩ የድጋፍ ሰልፎች፣ ሀገር አቀፍ እና ዓለም አቀፍ ኮንፍረንሶች፣ ኤግዚቢሽንና ባዛሮችም ጭምር በተመሳሳይ በሰላም እንዲደረግ አደረጃጀቱ አመርቂ ሥራ ሠርቷል። ይህ ውጤት የተገኘው ከሁሉም መዋቅር ጋር በመናበብ ሰላምና ፀጥታን ማስፈን በመቻሉ ነው።
አዲስ ዘመን፦ በአደባባይ በዓላት ሁከትና ብጥብጥ ለመፍጠር የሚሞክሩ ሰዎችንና መሣሪያዎችን ይዞ የመግባት ሙከራ በምን መልኩ ታከሽፋላችሁ?
አቶ ደሳለኝ ሥዩም፦ የአደባባይ በዓላት ሲኖሩ የሕዝብ እንቅስቃሴ በሰፊው ይኖራል። በሕዝብ እንቅስቃሴ ውስጥ ደግሞ የተለያየ የጦር መሣሪያ፣ ተቀጣጣይ ነገሮችን ይዞ ለመግባት የሚንቀሳቀሱ ኃይሎች ከዚህ በፊት አጋጥመዋል። ይህም ብቻ ሳይሆን አላስፈላጊ ኅትመቶችን፣ ጽሑፎችን የተከለከሉ እንደ ባንዲራ ዓይነት እና የመሳሰሉ ነገሮችን ይዞ ወደ በዓሉ (ሕዝብ ወደሚበዛበት ቦታ) ይዞ በመግባት ችግር የመፍጠር ሁኔታ አለ፤ ይህንን ለማስፈፀም የሚንቀሳቀሱ ኃይሎችም ነበሩ።
ይህንን በፍተሻ እና በክትትል ብቻ ለማስቆም። ይህንን ድርጊት ኅብረተሰቡ ራሱ እንዲገነዘበው የማድረግ ሥራዎች ተከናውኗል። ትልቁ ሥራም ይሄንን ጉዳይ አጀንዳ አድርጎ እንዲወያይበት ማድረግ ነው። ለምሳሌ በኢሬቻ በዓል ላይ የጦር እና የስለት መሣሪያዎችን ይዞ በመግባት የሚንቀሳቀሱ ኃይሎች ነበሩ። ይህንን የሚያደርጉት ድርጊቱን ፈፅሞ ሕዝብን ከመንግሥት ጋር፣ ሕዝብን ከሕዝብ ጋር ለማጋጨት የሚሠሩ ሰዎች ናቸው።
ይህንን በፀጥታ ኃይል መከታተል ብቻ ሳይሆን ከሕዝቡ ውስጥ በመሆን ይህንን ድርጊት ለመፈጸም ስለሚንቀሳቀስ ሕዝቡ እራሱ ተሳታፊ በመሆን መረጃ እንዲያቀብል የማወያየት ሥራ ሠርተናል። በመሆኑም ችግሩን እንዲረዳ እና ይህን መሰል ችግር ሲያጋጥም ቶሎ ለፀጥታ ኃይል አሳልፎ እንዲሰጥ የማድረግ ሥራ ተከናውኗል።
ከዚህ ያለፈውን በፍተሻ ኬላዎች፣ በጥናት፣ ከሚገኙ መረጃዎች ተከታትለን የመቆጣጠር ሥራ ስንሠራ ነበር። ይህንን ሥራ እንደ ሸገር ከተማ ብቻ ሳይሆን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርም የፀጥታ መዋቅሩ እንዲሁም በዙሪያው ያሉ ዞኖች እና ወረዳዎች መረጃ በመለዋወጥና በመመርመር የመቆጣጠር ሥራ ስንሠራ የቆየንበት እና ውጤትም ያገኘንበት ነው። ድርጊቱ ከጥቂት ጊዜ ወዲህ በጣም የቀነሰበት ሁኔታ ነው ያለው። ምክንያቱም ኅብረተሰቡ ችግሩን ተረድቶ አምኖበታል።
ተከራይቶ የሚኖረው ሰው ምን እንደሚያደርግ፣ ምን ይዞ እንደሚገባና እንደሚወጣ አከራዩ ያውቃል። ይህንን ይጠቁማል። አከራይ ተከራይ የማወያየት፣ በስም ዝርዝር ተከራዩን የመውሰዱ እና ማንነቱን የማወቅ ሂደት ሥራ እየተሠራ በመሆኑ ከጊዜ ወደ ጊዜ ለሰላም ጸር የሆኑ ድርጊቶች እየቀነሱ ነው።
አዲስ ዘመን፦ በፀጥታ ኃይሉ ላይ የሚቀርቡ አንዳንድ የሥነ ምግባር ጉድለቶችን ለመፍታት ምን ርምጃ ትወስዳላችሁ?
አቶ ደሳለኝ ሥዩም፦ መዋቅራችን በቂ ገንዛቤ ይዞ እና እውቀት ኖሮት በጥሩ ሥነምግባር ኃላፊነቱን እንዲወጣ ጥንቃቄ ይደረጋል። የፀጥታ ኃይሉ ኃላፊነቱን አውቆ መሥራት ስላለበት፤ ለሕዝብ የቆመ ኃይል መሆን ስላለበት፣ አገልግሎቱን እንዲሰጥ በቂ እውቀት እንዲኖረው ተደርጓል።
ከዚህ አንጻር የተለያዩ ሥልጠናዎች ሲሰጡ ነበር። በሥልጠናው ከሕገ መንግሥት ጀምሮ የተለያዩ ወታደራዊ እና የሥነ ምግባር ትምህርቶችን በባለሙያዎች እንዲሰጥ ተደርጓል። የሰላምና ፀጥታ ኃይሉም ይህንን ግንዛቤ በመያዝ ነው ሕዝብን ለማገልገል የሚወጣው።
በተለይ ይህንን ሥልጠና ለጋቸና ሲርና እና ለሚሊሻ አባላት በመስጠት ወደ ሕዝቡ ገብተው እንዲያገለግሉ እየተደረገ ነው። ይሁን እንጂ በዚህ ውስጥ ጥቃቅን ስህተቶች አይፈጠሩም ማለት አይቻልም። እየተፈጠሩ ቆይተዋል። እነዚህን ስህተቶች ለማረም መደበኛ አሠራር ዘርግተናል።
በዚህም በየጊዜው የፀጥታ ኃይሉ በራሱ አደረጃጀት የመገማገም (ሂስ ግለ ሂስ የማድረግ)፣ የከፋ ጥፋት ያደረሰውን በሕግ እንዲጠየቅ የማድረግ እና ከአባልነት እንዲሰረዝ የመሥራቱ ተግባር በሰፊው ተከናውኗል።
አባሉን ሙሉ የሚገልፅ ባይሆንም በተወሰኑ ግለሰቦች ላይ የሚታይ ክፍተቶችን የሚፈፅሙ አሉ። እነሱን እንዲታረሙ የሚደረግበት አግባብ አለ። በሕጋዊ አሠራር እና በውስጥ አደረጃጀት ለመፍታት እየሠራን ነው። ከዚያ ባሻገር ግን ይህ የፀጥታ ኃይላችን የምንለው ሌት ተቀን ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይል የነፃ አገልግሎት ሥራ እየሠራ ነው። የፀጥታ ኃይሉ ደመወዝ ተከፋይ አይደለም። ለሕዝብ ላገልግል ብሎ የሚሠራ ኃይል ነው። በዚህ መሠረት ቁርጠኛ ሆኖ እና አምኖበት እየሠራ በመሆኑ በከተማችን አስተማማኝ ሰላም ከማምጣት አንፃር ትልቁን ሚና እና ድርሻ እየተወጣ ነው።
አዲስ ዘመን፦ በከተማዋ ነዋሪ ላይ የተለየ ስጋት የሚጭሩ የፀጥታ ጉዳይ ገጥሟችሁ ያውቃል ?
አቶ ደሳለኝ ሥዩም፦ የፀጥታ ኃይሉ፣ የኅብረተሰቡ ተሳትፎ እና የሚመለከታቸው አካላትም በጥምረት ሰላምና ፀጥታን ለማስፈን ከሚያደርጉት ትብብርና ተሳትፎ በሸገር ከተማ ውስጥ የፀጥታ ችግር አልገጠመንም። የተለየ ነገር የለም። ጥቃቅን የሆኑ እና ከቁጥጥራችን ውጪ ያልሆኑ እንጂ በሕዝባችን ላይ ስጋት የሚደቅኑ ችግሮች አልተከሰቱም። ሕዝቡም ካለምንም ተፅዕኖ በሰላም ከቤቱ ወጥቶ ሲሠራ ውሎ ወደ ቤቱ የሚገባበት አግባብ ነው ያለው። በከተማዋ ማንኛውም ዜጋ ለመኖር ምንም አይነት እንቅፋት አያጋጥመውም።
አዲስ ዘመን፦ ነዋሪዎች በጫኝ እና አውራጅ ጉዳይ ላይ ቅሬታ ሲያቀርቡ ይደመጣል፤ ለዚህ ተግባር ምን አይነት የመፍትሔ ርምጃ ወሰዳችሁ?
አቶ ደሳለኝ ሥዩም ፦ በአዲስ አበባ ከተማ እና በሸገር ከተማ ትልቁ አጀንዳ ሆኖ ከተለያየ አካል ቅሬታ ሲቀርብ የነበረው የጫኝ እና አውራጅ ችግር ነው። በዚህ ጉዳይ ላይ ተጠይቀን ምላሽ ሰጥተናል። የአዲስ አበባ ከተማ የራሱን ደንብ አውጥቶ የመቆጣጠር ሥራ እየሠራ ያለበት ሁኔታ አለ። የሸገር ከተማም በተለያዩ ክፍለ ከተሞች ላይ እንደዚህ አይነት ቅሬታዎች ሲቀርቡ ስለነበር እንደ አንድ ትልቅ አጀንዳ በመያዝ የከተማው የፀጥታ ምክር ቤት ተወያይቶ አቅጣጫ አስቀምጧል።
ጫኝና አውራጆች ማንኛውንም ሰው (በተለይ ቤት ተከራይተው ሲገቡና ሲወጡ) እቃ ለመጫን ወይም ለማውረድ የሚጠይቁት የገንዘብ መጠን በጣም ከፍተኛ እና ሕዝቡንም በጣም ያማረረ ነበር። አሁን የሚደራጁት ወጣቶች ከባለንብረቱ ጋር በእውነተኛ ዋጋ ተነጋግረው፤ ባለቤትየው ‹‹አልፈልጋችሁም እራሴ አወርዳለሁ›› ካለ መብቱ ነው። ‹‹ልጆች፣ ጓደኞች፣ ወንድሞች አሊያም ዘመድ አዝማድ አሉኝ ያግዙኛል እራሴ አወርዳለሁ›› ካለ መብቱ ነው።
አሊያም የጫኝ እና አውራጁን ርዳታ ፈልጎ አውርዱልኝ ካለ ደግሞ በትክክለኛው ዋጋ እና ሁለቱ አካላት በሚስማሙበት መንገድ ተነጋግረው ሥራውን እንዲያሠራ የሚያስችል አቅጣጫ ወርዷል። ይህንን አቅጣጫ የፀጥታው ምክር ቤት ሲያስተላልፍ እኛም ለፀጥታ ኃይሎች ይህንን አቅጣጫ በማስቀመጥ የነበረውን የኅብረተሰቡን ቅሬታ እንዲረግብ ተደርጓል።
በተለይ ኮንዶሚኒየም አካባቢ ከጫኝ እና አውራጅ ጋር በተያያዘ ብዙ ውዝግቦች ይነሱ ነበር። ችግሩ በሸገር ከተማ ፉሪ አካባቢ፣ በኮዬ ፈጬ፣ በቱሉ ዲምቱ እና ሌሎች ክፍለ ከተሞች ላይ ተመሳሳይ ጥያቄ ይነሳ ነበር። አሁን ግን ለፖሊስ፣ ሚሊሻ ቀጥተኛ መመሪያ ተሰጥቷል። መሰል ውዝግብ የፈጠረ በጫኝ እና አውራጅ የተደራጀ አካል ካለ ተይዞ ለሕግ ይቀርባል።
እንደ መንግሥት መሰል መፍትሔ እየተወሰደ ቢሆንም አሁንም በስውር ኃይልን ተጠቅመው ሕዝቡን ለማስጨነቅ የሚፈልጉ ወጣቶች እንዳሉ አልፎ አልፎ መረጃው ይደርሰናል። በእነዚህ አካባቢዎች የፖሊስና የሚሊሻ ክትትል እንዲጠብቅ አቅጣጫ ወርዷል። በተከታታይ የማወያየት ተግባር በመሠራቱ አሁን በጫኝ እና አውራጅ ጉዳይ የተሻለ አፈፃፀም እየታየ ነው።
አዲስ ዘመን፦ በነዋሪዎች ላይ የሚከሰት ንጥቂያ እና ዘረፋን ለመቆጣጠር ጽሕፈት ቤታችሁ ምን እየሠራ ነው?
አቶ ደሳለኝ ሥዩም፦ በሸገር ከተማ በወንጀለኞች የሚፈጸሙ ጥቃቅን ወንጀሎች (በአሳቻ ቦታዎች በመጠበቅ ከሴቶች ቦርሳ፣ ሞባይል እና ሌሎች ቁሳቁስ የመስረቅ) ተግባር ቀደም ሲል ነበር። በአሁኑ ሰዓት የፀጥታ ኃይሉ ቁጥሩ በጣም ጨምሯል። ለሰባት ቀን ለሃያ አራት ሰዓት የሚለውን መርሕ ተከትሎ ፀጥታ ኃይሉ እንዲሠራ እየተደረገ ነው ያለው። በተለይ ሰዎች በሚበዙበት አካባቢ ፀጥታ ኃይሉ ሁለት ሦስት ሆኖ ክትትል እንዲያደርግ ይደረጋል። ከዚህ ቀደም መሰል የስርቆት ወንጀል ሲፈፀምባቸው የነበሩ ቦታዎችን በመለየት የተለየ ክትትል ይደረጋል።
አሁን አሳቻ ሰዓት እና ቦታ ጠበቀው ይህንን ወንጀል አይፈፅሙም ማለት ባንችልም አብዛኛውን ክፍሎች ግን ሽፋን በመስጠት ድርጊቱን ለመቀነስ እየሠራን ነው። የሰላምና ፀጥታ ጽሕፈት ቤቱ መደበኛ፣ ተንቀሳቃሽ፣ ስውር የጥበቃ ቦታዎች አሉት። እነዚህን ወንጀሎች በእነዚህ አደረጃጀት እና ስልት እየተከታተልን እንገኛለን።
በቀጣይ ክትትልና ቁጥጥሩን በቴክኖሎጂ ለማገዝ ሥራዎች እየተሠሩ ይገኛሉ። በተለይ የቴክኖሎጂ መሣሪያዎች እንደ ራዲዮ መገናኛ መሣሪያዎች እና ካሜራዎች በውስን ደረጃ በመኖራቸው እነዚህን በስፋት የሚገኙበትን አማራጭ እየተተገበረ ነው። በመሆኑም አሁን የሚታዩ በኅብረተሰቡ መሐል ገብተው የስርቆት ወንጀል የሚፈፅሙ አካላትን ሙሉ ለሙሉ ለማስቀረት ጥረት እየተደረገ ይገኛል። ይህንን ለማድረግ ሕዝባችን ከጎናችን ነው። በዚህ ጉዳይ ላይ ሕዝቡ ስርቆት የፈፀመውን ሌባ ወዲያው ተረባርቦ በመያዝ ለፀጥታ ኃይሉ እያስረከበ ይገኛል።
አዲስ ዘመን፦ የመኪና ስርቆት በከተማዋ ሲፈፀም በተደጋጋሚ ይታያል ይህንን መሰል ድርጊት በሸገር ከተማ ይኖር ይሆን፤ ወንጀሉን ለመቆጣጠር ምን ርምጃዎች እየተወሰዱ ነው?
አቶ ደሳለኝ ሥዩም፦ በከተማዋ ብዙም አልታየም። ነገር ግን አንድ ሁለት ጊዜ አጋጥሞናል። አንዱ መኪና ይዘው ሰውን አፍኖ በመውሰድ ወላጆቻቸው ገንዘብ እንዲሰጡ የማስገደድ ወንጀል ገጥሞናል። ይህንን ድርጊት በጂፒ ኤስ ቴክኖሎጂ በመታገዝ እና በሌሎች የረቀቁ የምርመራ ዘዴዎች በቁጥጥር ሥር በማዋል እንዲፈረድባቸው አድርገናል። ከመኪና ስርቆትም ጋር በተያያዘ ተመሳሳይ ነገሮች ነበሩ። ይሁን እንጂ መኪናው ተሰርቆ ሳይበተን እና አድራሻው ሳይጠፋ በፊት ደርሰንበታል። ይህንን መሰል ድርጊት በሸገር ብቻ ሳይሆን፣ ከሸገር አዲስ አበባ፣ ከአዲስ አበባ ሸገር እንዲሁም ወደተለያዩ ከተሞች ለመፈፀም የሚንቀሳቀሱ ወንጀለኞች አሉ። እነዚህን አካላት በየጊዜው የማደን ሥራ እየሠራን ነው። ይህንን ከፀጥታ ኃይሉ ጋር ቅንጅታዊ ሥራም እየተከናወነ ነው። ነገር ግን በከተማዋ የከፋ ጉዳት እስካሁን ድረስ አልደረሰም። ነገር ግን ብዙ ሙከራዎች ነበሩ።
እነዚህ ሙከራዎች በማክሸፍ ወንጀለኞቹን በፍርድ ቤት በማቅረብ እና እንዲቀጡ በማስቻል ስኬታማ ተግባር አከናውነናል። በተለይ የግለሰብ መኪኖችን በመውሰድ ወንጀል የሚፈፅሙ ሰዎች መኖራቸውን በማረጋገጣችንም በፖሊስ ኃይል ክትትል በማድረግ እየተቆጣጠርን ነው።
ነገር ግን ችግሩን ሙሉ ለሙሉ ለመቅረፍ መሥራት የሚገባን አሁንም በኅብረተሰቡ ውስጥ ነው። መሰል ምልክቶች ሲታዩ ኅብረተሰቡ ነቅቶ ለፀጥታ አካላት መረጃ በማቀበል እገዛውን ማድረግ ይገባዋል።
አዲስ ዘመን- ለሰጡን ሰፊ ማብራሪያ አመሰግናለሁ።
አቶ ደሳለኝ ሥዩም ፡– እኔም ከልብ አመሰግናለሁ።
በዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን ሰኞ ሰኔ 16 ቀን 2017 ዓ.ም