ኢትዮጵያ ታምርት ሲባል፣ የመጀመሪያው ነጥብ ምን ታምርት የሚለው ጉዳይ ሲሆን፤ እንዴትና በምን ታምርት የሚሉትም ተያያዥ ነገሮች ናቸው። በመሆኑም ኢትዮጵያ ምርት ታመርታለች፤ ይሄ ምርት ደግሞ በአንድ ዘርፍ ብቻ የሚከወን አይደለም፤ ይልቁንም በግብርናውም፣ በኢንዱስትሪውም፣ በማዕድንና ሌላውም ዘርፍ ተመጋግቦና ተሰናስሎ ሊከወን የሚገባው ተግባር እንጂ። ለዚህ ደግሞ እምቅ የተፈጥሮ ሀብት (መሬት፣ ውሃ፣ እና ሌሎችም ለማምረት የሚያስችሉ ነገሮች) አቅም አላት፤ ተስማሚ የአየር ንብረት እና መልክዓ ምድር አላት፤ የሰው ኃይል አላት። በመሆኑም ኢትዮጵያ እነዚህን አቅሞች ተጠቅማ ማምረት እና ወደ ብልጽግናዋ መድረስ ይኖርባታል።
ይሄ ምኞት ነው፤ ኢትዮጵያ አምርታ ከምትመኘው ብልጽግና እንድትደርስ የመሻት ከፍ ያለ ርዕይ ነው። ይሄን ምኞትና ርዕይ ደግሞ ከግብ ማድረስ ይገባል። ይሄ ደግሞ መነሳሳትን፣ ማቀድን እና አቅምን ተጠቅሞ ማድረግን የሚሻ ከፍ ያለ ኃላፊነትን የመወጣት ውሳኔን ይጠይቃል። በመሆኑም ኢትዮጵያ እንድታመርት፤ መጀመሪያ ምን እንደምታመርት ማወቅን፤ ሁለተኛም፣ ለማምረት ያላትን አቅም መለየትን፤ ሦስተኛም፣ የጎደላትን ለይቶ ማወቅንና ከየት መሙላት እንደሚቻል መገንዘብን፤ አራተኛም፣ እነዚህን አቅሞች አቀናጅቶ የመጠቀም መነሳሳትና መነሳሳቱን ወደ ተግባር የመቀየር ከፍ ያለ ቁርጠኝነትን፤ ብሎም ሥራዎችን በኃላፊነት መወጣትን ይጠይቃል።
በዚህ ረገድ ሁለት ነገሮችን በማሳያነት ማንሳት ይገባል። የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ታምርት ጉዞው ዛሬ ላይ የኢኮኖሚው ቀዳሚ ተሸካሚ የሆነው የግብርናው ዘርፍ ነው። ይህ ዘርፍ እንደ አገር የምግብ ዋስትናን የማረጋገጥ ጥረቱን ለማሳካት ብቻ ሳይሆን፤ ኢንዱስትሪውን በመመገብም ሆነ የውጭ ምንዛሬ ግኝትን በማሳደግ ረገድ እየተወጣ ያለው ሚና፤ እንዲወጣ የሚጠበቅበት ድርሻም እጅጉን የላቀ ነው። ስለዚህ የግብርናው ዘርፍን ምርትና ምርታማነት በማሳደግ ኢትዮጵያ እንድታመርት ማድረግ ቀዳሚው ተግባር ነው።
ይህ እንዲሆን ደግሞ ሊታረስ የሚችል ሰፊ መሬት አለ፤ ከፍ ያለ የውሃ ሀብትም አለ፤ ሰፊ የሰው ኃይል አለ። በአንጻሩ የቴክኖሎጂ እና የግብዓት ክፍተቶች አሉ። ስለዚህ አገር ያላትን ሀብት አውቆ፤ ያጠራትን ደግሞ ከመገኛቸው አምጥቶ አቀናጅቶ መጠቀም እና ግብርናውን በዘመናዊ መንገድ እንዲጓዝም በሳይንስና ቴክኖሎጂ እንዲደገፍ ማድረግ እጅጉን አስፈላጊ ነው።
ለዚህም ነው በአንድ በኩል ግብርናው ከዝናብ ጥገኝነት እንዲላቀቅና በዓመት አንድና ሁለት ጊዜ ከሚመረትበት አሠራር ወጥቶ፤ በመስኖ በመታገዝ በዓመት ሦስትና አራት ጊዜ እንዲመረት እየተደረገ ያለው። ለዚህም ነው በተበጣጠሰ ማሳ ላይ ሲካሄድ የነበረውን የአመራረት ሥርዓት በመቀየር፤ በኩታ ገጠም እና በሰፋፊ ማሳዎች ላይ በሜካናይዜሽን የተደገፈ እርሻን በማከናወን፤ በተገቢው ግብዓት እንዲደገፍ እና ለዚህም ከውጭ የሚገቡ የግብርና ግብዓቶችና ማሽነሪዎች ከቀረጥ ነፃ እንዲገቡ ማድረግ የተቻለው።
ለዚህም ነው አርሶአደሩ በበሬ ከማረስ ተላቅቆ በትራክተር እንዲያርስ፤ በኮምባይነር እንዲያጭድና ምርታማነቱን እንዲያሳድግ በሺዎች የሚቆጠሩ ማሽነሪዎች እንዲያገኝ እየተደረገ ያለው። ይሄ በመሆኑም ነው ድርቅና መሰል ችግሮች በተፈጠሩ ቁጥር ለርዳታ እጆቿን ስትዘረጋ የነበረች አገር፤ ዛሬ ላይ ስንዴን ከራሷ አልፋ ወደ ውጭ መላክ የጀመረች፣ «ኢትዮጵያን ኤይድ» በሚል እጆቿን ለድጋፍ የዘረጋች ኢትዮጵያን መፍጠር የተቻለው።
ሁለተኛው ዘርፍ፣ ኢንዱስትሪው ነው። አንድ አገር ምንም እንኳን ጠንካራ የግብርና መሠረት ቢኖራትም፤ የግብርናው ዘርፍ በባህሪው እየተተካ የሚሄድ ዘርፍ እንደመሆኑ በኢንዱስትሪው ዘርፍ መታገዝና በሂደትም ኢንዱስትሪው ኢኮኖሚውን እንዲረከብ ማድረግ አስፈላጊ ነው። በዚህ ረገድ በግብርናው ዘርፍ እየታየ ያለው እመርታ ለኢንዱስትሪው ግብዓትን በማቅረብና ከውጭ የሚገቡ የአግሮ ኢንዱስትሪዎችን ግብዓት በመተካት ላይ ይገኛል። ይሄን መልካም አጋጣሚ በመጠቀም የኢንዱስትሪውን ትራንስፎርሜሽን ማሳለጥ ተገቢ እንደመሆኑ፤ የአገር ውስጥ ባለሀብቱም፤ የውጭ ባለሀብቱ በኢትዮጵያ ያለው የዘርፉ ተሳትፎ እንዲያድግ ማድረግ ያስፈልጋል።
በዚህ ረገድ፣ በፖሊሲ የታገዙና አስፈላጊ የሆኑ የዘርፉ የማበረታቻ ርምጃዎች እየተወሰዱ እና ተጨባጭ ውጤትም እያሳዩ መሆኑ እሙን ነው። ይሄን ወደ በለጠ ስኬት ለማሸጋገርም ኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ተፈጥሯል፤ ንቅናቄውም በተጨባጭ ለውጥ ታጅቦ እየተጓዘ ይገኛል። ይሄንን ማስቀጠል እና የኢንዱስትሪውን አብዮት ለማቀጣጠል በዲፕሎማሲው፣ በሰላምና ፀጥታው፣ እንዲሁም መሰል ለአምራችነቷ አጋዥ የሚሆኑ ጉዳዮችን ማስቀጠል፤ አደናቃፊ የሆኑትን ማክሰም የተገባ ነው። በመሆኑም ኢትዮጵያ እንድታመርት ምን እንደምታመርት እና እንዴት እንደምታመርት መለየት፤ ለማምረት ያላትን አቅም እና መልካም እድሎች መገንዘብ፤ ከማምረት ሊያስተጓጉሏት የሚችሉ ጉዳዮችን ነቅሶ ማረም፤ እንዲሁም ብልጽግናዋን እውን ወደሚያደርግ ተግባራዊ ርምጃ ገብቶ ይሄንን በኃላፊነት መወጣት በእጅጉ ያስፈልጋል!
አዲስ ዘመን ግንቦት 1/2015