ሀገራችን ካላት ተስማሚ የአየር ጠባይ አንጻር ለረጅም ዘመናት ለኢኮኖሚዋ ምሰሶ ሆኖ የቆየው የግብርናው ዘርፍ ነው። ዘርፉን በማዘመን ለሀገር ኢኮኖሚ የተሻለ አቅም እንዲኖረው ለማድረግም በተለያዩ ጊዜያት ጥረቶች ቢደረጉም፤ የተገኘው ውጤት ግን ሀገሪቱ ያላትን አቅም የሚመጥን አይደለም።
መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፤ ሀገሪቱ 36 ሚሊዮን ሄክታር ሊታረስ የሚችል መሬት ባለቤት ነች፤ ከዚህ ውስጥ ጥቅም ላይ እየዋለ የሚገኘው 16 ሚሊዮን ሄክታሩ ብቻ ነው። ይህም ቢሆን ዘመናዊ ያልሆነ የአስተራረስ ዘዴን መሰረት አድርጎ የሚለማ መሆኑ በምርታማነት ላይ ያለው አሉታዊ ተጽእኖ ከፍተኛ ነው።
በእንስሳት ሀብትም ቢሆን በአፍሪካ ሶስተኛ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ደግሞ አስረኛ ደረጃ ላይ የመገኘቷ እውነታ እንደ ሀገር በዘርፉ ያለውን አቅም የሚያሳይ ነው፤ ይህም ሆኖ ግን ሀብቱን ዘመናዊ በሆነ መልኩ ለማልማት ባለመቻሉ ፤ በሀብቱ ያለን ተጠቃሚነት ዛሬም ቢሆን በብዙ ተግዳሮቶች እየተፈተነ ነው።
እንደ ሀገር የግብርናውን ዘርፍ ለማዘመን ከ1950ዎቹ ጀምሮ ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴዎች እንደነበሩ መረጃዎች ያመለክታሉ። በወቅቱ ሰፋፊ የሜካናይዜሽን እርሻዎች ተጀምረው ነበር፤ የእንስሳት ሀብቱንም በአግባቡ ለመጠቀም የሚያስችሉ ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴዎች ነበሩ። ሁኔታው ግን የ 1966ን ለውጥ ተከትሎ ረጅም ርቀት መሄድ ሳይችል ቀርቷል። በዘርፉ ላይ የተስተዋሉ ተስፋዎችም እየቀጨጩ ሀገሪቱ ለብዙዎች መትረፍ የሚያስችል አቅም ይዛ በምግብ እህል እራሷን መቻል አቅቷት፤ በጠባቂነት ዓመታትን አሳልፋለች። የረሀብም ተምሳሌት ለመሆንም ተገዳለች።
ይህንን ሀገራዊ እውነታ ለመለወጥ መንግሥት ከለውጡ ማግስት ጀምሮ ዘርፉን በማዘመን ዜጎች እና ሀገር ተጠቃሚ የምትሆንበትን የልማት ስትራቴጂ ተግባራዊ አድርጓል፤ በዚህም በዘርፉ አዲስ መነቃቃትና ስኬታማ ተሞክሮዎችን ማየት ተችሏል። በግብርናው ዘርፍ ለተሰማሩ ዜጎች ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን በተመጣጣኝ ዋጋ ፤ በብድርና በስጦታ ከማቅረብ ጀምሮ፤ ማዳበሪያና የምርጥ ዘርን በወቅቱ በማድረስ፤ የእርሻ መሬት ምርታማ የሚሆንበትን መንገድ በማመቻቸት አርሶ አደሩ በሥራው የተሻለ መነቃቃት እንዲኖረው፤ ተጠቃሚነቱን ከፍ እንዲል በስፋት እየሰራ ይገኛል።
ከሁሉም በላይ አርሶ አደሩ ዘመናዊነትን በሁለንተናዊ መገለጫ፤ በዘርፉ ምርታማነትን በማሳደግ የእርሱን ብቻ ሳይሆን የሀገርን እጣፈንታ መለወጥ የሚያስችል አቅም እንዳለው በተጨባጭ ማሳየት የሚያስችል ተሞክሮ ባለቤት እንዲሆን እያደረገው ይገኛል። አርብቶ አደር ዜጎቻችን መንግሥት በግብርናው ዘርፍ እየተከተለው ባለው ስትራቴጂ ተጠቃሚ በመሆን ለሀገር ትልቅ አቅም እየሆነ ባለው የስንዴ አርሻ ተሰማርተው ውጤት በማስመዝገብ ላይ ይገኛሉ።
ይህ በግብርናው ዘርፍ እየተስተዋለ ያለው ተጨባጭ እውነታ ሀገራችን እንደ ሀገር በምግብ እህል ራስን ለመቻል እያደረገች ያለው ጥረት ተስፋ ሰጪ መሆን የሚያመላክት ፤ ከዚህም ባለፈ በግብርናው ዘርፍ የዓለም አቀፍ ገበያው ተጠቃሚ የሚያደርጋትን አስቻይ ሁኔታ የሚያመቻች ነው። ይህም ሆኖ ግን ሀገሪቱ ካላት ገና ስራ ላይ ያልዋለ 20 ሚሊዮን ሄክታር መሬት አንጻር ፤ በዘርፉ ያለው የቤት ስራ ገና በብዙ ማሰብ ፣ ማቀድና ፈጥኖ መንቀሳቀስን ይጠይቃል። ከሁሉም በላይ ብዛት ያላቸውን የሀገር ውስጥና የውጭ ባለሀብቶችን ወደ ዘርፉ በስፋት እንዲገቡ ማበረታታትን ይጠይቃል።
አሁን ላይ ዘርፉን እንደ ሀገር ለማዘመን የተጀመሩ ጥረቶችን አጠናክሮ ከመቀጠልም ባለፈ ፤ ለዘርፉ መዘመን ዋነኛ ተዋንያን እንደሆኑ የሚታመንባቸውና ተስፋ የተጣለባቸው ግብርና የምርምር ተቋማት ራሳቸውን ለዘርፉ የተሻለ ስኬት ማዘጋጀት ይኖርባቸዋል። ከመቼውም ጊዜ በተሻለ መንገድ ከአርሶ አደሩ ጎን በመቆም የዚህ የሽግግር ወቅት ዋነኛ ባለ አደራ በመሆን ፤ ለኢትዮጵያ ነገዎች ተስፋና ለቀጣይ ትውልድ መነቃቃት የሚሆን ሙያዊ አስተዋጿቸውን ማበርከት ይጠበቅባቸዋል!
አዲስ ዘመን እሁድ ሚያዝያ 29 ቀን 2015 ዓ.ም