ሰላም ልጆች እንደምን አላችሁ ሳምንቱ ቆንጆ ነበር አይደል? ልጆች፤ ትምህርትና ሥራ ዝግ የሆኑባቸው በዓላት የእረፍት ቀናቶችን ጨምሮ ለጥናት ጥሩ ዕድል ይሰጣሉ። ባሳለፍነው ዓርብ ተከብሮ የዋለው የድል በዓልንም እዚህ ላይ ማንሳት እንችላለን።
በተለይ ፈተና እየተቃረበ ሲመጣ በበቂ ሁኔታ ለመዘጋጀት ጥሩ ተጨማሪ ጊዜያት ያስፈልጋሉ። ልጆች በእርግጥም ጎበዝ ተማሪ ለመሆን በቂ የጥናት ጊዜ ያስፈልጋል። አንዳንድ ልጆች ግን ጎበዝ ተማሪ የሚኮነው በየወሩ ወይም በየሦስት ወሩ ከፍተኛ ክፍያ የሚከፈልበት የግል ትምህርት ቤት በመግባት ነው ብለው ያምናሉ። ይሄ እምነት የልጆች ብቻ ሳይሆን የወላጆችም ነው። ብዙ ወላጆችም ልጆቻቸው ጎበዝ የሚሆኑላቸው ከፍተኛ ገንዘብ የሚከፈልበት የግል ትምህርት ቤት ሲገቡላቸው ብቻ ይመስላቸዋል። ስለዚህ በቂ ገንዘብ ባይኖራቸውም ልጆቻቸውን ከፍተኛ ገንዘብ በሚከፈልባቸው ትምህርት ቤቶች አስገብተው ያስተምራሉ። ግን ልጆቻቸው በእነዚህ ትምህርት ቤቶች በመማራቸው ብቻ ጎበዝና ውጤታማ ተማሪ አይሆኑላቸውም። በዚህ ወላጆች ከፍተኛ ቅሬታ ይሰማቸዋል።
እንደውም አንዳንድ ልጆቻቸው በትምህርታቸው ደከም ያሉባቸው ወላጆች ልጆቻቸው የሚማሩባቸው ትምህርት ቤቶች ድረስ በመሄድ ለምን ልጆቻችንን ጎበዝ አላደረጋችሁልንም ብለው እስከ መጠየቅ ሲደርሱ ይስተዋላሉ። በእርግጥ ልጆች ወላጆች ትክክል ናቸው። ትምህርት ቤቶች ለልጆች ጥሩ ትምህርት በመስጠት ጎበዝ፤ ጠንካራና ተወዳዳሪ ተማሪ እንዲሁም ወደፊት በአካልና በዕድሜ አድገው ትልቅ በሚሆኑበት ጊዜ በተለያየ የሥራ መስክ ተሰማርተው ሀገራቸውን የሚያገለግሉ ዜጎች እንዲሆኑ የማድረግ ከፍተኛ ኃላፊነት አለባቸው። ሆኖም ልጆች ትምህርት ቤቶች የእናንተ ጥረትና ፍላጎት በሌለበት ሁኔታ ብቻቸውን ምንም ሊያደርጉላችሁ ስለማይችሉ በትምህርታችሁ ጎበዝና ውጤታማ በመሆን ወደፊት አገራችሁን በሚፈለገው ሁኔታ ለማገልገል የየራሳችሁንም ጥረት ማድረግ አለባችሁ። በተለይ የተገኘውን ጊዜ በሙሉ ተጠቅሞ በማጥናት ጎበዝና ውጤታማ መሆን ይቻላል።
ቢሆንም በጨዋታ ዘና እያላችሁም እንጂ በጥናት ራሳችሁን በማጨናነቅ ብቻ ጎበዝ ተማሪዎች መሆን አትችሉም። አንዳንዴ ከትምህርት ውጪ በሆነ ጊዜ አባባና እማማ የሚያዟችሁንና አቅማችሁ የሚፈቅደውን ሥራ በመሥራት ሥራን መለማመድ አለባችሁ። ከነዚህ ውጪ የምታገኝዋቸውን ጊዜያት ሁሉ ለጥናት ተጠቅማችሁ የግድ በትምህርት ቤት ከሚሰጣችሁ በራሳችሁ ጥረት ጎበዝ መሆን አለባችሁ።
ልጆች ዛሬ የማስተዋውቃችሁ ተማሪ ቤዛዊት ጌታቸው እንደነገረችን በትምህርት ጎበዝ መሆን የቻለችው ከእረፍት ቀናት በተጨማሪ ሥራና ትምህርት ዝግ የሚሆኑባቸውን በዓላቶች በመጠቀም ነው። “በትምህርት ጎበዝ የሚኮነው በትምህርት ቤት በሚሰጠው ትምህርትና ከፍተኛ ብር የሚከፈልበት ትምህርት ቤት ገብቶ በመማር ብቻ አይደለም “የምትለው ቤዛዊት አዲስ አበባ ውስጥ አራት ኪሎ አካባቢ በሚገኘው በመስከረም ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የዘጠነኛ ክፍል ተማሪ እንደሆነችም ትምህርት ቤቷ ድረስ በመሄድ አይተናል። ጓደኞቿን ስታስጠና ትምህርት ቤቷ ውስጥ ያገኘናት ተማሪ ቤዛዊት ቅዳሜ ቀንን ጓደኞቿን የምታስጠናበት ቀን ነው።
በትምህርቷ እጅግ በጣም ጎበዝም ናት። ከአንደኛ ክፍል ጀምሮ አሁን እስከ ደረሰችበት የዘጠነኛ ክፍል ደረጃ አጋማሽ እስክትደርስ ድረስ ከክፍሏ አንድ አንደኛ የምትወጣ ጎበዝ የደረጃ ተማሪ ናት። ለዚህ ምክንያት የሆናት ከትምህርት ውጪ የሆነ ጊዜ ሁሉ ለጥናት በማዋሏ ነው። በተለይ ሥራና ትምህርት የማይኖርባቸውን የበዓላት ወቅት ለጥናት የምትጠቀምበትን ሁኔታ በጥናት መርሐ ግብሯ (ፕሮግራሟ) አካታለች። “ለምሳሌ ባለፈው ዓርብ በድል በዓል ቀን ትምህርት ቤት ዝግ ስለነበር ቀኑን በጥናት መርሐ ግብሯ አካታ ተጠቅማበታለች።
ልጆች ቤዛዊት በዚህ ወር የዓመቱን ቀን መቁጠሪያ እያየች ነው የጥናት መርሐ ግብሯን የምትከልሰው። ጥናቱ ፈተና እየተቃረበ በመምጣቱና ወላጆቿ ቤት በመቀየራቸው ምክንያት የባከነባትን ጥቂት የጥናት ጊዜ ለማካካስ ጭምር “ምንም ጥናት የማላጠናባቸውም የበዓላት ቀኖች አሉ። ለምሳሌ ለእንቁጣጣሽ ቀን አበባዮሆሽ ስለምጨፍርና ትምህርት ቤት ባለመከፈቱ አላጠናም። መጫወትና መደሰት ብቻ ነው የምፈልገው” ትላለች። ግን ሥራ ዝግ በሚሆንባቸው በዓላቶች በማጥናቷ ሌሎች የክፍሏ ተማሪዎችን በተለይም ጓደኛዋን በማስጠናት በትምህርታቸው ጎብዘው ደረጃቸውን እንዲያሻሽሉ አድርጋለች። በሷ ድጋፍ ጓደኛዋ የደረጃ ተማሪ መሆን ችላለች። “ከኬጂ እስከ አራተኛ ክፍል እማር የነበረው ከፍተኛ ገንዘብ በሚከፈልበት የግል ትምህርት ቤት ሲሆን ጎበዝ ነበርኩ”ትላለች። ባገኘችው እጋጣሚ በማጥናቷ መንግሥት ትምህርት ቤት ብትገባም ውጤቷ አለመቀነሱን ነግራናለች። መልካም እረፍት!
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን እሁድ ሚያዝያ 29 ቀን 2015 ዓ.ም