በሙዚቃ መንገድ ምልልሳቸው ለዘመናት የስኬትን ካባ እንደተጎናጸፉ በስተእርጅና ተሞሽረዋል። ጃዝ የውጪዎቹ የሙዚቃ ስልት ቢሆንም በአስገራሚ የቀመር ስሌት አላምደው የኢትዮጵያን ውሃ በማጠጣት ጥበባዊ አካለ ምስል አልበሰው ኢትዮጵያዊ አድርገውታል። የእድሜ መግፋት ጸንቶባቸው በዛለ ጉልበታቸው ዛሬ ላይ በቀስታ ወደ መድረክ ወጥተው ከሚወዷት ፒያኖ አጠገብ ቁጭ ሲሉ የተመለከታቸው ‹‹እውነት ችለው ሊጫወቱት ይሆን?›› ብሎ እራሱን መጠየቁ አይቀርም። ውስጣዊ የሙዚቃ ስሜታቸው ግን አሁንም እንደ ፍም የጋለ ገና አፍላ ወጣት ነው። በእርጅና ጭነት የተሸበሸቡ ጣቶቻቸው የፒያኖውን ቁልፎች ከመንካታቸው የአድማጭ ተመልካችን ልብ ይነካል፤ ቀልብን የሚሰልብ የሙዚቃ ድምጽም ኩልል ይላል።
አንጋፋው የኢትዮጵያ የጃዝ አባት የክብር ዶክተር አርቲስት ሙላቱ አስታጥቄ፤ በእርግጥም እሳቸው የሙዚቃ ውሃ ልክ ናቸው። ስለ እሳቸው ብዙ ተናግሮም ጥቂት እንኳን መግለጽ አይቻልም። በአፍላ ወጣትነት የተወዳጇትን ሙዚቃ እርጅና አለያያቸውም። ጸጉራቸው በሽበት ቢወረርም ልባቸው ግን በሙዚቃ ፍቅር ተነድፏል፤ ተወሯል። እኛም ስለ እኚህ ታላቅ የሙዚቃ ሰው ልንከትብ ወደድን።
ነሐሴ 19 ቀን 1943 ዓ.ም በጅማ ከተማ ተወለዱ። ገና በልጅነት የተቆራኘቻቸውን ሙዚቃን ከመውደድም አልፎ ያፈቅሯት ነበር፤ በቤተሰቦቻቸው ዘንድ ግን በቀላሉ ‹‹ይሁን›› ተብሎ የሚታለፍ ጉዳይ አልነበረም። በትምህርታቸው ጎበዝ ስለነበሩ የቤተሰቡ ሁሉ ፍላጎት ሙዚቀኛ እንዲሆኑ ሳይሆን በትምህርት ዓለም ወግ ማዕረጋቸውን እንዲያሳዩዋቸው ነበር። በዚህም ወደ እንግሊዝ ሃገር አቅንተው የምሕንድስና ትምህርት እንዲከታተሉ ከባሕር ማዶ ሰደዷቸው። በወጣቱ ሙላቱ አስታጥቄ ልብ መንበር ላይ የነገሠው ግን የሳይንስ እውቀት ሳይሆን የሙዚቃ ጥበብ ነበርና የማይሆን ነገር ሆነ። ሰዎች በቀደዱላቸው ለመጓዝ ሳይሆን ውስጣቸው የሚፈልገውን ለመሆን ወሰኑ። በውስጣቸው የሚንቀለቀለውን የሙዚቃ ወላፈን በማይሆን ነገር ለማጥፋት ፈጽሞ አልፈለጉም። እናም የተልዕኮ መንገዳቸውን በመቀየር ከሄዱባት ሃገር የማይነጥፈውን የሙዚቃ ጥበብ ለመቅሰም ቆርጠው ተነሱ።
በእንግሊዝ የታሰበላቸውን የቀለም ትምህርት ትተው የጃዝ ሙዚቃን የሚያውድ መዓዛ እየተከተሉ ወደ ሃገረ አሜሪካ አቀኑ። የሙላቱ አስታጥቄ ሕልም በፈረንጆቹ ጃዝ የሙዚቃ ጥማቸውን ማርካት አልነበረም። ይልቁንስ ከዚህ የጃዝ ባሕር ማንም ልብ ያላላትን ወርቃማ ዓሣ ተመልክተው ነበር። ዓሣዋን ለማጥመድ ወደ ባሕሩ ጠጋ ማለት የግድ ነበርና እንደ ኖህ መርከብ የገዘፈውን ጥበባዊ የሙዚቃ መርከባቸውን በልባቸው ይዘው ባሕሯን ማሰስ ጀመሩ። ትክክለኛ ምርጫ፣ ትክክለኛ ጉዞ፣ በስተመጨረሻም ትክክለኛዋን የስኬት ቁልፍ ጨበጡ። በስተመጨረሻም የኢትዮጵያን ውሃ የተጠማችን ዓሣ ከጥበብ ገንዳቸው ይዘው በድል ወደሃገራቸው ተመለሱ። ዓሣ ያለውሃ የሙላቱ አስታጥቄ ልብም ያለሙዚቃ አይሆንላቸውምና ለዓሣዋ የኢትዮጵያን የተቀደሰ ውሃ ለልባቸውም ማረፊያ ይሆን ዘንድ ‹‹የኢትዮጵያ ጃዝ›› የተሰኘ አዲስ የሙዚቃ ስልት አበጁ።
በመሠረቱ የጃዝ የሙዚቃ ስልት የውጪዎቹ ቢሆንም ሙላቱ አስታጥቄን ለየት የሚያደርጋቸው ባሕር ማዶ የተማሩትን የሙዚቃ ስልት ወደ ሃገራቸው በማምጣት ከሃገራቸው ባሕል፣ እሳቤ እና የሙዚቃ ሥርዓት ጋር ተጣጥሞ እንዲሄድ በማስቻል ድንቅ ውሕደትን መፍጠር በመቻላቸው ነው። በዚህ ሥራቸውም የውጪውን የጃዝ ስልት ኢትዮጵያዊ መልክ አላብሰው በአዲስ ሃሳብ የተመሠረተ ሌላ የሙዚቃ ምሰሶ ለማቆም ቻሉ። ‹‹ኢትዮ-ጃዝ›› የተባለውን የሙዚቃ ስልት በመፍጠር የኢትዮጵያን የጃዝ ሙዚቃ ዕድገት ከምንም አንስተው በለመለመ መስክ እንደወደቀች ፍሬ አደረጓት።
ሥራቸው ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለመላው ዓለምም አዲስ ነገርን ይዞ የመጣ ትልቅ ፈጠራ ነበር። በዚህም ከመወደድና ከመደነቅ አልፈው በመላው ዓለም በርካታ የኢትዮ-ጃዝ አፍቃሪዎችን ለማፍራት ቻሉ። ግሩም የፈጠራ ሥራቸውን ለመመልከት የበቃ ነጭ ሁሉ ቆሞ ለማጨብጨብ ይገደዳል። ብርቅዬና የዘመናት የኢትዮጵያ የሙዚቃ ታሪክ መንገድ ጠራጊ የሆኑት ሙላቱ አስታጥቄ ላለፉት 50 እና ከዚያ በላይ ለሆኑት ዓመታት በጃዝ ሙዚቃ ውስጥ ለጃዝ ሙዚቃ ኖረዋል። የዚህ ሙዚቃ መግቢያ ዋነኛው ቁልፍ እሳቸው ጋር ቢሆንም፤ ሕልውናው በእርሳቸው የዘመን ቁጥር ተለክቶ እንዲቀር ብቻ በጭራሽ አይፈልጉም። ከሙዚቃ ሥራቸው ጎን ለጎን ትልቁ የጉዞ መዳረሻቸው እንደሳቸው ያሉ የጃዝ ሙዚቃ ጠቢባንን ማፍራት ነው።
በሥራዎቻቸው የአብራውዝ ግራንት አሸናፊ የሆኑት እኚህ ኢትዮጵያዊ የሙዚቃ ቀማሪ ሊቅ በውጭ ሃገር ቆይታቸው አይረሴ የሆኑ መልካም ጊዜያትን አሳልፈዋል። ወደ አሜሪካን ሃገር በመሄድ የጃዝ ሙዚቃን ከማጥናትም ባሻገር በአሜሪካዋ የበርክሊ የሙዚቃ ኮሌጅ የመጀመሪያው ጥቁር የሙዚቃ ተማሪ ነበሩ። ባላቸው ድንቅ ብቃትና ተሳትፎም በመምህራኖቻቸው ዘንድ ተወዳጅ ነበሩ። ተወዳጅ ሆነው ብቻም አልቀሩ በዚሁ ኮሌጅ የአፍሪካን ትምህርቶች ክፍል አማካሪነትን ሹመት አግኝተዋል። በዚያው ሃገር ሳሉ ብቃታቸውን ለዓለም የሚያሳዩበትና ለሀገራቸው ኩራት ለመሆን የሚያስችላቸውን ሪቫን የሚቆርጡበት ሌላ አጋጣሚ ወደ እርሳቸው ሰተት ብሎ መጣ። ይህ ትልቅ እድል ደግሞ ‹‹ብሮክን ፍላወር›› ከተሰኘው ፊልም ተራራ ስር የመነጨ ጥም አርኪ ሥራ ነበር።
ለዚህ ፊልም ማጀቢያ ይሆን ዘንድ የጃዝ ሙዚቃ እንዲሠሩ ሙላቱ አስታጥቄ ሲጠየቁ አላንገራገሩም፣ ባልችልስ ብለውም ቅንጣት ታህል አልተጠራጠሩም። ይልቁንስ ያስተማሯቸውን ነጮችን አስቀምጠው፣ በጀግንነት ተነስተው ወደፊት ሄዱ። ለፊልሙ የሚሆን ግሩም ሙዚቃም አዘጋጁ። ሥራውም ብዙዎች ያልጠበቁትን ያህል የተለየ ነበር። ትልቅ አድናቆትንም አተረፉ። ይህም ሥራ በዓለማቀፉ የሙዚቃ ባለሙያዎች ዓይን ውስጥ እንዲገቡ አደረጋቸው። አንድ ጥቁር አፍሪካዊ ከነጮች መንደር የሙዚቃ ድግስ ላይ እየተገኘ ከመታደም ውጭ እንደዚህ ከመድረክ ወጥቶ መታየት ባልተለመደበት ወቅት የብዙ መድረኮች ፈርጥ ሆነው ማሳየታቸው አስገራሚ ጉዳይ ነበር። ሥራዎቻቸውን በመመልከት በኢትዮጵያ የጃዝ ሙዚቃ ፍቅር የተነደፉ የውጭ ሃገር ዜጎች ቁጥርም ጥቂት የሚባል አይደለም።
የኢትዮጵያ የጃዝ ሙዚቃ ሊቅ በኢትዮጵያ የጃዝ ሙዚቃ ውስጥ ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ ለኢትዮጵያ የሙዚቃ እድገት ላበረከቱት ጉልህ አስተዋፅዖ በተለያዩ ጊዜያት ልዩ ልዩ ሽልማቶች ተበርክተውላቸዋል። ከሽልማቶችም አልፎ በትውልዱ መካከል ሁሉ ዘመን የማይሽረውን ስጦታ ተጎናጽፈዋል። ለዚህ ትልቅ ውለታቸው በማለትም በሃሮማያ ከተማ አንድ አውራ ጎዳና በስማቸው ተሰይሞላቸዋል። እሳቸው የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆኑ የዓለም ሁሉ ሃብት ስለመሆናቸው ዓለም ሁሉ ይመሰክርላቸዋል። ለዓለም አቀፋዊ የሙዚቃ እድገት ስላደረጉት ታላቅና ጉልህ አስተዋፅዖ፣ በተጨማሪም ኮሌጅ ውስጥ በነበሩበት ወቅት በቀድሞ ተማሪዎች ላይ ላሳዩት አርአያነትም በቦስተን የሚገኘው የበርክሊ የሙዚቃ ኮሌጅ ግንቦት 4 ቀን 2004ዓም የክብር ዶክትሬት ዲግሪ ለመሸለም በቅተዋል። ከዚህም ባለፈ በሥራዎቻቸው የአብራውዝ ግራንት አሸናፊ ሆኖ መገኘታቸው ክብሩ የእርሳቸው ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያውያንና የመላው አፍሪካ ኩራትም ጭምር ነው።
ከቀመሱት ነገር ለሌላውም ማቅመስ ይወዳሉና በ2012ዓም እኚህ ታላቅ ሰው በጎንደር ዩኒቨርሲቲ በመገኘት ልምዳቸውንና የሕይወት ተሞክሯቸውን ለሙዚቃና አርት ተማሪዎች ያካፈሉበት አንድ መድረክ ነበር። እኔም የዚህ ዓምድ አዘጋጅ ይህንን እድል የመቋደስ አጋጣሚውን አግኝቼ ከአዳራሹ ተሰየምኩ። መቼም እኚህ ሰው ስለሙዚቃ በተለይም ስለጃዝ ሲያወሩ የሙዚቃ ጥበብ በእርሳቸው ላይ ቤቷን እንደሠራች ቁልጭ ብሎ ይታያል። በመድረኩ በነበሩ እያንዳንዱ ታዳሚ ልብ ውስጥም የሙዚቃን እውነተኛ ምንነት በማብራራት የሙዚቃ ጽንስ አስቀመጠዋል ለማለት ይቻላል። የኖሩትም ከተምሳሌትነት አልፎ ትልቅ የሕይወት ስንቅ ነው። እናም ከመድረኩ በኋላ እኚህን የጃዝ ንጉሥ የማውራት ሌላ እድል አገኘሁና ጠጋ ብዬ በነበረችን አጭር ቆይታ አንድ ነገር ለማለት ፈለኩ።
ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ እድሜዎን ሙሉ በሙዚቃ ውስጥ ለሙዚቃ ኖረዋል፤ ነገር ግን ከሙዚቃ ርቀው የግል ሕይወት የሚጀምሩበት ጊዜ ከአሁን በኋላ ይኖራል ብለው ያስባሉ? ስል ጠየኳቸው። ጥቂት አሰብ አደረጉና ፈገግ እያሉ ‹‹አዎን›› አሉኝ። እኔም ቀጣዩን ምላሻቸውን ለመስማት እየጓጓሁ ታዲያ መቼ ይሆን ስል ጥያቄዬን አስከተልኩላቸው። ‹‹መብላትና መጠጣት ያቆምኩ እለት ነዋ›› አሉኝ። ነብሴ ከሥጋዬ ተለይታ የሞትኩኝ እለት ማለታቸው ነበር። ብዙ ቢሠሩም ገና ምንም እንዳልሠሩ፣ ለሚመለከታቸው በእድሜ ብዙ የገፉ አዛውንት ቢመስሉም እሳቸው ግን በውስጣዊ መንፈሳቸው ገና ወጣት ናቸው። ቀርቦ ለሚያወራቸው ከጨዋታ አዋቂነታቸው በተጨማሪ ከፊታቸው የሚነበበው ትሕትናቸው ከአጠገባቸው መራቅን አያስመኝም።
በሕይወት እስካሉ ድረስ ዛሬም ነገም ሁሌም አዳዲስ ነገሮችን ለመሥራት መታተራቸው ግድ እንደሆነ ይናገራሉ። እርጅና በሚሉት የሕይወት ሰንሰለት ታጥረው ድካማቸውን እሹሩሩ ለማለት አይወዱም። ‹‹የተጠራሁት ለሙዚቃ ከሆነ እኔ አርፌ የኔን ሙዚቃ ታዲያ ማን ሊሠራልኝ ነው? ሙዚቃ ያለው የእድሜ ብል በቦረቦረው ሰውነታችን ላይ ሳይሆን በልብና ጭንቅላታችን ውስጥ ነውና እነዚህን ሁለት ነገሮች በስንፍና ካላስረጀናቸው በቀር የእድሜያችን ቁጥር ከሙዚቃ ሊለየን አይችልም›› በማለት በወኔ ሲናገሩ ማድመጥ በእርግጥም የሞተን ውስጣዊ መንፈስ ያርቃል። ስለ ኢትዮጵያ የጃዝ ሙዚቃ ቀማሪ የክብር ዶክተር አርቲስት ሙላቱ አስታጥቄና ሰለሥራዎቻቸው ያላነሳናቸው ብዙ ነገሮች ቢኖሩም፣ ለዛሬው ግን ረዥም እድሜን ከጤና ጋር ሰጥቶ ያቆይልን በማለት እናገባድ።
ሙሉጌታ ብርሃኑ
አዲስ ዘመን እሁድ ሚያዝያ 29 ቀን 2015 ዓ.ም