ኢትዮጵያውያን በረዥሙ የሥርዓተ መንግሥት ግንባታ ጉዟቸው፤ ከፍ ያለ የጥበብና የእውቀት ባለቤት ስለመሆናቸው የሚያሳዩ አያሌ አሻራዎች አሉ። የሥነ ሕንፃ፣ የኪነ ጥበብ፣ የቅረጻቅርጽ፣ የሥነ ጽሑፍ፣ የፍልስፍና፣ የስነፈለግ፣… ጥበብ ባለቤት ስለመሆናቸው ብዙ ማመሳከሪያዎች ዘመን ተሻግረው ዛሬም ሕያው ሆነው ይታያሉ። ሌላው ቀርቶ የራሳቸውን ፊደል ቀርጸው፣ የራሳቸውን ዘመን ቀምረው ከሚጠቀሙ ጥቂት የዓለም ሕዝቦች ውስጥ ከቀዳሚዎቹ ተርታ መሆናቸው ግልጽ ነው።
ይሄን እውቀት ግን ዝም ብለው ከፈጣሪ በተሰጣቸው ጸጋ ብቻ ያገኙት አይደለም። ይልቁንም በኢ መደበኛ የትምህርት ሥርዓት (በዋናነት በየቤተ እምነቶች፣ ከፊደል ቆጠራ እስከ ፈጠራ በሚገለጽ መልኩ) በሚሰጡ ትምህርቶች እንጂ። ለዚህም ብራና ፍቀው፣ ቀለም በጥብጠው የከተቧቸው የጥበብ ውጤቶቻቸው ምስክር ይሆናሉ። በዘመናት ጅረት ውስጥ ታዲያ ይሄ ኢመደበኛ የትምህርት ሥርዓት በመደበኛ የትምህርት ሥርዓት እየተተካ ሄደ። ትምህርት ከቤተ እምነቶች ወደ ዓለማዊው ትምህርት ቤት ተሸጋገረ።
ይሄ መልካም የሚባል አገራዊውንም፣ ዓለምአቀፋዊውንም እውቀት መገብየትን፤ በዚህም ኢትዮጵያውያን የራሳቸውን ጥበብ ከሌሎች ጋር አዋህደውና አናብበው ከፍ ያሉ ሥራዎችን እንዲሠሩ ዕድል የፈጠረም ነበር። ይሁን እንጂ በሂደት የትምህርት ሥርዓቱ ከአገራዊ እሴቱ እየተፋታ የውጭው ፍልስፍናና አመለካከት ላይ እየተንጠለጠለ ሄደ። ትውልድንም አገርንም ዘመን አሻግሮ ከፍ ላለ ክብር ያበቃው አገራዊው እውቀት ኋላ ቀር ተብሎ፤ ከውጭ የተገለበጠው እሳቤ በዘመናዊነት ተንቆለጷጵሶ የትምህርት አውዱን ዙፋን ተቆናጠጠ።
ሆኖም ዓሣ ከባህሩ ከወጣ ሕይወቱ እንደማይቀጥል ሁሉ፤ የኢትዮጵያም የትምህርት ሥርዓት ከባህሉ በተፋታ ቁጥር አገራዊ ፋይዳው እየወረደ፤ የእውቀትና የፈጠራ መድረክነቱ እየነጠፈ፤ በአንጻሩ የውጭው አስተሳሰብ ጥገኛ እየሆነ ሄደ። ይሄም ትውልዱ ከመፍጠር ይልቅ መኮረጅ ላይ እንዲያተኩር ብቻ ሳይሆን፤ ከክፍል ክፍል የሚደረጉ ሽግግሮችን ሳይቀር በፈተና ኩረጃ ላይ እንዲንጠለጠል አደረገው። ይሄን የኩረጃ መንፈስ ከፍ ያደረገው ደግሞ በትምህርት ሥርዓቱ ውስጥ ያሉ ተዋናዮች ጭምር ችግሩን አይቶ እንዳላየ ማለፍ ነበር።
ይህ የትምህርት ሥርዓቱ በዚህ ደረጃ ከራስ እውቀትና እሴት መፋታት የፈጠረው አጠቃላይ የትምህርት ውድቀት ታዲያ፤ ትውልድን ብቻ ሳይሆን አገርንም ከፍ ያለ ዋጋ አስከፍሏል። የዚህ ትልቁ ማረጋገጫ የሆነው ደግሞ የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ብሔራዊ ፈተና እንደ አገር በተለየ መልኩ በየዩኒቨርሲቲዎች እንዲሰጥ መደረጉ ነበር። ምክንያቱም በዚህ ፈተና ኩረጃ እንዳይካሄድ በመደረጉ ብቻ ከተፈተኑ አጠቃላይ ተማሪዎች ውስጥ ሦስት በመቶ ያህሉ ብቻ የፈተናውን ሃምሳ በመቶ መመለስ መቻላቸው ነው።
ይሄ ደግሞ እንደ አገር ያለው የትምህርት ሥርዓት ምን ያህል የታመመ እንደሆነ በግልጽ ያረጋገጠ ሲሆን፤ ችግሩን ቀደም ብሎ መለየት የተቻለ ቢሆንም በዚህ ልክ ተገንዝቦ ለመፍትሄው ያልተሠራ እንደመሆኑ በቀጣይ ለችግሩ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት እንዲሠራበት ያደረገ ነበር።
ለዚህ ሥራ መልካም አጋጣሚ የሚፈጥረው ደግሞ፣ ከአገራዊ እሴቶችና እውቀቶች የተፋታው የትምህርት ሥርዓት በአገራዊ እሴቶችና እውቀቶች ቅኝት እንዲታገዝ የሚያስችል፤ ለተማሪዎች ክህሎትና ሥነምግባር ትኩረት የሚሰጥ፤ የባለድርሻዎችን ብርቱ ድጋፍና ተሳትፎ የሚያሳድግ፤ የተማሪዎችን የመመራመርና የመፍጠር አድማስን የሚያሰፋ፤… የትምህርት ፖሊሲ መቀረጹ ነው። ይሄን ውጤታማ ለማድረግም በትምህርት ቤቶች፣ በመምህራን፣ በትምህርት ግብዓቶች እና በራሱ በመማር ማስተማርና ምዘና ሥርዓቱ ላይ እየተወሰዱ ያሉ አበረታች ርምጃዎች መኖራቸውም የሚበረታታ ነው።
የእነዚህ ድምር ውጤት በጠንካራ የዘርፉ አሠራርና አመራር ተደግፎ መሄድ ከቻለ፤ የትምህርት ሥርዓቱን ስብራት መጠገን ብቻ ሳይሆን የተሻለ አገራዊ አቅም ለመፍጠር በሚደረገው ጥረት ውስጥ ይሄን የሚሸከም የመፍጠርና የማሰላሰል አቅም ያለው ትውልድ ማፍራት ያስችላል። በመሆኑም ትምህርት ትውልድን በእውቀት እና በሥነምግባር የመቅረጽ ሚናውን እንዲወጣ የማድረግ ጅምር ሥራዎች ሊጎለብቱ፤ ለዚህም ሁሉም ባለድርሻ ኃላፊነቱን በአግባቡ ሊወጣ ይገባል!
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 30/2015