የፓርኪንሰን ህመም ከግዜ ወደ ግዜ እየባሰበት የሚሄድና እንቅስቃሴን የሚያውክ ከባድ የአእምሮ ህመም ሲሆን፣ በአብዛኛው እድሜያቸው ከ60 ዓመት በላይ የሆኑ ሰዎችን ያጠቃል።የህመሙ ዋነኛ መንስኤም በአእምሮ ውስጥ የሚገኘው ዶፓሚን የተሰኘው ንጥረ ነገር ማነስ መሆኑን የጤና ባለሞያዎች ይናገራሉ።
በቅርቡ በህመሙ ዙሪያ የተካሄዱ ጥናቶች ባይኖሩም፣ በኢትዮጵያ የፓርኪንሰን ታማሚዎች መጠን እየጨመረ መምጣቱን ሌሎች መረጃዎች ይጠቁማሉ።ህመሙ በአምስት አመቱ የጤና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ውስጥ እንዲካተት ተደርጎ እየተሰራ ይገኛል።ይሁንና እንደ ሌሎች ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች እኩል ትኩረት እንዳልተሰጠው ይጠቆማል።
የጤና ሚኒስቴር የፓርኪንሰን ህሙማን ማህበር ከተቋቋመበት ከ2003 ዓ.ም ጀምሮ በተለይ ከህመሙ ጋር በተያያዘ ያለውን የግንዛቤ ክፍተት በመሙላት ረገድ እየሰራ ይገኛል።የህመሙ ተጠቂዎችም ስለበሽታው በሚገባ አውቀው ህመሙ ከሚያሳድርባቸው የተስፋ መቁረጥ ስሜት እንዲወጡና ራሳቸውን እንዲንከባከቡ ድጋፍ እያደረገ ነው።
በአሁኑ ወቅት ደግሞ ማህበሩ ከፍተኛ የአቅም ችግር ላለባቸው ህሙማንና የማህበሩ አባላት ድጋፍ እያደረገ ሲሆን፣ ህሙማኑን በዘላቂነት ለመደገፍ የሚያስችል የህሙማን እንክብካቤና መርጃ ማእከል ለመገንባት ፍላጎት ቢኖረውም የመስሪያ ቦታ ማግኘት ግን ፈተና ሆኖበታል።
የፓርኪንሰን ሰፖርት ኦርጋናይዜሽን መስራ ችና ዋና ስራ አስኪያጅ ወይዘሮ ክብራ ከበደ እንደሚናገሩት፤ ማህበሩ ከመመስረቱ በፊት የፓርኪንሰን ህመመምን አስመልክቶ በህብረተሰቡ ዘንድ በቂ ግንዛቤ አልነበረም።ስለፓርኪንሰን ህመም በቂ መረጃ ባለመኖሩም በተለይ የህመሙ ተጠቂዎች ወደ ህክምና ተቋም ሄደው የመታከመም አድል አልነበራቸውም።የፓርኪንሰን ታማሚ ከሙሉ ጤናማነት ወደ ሙሉ ህመምተኝነት የሚለወጥ በመሆኑ ህመሙ በታማሚውና ታማሚውን በሚንከባከበው ቤተሰብ ላይ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተፅእኖ ሲያሳድር ቆይቷል።
እንደ ስራ አስኪያጇ ገለፃ ፤ማህበሩ የተመሰረተው የፓርኪንሰን ህመምን አስመልክቶ በቂ መረጃ ባለመኖሩና ይህንንም ተከትሎ ታማሚዎቹ ትኩረት በመነፈጋቸው ነው።ማህበሩም ለህሙማን በቂ ግንዛቤ ለመስጠትና ድጋፍ ለማድረግ እየሰራ ይገኛል።
ማህበሩ በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ እየተንቀሳቀሰ የሚገኝ ሲሆን፣ እስካሁንም 600 የፓርኪንሰን ታማሚ አባላትን በማቀፍ ድጋፍና እንክብካቤ እያደረገ ነው።በአሁኑ ወቅትም በተለይ የፓርኪንሰን ህሙማን በአንድ ማእከል እንክብካቤና ድጋፍ የሚያገኙበትን ሁኔታ ለመፍጠር እየሰራ ሲሆን፣ለዚህም ሁሉም አካላት ትኩረት እንዲሰጡ እየጠየቀ ነው።
የፓርኪንሰን ፔሸንትስ ሰፖርት ኦርጋናይዜሽን ኢትዮጵያ ዳይሬክተር አቶ ታለሞስ ዳት እንደሚሉት ማህበሩ አስካሁን ድረስ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ቤት ተከራይቶ እየሰራ ነው።የህሙማን መንከባከቢያና መርጃ ማእከል ለማቋቋም እየሰራ ሲሆን፣ ለእዚህም እንዲሆነው ከሶስት አመት በፊት ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ 4ሺ ካሬ ሜትር ቦታ እንዲሰጠው በደብዳቤ ጠይቋል።
ይሁንና የድርጅቱ የቦታ ጥያቄ የመሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ ለዚህ አይነቱ ዓላማ ቦታዎችን ለማህበራት ለግዜው መስጠት በማቆሙ የተነሳ ምላሽ ሊያገኝ እንዳልቻለ ዳይሬክተሩ ይገልጻሉ።ጥያቄው አሁንም እንደሚቀጥል ጠቅሰው፣ ጥያቄው ምላሽ የማያገኝ ከሆነም ማህበሩ ከተለያዩ ወገኖች የገንዘብ ድጋፍ የሚያገኝበት ሁኔታ ከተፈጠረ ማህበሩ ሌላ ቦታ ማግኘት የሚያስችል አማራጭ እንደሚፈልግ ይናገራሉ።
እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ፤ የፓርኪንሰን ህሙማን በአንድ ማእከል ተሰባስበው እርዳታ የሚያገኙበት ማእከል መገንባት አስፈላጊ በመሆኑ ለማእከሉ ግንባታ የመንግስትና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እንዲሁም የሁሉም ህብረተሰብ ድጋፍ ያስፈልጋል።በክልሎች ህመሙን አስመልክቶ በቂ ግንዛቤ ባለመኖሩ ቅርንጫፍ ቢሮዎችን መክፈት ስለሚያስፈልግ ለዚህም ተመሳሳይ ድጋፍ መደረግ ይኖርበታል።
ዳይሬክተሩ እንደሚሉት፤ ማእከሉን ለመገንባት የሚያስችል ረቂቅ ፕሮፖዛል ተሰርቷል።በዚህ መነሻነትም ለግለሰቦችና ለተለያዩ ተቋማት ረቂቅ ፕሮፖዛሉን በማስተዋወቅ ገንዘብ ለማሰባሰብ እየተሰራ ነው።በአጭር የፅሁፍ መልእክትም የገንዘብ ድጋፎችን ለማሰባሰብ ጥረት እየተደረገ ይገኛል። ከሚመለከታቸው የክልል ርእሰ መስተዳደሮችና ባለስልጣናት ጋርም በመነጋገር ተጨማሪ ድጋፎችን ለማግኘት ጥረቶች እየተደረጉ ናቸው።
ማእከሉ ከተገነባ ህሙማን በማእከሉ የማገገሚያ ህክምና አግልግሎት የሚያገኙበት ሁኔታ ይፈጠራል።አጠቃላይ የህክምና አገልግሎቶችን በአንድ ማእከል በቀላሉ እንዲያገኙም ይረዳል።በተጨማሪም ህሙማን በማእከሉ የመድሃኒት አገልግሎት፣ በህመሙ ዙሪያ የእውቀት ክፍተትን ሊሞሉ የሚችሉ ስልጠና እና የስነልቦና ድጋፎችን እንዲያገኙ ያግዛቸዋል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሰቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የነርቭ ህክምና መምህር ዶክተር ግርማ ደልታታ፤ ከሰላሳ አመት በፊት በተካሄደ ጥናት በኢትዮጵያ የፓርኪንሰን ታማሚዎች ቁጥር አነስተኛ እንደነበር አስታውሰው፣ ‹‹በአሁኑ ወቅት በፓርኪንሰን ዙሪያ የተካሄዱ ጥናቶች ባይኖሩም የታማሚዎች መጠን እንደሚጨምር ይገመታል››ይላሉ።
እንደ ዶክተር ግርማ ገለፃ፤ የፓርኪንሰን ታማሚዎች በስፋት ከሚያጋጥሟቸው ችግሮች ውስጥ የመድሃኒት፣ የማገገሚያ እና ህክምና አገልግሎት እጥረት ይገኙበታል።በግንዛቤ እጥረት አብዛኛዎቹ የፓርኪንሰን ታማሚዎች ወደ ህክምና ተቋማት ስለማይሄዱ ህክምናውን በሚፈለገው ልክ እያገኙም አይደለም።በመሆኑም በፓርኪንሰን ህመም ዙሪያ ለህብረተሰቡ ግንዛቤ መፍጠር፣ ህክምናውን ተደራሽ ማድረግና ታማሚዎች ወደ ህክምና ቦታ እንዲመጡ ማድረግ ይገባል።
ይህን ለመለወጥ በፓርኪንሰን ህሙማን ማህበር በኩል በርካታ ተግባሮች ተከናውነዋል ።በተለይ የፓርኪንሰን ህመምን በተመለከተ ለታማሚዎችም ሆነ ለህብረተሰቡ ግንዛቤ በመፍጠር ረገድ ትልቅ አስተዋፅኦ ሲያበረክት ቆይቷል።
በአሁኑ ወቅትም አቅም የሌላቸውንና ድጋፍ የሚሹ የፓርኪንሰን ታማሚዎችን ለዘለቄታው ለመርዳት የሚያስችል ማእክል ለመገንባት እቅድ መያዙን ዶክተር ግርማም ጠቅሰው፣ ማህበሩ በራሱ አቅም ብቻ ማእከሉን ማቋቋም እንደማይችል ይገልጻሉ።ማእከሉን እውን ለማድረግ የሁሉም ህብረተሰብ ድጋፍ እንደሚያስፈልግ ጠቅሰው፣መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችም ድጋፎችን ሊያደርጉ እንደሚገባ ይጠቁማሉ።
የጤና ሚኒስቴር የክሊኒካል አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አባስ ሀሰን ላለፉት አመታት በሀገሪቱ በዋናነት ትኩረት ተሰጥቶ ሲሰራ የቆየው በተላላፊ በሽታዎች ላይ መሆኑን ጠቅሰው፣ከቅርብ አመታት ወዲህ ዋነኛ የህብረተሰብ ጤና ችግሮች እየሆኑ በመጡት ተላላፊ ያልሆኑ በበሽታዎች ላይ ትኩረት ተሰጥቶ መስራት መጀመሩንም ይናገራሉ።
እንደ አቶ አባስ ገለፃ ፤የፓርኪንሰን ህመም ልክ እንደ ሌሎቹ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ልዩ ትኩረት የተሰጠው ባይሆንም፣ በአምስት አመቱ የጤና ትርንስፎርሜሽን እቅድ ውስጥ ተካቶ በተለይ ማህበረሰቡ በበሽታው ላይ በቂ ግንዛቤ እንዲኖረው እየተሰራ ነው።በዚህ ረገድም የፓርኪንሰን ፔሸንት ሰፖርት ኦርጋናይዜሽን እያደረገ ያለው ጥረት ይደነቃል፤ ይህን ጥረት መንግስት ሁሌም ይደግፋል።
መንግስት በጤና ሚኒስቴር በኩል የዜጎችን ጤና የማስጠበቅ ኃላፊነት አለበት።ይህን ኃላፊነቱን ለመወጣት ግን እንደ ፓርኪንሰን ያሉ የህሙማን ማህበራት ያስፈልጋሉ።ህብረተሰቡና የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላትም በጋራ ሊሰሩ ይገባል።በሽታውን በተመለከተ ግንዛቤ ለመፍጠር በጤና ሚነስቴር በኩል የተጀመሩ ስራዎች ያሉ ቢሆንም፣ በተመሳሳይ በመንግስት ደረጃ ያሉ የጤና ተቋማትም ይህን ስራ እንዲደግፉ ማድረግ ይገባል።
ከፓርኪንሰን ህመም ህክምና አገልግሎትና መድሃኒት ጋር በተያያዘ የሚነሱ ችግሮችን ለመፍታትም በመንግስት በኩል አስፈላጊው ጥረት እንደሚደረግ ጠቅሰው፣የማገገሚያ ህክምና አገልግሎት ችግርን ለመፍታትም አግልግሎቱ ከሆስፒታሎች ጋር እንዲተሳሰር መደረጉን ይገልጻሉ።አገልግሎቱ በሁሉም የጤና ተቋማት ተጠናክሮ እንዲሰጥም አስፈላጊው ጥረት እንደሚደረግም ያመለክታሉ።
በዋናነትም ማህበሩ ህሙማን የሚረዱበትና እንክብካቤ የሚያገኙበት ማእከል እንዲገነባና አገልግሎት እንዲሰጥ በጤና ሚኒስቴር በኩል አስፈላጊው ድጋፍ እንደሚደረግ አቶ አባስ ጠቅሰው፣ ማህበሩ ማእከሉን ማቋቋም የሚችል ከሆነ ህሙማንን በራሱ አቅም መርዳትና መንከባከብ የሚያስችለው በመሆኑ መንግስት ላይ ያለውን ጫና ያቃልላል ብለዋል።ሌሎች የመንግስት ሴክተር መስሪያ ቤቶችም ለጉዳዩ ትኩረት እንዲሰጡ ጤና ሚኒስቴር የበኩሉን ጥረት እንደሚያደርግም አረጋግጠዋል።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 22/2011
በአስናቀ ፀጋዬ