በትልቅ ጠረጴዛ ዙሪያ እየዞረች ፈጠን ፈጠን በማለት ሻማዎቹን በሥርዓት ሰድራ ለማስቀመጥ ትጣደፋለች፡፡ ቅልጥፍናዋ ልክ እንደምታመርታቸው ሻማዎች ደማቅና እንዲቀርቧት የሚጋብዝ ነው፡፡ ከ ወ/ ት ናድያ ሰይድ ጋር የተገናኘነው ሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ባዘጋጀው የሥራ ፈጠራ ኤግዚቢሽን ላይ ምርቶቿን ይዛ በቀረበችበት ወቅት ነው፡፡
የሰንላይት ሻማ አምራች ድርጅት መስራችና ስራ አስኪያጅ የሆነችው ናዲያ ከሰባት ዓመት የአረብ ሀገር ቆይታ ተመልሳ ነው ከሁለት ጓደኞቿ ጋር ወደዚህ ሥራ የገባችው፡፡ አሁን ላይ በተለያዩ ቦታዎች ቅርንጫፍ በመክፈት ከተለመደው ሻማ አንስቶ የተለያየ ሽታ፣ ቅርጽና ቀለም ያላቸውን ሻማዎች አምርተው በመሸጥ ላይ ናቸው፡፡
ናድያ በፀሀፊነት ሙያ ተምራ ብትመረቅም፤ በተማረችው ሙያ ዘርፍ ተቀጥራ እንጀራ ሳትበላበት በ1997 ዓ.ም ወደ አረብ ሀገር የተሰደደችው፡፡ ከሰባት ዓመት የአረብ ሀገር ቆይታ በኋላ በአባቷ መታመም ምክንያት ወደ ሀገሯ መምጣት ግድ ሆነባት እና ተመለሰች፡፡
ከስደት መልስ በተመረቀችው ሙያ በአንድ አስጎብኚ ድርጀት በመዝገብ ቤት እና ጉዳይ አስፈጻሚነት ተቀጥራ መስራት ጀመረች፡፡ በሥራዋ አማካኝነት አሁን አብራት ከምትሰራው ጓደኛዋ ጋር ተዋውቀው ነው ሻማ ወደ ማምረት ሥራ የገቡት፡፡
“በአስጎብኚ ድርጅቱ ከተቀጠርኩ በኋላ አዳዲስ ሰዎችን ለመተዋወቅ እድሉን አገኘሁ። አሁን ከእኔ ጋር በሽርክና የምትሰራው ጓደኛዬ ባጋጣሚ ለምን የራሳችንን የግል ሥራ አንሰራም የሚል ጥያቄ አቀረበችልኝ፡፡ በምን ዘርፍ ልንሰራ እንችላለን የሚለውን እያሰብን እያለ ነበር በሻማ ሥራ ስልጠና የሚሰጥ ድርጅት ሜክሲኮ አየንና ከፍለን ሰለጠን፤ ከዛም ወደ ሥራው ገባን፡፡” ትላለች፡፡
ስልጠናውን ካጠናቀቅን በኋላ ናዲያ ከአረብ አገር ሰርታ የተወሰነ ገንዘብ ስለነበራት ጓደኛዋን ደግሞ ቤተሰብ ረድቷት የሻማ መስሪያ ማሽን ገዙና ቤት ተከራይተው ወደ ስራው ገቡ። ምርት ማምረቱንም አንድ ብለው ጀመሩ፡፡ በወቅቱ ሲያመርቱ የነበረው የተለመደውን የሻማ አይነት ብቻ ቢሆንም፤ ቀስ በቀስ የምርት አይነታቸውን ለማስፋፋት ቻሉ፡፡
“ስንጀምር በተለምዶ እቤት ውስጥ የሚበሩ ሻማዎችን ነበር የምናመርተው፡፡ ሻማዎቹን የምናሽግበት ካርቶን እንኳን ስላልነበረ ስምንት ፍሬ በፌስታል እያሰርን መርካቶ እየወሰድን እናስረክብ ነበር፡፡ በዚህ ሁኔታ እየሰራንም ለምንድነው ተደራጅታችህ የመስሪያ ቦታ የማትወስዱት የሚል ሀሳብ ሰዎች አቀረቡልን፡፡” ስትል ትገልጻለች፡፡
በተሰጣቸው ምክር መሰረት ወደ ወረዳ ቀርበው ቦታ እንዲሰጣቸው የጠየቋቸው የወረዳ ሰዎችም መጥተው የሚሰሩትን ሥራ ከተመለከቱ በኋላ መስሪያ ቦታ ተሰጣቸውና ሥራቸውን አስፋፍተው መስራት ጀመሩ፡፡ ከዛ በኋላ ማሸጊያ ካርቶን በማዘጋጀት ሻማዎችን በካርቶን አሽገው ወደ መሸጥ ገቡ፡፡
ወደ ሻማ ማምረት ሥራ በሚገቡበት ወቅት መነሻ ካፒታላቸው 50 ሺህ ብር እንደነበር ትናገራለች። አሁን ላይ ከሶስት መቶ ሺህ ብር በላይ ካፒታል መድረስ ችለዋል፡፡
ከዚህ በፊት ሻማዎችን በተለያየ ቅርጽ፣ ቀለም እና ሽታ አምርቶ መሸጥ በሀገራችን ስላልተለመደ ቅርጽ ማውጫዎቹን በሀገር ውስጥ ማግኘት አስቸጋሪ ነበር፡፡
ሆኖም ናድያ እንግሊዝ ሀገር ያሉ ጓደኞቿ የተለያዩ ቅርጽ ማውጫዎችን ልከውላት ከተለመደው ቅርጽ ውጭ ሻማን ወደ ማምረት ገቡ፡፡
ከዚህ በፊት ቅርጽና ሽታ ያላቸው ሻማዎች በሀገራችን የሚሸጡ ቢሆንም፤ ከውጭ ሀገራት ነበር የሚገቡት፤ አሁን ላይ ግን ሀገር ውስጥ ማምረት ስለተቻለ የማስገባት ሁኔታው የቀነሰበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ ቅርጽ ማውጫ እቃዎቹ በሀገር ተመርተው ለገበያ የሚቀርቡ ቢሆንም ትንሽ ጥራት ላይ የሚቀር ነገር አለው ትላለች፡፡
ወደ አረብ ሀገር ተመልሳ ለመሄድ አስባ ዛሬ ነገ ስትል ባጋጣሚ ወደ እዚህ ሥራ የመግባት እድሉን ያገኘችው ናዲያ፤ “አንዳንዴ ነገሮች እንደተፈለገው ስለማይሆኑ እንጂ ለመስራትም ሆነ ለመኖርም እንደ ሀገር የሚሆን የለም፡፡ በዛ ላይ ብንሰደድም በመጨረሻ ተመልሰን መጥተን የምንሰራው ሀገር ላይ ነው፡፡ በተለይ ደግሞ የራስ ነገር ኖሮ መስራት ከተቻለ ማን እንደሀገር፡፡” ስትል ትናገራለች፡፡
የእነ ናዲያ ድርጅት ከተመሰረተ ስድስት ዓመታትን ያስቆጠረ ሲሆን፣ በእነዚህ ዓመታት አንድ አይነት ሻማ ከማምረት ወጥቶ የተለያየ ቅርጽ ያላቸውን ወደ ማምረት ተሸጋግሯል። ሌላው በአዲስ አበባ ከተማ የተለያዩ ቅርንጫፎችን በመክፈት በጅምላ ለሱቆች ያቀርባሉ። የሥራ ትዕዛዝ በብዛት በሚኖርበት ወቅት ደግሞ በግዚያዊነት አራት ሰራተኞችን ቀጥረው ያሰራሉ።
ምናልባት ውጭ ሀገራት ኖሮ የመጣ፣ ለሽታ ወይም ለተለየ ዝግጅት ካልሆነ ዘመናዊ ሻማዎችን የመጠቀም ባህሉ በጣም ዝቅተኛ ቢሆንም፤ ናዲያ ምርቶቿን ለመሸጥ የተለያዩ መንገዶችን ከመሞከር አልተጠቆጠበችም።
በዚህም ሻማዎቿን ለሱቆች ከማስረከብ በተጨማሪ፤ ኢኮማኮ፣ ኬ ኢትዮጵያ እና ሌሎች ድርጅቶች ጋር ግንኙነት በመፍጠር ባለ ኮከብ ሆቴሎች ላይም የባዛር ዝግጀት ሲኖር ይዛ ትቀርባለች፡፡
አሁን ላይ የተለምዶ ሻማዎችን ወደ ክልሎች ነው የምንልከው። ባለፈው ዓመት ደግሞ በሴት ነጋዴዎች ማህበር አማካኝነት ምርቶቿን ታንዛኒያ ወስዳ ማስተዋወቋን ትናገራለች። በቀጣይ ሕልሟ በስፋት አምርቶ ለአፍሪካ እና ለዓለም ገበያ ምርቶቹን ኤክስፖርት ማድረግ እንደሆነም ትገልጻለች፡፡
“ከጀመርንበት ግዜ አንጻር ሲታይ አሁን ላይ የሻማው ግብአት በጣም ውድ ነው፡፡ ይሄ ደግሞ የሻማ ምርቶች ላይ የዋጋ ጭማሪ እንዲኖር ያስገድዳል። ለዚህ መፍትሄ መሆን የሚችለው ግብዓቱን በስፋት ማስገባት ቢቻል የሻማውም ዋጋው ይቀንሳል፡፡ ለዚህ ደግሞ ቢያንስ እንደ እኔ ሻማ አምራች የሆኑ ድርጅቶች በማህበር ተደራጅተን የሻማ ግብአት በስፋት የምናስገባበት እድል ቢመቻች ሻማን በቅናሽ ለገበያ ለማቅረብ እና ኤክስፖርት ለማድረግ ይረዳል ፡፡” የሚል እምነት አላት ፡፡
ሌላኛዋ በዝግጅቱ ላይ ያገኘናት ሥራ ፈጣሪ ወ/ት በእምነት ግርማ ትባላለች፣ የልብስ ዲዛይነር ስትሆን፤ የሀገር ልብሶችን ቦርሳዎችን እና በአፍሪካ ጨርቅ የተሰሩ ልብሶችን ሰርታ ትሸጣላች። በእምነት ተወልዳ ያደገችው በኦሮሚያ ክልል ሲሆን፤ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን እዛው በትውልድ ቦታዋ ካጠናቀቀች በኋላ ነበር አዲስ አበባ መጥታ የቴክኒክና ሙያ ትምህርት ልትማር የቻለችው፡፡
በእምነት ምንም እንኳ ዲዛይነር ሆናለሁ ብላ አስባበት ባታውቅም ከልጅነቷ ጀምሮ ለሙያው የተለየ ፍቅር እንደነበራት ታስታውሳለች ፡፡ በእቤት ውስጥ የተለያዩ ዳንቴሎች እና የፌስታል ቦርሳዎችን ታላቅ እህቷ እያሳየቻት ትሰራ ነበር፡፡ አዲስ አበባ የመጣችው በሌላ የትምህርት ዘርፍ ለመማር ነበር፤ ነገር ግን ባረፈችበት የመኖሪያ አካባቢዋ በአጋጣሚ የቴክኒክና ሙያ ስለነበር በጋርመንት ለመማር ወሰነች፡፡
“ወደ ኮሌጅ የገባሁት በ2009 ዓ.ም ነበር፤ ከዚህ በፊት የእጅ ስራዎችን የመስራት ዝንባሌው ስለነበረኝ ጋርመንት ላይ ለመማር አልከበደኝም። ኮሌጅ እየተማርኩ ባለሁበት ወቅት ቤተሰብ የልብስ ማሽን ስለገዛልኝ፤ አንዳንድ ትእዛዞችን እየተቀበልኩ እቤቴ ውስጥ እሰራ ነበር፡፡ ከተመረኩ በኋላ ደግሞ አንዳንድ ቦታዎች ላይ ተቀጥሬ ሰርችያለሁ፡፡” ትላለች፡፡
“ቴክኒክና ሙያ ገብቼ መማሬ በልምድ ከሚገኝ እውቀት በላይ በሙያው ዘርፍ ያሉ አሰራሮችን እንዳውቅ እና ዓለም አቀፍ አሰራሮችን ለመረዳ አስችሎኛል፡፡ ምናልባት ባልማር በልምድ ላውቅ እችላለሁ፡፡ መማሬ ደግሞ የበለጠ አካዳሚካል እውቀት ኖሮኝ እንድሰራ እና በዘርፉ ከዓለም አሰራሮች ጋር እንድግባባ እድል ሰጥቶኛል፡፡” ትላለች፡፡
“ተቀጥሬ መስራቴ የበለጠ ሀገርኛውን ዲዛይን አወጣጥ እንዳውቅ አድርጎኛል ፤ በትምህርት የቻይና ወይም የሌሎች የዓለም ሀገራት ዲዛይንን የማውቀው በንድፈ ሀሳብ ደረጃ ሊሆን ይችላል ፡፡ ወደ ስራ ስገባ እነዚህን ንድፈ ሀሳቦች ወደ ሀገርኛው መቀየር እንዳለብኝ እና በሀገራችን የሚፈለገው የልብስ አይነት እንድለይ እድል ሰጥቶኛል ፡፡” ስትል ትገልጻለች፡፡
ተመርቃ ከወጣች በኋላ በልብስ ቤቶች፣ የትምህርት ቤትና ሌሎች መለዮዎች በሚሰፉባቸው ቤቶች ተቀጥራ ሰርታለች። አሁን ላይ የራሷን ልብስ ቤት ከፍታ ከልጆች እስከ አዋቂዎች ባህላዊ ልብስ ትሰራላች ፤ በተጨማሪነት ደግሞ የሴቶች ቦርሳ እንዲሁም ለሕጻናት የደብተር መያዣ የጨርቅ ቦርሳዎችን ታዘጋጃለች፡፡
ሥራ ስትጀምር እቤት ውስጥ ነበር ሰርታ የምታስረክበው፡፡ ደንበኞቿ እየሰፉ ሲመጡና ሱቅ የመክፈት አቅሙን ስታገኝ የራሷን ሱቅ ከፍታ መስራት ጀመረች፡፡ በራሷ ሱቅ በግል ከመስራት በተጨማሪ እድሉን ስታገኝ አብረዋት ከተማሩ ጓደኞቿም ጋር በሽርክና ትሰራለች። ሌላው የምትሰራቸውን ልብሶች እና ቦርሳዎች በሱቆቿ ከመሸጥ ባለፈ የተለያዩ ባዛሮች ሲዘጋጁ ይዛ በማቅረብ የማስተዋወቅ እና የመሸጥ ስራ ትሰራለች፡፡
አዳዲስ ፈጠራዎች ለማግኘት ማህበራዊ ሚዲያዎችን እንደ ግብዓት እንደምትጠቀም የምትገልጻው በእምነት፤ ያሉ ችግሮችን በማጥናት ለእነሱ መፍትሄ የሚሆኑ የፈጠራ ሥራዎችን ለመስራት እንደምትሞክር በመግለጽ፤ ነባር ስራዎችን በማየት አዲስ ስራዎችን ትሰራለች፡፡
“የሀገር ውስጥ ምርቶችን በመጠቀም ረገድ ገበያው ጥሩ የሚባል ነው፡፡ በማህበራዊ ሚዲያዎች የምናያቸውን ልብሶች ወደ ሀገር ውስጥ ለማምጣት ትንሽ ዋጋው ወደድ ይላል፡፡ ስለዚህ ደንበኞችን ለመሳብ የማያቸውን የውጭ ሀገር ምርቶች ተክቼ ለመስራት እጥራለሁ። ምክንያቱም እኛ የምንሰራው ድሮ እናቶቻችን በሚጠቀሙበት የክር አይነት ነው፡፡ ይህ ደግሞ ከጥራትም ከዋጋም አንጻር የተሻለ ነው፡፡”ስትል ትገልጻለች፡፡
በሥራዋ የሚያጋጥማትን ተግዳሮት የምታነሳው በእምነት፤ አንዳንዴ ደንበኞች ፈልገው ይሁን ወይም በእራሷ ምርጫ ለመስራት ስትፈልግ የምትፈልገውን የቀለም አይነት ያለማግኘት ቸግር አለ፡፡ “በዛ ወቅት ከቻይና የሚመጡ ጨርቆችንም ለመጠቀም እሞክራለሁ። ነገር ግን ጨርቁ የጥራት ችግር የሚኖረው ከሆነ ደንበኞች ቢገዙትም ስለማይቆይላቸው በሌላ አይነት ምርጫ እንዲተኩት አደርጋለው። “ትላለች፡፡
በእራሷ ሰፍታ ከምትሸጣቸው የልብስ አይነቶች በተጨማሪ፤ የደንበኛቿን ፍላጎት መሰረት በማድረግ የተሰሩ ልብሶችን ጎን ለጎን አምጥታ ትሸጣላች፡፡ ዋና የሚባለው የሥራ ግዜዋ ከሰኞ እስከ ቅዳሜ ባሉ ቀናት ሲሆን፤ አንዳንዴ ወደ መኖሪያ ቤቷ አምጥታ ምሽት ላይ ትሰራለች። በርከት ያሉ ትዕዛዞች በሚመጡበት ወቅት ደግሞ ለጓደኞቿም እንደምታስተላልፍ ትናገራለች፡፡
ለደንበኞች ምቹ ነገር መፍጠር እና ጥራት ያለው ነገር መስራት ከተቻለ ልብሱን ወዶት ሌላ ደንበኛም እንዲመጣ ይጋብዛል፡፡ ስለዚህ ቀጣይ እቅዷ ደንበኞች ሊደሰቱበት የሚችሉባቸውን ምርቶች በመስራት፤ ልብሶቹን በክልሎች በማስተዋወቅ እምርታ ለመላክ እቅድ አላት፡፡
“ሌሎች ችግሮች ያሉ ቢሆንም፤ ስራዎቼን ለማስፋፋት እቅድ ስላለኝ የመስሪያ ቦታ ትብብር ቢደረግ መልካም ነው፡፡ ምክንያቱም በቀን የቤት ኪራይ ከሚገኘው ገቢ ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ አለው፡፡ ምናልባት ከመንግስት በኩል የመስሪያ ቤቶች በቅናሽ የሚመቻቹበት ሁኔታ ቢኖር መልካም ነው፡፡” ትላለች፡፡
የተለያዩ ባዛሮች እየተዘጋጁ እንደሆነ በመግለጽ፤ በቀጣይም እንደዚ አይነት ኤግዚቢሽኖች በስፋት የሚዘጋጁበት ሁኔታ ቢመቻች ምርቶቻችን ለማስተዋወቅ እድል ይፈጥራል በማለት ትናገራለች፡፡
አመለወርቅ ከበደ
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ታኅሣሥ 8 ቀን 2017 ዓ.ም