በኢትዮጵያ ሕዳርና ታኅሳስ የወባ ስርጭት በከፍተኛ ደረጃ የሚጨምርባቸው ወራቶች ናቸው። ለዛም ነው በጤና ሚኒስትር፣ በክልል ጤና ቢሮዎችና በሌሎች አጋር አካላት በኩል በየዓመቱ የተጠናከረ ወባን የመከላከልና የመቆጣጠር ሥራ አስቀድሞ የሚከናወነው። በተያዘው ዓመትም ኢትዮጵያን ጨምሮ በሌሎች አፍሪካ ሀገራት የወባ ስርጭት በከፍተኛ ደረጃ በመጨመሩ ወባን የመከላከልና የመቆጣጠር ሥራው ቀድሞ ነው የተጀመረው። በተለይ ለወባ ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች የቅድመ ወባ መከላከልና መቆጣጠር ሥራዎች አስቀድመው በመሰራታቸው በሽታው ሊያስከትል የሚችለውን ከፍተኛ ጉዳት መቀነስ ተችሏል።
አሁንም የወባ ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች ላይ ስርጭቱ የከፋ ጉዳት እንዳያስከትል ጤና ሚኒስቴር ከክልል ጤና ቢሮዎችና ከሌሎች አጋር አካላት ጋር በቅንጅት እየሰራ ይገኛል። በዚህም በከፍተኛ ደረጃ የጨመረውን የወባ በሽታ የሕመምና የሞት ምጣኔ መቀነስ ተችሏል። በዋናነት ደግሞ የመጀመሪያ ጤና ክብካቤ እና የወባ በሽታ ቁጥጥርን ለማጠናከር የማኅበረሰብ ንቅናቄዎች ከጤና ሚኒስቴር፣ ክልል ከፍተኛ ኃላፊዎች ጀምሮ እስከ ቤተሰብ ድረስ በተለየ ትኩረት እየተሰራ ይገኛል። ከሰሞኑም ወባን የመከላከልና የመቆጣጠር ሥራው በምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝ አፈፃፀሙ ከፌደራልና ከክልል በተውጣጡ የዘመቻ ክትትልና ድጋፍ ቡድኖች ተገምግሟል፤ ግብረ መልስም ተሰጥቷል።
ለአብነትም ከፌዴራል እና ከክልል የተውጣጣ የተቀናጀ ክትትልና ድጋፍ ቡድን በጎንደር ከተማ ገብርኤል ጤና ጣቢያ እየተሰጠ ያለውን የወባ ሕክምና አሰጣጥ ተመልክቶ ግብረመልስ ሰጥቷል። በጎንደር ከተማ አስተዳደር የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎች ወረርሽኝ ምላሽ አሰጣጥ ቡድን መሪ አቶ አየሁ ጋሸ እንዳሉት፤ በጎንደር ከተማ ያለው የወባ ወረርሽኝ ሁኔታ ካለፉት ዓመታት ጋር ሲነፃፀር ጨምሯል፡፡ ከገጠር ወረዳዎች በተለየ መልኩ የአጎበር ስርጭትና የመድኃኒት ርጭት አለመኖር ከአየር ንብረት ለውጥና ከሰው ትብብር አናሳ መሆን ጋር ተዳምሮ አባባሽ በመሆኑ ወደፊት በቅንጅት መስራት ያስፈልጋል፡፡ በተጨማሪም የወባ በሽታን መድኃኒት የመላመድ አዝማሚያ በታካሚዎች ይታያል፡፡ በዚህ ዙሪያ ጥናት ተደርጎ መፍትሄ መሰጠት አለበት፡፡
በጤና ሚኒስቴር የሚኒስትር ዴኤታ አማካሪ አቶ ክበበው እይልኝ በበኩላቸው እንደሚገልፁት ፤የጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም እንደ ሀገር ጥሩ ውጤት የተገኘበት አሰራር በመሆኑ መጠናከር ይኖርበታል፡፡ የበሽታ መከላከል ሥራ ሃምሳ በመቶው በማኅበረሰቡ እጅ በመሆኑ የጤና ግንዛቤን ማሳደግ ይገባል፡፡ እንደ ወባ ያሉ በሽታዎችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር አመራሩና የጤና ባለሙያው አርአያ በመሆን የአካባቢ ንፅህናን መጠበቅ ላይ በዋናነት መስራት ይኖርበታል፡፡ የበሽታ ቅኝትን መሰረት ያደረገ የግብአት ስርጭትም አስፈላጊ ነው፡፡
በተመሳሳይ በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል የተሰማራው የድጋፋዊ ክትትል ቡድን በአሶሳ ከተማ አጠቃላይ ሆስፒታል፣ አሶሳ ጤና ጣቢያ፣ የመጀመሪያ ደረጃ ጤና ክብካቤ የሚሰሩ ሥራዎችን የቤት ለቤት ምልከታ አድርጓል። ቡድኑ በከተማው ውስጥ የሚገኙ ሰፋፊ ውሀ የተከማቸባቸው ሥፍራዎችን በማዳፈን እና በኬሚካል ማከም ሥራዎች ላይ ከክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳደር ከሚመራ የክልሉ የዘመቻ ቡድን ጋር ውይይቶችን በማድረግ አበረታች ሥራዎችን እየሠራ ይገኛል።
በውይይቱም የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጌታሁን አብዲሳ ወባን ከመቆጣጠር አኳያ ሕብረተሰቡ አካባቢውን ከማጽዳት፣ በመኝታዎች የወባ መከላከያ አጎበር በመጠቀም ከፍተኛ ሥራ እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል። ባለድርሻ አካላትን በማስተባበር በከተማ ውስጥ ትልልቅ ውሀ ያቆሩ በሕብረተሰቡ መኖሪያ እና አሶሳ ዩኒቨርሲቲ አካባቢ ተጠራቅመው ለወባ ትንኝ መራቢያ ዋነኛ ምክንያት የሆኑ ሥፍራዎችን ኬሚካል የማከም ሥራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙም ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ጠቁመዋል።
ከጤና ሚኒስቴር የዘመቻ ድጋፍና ክትትል ቡድን ጋር ባደረጉት ውይይት በክልሉ ዋና መዲና አሶሳ ከተማ ለትንኝ መራባት መንስኤ የተባሉ ትልልቅ የተጠራቀሙ የውሃ ማቆሪያ ቦታዎችን ማዳፈን እንዲሁም በኬሚካል የማከም ሥራ ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር መሆኑንም ይገልጻሉ። የክልሉ የዘመቻ ቡድን ተቋማት አመራሮችም ይህን ተግባር ቅድሚያ ሰጥተው እንዲፈፅሙም ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ አሳስበዋል።
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ይህ ለትንኞች መፈልፈልና መራባት ትልቅ መንስኤ የሆነውና ትኩረት ያልተሠጠው ሥፍራ በሕብረተሠቡ መኖሪያ አካባቢ የሚገኝ እና በዝናብ ወቅት ውሀዎችን በመያዝ የሚቀመጥ በመሆኑ የታቆረውን ውሀ መድፈን፣ ማፋሰስ እና በኬሚካል ማከም የመጀመሪያው ተግባር ሆኖ እየተሰራበት ይገኛል። የክልሉ ጤና ቢሮ ማኔጅመንት፣በአሶሳ ዩኒቨርሲቲ ከአሶሳ ከተማ ጤና መምሪያ ጋር በመቀናጀት ውሀ የተከማቸባቸው ቦታዎች እንዲደፈኑ የማድረግ ሥራ በስፋት እየተከናወኑ ነው።
ከዚህ ባለፈ የዘመቻ ቡድኑ አባላት በቤት ለቤት በአባወራዎች የሚሠሩ የመከላከል ሥራዎች ምልከታ የተደረገ ሲሆን አባወራዎቹ የአካባቢ ቁጥጥር ሥራና የአጓበር አጠቃቀም በጤና ኤክስቴንሽኖች ድጋፍ ተደርጎ እየተሰራ መሆኑን ምልከታ ተደርጓል። በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል የተሠማራው የዘመቻ ቡድን አስተባባሪ እስራኤል አታሮ እንደሚናገሩት፤ በአሶሳ ከተማ ለወባ መራባት መንስኤ የሆኑ ሥፍራዎችን በመለየትና አስፈላጊው እርምጃ መወሠዱ አበረታች ውጤቶች አምጥቷል፡፡ ሕብረተሰቡ መከላከል በሚችለው የወባ በሽታ የሚደርስበትን ጉዳት ለመታደግ የመከላከል ሥራው በክልሉ በሁሉም ቦታዎች ተጠናክሮ ሊሰራ ይገባል፡፡
በሌላ በኩል በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል የተሰማራው የጤና ሚኒስቴርና የክልሉ ጤና ቢሮ ግብረ-ኃይል በቤንች ሸኮ ዞን የተለያዩ ጤና ተቋማትን፣ የእማወራና አባወራ ቤቶችንና የልማት ጣቢያዎችን ምልከታና ድጋፍ የመስጠት ተግባራትን አከናውኗል፡፡ በዚህም በተለይ በኮብ ጤና ኬላ የወባ ሕሙማንን የመለየትና የመመርመር አገልግሎት በተጠናከረ መልኩ እየተከናወነ መሆኑ መመልከት ተችሏል፡፡
በወረዳው የአባወራ/እማወራ የቤት ለቤት ቅኝትም የተደረገ ሲሆን በአጎበር አጠቃቀምና በወባ በሽታ መከላከል ዙሪያ ያላቸው ግንዛቤ የተሻለ መሆኑን መገንዘብ ተችሏል፡፡ ይሁን እንጂ በወረዳው በ2015 ዓ.ም መጨረሻ ላይ ከተሰራጨው አጎበር ወዲህ አጎበር አለመሰራጨቱ በክፍተት ታይቶ ፈጣን ምላሽ እንዲሰጥ አቅጣጫ ተሰጥቷል፡፡ በወረዳው ሶስት ክላስተሮች የሚገኙ ሲሆን ከእነዚህም መካከል የበበቃ ክላስተር ከፍተኛ የወባ መራቢያ ቦታ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡ በዚህ ጣቢያ አካባቢ የሚድሮክ እርሻ ልማት (ልዩ ስሙ አብይ 1) ተብሎ በሚጠራው ጣቢያ 5 ሄክታር ስፋት ያላቸው ሁለት ውሃ ያቆሩ ሥፍራዎች ላይ የመስክ ምልከታ ተደርጓል፡፡
በዚህም የልማት ድርጅቱንና የአካባቢውን ማኅበረሰብ በማሳተፍ የማፋሰስ ስራው ተጀምሮ በአጭር ጊዜ እንዲጠናቀቅ የጋራ ስምምነት ላይ የተደረሰ ሲሆን በተለያዩ አካባቢዎች በኢንቨስትመንት ሥራ ላይ የተሰማሩ ባለሃብቶች ቅድሚያ ለአካባቢው ማኅበረሰብ ጤና ትኩረት ሊሰጡ እንደሚገባ፤ በተለይም ደግሞ በአሁኑ ወቅት የወባ ወረርሽኝን ለመከላከልና ለመቆጣጠር እንደሃገር በሚደረገው ርብርብ በግንባር ቀደምትነት መሳተፍ እንደሚገባቸው ተገልጿል፡፡
ከዚህ ባሻገር የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ወይዘሮ አለሚቱ ኡሞድን ጨምሮ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች በጋምቤላ ከተማ ለወባ ትንኝ መራቢያ ምቹ የሆኑ ረግራጋማ ሥፍራዎችን የማጽዳትና ውሃ ያቆሩ ቦታዎችን የማፋሰስ መርሐ ግብር ማኅበረሰቡን ባሳተፈ መልኩ አከናውነዋል። በመርሐ ግብሩ ላይ የተገኙት የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር አቤል አሰፋ የክልሉ አብዛኛው አካባቢና ያለው የአየር ሁኔታ ለወባ ትንኝ መራባት አመቺ መሆኑን ጠቅሰው፤ በሁሉም የክልሉ ወረዳዎች የሚገኙ የሕብረተሰብ ክፍሎች ውሃ ያቆሩና ለወባ ትንኝ መራቢያ የሆኑ ቦታዎችንና አካባቢዎችን ማጽዳትና ማፋሰስ እንደሚገባ ጠቁመዋል።
የግንዛቤ ሥራዎች ላይ በማተኮር፣ ማኅበረሰቡን ያሳተፈ ንቅናቄ በመፍጠር የአልጋ አጎበር አጠቃቀምን ማሻሻልና የቤት ለቤት የኬሚካል ርጭት በማከናወን የወባ በሽታ ስርጭትን ለመከላከል አስፈላጊ የሆኑ ተግባራትን ማከናወን እንደሚያስፈልግም ነው የገለጹት፡፡ በጤና ሚኒስቴር የጤናው ዘርፍ የሰው ሀብት ልማት መሪ ሥራ አስፈፃሚ እና የጋምቤላ ክልል የወባ መከላከልና መቆጣጠር ድጋፍና ክትትል ቡድን መሪ አቶ አሰግድ ሳሙኤል በበኩላቸው፤ በክልሉ በሚደረገው የወባ በሽታን መከላከልና መቆጣጠር እንቅስቃሴ ላይ ሁሉም የማኅበረሰብ አካላት በሽታውን መከላከል የሚጠቅሙ የጥንቃቄ መልዕክቶችን በመተግበር፣ ለበሽታው አጋላጭ የሆኑ ድርጊቶችን በማስወገድና የወባ መራቢያ ቦታዎችን በማጽዳት፥ ውሀ ያቆሩ ቦታዎችን በማፋሰስና ኬሚካል የተረጩ ግድግዳዎችን የከብት እዳሪ ባለመለቅለቅ የበሽታውን ስርጭት በመከላከሉ ረገድ የድርሻቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ያሳስባሉ፡፡
በጋምቤላ ክልል ነዋሪዎችም በአካባቢያቸው ውሃ ያቆሩ ቦታዎችን በማፋሰስ፣ ረግራጋማ ቦታዎችን በማጽዳት፣ አጎበርን በአግባቡ በመጠቀምና የግንዛቤ መልዕክቶችን በመተግበር የወባ በሽታን ስርጭት ለመከላከል በሚደረገው ርብርብ የድርሻቸውን ሚና እንደሚወጡ ነው የገለጹት።
ርዕሰ መስተዳድሯን ጨምሮ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ነዋሪዎች በተሳተፉበት የንቅናቄ ሥራዎች ላይ ባስተላለፉት መልዕክት ማኅበረሰቡን ያሳተፈ የንቅናቄ ተግባራት ላይ በትኩረት እንደሚሰራ አብራርተው ሁሉም የክልሉ ማኅበረሰብ በሽታውን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በሚሰሩ ሥራዎች ላይ ከክልሉ ጎን በመሆን የራሳቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
በሌላ በኩል ደግሞ ሀገር አቀፍ የወባ ወረርሽኝ ድጋፋዊ ጉብኝት እንዲሁም የመጀመሪያ ደረጃ ጤና ክብካቤ አገልግሎት ምልከታ አካል የሆነውና በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ ዞኖችንና ወረዳዎች ላይ ትኩረቱን ያደረገ የተቀናጀ ድጋፍና ክትትል እየተካሄደ ሲሆን በድጋፋዊ ጉብኝቱም የጅማ፣ የቡኖ በደሌ እና የኢሊአባቦር ዞኖች ላይ ምልከታ ተደርጓል።
የድጋፋዊ ቡድኑ አስተባባሪና በጤና ሚኒስቴር የጤና ስርዓት ኢኖቬሽንና ጥራት መሪ ሥራ አስፈፃሚ ዶክተር አባስ ሃሰን እንደሚገልፁት፤ በጎ ፍቃደኛ ወጣቶችን በመመልመልና በማሰማራት በወባ ወረርሽኝ ልየታ፣ ሕክምናና ሪፈራል ሥራዎችን እንዲያሳልጡ ስታንዳርዱን የጠበቀ ስልጠና መስጠት ተችሏል፡፡ በጎ ፍቃደኞች ወደ ማኅበረሰቡ እንዲወርዱ በማድረግ የተሰራው ሥራ ትርጉም ያለው ለውጥ ማምጣት አስችሏል፡፡
የበጎ ፍቃደኛ ወጣቶቹ ከወባ ወረርሽኝ ጎን ለጎን ያከናወኑት የቲቢ፣ ጉበት እና መሰል በሽታዎች ልየታና የቅብብሎሽ ሥራ መሰራት መቻሉ እንደተሞክሮ የሚወሰድ ነው፡፡ የኦሮሚያ ክልል እና በየደረጃው ያሉ መዋቅሮች የወባ ወረርሽኝን ለመቆጣጠር ላደረጉት ጥረት ምስጋና ይገባቸዋል፡፡ አሁንም ወረርሽኙ የሚስተዋልባቸው አካባቢዎችን በመለየት የመቆጣጠር እና የማከም ሥራውን በቁርጠኝነት መስራት ያስፈልጋል፡፡
የኦሮሚያ ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊ ዶክተር ተስፋዬ ክበበው እንደሚሉት፤ እስካሁን በተደረጉ ድጋፋዊ ጉብኝት ምልከታዎች አበረታች ሥራዎች ታይተዋል። በተለይ የወባ ወረርሽኝ በታየባቸው ዞኖች ላይ በአመራሩ በኩል ልዩ ትከረት ተሰጥቶ የተቋቋሙ ግብረ ኃይሎች፣ ቴክኒካል ኮሚቴዎች፣ የተሰሩ የግንዛቤና ንቅናቄ ሥራዎች እንዲሁም የተሰራጩ የአጎበር እና የተከናወኑ የኬሚካል ርጭቶች በሽታው ሊያደርስ ይችላል ተብሎ ከተገመተው ጉዳት በእጅጉ መቀነስ ተችሏል፡፡
የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ነጋሽ ስሜ እንዳሉት፤ የወባ ወረርሽኝን ከመቆጣጠር አንፃር እየተሰሩ ያሉ ሥራዎች አበረታች ናቸው፡፡ ሆኖም ለወባ መራቢያ አመቺ የሆኑ ውሃ ያቆሩ ቦታዎችን የማፋሰስ እና የማዳፈን እንዲሁም የኬሚካል ርጭት ሥራዎች አሁንም ትኩረት በመስጠት ተጠናክረው መቀጠል አለባቸው፡፡ በተለይ እንደ መቱ ካርል ኮንፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ያሉ ጥሩ አፈፃጸም ያላቸው ሆስፒታሎች ሌሎች ትኩረት የሚፈልጉ ሆስፒታሎችን ከመደገፍ አኳያ በትጋት መስራት አለባቸው፡፡
በድጋፋዊ ምልከታው በሶስቱ ዞኖች ውስጥ የሚገኙ አባወራዎችና እማወራዎች፣ የጤና ኬላዎች፣ ጤና ጣቢያዎች፣ እና ሆስፒታሎች በስፋት የተጎበኙ ሲሆን ለአመራሮችና ለባለሙያዎችም የገጽ ለገጽ ግብረ-መልስ መሰጠቱ ታውቋል፡፡
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ታኅሣሥ 12 ቀን 2017 ዓ.ም