መገኛው በእንጨት ሥራና የእደ ጥበብ ውጤቶች ከምትታወቀው ጥንታዊቷ የጅማ ከተማ ነው:: በልጅነቱ የተማረውን የእንጨት ሥራ ውጤቶችን ክህሎት በማዳበር ከሚኖርባት ጅማ ከተማ አልፎ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ከኢትዮጵያ አልፎ ደግሞ በሌሎች ሀገራት የሚገኙ ደንበኞችን ማፍራት ችሏል:: ወጣት ላይኔ ለማ ይባላል::
የላይኔ እደ-ጥበብ ሁሉንም አይነት የእንጨት ሥራ ውጤቶች፣ ቅርጻቅርጾች፣ የቤት ውስጥ ማስዋቢያዎችን ይሰራል:: ከሚኖርባት የጅማ ከተማ አልፎ ጊዜው በፈጠረው የቲክ ቶክ ማኅበራዊ ገጽ ላይ የሚሰራቸውን ሥራዎቹን በማስተዋወቅ በርካታ ተከታዮችን በገጹ ላይ አፍርቷል:: ‹‹ ወደ እዚህ ሥራ የገባሁት ከአባቴ ተምሬው ነው:: ጅማ በእንጨት ሥራ ውጤቶች ለረጅም ዘመናት የምታወቅ ከተማ ነች:: ›› የሚለው ወጣት ላይኔ አባቱ ምንም እንኳን የመምህርነት ሙያ ላይ ያገለግሉ የነበረ ቢሆንም የእደ ጥበብ ውጤቶች በልዩነት የተሳቡበት ዘርፍ መሆኑን ያስታውሳል::
አባቱ የተሳቡበትን ይህንን ሙያ ከዋናው የመምህርነት ሥራቸው ባለፈ የእንጨት ሥራዎችን ሲሰሩ ሙያውን ወደ ልጃቸው እንዲተላለፍም ይፈልጉ ነበር:: ላይኔ ይህንን የእደጥበብ ውጤት ከልጅነቱ ጀምሮ በማየቱ መሰረታዊ የሙያውን ክህሎት ሊቀስም ችሏል:: የዚህ ሙያ ባለቤት በመሆኑ የሚኮራው ወጣት ላይኔ ወደ ሥራው ዓለም ሲገባ የራሱን መንገድ ለመፈለግ ረጅም ጊዜ መውሰዱንም ያስታውሳል:: ‹‹ የተለያዩ ሥራዎችን ለመስራት ሞክሬያለሁ ከዚያ በኋላ ነው ይህንን በልጅነቴ የተማርኩትን ወደ ሥራ መለወጥ የቻልኩት፡ ›› ይላል::
‹‹ አንድን ሙያ ለመማር የሚጠይቀው ጊዜ እንደ ሚማረው ሰው ይወሰናል:: ፍላጎት እና ጥረት ያለው ሰው ከሆነ በአጭር ጊዜ ሊማረው ይችላል:: ›› ላይኔ በሥራው ላይ ትኩረት አድርጎ መስራት ከጀመረ አምስት ዓመታትን አስቆጥሯል:: ለረጅም ጊዜ ሲሰራበት የቆየውን ባኅላዊ ጥበብ ከዘመናዊ ጥበብ ጋር በማጣመር ለመማር ያለ ምንም አስተማሪ ወይም ባልተመቻቸ ሁኔታ በራሱ ጥረት መማሩን ገልጿል::
በእንጨት ሥራ ሙያ ውስጥ አብዛኛው ሥራዎችን ለማከናወን ዘመናዊ ማሽኖች ድካምን የሚያቀሉ እና ጊዜን የሚቆጥቡ ዘመናዊ መሳሪያዎች እንደሚገኙ ይገልጻል:: ላይኔ ሥራውን በጀመረበት ወቅት በአካባቢው የሚገኙ ባለሙያዎችን እና የሚፈልጋቸውን አነስተኛ ማሽኖች በመጠቀም እንደሆነ ያስታውሳል:: ‹‹ የምጠቀማቸው ማሽኖች ቢኖሩም አብዛኛውን ሥራ የምሰራው በእጅ ነው:: እነዚህ ማሽኖች በሌላው ዓለም ላይ ተመርተው በቀላሉ የሚገኙ ሲሆን ወደሀገራችን ሲገቡ ግን እንደ ቅንጦት እቃ ይታያሉ :: ከሚገዙበት ከፍተኛ ዋጋ በላይ ወደ ሀገር ውስጥ ለማስገባት የሚጠየቅባቸው ቀረጥ ከፍተኛ ነው:: የእደጥበብ ሥራዎች ውጤታቸው የእንጨት ሥራዎች ከመሆናቸውም ባለፈ በእጅ የተሰሩ መሆናቸው ዋጋቸውን ከፍ ያደርገዋል:: ነገር ግን ከዋናው የእንጨት ግብዓት የአዕምሮ ፈጠራን ለማሳረፍ ያለቀለት ግብዓት እንዲሆን የሚያግዙ ማሽኖች አስፈላጊነታቸው ጥያቄ ውስጥ የሚገባ አይደለም::››ሲል ችግሩን ያስረዳል:: እንደ ላይኔ ገለጻ በእደጥበብ ውጤቶች ዘርፍ የተሰማሩ በርካታ ባለሙያዎች ያሉ ሲሆን ለሌሎች ወጣቶች የሥራ እድል ፈጠራ ወደ ዚህ ሥራ እንዲሰማሩ ይህ ክፍተት መታየት ይገባዋል::
ላይኔ በአባቱ አማካኝት የተሳበበት የእንጨት ሙያ ከሚሰራው ሥራ ጎን ለጎን በመስራት ሙያውን ለማዳበር ችሏል:: በሙያው ላይ አምስት ዓመት ያክል ጊዜ ቆይቷል:: ወጣት ላይኔ ኑሮውን ያደረገው በጅማ ከተማ ውስጥ ቆጪ የምትባል ከተማ ውስጥ ነው:: ታዲያ እንጨት ሥራ የእደጥበብ ውጤቶቹን አንድ ደንበኛ ለሌላው ሰው በማስተላለፍ ሲሰራ ከቆየ በኋላ የሙሉ ጊዜ ሥራው በማድረግ በብዙዎች ዘንድ እውቅናን ማግኘት ችሏል::
ወቅቱ ሰዎች ሥራዎቻቸውን በሚሰሩበት ከተማ እና ቦታ ብቻ ተወስነው የሚያደርጉት ሳይሆን በሚኖሩበት ከተማ ሆነው በመላው ዓለም ተደራሽ መሆን የሚችሉበት ነው:: ላይኔም ጊዜው የፈጠረውን የቲክቶክ ማኅበራዊ ገጽ በመጠቀም የራሱን ሥራዎች ይዞ ብቅ ብሏል ::
ማኅበራዊ ገጽ ላይ በእደ ጥበብ ውጤቶች ላይ ሰዎች ያላቸው አቀባበል እምብዛም እንዳልነበር ይገልጻል:: በዚህም በገጹ ላይ ተከታዮችን ለማፍራት፣ ሰዎች ያላቸውን ግንዛቤ ለመቀየር እና ሥራውን ለማስተዋወቅ ሰፊ ጊዜን ወስዶበታል:: ‹‹ በሀገራችን ለእደጥበብ ውጤቶች ያለው ተቀባይነት በሌሎች ሀገራት እንደምንመለከተው አይደለም:: ›› የሚለው ላይኔ በቲክቶክ የማኅበራዊ ገጹ ላይ ሥራውን በማስተዋወቅ የራሱን የፈጠራ ሥራዎች በተለያየ መንገድ በማሳየት የእንጨት ሥራ ውጤቶች በተለያየ መንገድ መሰራት እንደሚችል በማሳየት በርካታ ተከታዮችን አፍርቷል::
በአንድ ወቅት በገጹ ላይ ኢትዮጵያን ካርታ የአንበሳ ምስልን በማድረግ የሰራው ማስዋቢያ ከፍተኛ እይታን ያገኘ ሥራው ነው:: በእንጨት ላይ በመቅረጽ የአንድ ሳምንት ጊዜ ወስዶ የሰራውን ይህንን ሥራን በማኅበራዊ ገጹ ላይ በጨረታ መልክ አቅርቦታል:: ጨረታውንም በሀገረ ካናዳ ኑሮውን ያደረገና የኢትዮጵያ መለያ የሆነውን የቡና ምርት በማስተዋወቅ እና ለገበያ በማቅረብ የሚታወቅ ድርጀት በዚሁ የማኅበራዊ ገጽ አማካኝነት የቀረበውን ጨረታ በ210 ሺህ ኢትዮጵያ ብር ሊያሸንፍ ችሏል::
‹‹ማኅበራዊ ገጽ ላይ ተከታዮችን ማፍራት ከባድ ነበር:: ነገር ግን በሒደት ሥራዬን የወደዱ በርካታ ደንበኞችን አግኝቼበታለሁ:: ›› ላይኔ በዚህ ገጽ አማካኝነት ከሚኖርባት የጅማ ከተማ አልፎ በውጭ ሀገር የሚኖሩ ደንበኞችን ማፍራት ችሏል:: ‹‹ ማኅበራዊ ሚዲያ ብዙ በጎ ሰዎችን ሥራዬን የሚያበረታቱ ሰዎችን ያገኘሁበት ነው:: ሥራዬን ለሚወዱ ደንበኞችም ከዚሁ ከጅማ ሆኜ እሰራላቸዋለሁ:: ››
የእንጨት ሥራ ውጤቶችን የቤት ውስጥ ማስዋቢያዎችን በሚሰራበት ወቅት ደንበኞቹ የሚሰራቸውን ሥራዎች በመመልከት እና የራሳቸውን ሀሳብ በማከል የሚያዙ ሲሆን ባለሙያው ላይኔ ደግሞ በሥራቸው ላይ የተሻለውን በማማከር የሚፈልጉትን እደ-ጥበብ ውጤት ይሰራላቸዋል ::
ወጣት ላይኔ በሥራው ላይ አምስት ዓመት ያክል ጊዜን ይቆይ እንጂ የእደ ጥበብ ውጤት ሥራዎች ላይ የሙሉ ጊዜ ሥራውን በማድረግ ትኩረቱን አድርጎ መሥራት ከጀመረ አንድ ዓመት ከመንፈቅ በላይ ሆኖታል:: ያለፉትን ጊዜያት ተቀጥሮ ከሚሰራበት ሥራ ባሻገር ባለው ጊዜ የተለያዩ የእንጨት ሥራ ውጤቶችን ሲሰራ ቆይቷል:: እነዚህ የእንጨት ሥራ ውጤቶች ከእሱ አልፈው በብዙዎች ዘንድ ተወዳጅነትን ሲያገኙ የሙሉ ጊዜ ሥራው ለማድረግ መወሰኑን ያስታውሳል:: ላይኔ በተለያየ የሥራ ዘርፍ ላይ ለመስራት ፍላጎት ኖሯቸው መስራት ለሚፈልጉ ወጣቶች የውሳኔ ሰው በመሆን እና ካላቸው እውቀት በመነሳት ለዓላማቸው ጠንክረው መስራት እንደሚገባቸው መልዕክቱን ያስተላልፋል ::
‹‹ እኔ ሥራዬን ስጀምረው በዙርያዬ ሥራዬን አይተው የደገፉኝ ሰዎች ነበሩ:: ነገር ግን የሚደግፉኝ ሰዎች ያገኘሁት መስራት በመጀመሬ ሙከራ በማድረጌ ነው ::››
ላይኔ እደ-ጥበብ የሥራው ስያሜ ሲሆን ከሚኖርባት የጅማ ከተማ ባለፈ በፈጠረው የማኅበራዊ ገጽ በርካታ ደንበኞችን ማፍራት ችሏል:: የራሱን የእደ ጥበብ ውጤቶች የሚሸጥበት ቦታ መክፈት የቅርብ ጊዜ እቅዱ ነው:: ወጣት ላይኔ ይህንን ከአባቱ የተረከበውን የእደጥበብ ውጤት በራሱ ጥረት ያዳበረው በመሆኑ ለሌሎች የሚሆን ትምህርትቤት መክፈት ደግሞ የማይቀር የወደፊት ሕልሙ ነው ::
ወጣት ላይኔ በሚሰራበት የሥራ ዘርፍ በስሩ ለሌሎች ወጣቶች የሥራ እድል መፍጠር ችሏል :: ከትምህርት ባሻገር የተለያዩ የሙያ ክህሎት ባለቤት መሆን ጠቃሚ መሆኑንም ጠቅሷል ::
‹‹ወጣቶች ይህንን የሥራ ዘርፍ እንዲማሩት እፈልጋለሁ:: በመሆኑም የመስሪያ እና የመማርያ ቦታ መሆን የሚችል፤ ሙያውን የሚወዱ ሰዎች መሰልጠን የሚችሉበትን የእደጥበብ ትምህርት ቤት መገንባት እፈልጋለሁ :: ››
ሰሚራ በርሀ
አዲስ ዘመን ዓርብ ታኅሣሥ 11 ቀን 2017 ዓ.ም