ሦስት ሀገራትን ያስተሳሰረው -ሔር ኢሴ

የሰው ልጅ ሰብሰብ ብሎ ሲኖር ግጭት ርቆት ሰላም ይቀርበው ዘንድ ሕግ ማውጣቱ የተለመደ ነው:: ችግሩ የሚወጡት ሕጎች በተለያየ ምክንያቶች ጊዜ በሄደ ቁጥር የመከበር እድላቸው እየቀነሰ በአዲስ ሕግ ይተካሉ:: በተለይ ካልተጻፉ የመረሳት እድላቸው ሰፊ ነው:: የሱማሌ ብሔር አካል የሆኑት የኢሳ ማኅበረሰቦች ሕግ አለመጻፉም ሆነ ጊዜው መርዘሙ በሕጋቸው ላይ ለውጥ አላመጣም::

ኢሳዎች “ሔር ኢሴ” ሲሉ የሚጠሩት ሕጋቸው ከወጣ 500 ዓመታትን ቢሻገርም ማኅበረሰቡ አሁንም ይተገብረዋል:: ሔር ሕግ ማለት ሲሆን ኢሴ የኢሳዎች መሆኑን ለማመላከት የገባ ነው:: በሔር ኢሳ አሁንም ፍትህ ይሰፍናል፤ በርካቶች የሕጉ ቅጣት እንዳያርፋባቸው ሲሉ መልካም ስብዕናን ተጎናጽፈዋል፤ ያጠፉት ስህተታቸው እንዳይደግሙት ተገስጸውበታል::

የኢሳ ማኅበረሰብ በኢትዮጵያ በጅቡቲና በሶማሊያ ይኖራሉ:: በኢትዮጵያ በዋናነት ከሱማሌ ክልል 11 ዞኖች አንዱ በሆነው ሲቲ ዞን በስፋት የሚኖሩበት ነው:: ይህ ማለት ከድሬዳዋ ምዕራብ አቅጣጫ 90 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ሲቲ ዞን፣ በኢትዮጵያ የጅቡቲ ድንበር ላይ እስከ አዋሽ ድረስ እንዲሁም በድሬዳዋ ከተማ በስፋት ይኖራሉ::

ሔር ኢሴ በሦስቱም ሀገራት የሚኖሩ የኢሳ ማኅበረሰብ የሚተዳደሩበት ያልተጻፈ ሕግ ነው:: ሕጉ ሕዳር 26 ቀን 2017 ዓ.ም የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስ እና ባሕል ድርጅት (ዩኔስኮ) የማይዳሰሱ የባሕል ቅርሶች ጥበቃ የበይነ መንግስታት ኮሚቴ 19ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ በማይዳሰሱ የሰው ልጅ ቅርሶች ወካይ ዝርዝር ውስጥ ተካቷል። ለኢትዮጵያ ስድስተኛው በዝርዝሩ የተካተተ የማይዳሰስ ቅርስም ነው::

በኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን የኢንታንጀብልና ኢትኖግራፊ ቅርስ ተመራማሪና የዲፓርትመንት አስተባባሪ ወይዘሮ ቀለሟ መኮንን ሕጉ በቅርስነት እንዲካተት መነሻ ጽሁፍ ከማዘጋጀት አንስቶ ሲመዘገብም ጉባኤው በተካሄደባት የፓራጓይ አሱንሲዮን ከተማ በአካል ተገኝታ የምስራቹን ሰምታለች:: እንደ አስተባባሪዋ ማብራሪያ፤‹‹ሔር ኢሴ›› በኢትዮጵያ በጅቡቲና በሱማሊያ የሚኖሩ የኢሳ ማኅበረሰብ አባላት በጋራ ሕጋችን ሲሉ የሚስማሙበትና የሚተዳደሩበት ሕግ ነው::

በተለያዩ ሀገራት የሚገኙት ኢሳዎች የሚጋሩት የመተዳደሪያ ሕጋቸውን ብቻ ሳይሆን መሪያቸውንም ነው:: መቀመጫው በድሬዳዋ ከተማ በሆነው ‹‹ኡጋዝ›› በጋራ ይመራሉ:: ኡጋዙ የሚሾመው መሪ ሲሆን፤ ለየት ያለ የጤና እክል ካልገጠመውና ማኅበረሰቡ አምኖበት የሾመውን ኃላፊነት እስከተወጣ ድረስ ሹመቱ የእድሜ ልክ ነው:: ግን ከማኅበረሰቡ ወግና ደንብ ያፈነገጠ ነገር ሲፈጽም ያኔ መሪነቱ ያበቃል:: ኢሳዎች ተሰብስበው በጋራ እንደሾሙት ተሰብስበው በጋራ ያወርዱታል:: ሕጉ በ16ኛው ክፍለ ዘመን የወጣ ሲሆን፤ ሳይጻፍ ከትውልድ ወደ ትውልድ የተሸጋገረ ባሕላዊ ሕግ መሆኑ ልዩ ያደርገዋል::

‹‹ሔር ኢሴ›› የኢሳ ማኅበረሰብ ያልተጻፈ ሕግ የማኅበረሰቡ መገለጫ እሴት ነው የምትለው ወይዘሮ ቀለሟ፤ ሔር ኢሴ ከትውልድ ወደ ትውልድ በቃል እየተላለፈና እየተተገበረ የመጣ መተዳደሪያ እንደሆነ ታስረዳለች:: አሁንም የሚተገበር የማኅበረሰቡ ሕያው ቅርስ እንደሆነም ትናገራለች:: ሕጉ የተጀመረው አሁንም በሀገራችን ማኅበረሰቡ በዋናነት በሚገኝበት ሲቲ ዞን በሚገኝ ሲቲ ተራራ ላይ እንደሆነም ታብራራለች::

እንደ አስተባባሪዋ ገላጻ፤ ከማኅበረሰቡ የተውጣጡ 44 አባቶች በብሔሩ አጠራር ‹‹ገንዴ›› የሚሰኙ በተራራው ላይ ክብ ሰርተው ወራትን ያስቆጠረ ምክክር አርገዋል:: በወቅቱ 44ቱን አባቶች ምግብ በማብሰልና አስፈላጊ ነገሮችን በማቅረብ ስታግዛቸው የነበረች ‹‹ሲቲ›› የምትባል ሴት ነበረች:: ተራራውና አካባቢው የእሷን ሥም ተጋርቶ መጠሪያው ሲቲ ሆኖ ቀረ::

እርስ በእርስ የሚፈጠሩ ግጭቶችን ለመፍታት፣ ከቀላል እስከ ከባድ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን ለመከላከል ብሎም ሁሉንም እኩል የሚያስተዳድር ሕግ መደንገግ እንደሚያስፈልግ በማኅበረሰቡ አባላት በመታመኑ ባሕላዊ ሕጉ እንደወጣ ይነገራል። ሕጉ ረዥም ጊዜ ያስቆጠረ መሆኑና በሦስቱም ሀገራት የሚገኙ የኢሳ ማኅበረሰብ አባላት በአንድ መሪ መመራታቸው ልዩ ያደርገዋልም::

ወይዘሮ ቀለሟ እንደሚሉት፤ መሪው ሁሉንም እኩል ያገለግላል:: ሕጉ ለሴቶች፣ ለሕጻናት፣ ለአካባቢ ጥበቃና ለዘላቂ ሰላም ልዩ ትኩረት ይሰጣል:: የማኅበረሰቡ አባላት “ማንም ከሕጉ በላይ አይደለም፤ በታችም አይደለም፤ ሕጉ ለሁሉም እኩል ነው” የሚል አባባልም አላቸው:: በዚህም ሕጉን በስድስት ዋና ዋና ክፍሎች በመክፈል ይጠቀሙበታል:: 160 አንቀጾች፣ 336 ንኡስ አንቀጾችና 444 መመሪያዎችም ያሉት ነው::

የነፍስ ግድያ ወይም የአካል ጉዳት የሚዳኝበት ክፍል ‹‹ሔር ዲግ›› ይሰኛል:: የንብረት ጉዳይ የሚታይበት ደግሞ ‹‹ሔር ደቀቃል›› ይባላል:: የሰብአዊነት መብት ጥሰት እንዳይኖር ጥበቃ የሚደረግበት የሕጉ ክፍል ‹‹ሔር ዴር›› በማለት ይጠሩታል:: የማኅበረሰቡ ባሕልና ወግ የሚጠበቀውን ሕግ ደግሞ ‹‹ሔር ደቃን›› ይሉታል:: የመሬት ጉዳዮች የሚታዩበት ‹‹ሔር ዲል››፤ በአካባቢው ለሚኖሩ ሌሎች ብሔረሰቦች ከለላ ማድረግን የተመለከቱ አንቀጾች ያሉበት ክፍል ‹‹ሔር ዲብለህ›› በመባል ይጠራሉ:: ከዚያም ባሻገር ማኅበረሰቡን የሚያስተዳድረው ኡጋዙ የሚመረጥበትና የሚሾምበት ሂደት በሕጉ የማኅበረሰቡን ባሕልና ወግ ለመጠበቅ በወጣው ሔር ደቃን በዝርዝር የተቀመጠበት ነው::

ሔር ኢሴ ከቀላል ጥፋቶች አንስቶ እስከ ከባድ ወንጀሎችን ይዳስሳል የምትለው ወይዘሮ ቀለሟ፤ ሕጉ በወረቀት አይጻፍ እንጂ በማኅበረሰቡ ልቦና ውስጥ ሰፍሯል::ኢሳዎች ለእያንዳንዱ ጥፋት ቅጣቱ ምን እንደሆነ ያውቁበታል:: ከቀላል አለመግባባት አንስቶ እስከ ግድያ የሚደርስ ጥፋት ሲከሰትም ይዳኙበታል:: ቅጣትም ያስተላልፉበታል ስትልም ታስረዳለች::

የጠፋው ጥፋት ቀላል በሚሆንበት ወቅት የፍትህ ሥራው የዛፍ ጥላ ሥር ይከናወናል:: ወንጀሉ ከፍ ያለ ሲሆንና የደም ካሳ የሚፈልግ ሲሆን ወንዝ መሃል ይካሄዳል:: በሕጉ ሴቶችና ሕጻናት የሚከበሩ ናቸው:: እነሱ ላይ መድፈር ጥቃትና ሌላም አላስፈላጊ ነገር ከደረሰ ፈጻሚው ይገለላል:: በእነዚህ ወንጀሎች ላይ ከበድ ያለና የማያዳግም ቅጣት ስለሚጣል በማኅበረሰቡ ዘንድ በብዛት እንደማያጋጥም ትናገራለች::

የብሔረሰቡ ሽማግሌዎች እንደሚናገሩት፤ ሔር ለእነሱ ከምንም በላይ ነው:: ሁሉንም የሔር ኢሴ ባሕላዊ ሕግ አንቀጾች ያከብራሉ፤ ማሕበራዊ ችግሮቻቸውንም ይፈቱበታል:: ሔር ዲሞክራሲን መሠረት ያደረገ ስለሆነ ፍትሐዊነቱ የጎላ ነው:: ምንም ይሆን ምን በኢሳ ማሕበረሰብ መካከል የተነሳ ችግርም ይሁን ግጭት ከሔር ኢሴ ውጭ አይሆንም:: ሕጉ ሁሉን አቀፍ በመሆኑ ማንኛውም የማሕበረሰቡን ወግና ባሕል የለቀቀ ነገር በሙሉ ይስተካከልበታል::

ኢሳዎች ከልጅነታቸው ጀምሮ ሕጉን እያጠኑት፤ ሲተገበር እያዩና እየተለማመዱ እንዲሄዱ ይደረጋል:: ሕጻንና ወረቀት የያዘውን አይለቅም ነውና ሔር ኢሴ በወረቀት ባይሰፍርም ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተሸጋገረ እዚህ ደርሷልም ይላሉ::

አስፈላጊ ሲሆን ኡጋዙ በተገኘበት በሦስቱም ሀገራት የሚገኙ የኢሳ ማኅበረሰብ ተወካዮች ተገናኝተው ይመክራሉ:: በዚህም ምን ክፍተት አለ? ምን ችግሮች አሉ? በቀጠናው ምን አጋጠመ? እንዴት ይፈቱ? በሚል ሳምንት የሚፈጅ መድረክ አላቸው:: ስለዚህም ሰዎች ሀገር አቋርጠው ይገናኛሉ፤ በቁምነገር ቀናት ወስደው ይመክራሉ::

ከዚህ ቀደም የማኅበረሰብ ተወካዮቹ በተገናኙበት አንድ ወቅት መታደም መቻሏን የምትናገረው አስተባባሪዋ፤ ኢትዮጵያና ጅቡቲ ድንበር አካባቢ በምትገኘው አይሻ በምትባል የሀገራችን ቦታ ተገናኝተው ሲመክሩ የተመለከተችበትን ሁኔታ እንደማትረሳው ትናገራለች:: በምክክራቸውም ጊዜ ወስደው መረጃ ተለዋውጠው ለተፈጠሩ ችግሮች መፍትሄ አስቀምጠው እንደሚለያዩ ምስክርነቷን ትሰጣለች::

የኢሳዎች የሕግ አከባበር ለሌሎች አካባቢዎችም የሚሆን ነው የምትለው ወይዘሮ ቀለሟ ሀገራትን ማስተሳሰሩ አንድ የሚለየው ነገር ነው:: መሪው (ኡጋዙ) ኢትዮጵያ፣ ጅቡቲ እንዲሁም ሶማሊያ ለሚገኙ የማኅበረሰቡ አባላት በእኩል የሚያገለግል መሆኑና ሕጉ በቃል ያለ መሆኑ የተለየ ባሕሪ ነው ባይም ናት::

ሀገራችን ከሔር ኢሴ በፊት አምስት የማይዳሰሱ ቅርሶችን አስመዝግባለች የምትለው አስተባባሪዋ ሔር ኢሴ ብዝኃ ሀገራዊ ሰነድ (መልቲናሽናል) የሚታይበት መሆኑ ልዩ እንደሚያደርገው ትገልጻለች:: ይህ ማለትም ከአንድ በላይ ሀገራት በጋራ ቅርሳቸውን ሲያስመዘግቡ የታየበት ነው በማለትም ታብራራለች::

በ2015 ዓ.ም ሕጉ በቅርስነት እንዲመዘገብ ለዩኔስኮ ሲቀርብ ኢትዮጵያ አስተባባሪ ነበረች:: ጅቡቲና ሶማሊያም ተሳታፊ ሆነው ሰነዱ ቀርቧል:: ሰነዱ ተዘጋጅቶ ከተላከ በኋላ ክትትል እንደሚያስፈልግ ስለታመነበት ኢትዮጵያ የአስተባባሪነት ሚናዋን ተጫውታለች:: ከሦስቱም ሀገራት ወኪል ቡድን ተቀምጦም ሥራውን እንዳከናወነ ታነሳለች::

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስ እና ባሕል ድርጅት (ዩኔስኮ) የማይዳሰሱ የባሕል ቅርሶች ጥበቃ የበይነ መንግስታት ኮሚቴ 19ኛ መደበኛ ስብሰባውን በፓራጓይ አሱንሲዮን ባካሄደበት ወቅት በጉባኤው ላይ ተገኝተው ኢትዮጵያን በመወከል ንግግር ያደረጉት የሱማሌ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኢብራሂም ኡስማን፤ ዩኔስኮ ሔር ኢሴ የሶማሌ ኢሳ ማኅበረሰብን ያልተጻፈ ባሕላዊ ሕግ የሰው ልጆች ወካይ ዓለምአቀፍ የማይዳሰስ ቅርስ ሆኖ እንዲመዘገብ በማድረጉ ምስጋና አቅርበዋል::

ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታም ሕጉ በዋናነት ችግሮች ሥር ሳይሰዱ እልባት በመስጠት የሚዳኝበት እና አሸናፊና ተሸናፊ ሳይኖር መፍትሔ በማበጀት ሰላምን ለማስፋን ያለው ፋይዳ ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል። ባሕላዊ ሕጉ ሃይማኖት እና መደበኛ ሕግን የማይጻረርና ማኅበረሰቡ ከ16ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ ተስማምቶ ያጸደቀው መሆኑንም አመልክተዋል።

የረጅም ጊዜ የታሪክ እና የማንንት መገለጫ የሆነው ሕጉ በየዘመኑ ትውልዱ የራሱን አሻራ ያሳረፈበት ማኅበራዊ እሴት ነው:: ባሕላዊ ሕጉ መመዝገቡ ለሕጉ ቀጣይነት ትልቅ አስተዋጽኦ የሚያደርግና የሦስቱን አገራት ማኅበረሰቦች በማስተባበር ሰላማቸው ዘለቄታዊ በሆነ መንገድ እንዲጠበቅ ከማድረግ አኳያ ቁልፍ ሚና እንዳለውም አብራርተዋል። የሕጉ መጽደቅ ቀጣናዊ ትብብርን ለማጎልበት እና የተቀናጀ የቅርስ እንክብካቤና ጥበቃ ሥራ እንዲኖር አስተዋጽኦ እንደሚያደርግም አስረድተዋል።

እንደ አስተባባሪዋ ወይዘሮ ቀለሟ አስተያየት፤ ቅርሱ በመመዝገቡ ማኅበረሰቡ ይነቃቃል:: ባሕላዊ ሕጉ በዓለም መድረክ ሲነሳ ማኅበረሰቡ “ይሄም አለ” ብሎ ለባሕላዊ ውይይቶች እድል እንዲሰጥ ይሆናል:: ወጣቱ ስለቅርሱ እንዲያውቅና ትኩረት እንዲሰጥ ያግዛል:: ለቀጣይ ትውልድ ጠብቆ ለማስተላለፍ እድልም ይሰጣል:: ከአካባቢ ጥበቃ አንጻርም የመተግበሪያ ቦታዎች እውቅና እንዲኖራቸውና እንዲጠበቁ ያደርጋል:: የማኅበረሰቡን እሴትና ዋጋ ለመረዳት ያስችላል::

ቅርሱ የማኅበረሰቡ ቢሆንም ከተመዘገበ በኋላ የሀገር እንዲሁም የዓለም ጭምር ሆኗልና ለባሕል ትውውቅ፤ ለመከባበር፣ ለገጽታ ግንባታ፤ ባሕላዊና ማኅበራዊ ግንኙነትን ለማዳበር ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል:: ሌሎች ማኅበረሰቦች መሰል እሴታቸውን እንዲጠብቁና እንደሀገርም ትኩረት እንዲያገኝ እድል ይፈጥርላቸዋልም ብለዋል::

ቤዛ እሸቱ

አዲስ ዘመን ዓርብ ታኅሣሥ 11 ቀን 2017 ዓ.ም

 

Recommended For You