የትውልድ ቦታቸው በቀድሞው ጎጃም ጠቅላይ ግዛት ይልማ እና ዴንሳ አውራጃ ነው:: ገና የአምስት ዓመት ሕጻን ሳሉ አጎታቸውን ተከትለው አዲስ አበባን ተዋውቀዋል:: አዲስ አበባን በዚህ ዕድሜያቸው የመተዋወቅ ዕድል የገጠማቸው የዕለቱ እንግዳችን የልጅነት ዕድሜያቸውን በጫወታና በትምህርት ማጣጣም የቻሉት በአዲስ አበባ ቢሆንም፣ ትምህርታቸውን ሳያጠናቅቁ በአፍላ ዕድሜያቸው ነው ወታደር ቤት የገቡት:: መስዋዕትነትን ጭምር በሚጠይቀው የውትድርናውን ዓለም ሕይወት ‹‹ሀ›› ብለው ሲማሩ ሥነ-ሥርዓትን፣ ጨዋነትንና ቁርጠኝነትንም ተምረዋል::
ፍጹም ሥነሥርዓትንና የዓላማ ጽናትን ከተማሩበት ወታደር ቤት የነበራቸውን ቆይታ አጠናቅቀው ሲቪል በመሆን ማኅበረሰቡን በተቀላቀሉ ጊዜ አዲስ የሕይወት መስመር ነው የጠበቃቸው:: ከወታደር ቤት ውጭ ያለውን ሕይወትም እንዲሁ ለመኖር የሕይወትን ውጣ ውረድ ከዝቅታው ዝቅ ብለው ተምረዋል:: ቀልጣፋ፣ ሥራ ወዳድና ፈጣን በመሆናቸው ሕይወትን ከውትድርና ውጭ ለመምራት ብዙም አልተቸገሩም:: ለመኖር መሥራት የግድ እንደሆነ በማመን ሥራ ሳይመርጡና ሳይንቁ በድለላ ሥራ ተሰማርተው በርካታ ዕውቀትና ልምድ መቅሰም ችለዋል::
በድለላ ሥራ ጥቂት የማይባሉ ዕውቀት፣ ልምድና ማኅበራዊ ግንኙነትን ማዳበር የቻሉት የዕለቱ የስኬት እንግዳችን በተለያዩ የንግድ ሥራዎች ተሳትፈው ውጤታማ መሆን የቻሉ ታታሪ፣ ትጉህና ጠንካራ ሠራተኛ ናቸው:: ‹‹ሥራ ሰውን ያስከብራል›› የሚል የጸና አመለካከት ያላቸው በመሆኑ ለሚገጥማቸው መሰናክሎች ሁሉ ፊት ሳይሰጡ ከላይ ታች በማለት ትጋታቸው ፍሬያማ መሆን እንዲችል ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል:: ጥረታቸው ተሳክቶም ቱአር ኤን ፈርኒቸር የቤትና የቢሮ ዕቃዎች አምራች ድርጅት እንዲሁም ዘመናዊ ሆቴል መገንባት ችለዋል:: ትናንት ከውትድርና ተነስተው በድለላ ሥራ ያካበቱትን ዕውቀት ተጠቅመው በተለያዩ የንግድ ሥራዎች ውስጥ ገብተው በመሥራት ዛሬ ከስኬት ማማ ላይ የደረሱት እንግዳችን መቶ አለቃ ሰለሞን አዳሙ ይባላሉ::
ከገጠሪቷ ኢትዮጵያ ወጥተው አዲስ አበባ ጠቅላይ ሰፈር ወይም ኳስ ሜዳ አካባቢ ያደጉት መቶ አለቃ ሰለሞን፤ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን በቀድሞ ስሙ ወሰንሰገድ በአሁን አጠራሩ የካቲት 23 ትምህርት ቤት ተከታትለው በአዲስ ከተማ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በሚከታተሉበት ወቅት ወታደር ቤት መግባታቸውን ያስታውሳሉ::
የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ሳያጠናቅቁ ውትድርናን የተቀላቀሉት መቶ አለቃ፤ በ1973 ዓ.ም በቀድሞው 21ኛ ተራራ ክፍለ ጦር በውትድርና ሙያ ተቀጥረው ታጠቅ ጦር ሰፈር የውትድርና ሥልጠናን በተግባር ተከታትለዋል:: ወታደር ሆነው ሀገራቸውን ለማገልገል ወጥቶ ማደርን ‹‹ሀ›› ብለው የጀመሩት መቶ አለቃ ሰለሞን፤ ከ1974 እስከ 1977 ዓ.ም ድረስ ኤርትራ ዘምተዋል:: የሕይወት መስዋዕትነትን በሚጠይቀውና ታላቅ ሙያ በሆነው የውትድርና ሙያም በተለያዩ አካባቢዎች በውጊያ ተሳትፈዋል::
ከውጊያ በመለስም በዕጩ መኮንንነት የተወዳደሩት መቶ አለቃ ሰለሞን፤ “ሐረር ሚሊቴሪ አካዳሚ” ወይም “ሁርሶ” ይባል በነበረው ማሰልጠኛ የዕጩ መኮንንነት ሥልጠና መውሰድ የሚያስችላቸውን ውድድር አልፈው ሠልጥነዋል:: በሥልጠናው ወቅት ባሳዩት ተሳትፎና ባስመዘገቡት ከፍተኛ ውጤት በማሰልጠኛ ተቋሙ መምህር ሆነው የመቅረት ዕድል አጋጥሟቸዋል:: መቶ አለቃ ሰለሞን፤ የደርግ መንግሥት ወድቆ የኢሕአዴግ መንግሥት ሥልጣኑን እስከተቆጣጠረበት 1983 ዓ.ም ድረስ በጦር ትምህርት ቤቱ በካርታ ንባብ ወይም በቶፖግራፊ መምህርነት አገልግለዋል::
ኢሕአዴግ በትረ ሥልጣኑን ሲቆናጠጥ ከጦር ትምህርት ቤቱ በተሰናበቱ ማግስት የሕይወት መስመራቸውን ከውትድርና ወደ ድለላ ሥራ የቀየሩት መቶ አለቃ ሰለሞን፤ ቀልጣፋና ፈጣን በመሆናቸው ሕይወትን ከጦር ቤት ውጭ ለመምራት ያስችለኛል ያሏቸውን በርካታ ሥራዎች ሠርተዋል:: በቅድሚያ የድለላ ሥራን ሲቀላቀሉ መርካቶ ውስጥ በሸቀጣ ሸቀጥ ንግድ የተሠማሩ ዘመዶቻቸው ጥሩ መጠጊያ ሆነዋቸው እንደነበር ያስታውሳሉ:: ሸቀጣ ሸቀጥን በመደለል የንግድ ሥራን አቀላጥፈው ሠሩ:: ወቅቱ ኤርትራ ከኢትዮጵያ የተገነጠለች ቢሆንም፣ ግጭትና ጦርነት አልነበረምና ኤርትራውያኑ ኢትዮጵያ ውስጥ እንደፈለጉ ተንቀሳቅሰው ይነግዱ ነበር፤ ይህም እሳቸው ለጀመሩት የድለላ ሥራ ጥሩ አጋጣሚ ፈጠረላቸው::
በወቅቱ ኤርትራውያኖች የተለያዩ ሸቀጣ ሸቀጦችን በደሴ በር በኮንትሮባንድ ያስገቡ እንደነበር የሚያስታውሱት መቶ አለቃ ሰለሞን፣ ዕቃዎቹን የሚሸጥላቸው ሰው በሚፈልጉ ጊዜ እርሳቸው አቤት ብለው ከኤርትራውያኖቹ ቀርበዋል:: ኤርትራ በነበራቸው ቆይታም ቋንቋቸውንና ባሕል አመላቸውን ማወቅ የቻሉት መቶ አለቃ ሰለሞን፤ እርሱን ማወቃቸው ከኤርትራውያኖች ጋር በቀላሉ ለመግባባትና ለመሥራት ምቹ ሁኔታን ፈጠረላቸው:: እናም የድለላ ሥራው አልጋ በአልጋ ሆነላቸው:: በወቅቱ ኤርትራውያኖቹ በደሴ በር የሚያስገቡትን የተለያዩ ሸቀጦች መቶ አለቃ ሰለሞን ተረክበው መርካቶ በመሸጥ የንግድ ሥራቸውን ማቀላጠፍ ቻሉ::
የሚያመጡትን ዕቃ ተረክበው መርካቶ ውስጥ በመሸጥ ከፍተኛ ገንዘብ ያገኙ እንደነበር ያስታወሱት መቶ አለቃ ሰለሞን፤ የንግድ ሥራን በዚሁ መንገድ እንደተለማመዱትና ከኤርትራውያኖቹ ጋርም የቤተሰብ ያህል ተቀራርበው በመሥራት ሦስት ሺ ብር ማጠራቀም ቻሉ:: ሦስት ሺ ብር በወቅቱ ትልቅ ገንዘብ እንደሆነ ያነሱት መቶ አለቃ ሰለሞን፤ የንግድ ሥራቸውን ለማሳደግ የሲጋራ ጅምላ ንግድ ፈቃድ በማውጣት ወደ ሲጋራ ንግድ ተዘዋውረዋል::
‹‹ሥራ አልመርጥም አጋጣሚው የፈጠረልኝን እና የተመረጠልኝን ሥራ ሁሉ እሠራለሁ›› የሚሉት መቶ አለቃ ሰለሞን፤ የሲጋራ ንግዱ ብዙም አላስደሰት አላቸውና ወደ እህል ንግድ ፊታቸውን አዞሩ:: ወደ እህል ንግድ ለመግባት ያሰቡት ጤፍ የሚመረትባቸውን የተወሰኑ አካባቢዎች ማወቃቸውን መሠረት በማድረግ እንደሆነ ያስታውሳሉ:: በወቅቱ ከሲጋራ ንግድ ያተረፉትን አሥር ሺ ብር ይዘው ሀዲድ ገበያ አካባቢ በአራት መቶ ብር ቆርቆሮ ቤት በመከራየት የእህል ንግዱን ጀመሩ::
የእህል ንግድ ከፍተኛ ገንዘብ የሚፈልግና ወቅትን ተከትሎ የሚሠራ እንደሆነ የሚገልጹት መቶ አለቃ ሰለሞን፤ በቆርቆሮ ቤት ውስጥ በተከማቸው ኩንታል ላይ እየተኙ ዘበኛም ነጋዴም ሆነው አሳልፈዋል:: ትንሽ ጊዜ እንደነገዱም አዋጭ አልሆን ሲላቸው ሌሎቹን ንግዶች እንደተውት ሁሉ ከእህል ንግድም ራሳቸውን አሰናበቱ::
ታታሪ፣ ብርቱና ሥራ ወዳድ የሆኑት መቶ አለቃ ሰለሞን፤ በሌላ የንግድ ሥራ ብቅ በማለት መርካቶ ዱባይ ተራም ገብተው ሽንሽን ሱቅ በመከራየት በቡቲክ ንግድ ላይ ሠርተዋል:: በወቅቱ ከግብጽና ከሌሎች ሀገራት ጭምር በሻንጣ የሚመጡ የተለያዩ አልባሳት፣ ዊግና ሌሎች ቁሳቁስን ተቀብለው ነግደዋል:: ጎን ለጎንም ወደ ድሬዳዋ በማቅናት የጉምሩክ ዕቃዎችን በመጫረት የንግድ ሥራቸውን ማሳለጥ ቀጠሉ:: በዚህ ጊዜ ከኮንትሮባድ ጋር በተያያዘ ንብረታቸው በመንግሥት ተወርሶ የንግድ ሥራቸው ወደ ኪሳራ ገጥሞት እንደነበርም አልሸሸጉም::
ይሁንና ከደረሰባቸው ኪሳራ እንዴት መውጣት እንደሚችሉ ያወጡና ያወርዱ እንደነበር ያነሱት መቶ አለቃ ሰለሞን፤ የደረሰባቸውን ችግር የሰሙ ወዳጅ ዘመዶቻቸው በሃሳብም በገንዘብም ያግዟቸው እንደነበር ያስታውሳሉ:: በወቅቱ ከወዳጆቻቸው መካከል አንደኛው ለሥራ ማስጀመሪያ በሚል አፈላልጎ 20 ሺ ብር እንደሰጣቸውም ያስታውሳሉ::
መቶ አለቃ ሰለሞንም፤ ይህን ብር በመያዝ ወደ ኪሳራ ያመራውን ንግድ ለማነቃቃት ወደ ድሬዳዋ ሲያቀኑ በጉዟቸው የወታደር ቤት ጓደኛቸውን ያገኛሉ:: ይህ አጋጣሚ ዛሬ እያስተዳደሩት ያለውን ቱአር ኤን ፈርኒቸር የቤትና የቢሮ ዕቃዎች ማምረቻ ድርጅትን እንዲያቋቁሙ መሠረት ጥሎላቸው አልፏል:: በወቅቱ ወታደር ቤት የሚያውቁት የልብ ወዳጃቸው የጣውላ ሥራ ይሠራ እንደነበር ሲያጫውታቸው ሥራውን በጋራ ለመሥራት የወሰኑት በዛው ቅጽበት ነበር::
የጣውላ ሥራውን በጋራ ለመሥራት በወሰኑ ማግስትም ጣውላው በሚገኝባቸው የተለያዩ አካባቢዎች በመንቀሳቀስ መግዛትና መሸጥ ቀጠሉ:: ሁለት ሆነው በጀመሩት የጣውላ ንግድ ሥራ መንገድ ላይ ሌላ የወታደር ቤት ወዳጃቸውን አግኝተው ሦስት ሆነው ሲሠሩ ቆይተዋል::
ሥራው አዋጭ ቢሆንም የኮንትሮባንድ ባሕሪ ያለውና አስቸጋሪ ሥራ መሆኑን በመረዳት ጣውላ ከመሸጥ ይልቅ የጣውላ ምርቶችን መሸጥ የተሻለ እንደሆነ በማመን ጓደኛሞቹ ጣውላ ከመሸጥ ጣውላ ወደ መግዛት ተሸጋገሩ:: በዚህ ጊዜ ጣውላ ከሸጡላቸው ደንበኞች ቀሪ ሂሳብ ለመቀበል ወደ መገናኛ ያቀኑት መቶ አለቃ ሰለሞን፤ በዚህም የገበያውን ፍላጎትና አዋጭነቱን መረዳት እንደቻሉ ያስታውሳሉ:: ይህን የተረዱት መቶ አለቃ ሰለሞን፤ ሳይውሉ ሳያድሩ መሸጫ ቦታውን አፈላልገው በመከራየት ሞራሌ፣ አንጎላሬ፣ ጣውላ፣ መዝጊያና ክፈፍ የተባሉ ምርቶችን መሸጥ ጀመሩ:: በወቅቱ ጓደኛቸውም በግሉ ራሱን ችሎ መነገድ ጀምሮ እንደነበር አጫውተውናል::
ጣውላ ከመሸጥ ወጥተው የጣውላ ምርቶችን በመሸጥ ሦስት አስርት ዓመታትን ያስቆጠሩት መቶ አለቃ ሰለሞን፤ በአሁኑ ወቅት ሁለት ቦታዎች ላይ የተለያዩ የቤትና የቢሮ ዕቃዎች ማምረቻ ፋብሪካዎችን ማቋቋም ችለዋል፤ አንደኛውና የመጀመሪያው ማምረቻ አስኮ፣ ሁለተኛው ወሰን ግሮሰሪ መንገድ አካባቢ፣ ሦስተኛውና መጠነኛ ማምረቻ ያለው ነገር ግን በዋናነት መሸጫ የሆነው ድርጅት ደግሞ መገናኛ ላይ ይገኛል::
ቱአር ኤን ፈርኒቸር የቤትና የቢሮ እቃዎች ማምረቻ ድርጅት በዋናነት የሚያመርተው የቤት ውስጥና የኮንስትራክሽን ፈርኒቸሮችን እንደሆነ የጠቀሱት መቶ አለቃ ሰለሞን፤ ኮንስትራክሽን ፈርኒቸር የሚባሉት እንደ ኪችን ካቢኔት፣ ካፕቦርዶች፣ የግድግዳ ቁምሳጥኖች፣ የደረጃ መወጣጫዎች፣ ፐርኬዎች፣ ምንጣፎችና አጠቃላይ ከግንባታ ጋር አብረው ሊሄዱ የሚችሉ ምርቶችን ያመርታል:: ከዚሁ ጋር በተያያዘ ለግንባታ አጋር የሚሆኑ ጣውላዎች፣ ሞራሌና ሌሎችንም አዘጋጅተው ለገበያ ያቀርባሉ:: የቤት ውስጥ ፈርኒቸር የሚባሉትን እንደ ሶፋ፣ የምግብ ጠረጴዛና ሌሎችንም ያመርታሉ:: የድርጅታቸው ምርቶች በጥራትና በጥንካሬያቸው ተፈላጊ እንደሆኑ የሚናገሩት መቶ አለቃ ሰለሞን፤ ለምርቶቹ ገበያቸውም ቤት የሚሠሩ ግለሰቦችና የተለያዩ ድርጅቶች እንደሆኑ ነው ያስረዱት::
ከውትድርና ውጭ ያለውን ሕይወታቸውን በድለላ ሥራ ‹‹ሀ›› ብለው የጀመሩት መቶ አለቃ ሰለሞን፤ አንድ ብለው የጀመሩት ሥራ ሁለት፣ ሦስት እያለ ዛሬ ከደረሰበት ደረጃ መድረሱ ለሥራ ባላቸው ትጋትና ቁርጠኝነት እንደሆነ በማንሳት ሰው ከለፋና ከጣረ ከከፍታው ከፍ ማለት እንደሚችል ይናገራሉ:: መቶ አለቃ ሰለሞን፤ ዛሬ ከታወቁበት ቱአር ኤን ፈርኒቸር የቤትና የቢሮ ዕቃዎች ማምረቻ ድርጅት በተጨማሪ ዘመናዊ ሆቴል እየገነቡ እንደሆነም ይናገራሉ::
የሆቴል ግንባታውን እያከናወኑ የሚገኙት ከአዲስ አበባ 32 ነጥብ ስድስት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ሰንዳፋ በኬ ከተማ ሲሆን፤ ሆቴሉ ደረጃውን የጠበቀና ዘመናዊ እንደሆነ ተናግረዋል:: 41 ክፍሎች፣ አራት የስብሰባ አዳራሾች እንዲሁም ለአካል ጉዳተኞች ምቹ የሆኑ አራት ክፍሎች ያሉት ነው:: አራት ሺ ካሬ ሜትር ስፋት ባለው ቦታ ላይ ያረፈ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት ግንባታው እየተጠናቀቀ ይገኛል::
የሥራ ዕድል በመፍጠር ረገድም የድርሻቸውን እየተወጡ ያሉት መቶ አለቃ ሰለሞን፤ በፈርኒቸር ብቻ አዲስ አበባ ላይ 120 ለሚደርሱ ዜጎች የሥራ ዕድል ፈጥረዋል፤ አስኮ በሚገኘው ድርጅታቸውና በሆቴል ግንባታው የተሠማሩ ሠራተኞችን ጨምሮ 110 ለሚደርሱ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር የቻሉ ሲሆን፣ በድምሩ 330 ለሚደርሱ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር ችለዋል::
መቶ አለቃ ሰለሞን ማኅበራዊ ኃላፊነትን በመወጣት ረገድ በርካታ በጎ ተግባራትን የሚያከናውኑ ቢሆንም በዝርዝር ከመግለጽ ተቆጥበዋል:: ይሁንና ወታደር ቤት እያሉ የሚያውቋቸው በተለይም ጉዳት የደረሰባቸው ጓደኞቻቸው ከመቶ አለቃ ሰለሞን በርካታ ድጋፎች እያገኙ እንደሆነና ሌሎች ለተቸገሩ ሰዎችም በተለያየ መንገድ ድጋፍ ሲያደርጉ እንደነበርና አሁንም እያደረጉ እንደሆነ ከጓደኞቻቸው መረዳት ችለናል:: ከዚህ በተጨማሪም ግብር በአግባቡ ከመክፈል ባለፈ ሀገራዊ ለሆኑ ማንኛውም ጥሪዎች ፈጣን ምላሽ እንደሚሰጡም አጫውተውናል::
ከውትድርና ተነስተው በድለላና በተለያዩ የንግድ ሥራዎች ያለፉት መቶ አለቃ ሰለሞን፤ ወታደር ሆነው የገነቡት ማንነት ዛሬ ለደረሱበት ደረጃ ወሳኝ መሠረት የጣለ መሆኑን በመጥቀስ፣ ማንኛውም ዜጋ ወታደር ሆኖ ማለፍ እንዳለበት ይመክራሉ፤ ‹‹መንግሥት ብሔራዊ ውትድርናን መጀመር አለበት›› ሲሉም ነው የሚያስገነዝቡት:: እያንዳንዱ ዜጋ ወታደር ሆኖ መውጣት ከቻለ ጨዋነት፣ አገር ወዳድነትና ሕይወትን የሚለውጡ በርካታ ቁምነገሮችን ከውትድርና ሞያ መማር እንደሚችል በመግለጽ ሁሉም ሰው የወታደር ስብዕና ቢኖረው መልካም ነው ይላሉ::
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 28/2015