ዕለቱ እንደወትሮው ነው:: ልክ አንደትናንቱ ዛሬን ንጋት ተክቶታል:: ወፎቹ ተንጫጭተው ፀሀይ ማልዳ ፈንጥቃለች:: ጨለማው ገፎ ቀኑ ሊጀምር ተሰናድቷል:: ሀሳብ ውሎ የሚያድርበት የወይዘሮዋ ዓይምሮ ዛሬም ከልምዱ አልታቀበም:: አርቆ እያለመ ያቅዳል:: ከጭንቅ ጓዳው ገብቶ የቋጠረውን እየፈታ፣ የፈታውን ዳግም ያስራል::
ወይዘሮዋ ሁሌም ቢሆን እንዲህ ናት:: የጎደለ፣ ያልሞላው ዕልፍኝ ያሳስባታል:: በእጇ ያሉ በርካታ ነፍሶች የእሷ ጉዳይ ከሆኑ ቆይተዋል:: የእነሱ ህልውና፣ የህይወት ጓዛቸው ከትከሻዋ አርፏል:: ሸክሙ ቢያጎብጣትም ‹‹ደከመኝ›› ይሉትን አታውቅም:: መሽቶ እስኪነጋ ከጎናቸው ትቆማለች:: ህይወቷ ከህይወታቸው፣ ኑሮዋ ከኑሯቸው ተቆራኝቷል:: ለነዚህ ነፍሶች ከፈጣሪ ቀጥሎ ተስፋቸው ናትና ህመማቸው ያማታል፣ መከፋት ማዘናቸው ከልብ ያስነባታል::
ከአስራ ሁለት ዓመት በፊት
ዛሬም ሌላው ቀን መሽቶ ነግቷል:: አሁንም የወይዘሮ ሙዳይ ልቦና መልካምና ደጉን እያቀደ ያስባል:: ማለዳውን ከበሯ የደረሰችው እንግዳ ከሌሎች ጋር ጠንከር ያለ ወግ ይዛለች:: በዚህ ማለዳ እሷን መሰል እንግዳ ማየት ለሙዳይና ለስራ ባልደረቦቿ ብርቅ አይደለም:: ሁሌም ልጆች ይዘው የሚመጡ፣ ችግራቸውን የሚያስረዱ፣ ‹‹እርዱን፣ ተቀበሉን›› የሚሉ ወገኖች በርካታ ናቸው::
የእነሱና መሰሎቻቸው ችግር ዕንቅልፍ የነሳት ሙዳይ ምትኩ በልጅነት ዕድሜዋ የወጠነችው በጎነት ዛሬ ከፍሬ ደርሷል:: በርካታ ውጣውረዶችን ተሻግራም ለተቸገሩት ደራሽ፣ ላዘኑት ዕንባ አባሽ ከሆነች ዓመታት ተቆጥረዋል::
የሰዎች መከራና ችግር ሕመም ሆኗት ያቋቋመችው ግብረሰናይ ድርጅት ጥላ የሆናቸው በርካቶች ለችግራቸው መላና መፍትሄ አግኝተዋል:: ዛሬም ወደግቢው የሚመጡ፣ የህይወት ሸክም የከበዳቸው ነፍሶች ጥቂት አይደሉም:: ሙዳይ በማለዳው ከድርጅቱ ሰራተኞች ጋር የምታወጋው ሴት ጉዳይ ከዚሁ ሀሳብ እንደማይርቅ ገምታለች፡ በዛሬዋ እንግዳና በሰራተኞቹ መካከል ያለው ንግግርም ተራ ጨዋታ አለመሆኑ ገብቷታል::
ሙዳይ የምትሮጥ፣ የምትጣደፍበት ብዙ ጉዳዮች አሏት:: ትናንት በይደር የተወችው፣ ለዛሬ የቀጠረችው ብዙ ውጥን አለ:: ልትወጣ ተጣድፋለች:: በድንገት ግን ጆሮዋ ዘው ያለው ቃል ባለችበት አደንዝዞ ከእርምጃዋ አቀባት:: ሴትዮዋ ስለ አንድ ትንሽ ልጅ ታሪክ እያወራች ነው:: እየደጋገመች ‹‹እባካችሁ ባይሆን አብሉት፣ አጉርሱት ስትል ትማጸናለች::
ሙዳይ ይህን ቃል መልሳ መስማት አልቻለችም:: ውስጧ በእጅጉ ሲዝል፣ ሲፈተን ተሰማት:: ሴትየዋ እያወራች ያለችው ምግብ ቀምሶ ስለማያውቅ አንድ ትንሽ ልጅ ነው:: ሙዳይ ልማደኛ ዕንባዋ ከዓይኖቿ ተዘርግፎ ደረቷን ገምሶ መውረድ ያዘ::
ህጻን ልጅ ይልሰው ይቀምሰው አጥቶ ‹‹አብሉልኝ፣ አጠጡልኝ የመባሉ ተማጽኖ ከልብ አሳዝኗታል:: እሷ ሁሌም ለችግር ደራሽ ነች:: ጆሮዎቿ ክፉ ሰምተው፣ እግሮቿ ተራምደው አያልፉም:: እጀ ሰፊ መዳፏ ከመስጠት ባሻገር የወደቀን ሊያነሳ አይጠየፍም:: ምግብ በልቶ ስለማያውቀው ህጻን የሰማችው እውነት እንደ አዲስ ሆድ አስብሶ እያስለቀሳት ነው::
ሁሉም የእንግዳዋን ያልተለመደ ንግግር አልተቀበሉም:: ልጅ ያለምግብ መኖሩ ፈፅሞ አይታመንም:: እናም ይህች ሴት እርዳታ ለማግኘት ስትል ያመጣችው ሰበብ መሆኑን ገመቱ:: ሙዳይ በሴትየዋ ንግግር ልቧ ቢነካ በዕንባዋ ጭጋግ ምላሹን ልታገኝ ሻተች:: ውስጧ ያለውን ሀሳብ ከጥያቄ አዛምዳም ማብራሪያ ጠየቀች:: እንግዳዋ ስለ ሁሉም አልዘገየችም:: አንድ በአንድ እየተነተነች ታሪኩን መናገር ጀመረች::
ህጻኑ ብዘዎች እንደገመቱት የእሷ ሳይሆን የጎረቤት ልጅ ነው:: ከተወለደ አንስቶ ምግብ ይሉትን ቀምሶ አያውቅም:: ስለእሱ መኖር ግድ ያላት ይህች ሴት የልጁን ከፊል ታሪክ ለወይዘሮ ሙዳይ አወጋቻት:: ያለችው ሁሉ የሚታመን አይመስልም:: ጥቂት ቆይቶ ሴትየዋ ልጁን በአካል ይዛው እንድትመጣ ተወሰነ:: በዚህ ቃል ተስማምተውም በቀጠሮ ተለያዩ::
ማግስቱን
እነሆ ዛሬም የወይዘሮ ሙዳይ የሩጫ ቀን ነግቷል:: እንደሁልግዜው ማለዳዋን በተለመደው የስራ ትጋት ጀምራለች:: በክፍሉ በርከት ያሉ ህጻናት ቁርስ ለመብላት ተቀምጠዋል:: ሙዳይ ለትንንሾቹ ወተት እየቀዳች ዳቦ ነክራ ታጎርሳለች:: በድንገት ካጎነበሰችበት ቀና አለች:: የትናንትናዋ ሴት ልጅ አዝላ ቆማለች:: ዓይኗን ከታዘለው ህፃን ሳትነቅል በፈገግታ ተቀበለቻት::
ልጁ ከእንግዳዋ ጀርባ እንደታዘለ ተኝቷል:: የሁለት ዓመት ህጻን ነው:: ሙዳይ ሴትዬዋ የመጣችበትን ጊዜ እንደ መልካም አጋጣሚ ቆጥራዋለች:: በዚህ ሰዓት ልጆቹ ቁርሰ ይመገባሉ:: ለሴትዬዋ ልጁን እንድታወርደው ነገረቻት:: ያለቻትን አደረገች:: ያዘለችበትን ጨርቅ ፈትታ ልጁን ማውረድ ስትጀምር ቤቱ በተለየ ክፉ ሽታ ታወደ::
የህጻኑ ልብስ በእጅጉ ቆሽሷል:: ውሀ ነክቶት የማያውቀው አካሉ ከቁስቁልና ተዳምሮ ችግሩን ያሳብቃል:: ልማደኛው የሙዳይ ልብ በሀዘን መድማቱን ያዘ:: የምታየውን አምኖ መቀበል ተሳናት:: ቀረብ ብላ ህጻኑን አስተዋለችው:: እጅግ የሚያምሩት ትላልቅ ዓይኖቹ ያሳሳሉ:: ድፍት ያለ ጥቁር ጸጉሩ የተለየ አድርጎታል::
ወዲያው ልጁን ተቀብላ ልብሱን ቀየረች:: በጥንቃቄ ታቅፋ ከህጻናት ወንበር ደጋግፋ አስቀመጠችው:: ወተት ቀድታ ዳቦ ነከረችና ወደ አፉ ተጠጋች:: መራቡን ስለምታውቅ ፈጥኖ አፉን እንደሚከፍት ገምታለች:: በልጁ ገጽታ የተለየ ስሜት አላየችም:: የምታደርገውን እንዲያውቅ ምልክት ሰጠችው:: የታሰበው አልሆነም:: ልጁ ምግብ ቀምሶ አያውቅምና የማኘክ ሙከራ እንኳን አላሳየም::
እሷን ጨምሮ የግቢው ሰራተኞች በዕንባ ተራጩ:: ተስፋ ያልቆረጠችው ሙዳይ ወተት ያራሰውን ዳቦ ይዛ ዳግም ወደ ልጁ ተጠጋች:: ህፃኑ አሁንም በአፉ ስለደረሰው ምግብ አንዳች ያወቀው የለም:: በጥርሶቹ መሀል ያለውን ዳቦ እንደያዘ ደቂቃዎች ተቆጠሩ:: ህፃኑ በቀን አንዴ ብቻ በጡጦ ከሚቀምሰው የጤፍ አጥሚት በቀር ከምግብ ተገናኝቶ አያውቅም::
ሙዳይ ዛሬም ድረስ የምታለቅስበት ይህ ታሪክ ዕለቱን የነበረው ገጽታ የተለየ እንደነበር ታስታውሳለች:: ልጁ ምግብ ቀምሶ አለማወቁ ከታየ በኋላ ያመጣችው ሴት እያመላለሰች እንድታበላው ተወሰነ:: እንዲያም ሆኖ የልብ አልደረሰም:: ልጁ አሁንም ከጉዳት አላመለጠም:: ሁኔታው አሳሳቢ ቢሆን ሌሎች አማራጮች ሊፈለጉ ግድ ሆነ:: እሱነህን ልትቀበለው ከውሳኔ ደረሰች::
ይህ ከመሆኑ በፊት ሙዳይ ስለልጁ እናት አባት ማወቅ ፈለገች:: እንደ እናት መከታ የሆነችውን የጎረቤት ሴትም ጠየቃቻት:: ለህጻኑ ወላጅ እናት ያልሆነችው ድንቅ እናት ታሪኩን አልደበቀቻትም:: ስለ ትንሹ ልጅና ስለ ወላጆቹ ያለውን ሀቅ አንድ በአንድ ነገረቻት::
እውነታ
ባልና ሚስቱ ትዳር ይዘው ጎጆ ወጥተዋል:: ኑሯቸው ድህነት ባያጣውም ዓይናቸውን በዓይናቸው ለማየት ይሻሉ:: የጎደለው ህይወት ባይሞላም፣ ወግና ልማድ መቀጠሉ አይቀርም:: የጥንዶቹ ዓለም የልጅ ሳቅና ጨዋታ ነው:: በልጅ ፍሬ የጎደለ ተስፋቸው ይሞላል:: የደበዘዘ ሳቃቸው ይደምቃል:: አሁን የባልና ሚስቱ ውጥን ተሳክቷል:: ወይዘሮዋ ወንድ ልጅ ወልዳ ታቅፋለች::
ለጥንዶቹ ትዳር ደማቅ ብርሀን የሆነው ጨቅላ በዓይን ሊያዩት ያሳሳል፣ ዓይኖቹ፣ ጸጉሩ፣ መላው ሰውነቱ ያምራል:: ይህን ያስተዋሉ ወላጆች ለልጃቸው ይሆናል፣ ይመጥናል ያሉትን ስም ቸሩት ‹‹የእሱነው›› ብለው ሰየሙት::
ትንሹ የእሱነው በእናቱ ዕቅፍ ተኝቶ ይውላል:: የተለየ ባህርይ የለውም:: ከፍ ማለት ሲጀምር ወላጆቹ ለውጡን አብዝተው ናፈቁ:: ዕድሜውን እየቆጠሩ፣ መዳህ መሮጡን አሰቡ:: ማውራት መሳቁን ጠበቁ:: እሱነህ በእነሱ ምኞት ልክ አልፈጠነም:: እንደዕድሜ እኩዮቹ አልተነሳም፡፣ አልሳቀም፣ አልቦረቀም::
እሱነህ ስድስት ወር ሲሞላው ወላጆቹ እውነቱን አወቁት:: የህጻኑ የሚያምሩ ዓይኖች ፈጽሞ አያዩም፣ ሰውነቱ አይንቀሳቀስም፣ አንደበቱ ቃል አያወጣም:: እናት አባት ተስፋ ቆረጡ:: የአካባቢውን አፍ፣ የመንደሩን ጉምጉምታ ፈሩ::
ውሎ አድሮ ክፉ ወሬ ከጆሯቸው ደረሰ:: የልጃቸው እንዲህ መሆን ከእርግማን፣ ከሀጢያት ብዛት የመጣ መሆኑ ተነገራቸው:: እነሱም ማስተባበሉን አልፈለጉም:: እሱነህ በሀጢያት የመጣ፣ በእርግማን የተገኘ ፍሬ መሆኑን አመኑ::
ይሙት! በቃ
የእሱነህ እናት አባት የሀጢያት፣ የእርግማን ፍሬ ነው ያሉትን ልጅ ሊያቅፉት፣ ሊንከባከቡት አልፈለጉም:: ስድስት ወር እንደሞላው በዓይኑ ብርሀን ተስፋ ቆረጡ:: ጡት አስጥለው በአንዲት ጡጦ የጤፍ አጥሚት አስለመዱት::
አሁን ራሱን የማያውቅ፣ ዓይኑ የማያይ፣ ልጅ አያስፈልጋቸውም:: እስትንፋሱ እስካለ በህይወት እንዲኖር ፈቅደውለታል:: ከአንድ ጨለማ ቤት ዘግተውበት ሲውል ተለክታ የምትጣልለት አንዲት ጡጦ በአጥሚት ተሞልታ ትጣልለታለች:: እሷን በደመነፍስ እየማገ ከራሱ ዓለም ይታገላል:: መራቡን፣ መሽናት መቃጠሉን የሚያውቅለት፣ የለም::
ትንሹ እሱነህ ዕድሜው ሁለት ዓመት እስኪሞላ ምግብ የሚባል ቀምሶ፣ አላምጦ አያውቅም:: ያለሰው ትንፋሽ በጨለማ ቤት ያሳለፋቸው ቀናት ልጅነቱን ነጥቀውታል:: ከሰውነት ተራ አውጥተው በጉስቁልና አራቁተውታል:: ትንሹ ልጅ ሰው ባለበት ዓለም ከዓለም ተገልሎ፣ በወላጆቹ ተጠልቶ ፈታኝ የመከራ ቀናትን ገፍቷል::
ይህን ሁሉ ግፍ በቅርብ የምታየው የአምስት ልጆች እናት በእሱነህ ጉስቁልና ልቧ ሲያዝን ኖሯል:: እንዳትወስደው አቅሟ አይችልም:: እንዳትቃወም እሱነህ በወላጆቹና በአካባቢው የእርግማን ፍሬ መሆኑ ታምኖበታል:: እንዲያም ሆኖ ዝም አላለችም:: እውነታውን ይዛ፣ ህጻኑን አዝላ ከሙዳይ በጎ አድራጎት ድርጅት ደረሰች::
አዲስ ዓለም
ወይዘሮ ሙዳይ የእሱነህን ችግር በአይኗ ካየች ወዲህ ዕንቅልፍ ይሉት አጥታለች:: የትንሹን ልጅ የመኖር ተስፋ ልታስቀጥል፣ የዓይኖቹን ጤንነት ልታረጋግጥ ጥረቷን ይዛለች::
አንድ ማለዳ ሙዳይ ህጻኑን ለአንዲት እናት አስይዛ ወደ ሆስፒታል ጉዞ ጀመረች:: እየነዳች ነው:: ሁሌም በመንገዷ ዓይኖቿ ግራ ቀኝ ያያሉ:: በአጋጣሚ ትራንስፖርት የሚጠብቁ አቅመ – ደካሞች ካገኘች ጠርታ ታሳፍራለች:: የዛን ዕለትም አንድ ሽማግሌ በርቀት ብታይ አጠገባቸው ደርሳ ቆመች:: ሰውየው አመስግነው ከመግባታቸው በፊት አንዲት ወጣት ቀድማቸው የጋቢናውን በር ከፍታ ገባች::
ሙዳይ የልጅቷ ድርጊት ቢያስገረማትም አንዳች አላለችም:: ወዲያው ሁሉንም ይዛ ጉዟዋን ወደፊት ቀጠለች:: ከጋቢናው የተቀመጠችው ሴት ለመናገር አልዘገየችም:: ፊቷን ወደኋላ አዙራ ስለህጻኑ ማብራሪያ ጀመረች:: በቅድሚያ ልጇ እንደሆነ ጠየቀቻት:: መልሱን አስክትሰማ አልቆየችም:: የጤና ባለሙያ መሆኗን ነግራት በህጻኑ ላይ ስለሚታየው ችግር ይበልጥ ቅርበት እንዳላትና በሙያዋ ልትረዳት እንደምትፈልግ ነገረቻት:: ቀልጣፋዋ ወጣት ካሰበችው ደርሳ ስትወርድ ሙሉ ማንነቷን የሚገልጽ የአድራሻ ካርድ ትታላት ነበር::
ሁሉ ለበጎ
ሙዳይ የዛን ቀን ከሆስፒታሉ ደርሳ ስለህጻኑ ችግር ተረዳች:: ለዓይኑ አለማየት ቀዶ ህክምና ቢኖርም ከሂደቱ በኋላ አይኑ ላያይ፣ እሱም ሊሞት እንደሚችል ተነገራት:: ምግብ ለማስለመድም በህክምናው የተካነ የራሱ ባለሙያ እንደሚያስፈልግ ተብራራላት::
ይህን በሰማች ጊዜ ሙዳይ ጠዋት መኪናዋን ከፍታ የገባችውን ወጣት አስተውሳ ስልኳን አነሳች:: ወጣቷ በሀኪሞቹ የተነገራት አይነት በሙያው የተካነች ሴት ነበረች:: ሙዳይ ህልም የመሰላትን እውነት እያሰበች ነው:: የስልክ ጥሪዋን ‹‹ሀሎ››ስትል የተቀበለችው ወጣት ለይሁንታዋ እጅግ ፈጣን ሆነችላት::
ትንሹ ልጅ በሙዳይ
ዛሬ እሱነህ የአስራ ሁለት ዓመት ልጅ ነው:: ሰውነቱ በእጅጉ አምሮ ተለውጧል:: በህክምናው ብዙ ቢሞከርም ውጤቱ እንደታሰበው አልሰመረም:: ልጁ አሁንም መናገር፣ ማየትና መንቀሳቀስ አይችልም:: በእናት አባቱ ይሁንታ ድርጅቱ ልጁን ከተረከበ ወዲህ ከግቢው ቤተሰቦች ጋር ተቀላቅሏል:: የራሱ ተንከባካቢ ሞግዚት አለው:: ህጻኑ ምግቡን ለይቶ የሚያውቀው በሽታና መአዛው ነው:: አመጋገቡ እንደሌሎች አይደለም:: የሚቀምሰው ሁሉ በተለየ ጥንቃቄና ጥራት ይዘጋጅለታል::
ትንሹ ልጅ ለሬዲዮና ሙዚቃ የተለየ ስሜት አለው:: እነዛ ውብ ዓይኖቹ ዛሬም ለብርሀን አልታደሉም:: የሚወደውን ሰው በጭብጨባ ይቀበላል:: የማይፈልገው ሲኖርም ብስጭት መገለጫው ነው:: የሴት ድምጽ ሲሰማ ‹‹እማ..›› እያለ ይጣራል፣ ከወንድ ድምጽ ቀጥሎም ‹‹አባ…›› ማለት ልማዱ ነው:: እንዲህ መሆኑ ብቻ ለሙዳይና አጋሮቿ ታላቅ ተስፋ ነው::
ከዓመታት በፊት ከሙዳይ ጋር የመንገድ አጋጣሚ ያገናኛቸው ወጣት ዛሬ የእሱነህ የግል ባለሙያ ነች:: ምግብ መብላትን፣ ራስ ችሎ መቀመጥን በብዙ ጥረት አስለምዳዋለች:: የግቢው ቤተሰብ እሱነውን በተለየ ፍቅር ያየዋል:: በህክምናው ተስፋ ቢያጣም ስለእሱ መኖር ሁሉም በየዕምነቱ ይጸልይለታል:: እሱነህ ትናንት በወላጆቹ፣ በማህበረሰቡ የተጣለ ጨቅላ፣ ባልተገባ አመለካካት ‹‹ይሙት በቃ›› ተፈርድቦት ሁለት የስቃይና የጨለማ ዓመታትን የገፋ ምስኪን:: ፍጡር መሆኑ ተዘንግቶ ከአፈር ከትቢያ የተጣለ ህጻን:: ዛሬ ክቡር የሰው ልጅ መሆኑ ቢለይ ማንነቱ ሚዛን ደፍቷል:: ታላቅነቱ ተመስክሮም ንጹህ የሙዳይ ወርቅ ሆኗል::
መልካምሥራ አፈወርቅ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 28/2015