ስለ ልጅ – የእናት ትከሻ

በጀርባዋ በዕድሜው ከፍ ያለ ልጅ አዝላ ስትራመድ ያያት ሁሉ በሁኔታዋ ይገረማል። ፊቷ ላይ መሰልቸት አይነበብም። ሁሌም በፈገግታ፣ በብሩህ ገጽታ ትታያለች። እሷ ስለልጇ ካሏት ጉልበቷ ይበረታል፣ ጥንካሬዋ ያይላል። ‹‹ለላም ቀንዷ አይከብዳት›› ሆኖ በየቀኑ ልጇን አዝላ ትጓዛለች። መሽቶ በነጋ ቁጥር ብርቱ ትከሻዋ ልጇን ለማዘል ይዘጋጃል። ሁሌም ፈጣን ነች። ቀልጠፍ ያለ አረማመዷ ትልቅ ልጅ ያዘለች አያስመስላትም።

የታምሩ እናት…

ዛሬ ታምሩ አስራሶስት ዓመት ሆኖታል። ለእናት እማዋይሽ ግን አሁንም ልክ እንደ ሶስት ዓመት ህጻን ነው። ታምሩ ከተወለደ ጊዜ አንስቶ በእግሩ መራመድ አይችልም። እስከዛሬ የእናቱ ጀርባ ምቹ ማረፊያው ነው። የትም ብትሄድ ከእሷ አይለይም። አሁን ደግሞ ዕድሜው ጨምሯል፣ ሰውነቱ ከብዷል፣ ውሎ አድሮ ከጉርምስና፣ ከወጣትነት ይደርሳል። ለእናት እማዋይሽ ግን ይህ ሁሉ አይገርምም። በሌሎች ዓይን የሚከብደው እውነት በእሷ ዘንድ ሁሌም ቀላል ነው። ሰው ባያት ቁጥር ለውስጧ እንዲህ ትለዋለች፣ ‹‹ልጄ ለእኔ ስጦታዬ ነው›› ።

ከዓመታት በፊት…

የሁለት ሴት ልጆች እናት የሆነችው ወይዘሮ ሶስተኛ ልጇን ነፍሰጡር ናት። በሥራ ባተሌ ብትሆንም ስለጤናዋ ትኩረት አላት። በየጊዜው የዕርግዝና ክትትል ታደርጋለች። እስከዛሬ የተሻለ ነው ባለችው የግል ህክምና ላይ ነበረች። ዘጠነኛ ወሯን ስትይዝ ግን ሀኪሟ ወደ ጥቁር አንበሳ ሆሰፒታል መሄድ እንዳለበት ነገራት። በድንጋጤ ክው ብላ ለምን ስትል ጠየቀች። ሀኪሙ የአልትራሳውንዱን ውጤት እያነበበ አራተኛ ወሯ ላይ የተነገራት ጉዳይ ስለመኖሩ ጠየቃት። ፈጽሞ የሰማችው ነገር አለመኖሩን መለሰች።

እንደተባለው ሆኖ ወደ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል አመራች። አሁን የመውለጃ ወሯ ገብቷል። ቢደክማትም በየጊዜው ምልልሷን ጀምራለች። የሀኪሞች ቀጠሮ ቀጥሏል። የእሷም ምልልስ እንዲሁ። ሳምንት አልፎ ሳምንት በመጣ ቁጥር መውለዷን ናፈቀች። ሀኪሞችም ይህን ቀን ጠበቁት። ጊዜ የተቆጠረለት ምጥ በሰአቱ አልመጣም። አሁን እንደዋዛ ዘጠነኛው ወር እያለፈ ነው።

እማዋይሽ ከሆስፒታሉ ደጃፍ አልጠፋችም። በእሷ አቆጣጠር እርግዝናዋ አስረኛ ወሩን ይዟል። የሀኪሞቹም ግምት ከዚህ አላለፈም። አሁንም ቀን የምትቆጥረው ወይዘሮ አስረኛው ወር እንዳለፈ ተናገረች። ሀኪሞቹ ‹‹ሀሰት›› ሲሉ አልሞገቷትም። ምጡ በራሱ ጊዜ እስኪመጣ መጠበቅ እንደሚያስፈልግ ነገሯት። እየጨነቃት ፣ እያዘነች እንደሰማይ የራቃትን ቀን በትዕግስት ጠበቀች።

የአርግዝናዋ አስራአንደኛ ወር ‹‹አንድ…››ሲል ጀመረ። አሁን የወይዘሮዋ ውሎ በዕንባ መታጀብ ይዟል። እየጨነቃት፣ በራሷ ክፉ ዕድል እያዘነች ነው። ይህ ስሜት ግን በውስጧ የሚመላለሰውን እውነት ለሀኪሟ አሳውቃ ከውሳኔ እንድትደርስ አስገድዷታል። እሷ ሁለት ልጆች አላት። እነሱ አድገው ለቁምነገር እንዲደርሱ የእሷ በሕይወት መኖር ግድ ይላል። በሆዷ ያለው ልጅ ጤናማ ካልሆነ ደግሞ ውሳኔ ሊሰጥበት ያስፈልጋል።

ጭንቀቷን የተረዱት ሀኪሞች ወይዘሮዋ ሁለት ጊዜ እንድትጎዳ አልፈለጉም። አሁንም ምጡ በራሱ ጊዜ እንዲገፋ መጠበቁን አምነውበታል። የተባለችውን ሰምታ ወደቤቷ የገባችው እማዋይሽ ስለራሷ ማሰብ ትታለች። ዘጠነኛ ወሯ ካለፈ ወዲህ አዲሱን ህጻን በጉጉት እየጠበቀችው አይደለም። ከሀኪሞቹ ጭላንጭል ተስፋ ያላገኘችው ወይዘሮ ወልዳ የምትታቀፈው ህጻን እንደሌለ አውቃለች። የሚሆነው ሆኖ ለልጆቿ በህይወት መትረፍን ብቻ ትሻለች።

አዲሱ ዓመት ጀምሯል። ዕንቁጣጣሽ በድምቀት ተከብሮ ካለፈ ጥቂት ቀናት ተቆጥረዋል። የእርግዝናዋ አስራሁለተኛ ወር የገባው ወይዘሮ ዛሬም በተስፋ መቁረጥ አንገቷን ደፍታ ውላለች። መላ የጠፋለት ጉዳይ ከእሷ አልፎ የሚውቋትን ሁሉ እያነጋገረ ነው። አሁንም ‹‹በራሱ ገፍቶ ይምጣ›› የተባለውን ምጥ በተስፋም፣ ያለተስፋም መጠበቁ ግድ ብሏታል። አሁንም አስራሁለት ወራትን ካስቆጠረ እርግዝና መልካም ነገር እንደማይጠበቅ እያመነች ነው።

ከአስራ ሁለት ወራት በኋላ …

አዲሱን ዓመት ተከትሎ የሚመጣው የመስቀል በዓል በአክባሪዎቹ ዘንድ በጉጉት ይጠበቃል። ለእማዋይሽ ግን ይህ ቀን ከወትሮው የተለየ አልሆነም። ዛሬም በኀዘን አንገቷን አስደፍቶ ያስቆዝማት ይዟል። ለእሷ ዕለቱ ዓውደ ዓመት አልሆነም። ልክ እንደትናንቱ በጭንቅ ተቀብላዋለች። በድብርትም ውላለች። በድንገት የተሰማት ህመም ግን ሁኔታዎችን በፍጥነት ሊለውጥ አልዘገየም። ወይዘሮዋ ይህ ስሜት ምጥ መሆኑ አልጠፋትም። ድንጋጤ አይሉት ደስታ ወረራት። ጊዜ አልፈጀችም ። በፍጥነት ወደ ሆስፒታል ሄደች።

ከሆስፒታሉ ስትደርስ ጊቢው ያለወትሮው ጭር ብሏል። ከጥቂት ባለሙያዎች በቀር ማንም በሥፍራው የለም። ወደሚመለከታቸው ጠጋ ብላ የመጣችበትን ጉዳይ ተናገረች። ቀኑ ዓውደ ዓመት መሆኑን ያስታወሷት የዕለቱ ተረኞች ሀኪም እንደሌለ ነገሯት፣ አንድ መርፌ ወግተውም ወደቤቷ መለሷት።

ከሃያአራት ሰአት ቆይታ በኋላ ወይዘሮዋ በሆስፒታሉ እገዛ ወንድ ልጅ ወለደች። በሕይወት ስለመኖሩ ዓይኗን አላመነችም። እውነቱ ግን ከዚህም ያለፈ ሆነ። አምርሮ የሚያለቅሰው አዲሱ ጨቅላ በእርግጥም አጠገቧ ነው። በግርምታ እያየችው የሀኪሞቹን ገጽታ አስተዋለች። በሕይወት ስለመቀጠሉ ተስፋ አልሰጧትም።

አምጥተው ያስታቀፏትን አሳዛኝ ህጻን በስስት እያየች ዳሰሰችው። ጀርባው ላይ በግልጽ የሚታይ ፊኛ መሰል ነገር ተቀምጧል። እናት ምንድነው? ስትል ጠየቀች። ምላሽ ከማግኘቷ በፊት ግን ፊኛ መሰሉ ነገር እጇ ላይ ፈንድቶ ነበር።

እናት በውቅቱ በግልጽ ባይገባትም የህጻኑ ጀርባ ክፍት ነበር። ይህ አጋጣሚ ከስንት አንዴ በእርግዝና ጊዜ በጨቅላ ህጻናት ላይ የሚከሰት ነው። ሀኪሞቹ በፎሊክ አሲድ እጥረት የሚፈጠር ችግር መሆኑን ይናገራሉ። ለወይዘሮዋ ግን ይህ አይነቱ ገጠመኝ ፍጹም አዲስና ያልተለመደ ነው።

አሁን ህጻኑ ሙቀት እንዲያገኝ ወደ ሌላ ሆስፒታል መሄድ ይኖርበታል። ‹‹ልጅ ይኖረኛል›› ብላ ያላሰበችው እናት ለህጻኑ የሚሆን ልብስና መታቀፊያ አላዘጋጀችም። ለሊቱን ወደተባለው ስፍራ ልጁን ለመውሰድ የተነሱ ጎረቤቶቿ በጋቢዋ ጠቅልለው ከአጠገቧ ይዘውት ወጡ።

በሆስፒታሉ ብቻዋን የቀረችው እናት ህጻኑን ወደ ሌላ ሆስፒታል ልካ የሚሆነውን መጠበቅ ያዘች። ከአስራሁለት ወራት እርግዝና በኋላ ሕይወት ያለው ልጅ መውለዷ አሁንም እያስገረማት ነው። ጥቂት ቆይቶ ህጻኑን ይዘውት የወጡት ሰዎች ተመልሰው መጡ። የሄዱበት ጉዳይ እንደታሰበው አልተሳካም። አሁን ልጇ ዳግም ከጎኗ ተኝቷል። ደስ ብሏታል። ማግስቱን ሊጎበኝዋት የመጡት ሀኪሞች ወደ ቤቷ መሄድ እንደምትችል አረጋግጠዋል።

አሁን ወይዘሮዋ ቤቷ ገብታ አረፍ ብላለች። እስካሁን በትንሹ ልጅ ያስተዋለችው አዲስ ነገር የለም። ከቀናት በአንዱ ግን በመታቀፊያው ላይ የተለየ ነገር ያየች መሰላት። የጠቀለለችበት ፎጣ ባልተለመደ ሁኔታ እየራሰ፣ እየወረዛ፣ ነው። እናት እማዋይሽ ባየችው እውነት በእጅጉ ደነገጠች። ቀስ ብላ የልጇን አካል በስሱ ዳሰሰችው። በጀርባው በኩል የፈነዳ ነገር አለ። የፎጣውን ውርዛት ዳግም እያየች መነሻውን አጠናች። ምክንያቱ አልጠፋትም። ከጀርባው እየፈነዳ የሚፈሰው እርጥበት ነበር።

በህክምና ቀጠሮዋ ቀን እማዋይሽ ህጻኑን ይዛ ሀኪሞች ፊት ቀረበች። የልጁን ችግር በወጉ የተረዱት ባለሙያዎች ቀዶ ህክምና እንደሚያስፈልገው ነገሯት። ብትደነግጥም ምርጫ አልነበራትም። ሁለተኛ ወሩ ላይ የመጀመሪያው የጀርባ ላይ ቀዶ ህክምና ተካሄደ። ይህ ከተጠናቀቀ ጥቂት ቀናት በኋላ በጭንቅላቱ ላይ የከፍታ ለውጥ ታየ። እያደገ እየተለወጠ የመጣው ሂደት መፍትሄ ማግኘት ነበረበት። ሁለተኛ ዓመቱ ላይ ሁለተኛው ቀዶ ህክምና ተደረገለት።

ልጁን ጠቅልለሽ ጣይው…

እማዋይሽ ጤና ያጣ ልጇን ከአጠገቧ አታርቅም። ብዙ መከራና ስቃይ እየከፈለችበት ነውና እንደ ዓይኗ ብሌን ታየዋለች። ይህ እውነት ግን በባለቤቷ ዘንድ አልተደገፈም፣ ባልና ሚስት ልጁ ከተወለደ ጊዜ አንስቶ ሰላም የላቸውም። ባል ለእሱ የመጀመሪያ ልጁ ቢሆንም ዕለት በዕለት እያየው ተስፋ ቆርጧል። ሁልጊዜም እንደማይበጅ፣ እንደማይጠቅም አድርጎ ይናገራታል። ልጃቸው ለመንግሥት፣ አልያም ለሚያሳድጉ ሰዎች ቢሰጥ ደስታው ነው። እንደውም አንዳንዴ ከቤት እንድታርቀው ጠቅልላ እንድትጥለው ይገፋፋታል።

የእማዋይሽና የባለቤቷ ኑሮ በተቃርኖ ሆኗል። አሁን ለእሷና ለልጇ ከራሷ በቀር ማንም እንደሌለ አውቃለች። ከቀድሞ ትዳሯ የወለደቻቸው ሁለቱ ሴት ልጆች ዕድሜያቸው ገና ነው። ፈጽሞ ከጎኗ የሚቆሙና በኑሮ የሚያግዟት አይደሉም። ህጻኑ ሁለተኛ ዓመቱን እንዳለፈ አባቱ ቤቱን ትቶ ሊሄድ ግድ ሆነ። ወይዘሮዋ አልተቃወመችውም። ፍርድቤት አቁማ አልሞገተችውም። በይሁንታ መልካሙን ተመኝታ ሸኘችው።

የእናት እማዋይሽ የመከራ ሕይወት አንድ ሲል ቀጠለ። የቤት ኪራዩ ችግር ፣ የኑሮው ጫና፣ ልጆች የማሳደጉ ሃላፊነት በእሷ ጫንቃ ብቻ አረፈ። ከሁሉም ግን የትንሹ ልጅ ጉዳይ ያሳስባታል። በመከራ ፣በችግርና በብቸኝነት እየተሰቃየች ታሳድገዋለች። ለእሷ የልጇ መኖር ትርጉሙ ይለያል። ብዙ ብትሆንበትም እንደአባቱ አትሰለችውም፣ አትጠላውም።

ልጇ አይኖርም፣ ይሞታል፣ ቢባልም ዛሬ በሕይወት አለ። በአባቱ ይጣል፣ ይወርውር ተብሎ የተፈረደበት ጨቅላ አሁንም ከጎኗ ነው። ይህን ሀቅ ደግሞ ለመጠሪያነት በሰጠችው ስያሜ ገልጻዋለች። ብዙ ላየችበት፣ ለተፈተነችበት ውድ ልጇ ‹‹ታምሩ›› ስትል ስም አውጥታለች።

ዛሬም ታምሩና እናቱ ብቻቸውን ናቸው። የጭንቅላቱ ቀዶ ህክምና ከተደረገ በኋላ ጥቂት ለመዳህ ሞክሮ ነበር። ውሎ አድሮ ግን የታሰበው አልሆነም። የታየው የዳዴ ተስፋ ሳይቀጥል ቀረ። በድንገት ከዊልቸር ላይ መውደቁ ደም ወደ ጭንቅላቱ እንዲፈስ ምክንያት ሆኖ ከእንቅስቃሴ ታቀበ። ታምሩ በደረሰበት አደጋ አጥንቱ ተሰብሮ ነበር።

ችግሩን ተከትሎ የጭንቅላት ቲቪ መከሰቱ ደግሞ በብዙ ስቃይ አመላለሰው። ከሁለተኛው የጀርባ ቀዶ ህክምና በኋላ ለስምንት ወራት አንዳች ሳይናገር አንደበቱ ተዘግቶ ነበር። በተደጋጋሚ ‹‹ሞቷል›› ተብሎ የተለቀሰበት ጊዜ ጥቂት አልነበረም ። ከዚህ ሁሉ ትግል በኋላ የእናት ትከሻ እሱን ለማዘል ተዘጋጀ። ወይዘሮዋ ታምሩን እያዘለች በኑሮና ሥራዋ ባዘነች።

በየቤተክርስቲያኑ በበዓላት ቀን የምትሸጠው ጧፍ መተዳደሪያዋ ነው። ልጇን ከጎኗ አስተኝታ ያያት ሁሉ በኀዘኔታ ከእሷ ለመግዛት ልቡ ይፈቅዳል። የወጥ ቤት ረዳትነት ባገኘች ጊዜም ሰርታ ትገባለች። ልጇ ህክምና ባለው ቀን በጀርባዋ አዝላ የቻለችውን በአውቶቡስ ቀሪውን በእግሯ መጓዝ ልማዷ ነው። ዳይፐር ለመግዛት አቅሙ ስለሌላት ለህጻኑ ሽንት የምታስርለት ጨርቅ ከልብሷ ቀዳ ነበር።

አንዳንዶች ታዲያ ገና ሲያይዋት አፍንጫቸውን ይዘው ይርቋታል ፤ እንዳትቀርብ፣ እንዳትጠጋቸው ያገሏታል። እማዋይሽ አንዳንዴ በሁኔታዎች ትከፋለች። በሩቅ አይተው ከንፈር በሚመጡት፣ አፋቸውን ይዘው በሚያሽሟጥጡት ሰዎች ድርጊት ታዝናለች። ዛሬም ድረስ ታምሩ የዳይፐር ተጠቃሚ ነው።

እንዲያም ሆኖ እናት ልጇ ከፈጣሪ የተቸራት ስጦታ ለመሆኑ ለአንድም ቀን ተጠራጥራ አታውቅም። ስለሁሉም ፈጣሪዋን ታመሰግናለች። ደግነቱ የቀን ውሎዋ በክፉ አጋጣሚዎች ብቻ የተሞላ አይደለም ። በርካታ ልበ መልካሞች ደግሞ ስለእሷ ሕይወት ይጨነቃሉ። ችግሯን ባዩ ባገኝዋት ቁጥር የእጃቸውን ይሰጧታል። ለዳይፐር፣ መግዣ፣ ለቀለብ መሸመቻ ይሸጉጡላታል። ስለእነሱ ሁሌም የተለየ ክብር አላት።

ክፉ ቀናት …

ታምሩ ገና ህጻን ሳለ እናት እማዋይሽ የሥራ አማራጮች አልነበሯትም። እሱን ተንከባክቦ ሌሎች ልጆቿን ለማሳደግ እጅ ያጥራታል። በቂ ምግብ ስለማትወስድ ጡቶቿ ይደርቃሉ። ለህጻኑ ቆርሳ እንዳታጎርስ ጓዳ ሞሰቧ ባዶ ነው። አንገቷን ደፍታ ታስባለች፣ አምርሮ የሚያለቅስ ልጇን ስታይ የምትይዝ ፣ የምትጨብጠው ይጠፋታል።

አንድ ቀን ግን ነገሮች ሁሉ የከፉ ሆኑባት። በቤቱ የሚላስ የሚቀመስ አልነበረም። ዛሬም ልጇ ዓይኖቹን በዓይኗ ላይ ያንከራትታል። እንደራበው አልጠፋትም። የደረቁ ወተት አልባ ጡቶቿን አየያቸው። አንዳች የሚፈይዱት የለም። ፈጥና ወደጓዳዋ ገባችና ማንጎዳጎድ ጀመረች።

በድንገት እጆቿ ከአንድ ዕቃ ጋር ተገናኙ። ፈጥና ከፈተችው። ርጋፊ የበቆሎ ዱቄት አለበት። አልዘገየችም። በቆሎውን በውሃ በጥብጣ እንደአጃ አፈላችው። ከዚህ ቀድሞ በቆሎ ሲበላ እንጂ ሲጠጣ አይታ አታውቅም። እንባ እያነቃት ከታምሩ አፍ አደረሰች። የተራበው ልጅ የሰጠችውን አልገፋም። እናት መጠጣቱን ስታይ ‹‹እፎይ›› አለች። ዛሬም ድረስ እማይዋሽ እነዚያን ቀናት ስታስታውስ በዕንባ ትታጠባለች።

ዘመነ ኮረናን እማዋይሽ በእጅጉ የተፈተነችበት ነበር። ታምሩን አዝላ ለመዞር ፣በሥራ ላይ እንዳሻት ለመዋል የተደናቀፈችበት ክፉ ጊዜ። አንዳንዴ ሕይወት ግድ ሲላት ልጇ ላይ በር ዘግታበት ከቤት ትወጣለች። እንዲህ ማድረጓ ጊዜው ቢያስፈራት ችግሩ ቢፈትናት ነው። ከቀናት በአንዱ ግን ካልታሰበ አጋጣሚ ተገናኘች።

የዛን ዕለት ለቤቷ የጎደለውን ማገዶ ለማምጣት ርቃ መሄድ ነበረባት። ታምሩ ሁለተኛውን የጀርባ ቀዶ ህክምና አድርጎ ከቤት ተኝቷል። ቁስሉ በወጉ አልጠገገም። ዕንቅልፍ እንዳሸለበው ስታይ ከመንቃቱ በፊት ደርሳ ለመምጣት አሰበች። አልዘገየችም። እንደሁልጊዜው በሩን በላዩ ቆልፋ እየተጣደፈች ወጣች።

እናት ከሄደችበት ስትመለስ ያየችውን ማመን ተሳናት። የታምሩ ቁስል ባልተለመደ ሁኔታ ክፉኛ እየደማ ነው። ቀዶ ህክምናው ለዚህ እንደማያደርሰው ታውቃለች። እንደቀድሞው ስፌቱ አይታይም። በአንዴ ልብስና አካሉ በደም መነከሩ አልገባትም። እማዋይሽ ጉዳዩን ያወቀችው በቤቱ ወዲያ ወዲህ የሚሉ አይጦችን ስታይ ነበር። የታምሩን ቁስል እንዳይሆን ያደረጉት እነዚህ ፍጥረቶች ነበሩ።

ይህ የሆነው ታምሩ ለስምንት ወራት አንደበቱ ተይዞ በዝምታ ወስጥ በቆየበት አጋጣሚ ነበር ። እናት በወቅቱ የሆነውን ሳትናገር ለህክምና ብታደርሰውም። ይህ እውነት ግን ዛሬም ድረስ ዕንቅልፍ እየነሳ ያባንናታል።

እናትልጅ ዛሬ…

ዛሬም የእናት እማዋይሽ ጀርባ የአስራሶስት ዓመቱን ልጅ ለማዘል አልደከመም። አንዳንዴ በአቅም ጉልበት ማጣት ትፈተናለች። ታምሩ ነገ ዕድሜው ሲጨምር ችግሩ እንደሚከፋ አይጠፋትም። ከዚህ በላይ ግን መፍትሄ አላገኘችም። እንደምኞቷ ሆኖ ሞት እሱን ከፊት፣ እሷን ከኋላ አስከትሎ እስኪወስዳቸው ስለልጅ መኖር፣ የእናት መውደቅ መነሳት እንዲህ ሆኖ ይቀጥላል።

መልካምሥራ አፈወርቅ

አዲስ ዘመን ጥቅምት 23/2017 ዓ.ም

 

Recommended For You