በፅኑ ብርታት- ካንሰርን ድል መንሳት

ገና በልጅነታቸው እናታቸውን በሞት ያጡት ልጆች አስተዳደጋቸው ሀዘን የሞላው ነበር። ወጣቷ እናት እነሱን በወጉ ሳታሳድግ፣ ዓለም ሲሳያቸው ሳታይ ድንገቴው ሞት ነጥቋታል። ይህ እውነት ለትንንሾቹ ልጆች ከሰቀቀን በላይ ነው፡፡

ልጆቹ ዛሬም ሞቷን እያመኑት አይደለም። አሁንም የእናታቸውን ውሎ መግባት ይሻሉ። ራሳቸውን እየዳበሰች፣ ዓይናቸውን በስስት እያየች በፍቅር እንድትጠራቸው ይናፍቃሉ። ሁሌም የእናት ጠረኗ ውል ይላቸዋል። ድምጽዋ ይሰማቸዋል። በልጅነት እናትን በሞት ማጣት ልብ ይሰብራል። ሆድ ያስብሳል፣ ይህ ዕድሜ ያለ እናት ሕይወት የሚጎድልበት፣ ኑሮ በእጅጉ የሚከብድበት ነው፡፡

ሕይወት…

እናቷን በልጅነት ዕድሜዋ ያጣችው ሕይወት ከታላቅና ታናሽ እህት ወንድሞቿ ጋር ይህን የመከራን ግዜ ኖራዋለች። እናታቸው ከሞተች ወዲህ ሁሉም በፈተና መሀል ተመላልሰዋል። የዛኔ ሕይወት በልጅነት ዕድሜዋ ስለእናቷ ሞት ሲወራ ምክንያቱን ጭምር ስትሰማው አድጋለች። እናታቸው በካንሰር ታማና ተሰቃይታ ብታልፍም በወቅቱ ግን ሕክምና አልወሰደችም።

ሕይወት ይህን እውነት ካወቀች ወዲህ ‹‹ካንሰር›› ይሉትን ቃል ስትፈራው፣ ስትጠላው ኖራለች። ይህ ሕመም እናቷን ከእሷ ነጥሎ ወስዷል። እህት ወንድሞቿን አሳቆ፣ በናፍቆት፣ አራቁቷል። እሷ በእናትና ልጅ መሀል የሰላ መቀስ ስለሆነው ካንሰር ያላት ምስል በዓዕምሮዋ የገዘፈ ፣ በማንነቷ ጎልቶ የተጻፈ ታሪክ ነው፡፡

ከዓመታት በኋላ…

እነሆ! ልጅነት እንደ ጥላ፣ እንደጤዛ ሆኖ አለፈ። በእናት ፍቆትና ፍቅር ተቋጥሮ፣ በሀዘን ትካዜ ተላብሶ የኋሊት የቀረው ይህ ግዜ አይረሴ ትዝታዎችን አዝሏል። እነዚህ መልኮች የሕይወት በጎ፣ ክፉ ገጽታዎች ናቸው። በእሷ ልቦና ጠብቀው ታስረዋል። በዋዛ የማይረሱ፣ በቀላሉ የማይተዉ ሀቆችን ይዘዋል።

ሕይወት ዛሬ ትልቅ ሰው ሆናለች። ልጅነቷ ከእናቷ ማንነት ተዛምዶ ቢጻፍም የራሷን ኑሮ ልትመሰርት ግድ ሆኗል። ትዳር ይዛ ጎጆ ወጥታለች። የልጆች እናት ከሆነች ወዲህ ደግሞ ብዙ ታስባለች ። በእሷ ያጣችውን የእናት ፍቅር በእነሱ አሻግራ ስታየው ውስጧ ይረበሻል። ሁሌም ክፉ እንዳታይ፣ እንዳትሰማ፣ ትመኛለች። ልጆቿ ለእሷ የጎደለ ዓለሟን የሚሞሉ፣ ያለፈ ታሪኳን የሚያስረሱ ምክንያት ናቸው።

ዳባሾቹ ጣቶች…

አንድ ቀን ሕይወት ከቤቷ ልጇን ታቅፋ ተቀምጣለች። ከወለደች ጥቂት ወራት አልፈዋል። የስድስት ወር ዕድሜ ያላት ጨቅላ እንደልማዷ እጆቿን ከእናቷ ጡት ጣል አድርጋ እየጠባች ነው። ሕይወት በድንገት ከአንድ ጡቷ ላይ የተለየ ምልክት ያየች መሰላት። በጥርጣሬ እጇን ሰደድ አድርጋ ብይ መሳዩን ጠጣር በስሱ ዳበሰችው። ሁኔታውን አላመነችም። እንደደነገጠች፣ እንደፈራች ዳግም ጣቶቿን እየቀያየረች ዳሰሰች፣ ዳሰሰች…: ፡፡

አሁንም የጣጠረ፣ ከዚህ ቀድሞ አይታው፣ ነክታው የማይታወቅ ነገር በእጆቿ መሀል መኖሩን አረጋገጠች። ሕይወት በስሙ ስትፈራውና ስትሸሸው የነበረው አስደንጋጭ ስም በዓይምሮዋ ውል አለባት። ‹‹ካንሰር››። ታመው የማይድኑት ክፉ ደዌ፣ እናትን ከልጆች የሚለያይ፣ ሕይወትን በአጭሩ የሚያስቀር ነጣቂ ሌባ።

ሕይወት ምልክቱን በጣቶቿ ዳብሳ ካረጋገጠች በኋላ ወደ ምርመራ እስክትሄድ አልቆየችም። በጡቷ ላይ ያየችው ነገር ‹‹ካንሰር›› ለመሆኑ በፍጹም ልቧ አምና ተቀበለች። ያለአንዳች ጥርጣሬ ለውስጧ ሀቁን ያቀበለችው ወይዘሮ ለቀናት ስጋቷን ይዛ በዝምታ መቀመጥ ውሳኔዋ ሆነ።

እናት ይህን እውነት ካወቀች ወዲህ ፈጽሞ በባህርይዋ ለውጥ አልታየም። ችግሯ ጎልቶ እንዳይወጣ በእርምጃዋ ሁሉ መጠንቀቅ ያዘች። እንደቀድሞው ለልጇ በረከቷን አልነፈገቻትም። ባሻት ሰዓት ጡቷን አውጥታ ታጠባታለች። ስታለቅስ እንደ ብሶቷ አብራት አታለቅስም። ሀዘን፣ ጭንቀቷን በውስጧ አምቃ ትብሰለሰላለች፡፡

ሕይወት በዝምታ ውስጥ መጓዟን ቀጥላለች። ትንሽዋ ዕባጭ አሁንም ከቀኝ ጡቷ ላይ እንደተቀመጠች ነው። ብይ መሳይ፣ የማትለሰልስ፣ የማታሟልጭ ጠጣር። ሕጻንዋ በዕድሜ እያደገች ነው። በየጊዜው የእናቷን ጡት ማግኘት ትሻለች። እናት ጥርጣሬ ቢገባትም ለልጇ ጡት መስጠቷን አልተወችም፡፡

ልጇ አንድ ዓመት ሲሞላት የጡቷ ወተት ቀነሰ። ይህን ተከትሎ ምልክት የታየበት ጡት ልዩነቱ ይስተዋል ጀመር። በየቀኑ እድገቱ ለውጥ እያመጣ፣ መጠኑ እየጨመረ ሄደ። ይህኔ ሕይወት በእጅጉ ጨነቃት። አሁን እስከዛሬ ደብቃ የያዘችውን ሚስጥር ለአንድ ሰው መተንፈስ፣ .ማካፈል ይኖርባታል። ወይዘሮዋ ለቀናት ከራስዋ ጋር ስትወዛገብ ቆየች። ከቀናት በአንዱ ግን ባለቤቷን ፊት ለፊት አስቀምጣ የሆነውን ሁሉ አንድ በአንድ ነገረችው፡፡

ባለቤቷ የሕይወትን ቃል በጥሞና አደመጠ። ቢደነግጥም ቀጥሎ ያለው ውሳኔ ከራሷ እንዲመጣ ፈልጓል። ውሳኔው ፈጣንና አይቀሬ የሚባል ነው። ወደ ሕክምና ዘልቆ ተገቢውን ምርመራ ማካሄድ። ይህን ጉዳይ ሕይወትም ብትሆን አሳምራ ታውቀዋለች። ቃሉ ከባሏ አንደበት ከመውጣቱ በፊት ግን በተለየ ማስጠንቀቂያ አገደችው፡፡

ባል በግርምታ እያስተዋላት ለምንና እንዴት? ሲል ጠየቀ። የሚስቱ ምላሽ አጭርና ፈጣን ነበር። ‹‹እኔ በፍጹም ወደ ሀኪም ቤት መሄድ ‹‹አልፈልግም›› አለችው። ባል አሁንም ተጨማሪ ማብራሪያ ፈልጓል። ካልተመረመረች፣ ካልታከመች ዕጣ ፈንታዋ እያሳሰበው ነው። መልሶ ይህንኑ ስጋት በጥያቄ ደገመላት። ሕይወት ለምላሹ አልዘገየችም። ሆስፒታል ሄዳ፣ ከመመርመር፣ ይልቅ ለራሷ ብትጸልይና በሌሎችም ብታጸልይ እንደሚሻል አስረዳችው፡፡

ባለቤቷ ሀሳቧን አልተጋፋም። ሁሉም ውሳኔ ከራሷ እስኪመጣ መታገስ እንዳለበት ወሰነ። ቀናቶች እንደዋዛ አንድ ሁለት ብለው ቆጠሩ። ከወይዘሮዋ የመጣ አዲስ ውሳኔ የለም።

አጋጣሚው…

ከቀናት በአንዱ ወይዘሮዋ ከአንድ ሆስፒታል ተገኘች። በስፍራው የመሄዷ ምክንያት አልጋ ይዛ የተኛችን አንዲት ሴት ለመጠየቅ ነበር። እንደ ልምድና ወጉ ሕመምተኛዋን ጠጋ ብላ ስለጤናዋ አወጋቻት። በንግግራቸው መሀል ድንገት የሰማችው እውነት ግን ወደ ራሷ ሊመልሳት ግድ አለ። አጋጣሚ ሆኖ የሴትዬዋ ሕመም የጡት ካንሰር ነበር።

ሕይወት ይህን ካወቀች በኋላ ከራሷ ጋር አወጋች። እሷ ደብቃ የያዘችው ሚስጥር አንድ ቀን ለአደጋ እንደሚያጋልጣት አልጠፋትም። ያለፋታ ማሰብ መጨነቋ ቀጠለ። ያለፈችበት የልጅነት መንገድ፣ የእናቷ ሕመምና ስቃይ፣ የእሷ እጣፈንታና የቤተሰቦቿ ሁኔታ በዓይነ ሕሊናዋ ተመላለሰ። አሁን ውስጧ በእጅጉ እየሞገታት ነው።

ሕይወት በድንገት ዞር ስትል ከአንዲት ነርስ ጋር ዓይን ለዓይን ተጋጨች። ነርሷ በትምህርት ዓለም የምታውቃት አብሮ አደጓ ነች። አንዳች ነገር ውስጧን ሲቀለው ተሰማት። ከብይ መጠን አልፎ የዕንቁላል ያህል አድጎ የሚሰማት ዕብጠት ዛሬም ከእሷ ጋር ነው፡፡

ሁለቱ ሴቶች ሰላም ከተባባሉ በኋለ ሕይወት ለባልንጀራዋ ስጋቷን ገለጸችላት። በጡቷ ላይ ያለውን ምልክት አሳይታም የሆነውን ሁሉ ተናገረች። የጤና ባለሙያዋ ጉዳዩን እንደዋዛ አላየችውም። ስለመዘግየቷ፣ ስለዝምታዋ ወቅሳ በአስቸኳይ የጤና ምርመራ ማድረግ እንደሚኖርባት አሳሰበቻት፡፡

የነበረው – እንደነበረ …

ሕይወት ከባልንጀራዋ ከተለየች በኋላ ሁሉን ረስታ በቀድሞ መንገዷ ቀጠለች። ስለራሷ ማሰብ፣ ስለጤናዋ መጨነቅ ተወች። ለቀናት የነበረው እንደነበረው ሆኖ ቀጠለ። ከእሷና ከባለቤቷ በቀር ሚስጥሯን የሚያውቅ የለምና በነገሮች አልተጨነቀችም፡፡

ከቀናት በአንዱ ማለዳ የእጅ ስልኳ በድንገት አንቃጨለ። አንስታ አየችው። የምታውቀው ቁጥር አይደለም። ቢሆንም ጥሪውን አልገፋችም። ወደ ጆሮዋ አስጠግታ ‹‹ሀሎ›› ስትል ምላሽ ሰጠች። በቅርቡ ያገኘቻት ነርስ ጓደኛዋ ነበረች። የስልክ ቁጥሯን ከምታውቃቸው ሰዎች መውሰዷን ነገረቻት፡፡

ነርሷ ቀጭን ትዕዛዝ ስትሰጣት አልዘገየችም። በማግስቱ ጠዋት በአስቸኳይ ከሆስፒታሉ ተገኝታ ምርመራውን እንድታደርግ አሳሰበቻት። ሕይወት እንደቀድሞው ‹‹እምቢኝ›› ልትል አልደፈረችም። እንደምትመጣ ቃል ገብታ ስልኩን በስንብት ዘጋች። ሌቱ አልፎ ማለዳ ሆነ። ጨለማው መንጋቱ በወፎች ጫጫታ ተበሰረ።

ሕይወት ‹‹እንድትመጪ›› በተባለችበት ጠዋት ከሆስፒታሉ ስትደርስ በውጣ ውረድ አልተቸገረችም። ነርስ ባልንጀራዋ ሁሉን አመቻችታ ጠበቀቻት። ዕለቱን ተገቢውን የጤና ምርመራ በወጉ ወስዳ አጠናቀቀች። ሁሉን ስትጨርስ የውጤቱን መልስ ለመስማት ቀነ- ቀጠሮ ወስዳ ነበር፡፡

የምርመራው ውጤት…

እነሆ! የቁርጡ ቀን ደርሷል። አሁን ወይዘሮዋ ከሀኪሟ ፊት ቀርባለች። እሷ ሁሉን ለመቀበል ዝግጁ መሆኗን ለራሷ ስትነግረው ቆይታለች። በግል ሙከራዋ ባደረገችው ጥረት ደግሞ ሊሆን የሚችለውን ስትገምት ነበር። እንዲያም ሆኖ ትክክለኛውን ውጤት ከተገቢው አካል ማወቅና መስማት አለባት፡፡

ዕለቱን ከሀኪሞች አንደበት የተሰማው የምርመራ ውጤት እንደተገመተው ሆነ። ሕይወት አንድ ጡቷ በካንሰር ተጠቅቷል። ወይዘሮዋ ይህን ውጤት አስቀድማ የገመተችው ቢሆንም እውነቱን አምኖ ለመቀበል ተሳናት። ለመቆም መቀመጥ እስኪሳናት ተንገዳገደች። ይህ ግዜ ለሕይወት እጅግ ከባድና ፈታኝ ነበር።

ውሎ አድሮ ራሷን ለማረጋጋት ሞከረች። በቀላሉ አልሆነላትም። መለስ ብላ ወደልጅነቷ ተጓዘች። እናቷ የሞቱት በካንሰር ታመው ነበር። በወቅቱ ሕክምና ያለማድረቸውን ታውቃለች። እንዲህ ከሆነ በርካታ ዓመታት አልፈዋል። ሕይወት ለቤቱ የመጨረሻ ልጅ ነች። በቤተሰቡ ታሪክ የእናቷ ዕጣ ፈንታ የተደገመው ግን በእሷ ላይ ሆኗል።

የሶስት ልጆች እናት ለሆነችው ሕይወት ይህን እውነት እንደዋዛ አምኖ መቀበሉ ይከብዳል። የእሷ አስተዳደግ ነፍስ ባላወቁ ልጆቿ እንዲደገም አትሻም። ጠዋት ማታ በለቅሶ፣ በሀዘንና ትካዜ አንገቷን ደፋች። አሁን ከአንድ ውሳኔ የምትደርስበት ግዜ ነው። ስለራሷ ጤና፣ ስለ ልጆቿ መኖር ታስባለች። እንደትናንቱ በዕምቢታ፣ በዝምታ መቀጠል የለባትም፡፡

ሕይወት የሚሆነውን ሁሉ በይሁንታ ከወሰነች በኋላ ለሕክምናው ራሷን አዘጋጀች። ከሀኪሞቿ የምትባለውን ለመፈጸምም ፈቃደኛ ሆነች። በወቅቱ ጡቷ ላይ ያለው ዕባጭ በቀላሉ ወጥቶ ሕይወቷ እንደሚቀጥል ገምታ ነበር። ከዚህ በኋላ ቀኝ ጡቷ ሙሉ ለሙላ እንደሚነሳ ሲነገራት ግን ክፉኛ ደነገጠች፡፡

ጡት ማለት ለሴት ልጅ ልዪ መገለጫ ነው። ይህ ተፈጥሮ ከውበት በላይ ሆኖ ሕይወትን ይታደጋል፤ የውስጡ በረከት የእናት ልጅ ፍቅር ማሰሪያ ገመድ ነው። ሕይወት የምትሰማው ሁሉ ከአቅሟ በላይ ሆኗል። ቀጥሎ ያለውን ሀቅ አንድ በአንድ እስክታውቅ አትጠብቅም። ይህ ከመሆኑ በፊት በሩጫ ስፍራውን ለቃ ወጣች፡፡

በወቅቱ ሕይወት የተሰማትን ለማስታወስ ይከብዳታል። በአካል ትኑር፣ ትሙት፣ ትውደቅ፣ ትነሳ የምታውቀው አልነበረም። በአየር ላይ የተንሳፈፈች ያህል፣ እየታያት ነው። ማንም ደርሶ ቢያጽናናት፣ አይዞሽ ብሎ ቢያቅፋት የምታይ፣ የምትሰማ አይደለችም። ልጆቿን እያሰበች ነው። በእሷ ስር የምታስተዳድራቸው ቤተሰቦች ውል ይሏት ይዘዋል። ወይዘሮዋ ከዚህ በኋላ ቤቷ ባትገባ ማንንም ባታይ፣ ትወዳለች። እንደነገሩ ኑሮ የጀመረችው ሕይወት በብዙ ጉዳዮች ጎዶሎዋቿ በረከቱ። ቤቷ አስጠላት፣ ልጆቿን መንከበካብ፣ በወጉ ከሰው ማውጋት ተወች፡፡

የተስፋ ቃል…

የሕክምና ባለሙያዎች በየግዜው በአሳዛኝ አጋጣሚዎች ያልፋሉ። ታካሚዎቹ ሲድኑላቸው የሚረኩትን ያህል ጉዳታቸውም ይሰማቸዋል። የዛን ቀን የሕይወትን ምርመራ የያዘው ዶክተር የድንጋጤ ሩጫዋን ባየ ግዜ በዓይኑ ብቻ አልሸኛትም። እስከ መውጫው በር ከኋላዋ ተከትሏታል። እሷ ግን ወደቀደመው ውሳኔዋ ለመመለስ ፈጥና ነበር። ደጋግማ ‹‹አልታከምም ›› ስትል ቁርጡን ነግራዋለች።

በሌላ ቀን ይኸው ሀኪሟ በመኪና እያለፈ ሕይወትን ከመንገድ ላይ አያት። እንዳላየ ፊቱን ማዞር አልፈለገም። ስለእሷ ዕንቅልፍና ሰላም ካጣ ቆይቷል። ገና ሲያያት ከእሷ አንድ ቃል ጠብቋል። መኪናውን አቁሞ መታከም ያለመታከሟን ጠየቃት። መልሳ የፊቱን ሀሳቧን ደገመችለት። ‹‹አልታከምም፣ ፈጽሞም አልመጣም›› አለችው፡፡

አሁንም ጊዚያቶች እየነጎዱ ነው። ከምርመራዋ በኋላ ስምንት ወራትን የቆጠረችው ሕይወት አካል አይምሮዋ እየደከመ፣ ሁኔታዎች እየሰለቿት ነው። ከቀናት በአንዱ ግን ነባር ውሳኔዋ ሊሻር ቀኑ ደረሰ። እምቢታዋን ትታ ለሕክምናው እጅ ሰጠች። ሀኪሟ ፊት በቀረበች ግዜ የዓይኖቿ ዕንባ አልደረቁም፤ ያለማቋረጥ ታለቅስ፣ ታነባ ነበር፡፡

በየአፍታው በዕንባ የምትታጠበውን ወይዘሮ ያስተዋለው ሀኪም። በተስፋ የፈካ ገጽታውን ይዞ ወደእርሷ ቀረበ። በእግሮቿ ስር ተንበርክኮም ‹‹አይዞሽ እኔ በአግባቡ አክሜ አድንሻለሁ›› ሲል ቃል ገባላት። ሕይወት ከዚህ ቃል በኋላ አዝላው የቆየችው ከባድ ጭንቀት ከትከሻዋ ሲወድቅ ተሰማት። ውስጧ በተስፋ ረሰረሰ፣ የመዳን ህልሟ ዕውን ሆኖ ታያት፡፡

እንዳያልፉት የለም…

ቀጣዩ ሕክምና ከመካሄዱ በፊት የሚሆነው ሁሉ ተነገራት። ዳግመኛ ምርመራ ማካሄድ ግድ እንደሚል አወቀች። ሕይወት ጭንቀቷ አገረሸባት። ያሳለፈችው ስቃይ በፊቷ ተመላለሰ። ምርመራውን ብትጠላውም ከባዱን ችግር ልትጋፈጥ መሆኑን ስታውቅ ራሷን አበረታች። ግራ ቀኝ አይታ ወሰነች። ጥንካሬን ለብሳ፣ በጽኑ ልብ ቆመች። ካንሰርን በብርታት ታግላ ድል ልትነሳው ቆረጠች፡፡

አሁን ሕይወት እንደትናንቱ በብቸኝነት አትጓዝም። የገጠማትን ሁሉ ለወዳጅ ዘመድ፣ ለጓደኛ ጎረቤት ነግራለች። እንዲህ ማድረጓ ብዙዎች በገንዘብ እንዲያግዟት በሀሳብ እንዲያበረቷት ምክንያት ሆኗል። ሕይወት ኬሞ ቴራፒውን በጽናት ካጠናቀቀች በኋላ ተጨማሪ የምትወስደው ሕክምና ይቀጥላል። እሱን ስትጀምር ከበዳት፣ አልቻለችም። ውስጧ የተረታ ያህል ተንገዳገደ። ግን አልወደቀችም፡፡

ዛሬን …

አሁን ሕይወት በአዲስ ጎዳና እየተራመደች ነው። ትናንት ባለመመርመር ያባከነችው ግዜ አይረሴ ትምህርት ሆኖ በምሳሌነት ይታወሳል። እሷ ካንሰርን በጥንካሬ ታክማ ስትድን በበርካታ እሾኀማ መንገዶች ተመላልሳ ነው። ዛሬ ግን የዚህ መንገድ ሰበብ በርካታ ነፍሶችን አትርፏል። ትናንት የቆጠረቻቸው የማይነጉ ሌቶች፣ የማያልፉ የቀን ጨለማዎች ዛሬ ግራ ለገባቸው ሁሉ ብርሀን መፈንጠቅ ጀምረዋል።

እነሆ! ያጠናቀቅነው ወርሀ- ጥቅምት የጡት ካንሰር ወር ሆኖ ይከበራል። በዚህ ወቅት ሕይወትን የመሰሉ በጡት ካንሰር የተፈተኑ ብርቱዎች ጥንካሬያቸው ይመሰከራል። ለእነዚህ ጽኑ ሴቶች እያንዳንዷ ደቂቃ የተለየ ትርጉም አላት። ትናንትን እንደታሪክ፣ ዛሬን እንደ ዕድል፤ ነገን እንደ ተስፋ ይቆጥሩታል።

መልካምሥራ አፈወርቅ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ጥቅምት 30 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You