የትምህርት ጉዳይ ከአንድ ማኅበረሰብ አልፎ ለአገር ያለውን ጥቅም ማብራራት ለቀባሪው የማርዳት ያህል ነው። የትምህርት ጉዳይ በተለይም በዚህ ዘመን የእያንዳንዱን ቤት የሚያንኳኳ እንደመሆኑ ማንም በቀላሉ የሚመለከተው አይደለም። በዚህ ዘመን ተፈጥሮ ፊደል አለመቁጠር ወይም ከቶ አለመማር የሚቻል አይደለም። ከሌላው ዓለም ጋር እኩል መራመድ ቢከብድ እንኳን ሰፊ ልዩነት እንዳይኖርና የእውቀት ክፍተት እንዳይፈጠር ትውልድ የግድ መማር አለበት። ይህ ደግሞ ከግለሰብ ወይም ከማኅበረሰብ አልፎ በአገር ላይ ያለው ተፅዕኖ እንዲህ በቀላሉ የሚገለፅ እንዳልሆነ ለማንም የተደበቀ አይደለም።
ትምህርትን ለሁሉም የማዳረስ ጉዳይ በተለይም እንደ አዲስ አበባ ባሉ ትልልቅ የሀገራችን ከተሞች በመንግሥት ብቻ የሚሸፈን አለመሆኑ አያከራክርም። ስለዚህም በርካታ የግል ትምህርት ቤቶች ተፈጥረዋል። ቀላል የማይባል የማኅበረሰብ ክፍልም ባለው አቅም ላይ ተመሥርቶ ወዶም ይሁን ተገዶ ልጁን ወደ ግል ትምህርት ቤት ይልካል። የግል ትምህርት ቤቶች ሲነሱ ግን ሁሌም ከክፍያ ጋር በተያያዘ የሚማረረው የማኅበረሰብ ክፍል ጥቂት አይደለም። ባለፉት ጥቂት ዓመታት መንግሥት የግል ትምህርት ቤቶች ክፍያ እንዳይጨምሩ ያወጣውን መመሪያ ተከትሎ እፎይ ብሎ የነበረው ሕዝብ አሁን ወደ ምሬቱ ተመልሷል።
የዘንድሮው የትምህርት ዘመን ተገባዶ መጪውን የትምህርት ዘመን በመጠባበቅ ላይ በምንገኝበት በዚህ ወቅት ከሰሞኑ ከትምህርት ቤት ክፍያ ጭማሪ ጋር በተያያዘ አስደንጋጭ ነገር ያልሰማ የለም። በርካታ የግል ትምህርት ቤቶች ሰሞኑን በግላቸውም ከወላጅም ጋር ተሰብስበው ነበር። በዚህ ስብሰባም ላይ በመጪው የትምህርት ዘመን ክፍያ ላይ የሚደረገው ጭማሪ አስደንጋጭና ብዙዎችን ያሳሰበ ነው። ሁሉም የግል ትምህርት ቤቶች ማለት ይቻላል በመጪው የትምህርት ዘመን ቢያንስ መቶ በመቶ ጭማሪ ለማድረግ እንዳሰቡ ወይም እንደወሰኑ ተሰምቷል። ሁለት መቶ ፐርሰንት ለመጨመር የተዘጋጀም አለ። ይህን ለማድረግ የተዘጋጁትም ባለፉት ጥቂት ዓመታት ትምህርት ቤቶቹ ክፍያ ላይ ጭማሪ ባለማድረጋቸው በቀጣይ ከወላጅ ጋር ተወያይተው እስከ ሁለት መቶ ፐርሰንት እንዲጨምሩ መንግሥት ይሁንታ እንደሰጣቸው በማስረዳት ነው።
ካለው የኑሮ ውድነት አንፃር ትምህርት ቤቶች የክፍያ ጭማሪ አያድርጉ ማለት ይከብዳል:: ጥያቄው ክፍያ ላይ ጭማሪ ለማድረግ ትክክለኛው ጊዜ አሁን ነው የሚለው ነው:: በኑሮ ውድነት የተነሳ ያልጨመረ ሸቀጥ ያልጋሸበ የአገልግሎት ክፍያ የለም:: ይህም እንኳን ዝቅተኛ የኑሮ ሁኔታ ላይ የሚገኘውን ማኅበረሰብ መካከለኛ ገቢ አለው ተብሎ የሚታሰበውንም እጅ ከወርች አስሮት ይገኛል:: አስቡት በዚህ የኑሮ ውድነት የተማረረ ማህበረሰብ ላይ ሁለት መቶ ፐርሰንት የትምህርት ክፍያ ሲጨመርበት:: እሺ ትምህርት ቤቶች ክፍያ ላይ የግድ መጨመር ካለባቸውስ በዚህ መልኩ የተጋነነ ጭማሪ ማድረግ ተገቢ ነው?::
የትምህርት ቁሳቁሶች መወደድ ጭማሪ ለማድረግ አንድ ምክንያት ነው ብለን እናስብ፣ መምህራንም እዚህ ግባ በማይባል ደመወዝ የኑሮ ውድነቱ ሰለባ በመሆናቸው የደመወዝ ማሻሻያ እንዲደረግላቸው ጭማሪ ማድረጉ የግድ ነው ብለንም በቅንነት ካሰብን ጭማሪው ምክንያታዊ ሊሆን ይችላል:: ያም ሆኖ ቢያንስ ሃምሳ በመቶ ጭማሪ ማድረግ ሲቻል እስከ ሁለት መቶ በመቶ ጭማሪ ማድረግ ትምህርትን እንደ አንድ ማኅበራዊ ኃላፊነት ከመቁጠር ይልቅ ሸቀጥ ማድረግ ይሆናል::
ይህ አይነት የተጋነነ ጭማሪ የሚለውጠው ነገር አለመኖሩ ደግሞ ይበልጥ አሳሳቢ ነው:: ይህ በእጅጉ የጋሸበ ጭማሪ ዳፋው ወላጅን በማማረር ብቻ አይቆምም፣ ጭማሪው የሚደረግበት ወላጅ ምናልባትም ነጋዴ ሊሆን ይችላል:: የትምህርት ቤት ክፍያ ተጨምሮብኛል ብሎ እሱም በሚነግደው ሸቀጥ ወይም በሚሰጠው አገልግሎት ላይ ማካካሻ የመሰለውን ጭማሪ ያደርጋል:: ሌላውም በዚህ መንገድ ይቀጥላል:: በዚህም መምህራን ጭምር ተጎጂ እንጂ
ተጠቃሚ ሊሆኑ አይችሉም:: ትምህርትም ትምህርት ቤቶቹም የሚኖሩት መምህራን ሲኖሩ ነው:: መምህራን ከሌሉ ሁሉም የለም:: ይህ ደግሞ እንደ ሀገር ትልቅ አዙሪት ውስጥ የሚከተን አደጋ ሊሆን ይችላል:: አንዳንዶቹ ትምህርት ቤቶች እስከ ሁለት መቶ በመቶ ጭማሪ ለማድረግ ያሰቡት ወላጅን ትምህርት ቤቱን ወደ ኢንተርናሽናል ደረጃ ለማሳደግ በማሰብ መሆኑን ሊያሳምኑ ሲሞክሩ ከማየት በላይ የሚያበሳጭ ነገር የለም:: ይህ ‹‹ዓይንህን ጨፍን ላሞኝህ›› የሚሉት አይነት ነው:: እውነት ለመናገር እንዲያው አንድ ትምህርት ቤት ሲያስተምርበት ከኖረው ሥርዓት ወጥቶ ድንገት ብድግ ብሎ ዛሬ ኢንተርናሽናል ላደርገው ስለሆነ ሁለት እጥፍ ጭማሪ አደርጋለሁ ማለት ቀልድ ነው:: አቅሙ ያለው ወላጅ እሺ ይሁን ብሎ ቢቀበል እንኳን ነገ የትምህርት ቤቱ ስያሜ ላይ ኢንተርናሽናል የሚል ቅፅል ከመጨመር የዘለለ ነገር እንደማይኖር ሁሉም ልቦናው ያውቀዋል::
አንድ ግለሰብ በግሉም ይሁን ከሌሎች ጋር ተጣምሮ በአክሲዮን ትምህርት ቤት ሲከፍት መጀመሪያ ዓላማው ግልፅ መሆን አለበት:: እኛ ጋር ግን ትምህርት ቤቶችን በሚከፍቱ ሰዎች ግልፅ የሆነ የግንዛቤ ወይም የአመለካከት ችግር አለ:: ትምህርት ቤት ንግድ አይደለም፣ እንደ ሸቀጥም የሚታይበት ዓለም የለም:: ትልቅ ትርፍ ለማጋበስ ተብሎም አይከፈትም:: ከዚያ ይልቅ ማኅበራዊ ኃላፊነት መሆኑን ስንቶቹ የትምህርት ቤት ባለቤቶች ያውቁታል?:: አሁን የታሰበው የተጋነነ ጭማሪ መልሱን በግልፅ ይነግረናል:: ሕዝብ በከፍተኛ የኑሮ ውድነት ፍዳውን እያየ በሚገኝበት ወቅት እስከ ሁለት መቶ ፐርሰንት ለመጨመር ማሰብ ማኅበራዊ ኃላፊነትን ወደ ጎን ትቶ እንደ ስግብግብ ነጋዴ ትርፍ ማግበስበስ ካልሆነ በቀር ሌላ ምን ሊባል ይችላል?::
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 28/2015