ከሄደበት ሰመመን የፕሮፌሰር ሃሮልድ ሃሳብ መለሰውና መቆያ ይሆናቸው ዘንድ ለሃኖስ “ስትበሉ ችኮላ፣ ትምህርት ለመጨረስ ችኮላ፣ ሥራ ለመቀጠር ችኮላ፣ በእዚህ አንጻርማ ለመሞትም ትቸኩላላችሁ፤ ይለን ነበር” አላት ነብዩ ነገር የተሰነቀረበት ይመስል ጺሙን እየላገ።
“እኔና አንቺም ተቻኩለን ነው ለእዚህ የበቃነው ማለትህ ነው?” አለች እቅፏን አላልታ። “ከገጸ ባህሪያትህ ጋር እየተጫወትክ የኔን ዓለም አደበዘዝከው፤ ስታየኝ ደመ ቀዝቃዛ እመስልሃለሁ?” አለች አሁንም ጀርባውን ሰጥቷት ስላደረ ክፉኛ ተናዳ። “የሚሞት ልጅ ሳይሆን የማይሞት ሥራ ነው የምፈልገው አልኩሽ” አለ ቆጣ ብሎ እየመለሰላት። “እኔ ታዲያ የቡና ሙቀጫ ነኝ ባሻህ ሰአት አንስተህ የምትጥለኝ?” አለች አንድ ጊዜ አበቅ የለሽ ጎንደር ሲዝናኑ
“የቡና ሙቀጫ ማንም ለሚዋሰው፣
እኔ ላንቺ ብዬ አልጣላም ከሰው።”
ሲል ላዝማሪ ያቀበለውን ግጥም አስታውሳ። “አንተ አልክ አለ ክርስቶስ” አለ ቀጭን ሳቅ አስከትሎ የኬን ፎሌትን “ፍሊክስን (እንስቷ ሰላይ)” መጽሐፍ እየገለጠ።
ነብዩ የሃኖስን ንግግሮች ባላመጠ ቁጥር ከበዓሉ ግርማ ሥራዎች ውስጥ የካድማስ ባሻገርን ምዕራፎች በምናቡ እያሰሰ ከአበራ ወርቁና ሃይለማርያም ካሳ ወግ ሃሳብ ይዘግናል። በፋሲካው ዋዜማና በተሻረችው ቅዳሜ ሁለቱ ጓደኛሞች እየሱስ ከመነሳቱ በፊት ትንሳኤውን እየጠጡ ሊቀበሉት ገነት ሆቴል ሲገቡ ይነበባል። ያጋጩት ጽዋም አስተጋብቶ በነብዩ የልቦና መስኮት በኩል ብቅ አለ።
“ግለኝነት ያጠላበት ማህበራዊ መስተጋብራችን፣ እኔነት የሸረሸረው እኛነታችን፣ የሀገር ፍቅራችን፣ የንባብ ባህላችን ትንሳኤ ያስፈልገዋል፤ እኔና ሃኖስሥ? “ በማለት ራሱን ሲጠይቅ የሃሳብ መዘውሩ ላንባ እንደጨረሰ ወፍጮ ቀጥ አለበትና “ቆይ እኔ የምልሽ” አለ መጽሐፉን ጥሎ ክንዷን ያዘና ከጉያው እየሸጎጣት።
ሃኖስ ይህን አጠራሩንና አስተቃቀፉን ምን ሲሻ እንደሆነ በውል ታውቀዋለች። ገና በትውውቃቸው ማለዳ “ይሄን ሁሉ ውበት ለብቻሽ መጠቅለሉ ግፍ አይሆንብሽም? ለነገሩ ባልሽ ስለምሆን ከቅናት ቅንነት አተርፋለሁ ብዬ አምናለሁ” ሲል ነበር የነቆራት። ነብዩ “ነጭናጫ ሚስት ለትዳር ባትሆንህም ፈላስፋ ታደርግሃለች” የሚለውን የሶቅራጠስን ሃሳብ ይስማማበታልና ነው።
“እሺ አንተ የምትለኝ” አለች ጆሮዋን እየሰጠችው። “ታውቂያለሽ አይደል? ያንቺ ፍቅርና የጅብ ቅንድብ እንቅልፍ እንደሚነሳ?” በማለት ኩርፊያዋን አለዝቦ ለፍቅር አምላክ መባ እንዲያቀርቡ መላ ማበጀቱ ነበር፤ ዳሩ ምን ይሆናል! “የሰው ጅብ ነሽ እያልከኝ ነው?” ስትል ነገሩን ገልብጣ በመረዳት አንባረቀችበትና ወደለየለት ጸብ መራችው እንጂ።
ነብዩ “እንዴት ያለችው ነገር ፈታይ ናት እባካችሁ?” አለ በሽፋኑ ደልሎት ይዘቱ ከንቱ እንደሆነበት መጽሐፍ ግምቱን እየኮነነ። አንድ ጊዜ ገና ያፍላ ፍቅር ላይ እንዳሉ “የኔ ውድ ዛሬ አምሮብሻል” ሲላት “ከዚህ በፊት አስጠላ ነበር?” ትልና ለንቦጯን ትጥላለች። እንዲሁ ሌላ ቀን ሲገናኙ “የኔ ውድ ዛሬ ጸዳ ብለሻል” ሲላት “ከዚህ በፊት እቆሽሽ ነበር?” ስትል ልማደኛ ነገር ፈታይነቷን ታሾረዋለች። “ደራሲና እግዜር የማይችሉት ምን ነገር አለ? የገጸባህሪያቱ ሃዘንና ንጭንጭ፣ ክፋትና ተንኮል፤ እግዚኦ ትግስታቸው! ነቀፌታን ከከበሬታ፣ ሙገሳን ከወቀሳ እንዳመጣጡ ሁሉንም በሚዛን የሚዳኙ የተፈጥሮ የወገብ ልክ ናቸው” አለ ነብዩ የሃኖስ መልክ ብቻ መሆን እጅጉን አሳስቦት።
ትዝ ይለዋል በመጀመሪያ እለት ግንኙነታቸው የባጥ የቆጡን እየለፈለፈ ከአንድ ሬስቶራንት ይዟት ገባና ያዘዙት እስኪመጣ ድረስ አብዝቶ የሚወደውን “ኦሮማይ” መጽሃፍ ሊጋብዛት ፈልጎ “ኦሮማይን ታውቂዋለሽ?” በማለት ጠየቃት። “የጾም ነው የፍስክ?” ያለችው እድሜ ልኩን ሲያስቀው ይኖራል። በውብ ቃላት ከሽኖ ፍሬ ሃሳቡ ሲጨመቅ ረብ የለሽ ድርሰት የሚያግተለትል ጸሃፊ ነኝ ባይ አንጀቱን ያደብነዋል፤ ሃኖስም የጽሁፍ ዶፍ የገበያ ጎርፍ እንዳመጣው ግልብ ደራሲ ሆነችበትና ዘናጭ ራቁትነቷን ለመሸፈን ሽቶ የጥበብ ልብስ አሰፍቶላት ነበር ልቦናዋን ነፈገችው እንጂ።
ጸባቸውም ይህ ነው። “ከግሃዱ ዓለም ተነጥለህ፣ በምናብ ሴቶች ተቃኝተህና የሙታንን መንፈስ ወርሰህ የኔ ስሜት ግድ የማይሰጥህ በድን ነህ” አለች ሃኖስ ከሻሽ የተረፈ ጸጉሯን ሰብስባ የተገላለጠውን አልጋ የባሰ እየመነቃቀረች። ነብዩ ከዋክብትና ጨረቃ ያንገት ድሪ፣ የእጅ አንባር፣ የጣት ፈርጥና የግር አልቦ ሆነው ያቆነጇትን ተፈጥሮ ባረፉበት ሆቴል መስኮት አሻግሮ እየተመለከተ አድናቆቱንም ተማጽኖውንም ከልቡ ጽላት እንዲህ ሲል ከተበ፤ “ከራሴ ተጣልቼ፣ ከጥበብ ተጋብቼ፣ አለሁልሽ ተፈጥሮ የምወድሽ።”
አይኑ ስር የሚገማሸረው የጣና ሞገድ ረግቦ እንቅልፍ ሲያሸልብ የሆዳቸውን ጥያቄ ለመመለስ የሦስት ዓመት ህጻን ቢንጠራራ የማይደርሰው ሚኒ ስከርት የለበሱ የመንፈስ ድሆች የዘነጡ ራቁቶች እይታው ውስጥ ገቡና “ባእሉ ግርማን፣ አያ ሙሌን፣ ጋሼ ስብሃትን ያፈራህ ማህጸን እባክህ ተፋረደን?” አለ አይኖቹን በእጆቹ ከልሎ። ቀጠለና “በተፈጥሮ ውስጥ እልፍ መጽሃፍት ቢኖሩም መጽሐፍት የሚጻፉት መጽሐፍ እንድንሆን እንጂ አንብበናቸው እንድንቀር ብቻ አይደለም። የእውቀት መንገድ ልብ ስለሆነ ቀዳሚ አንባቢያችን ከልብ ይጀምራል፤ ልባችንን ማንበብ ያልቻልን እንደሆነ ወደተፈጥሮ እንዝለቅ፤ እሱም ባይቻለን በመገለጥ የሚታደለንን ንባብ ልብ እንበል፤ መገለጡም ባይገለጥልን የመጨረሻው መዳረሻችን መፍሰሻ ቦያችን ልብንም ተፈጥሮንም ዘንቀን የምናነብበት አድማሳችን መጽሐፍ ነውና እናንብብ” አለ የሚሰማው ያለ ይመስል ጮክ ብሎ እየተናገረ።
ሃኖስ ከኋላው መጥታ ጀርባውን የሾሉ ጡቶቿ ሲወጉት በትክሻው አልፈው አንገቱ ላይ የተጠመጠሙትን እጆቿን ሳመና መስኮቱን ሳይዘጋ መጋረጃውንም ሳይመልስ ወደአልጋው በቀስታ አዘገመ፤ ሃኖስ ግን ርምጃው በርክቶ መኝታው ራቃትና በልጅነቷ የሰማችው ስላቅ የበዛበት ግጥም ታወሳት።
“በነጠላ ጫማ ባንቺ አረማመድ፣
እንዲህ ቅርብ ነው ወይ የማርቆስ መንገድ።”
ሀብታሙ ባንታየሁ
አዲስ ዘመን ዓርብ ሚያዝያ 17 ቀን 2017 ዓ.ም