ልዩነታችን ለምን ሰፋ?

ልዩነት ተፈጥሯዊ ነው። ሁሉም ሰው አንድ አይነት ምንነትና ማንነት እንዲኖረው አይጠበቅም። እንዲያውም በሠለጠነው ዓለም ትልቁ የልዕልና መገለጫ ልዩነትን ማክበር ነው። የሠለጠኑ ናቸው በሚባሉት የምዕራባውያን ሀገራት አንዱ መገለጫ የግለሰቦች ልዩነት መከበር ነው። አንድ ሰው ፍላጎቱ ያዘዘውን ነገር ሲያደርግ ማንም ከምንም አይቆጥረውም ማለት ነው። ይህ የሰዎችን መብት ማክበር የሰው ልጅ የልዕልና መገለጫ ነው።

የእኛ የኢትዮጵያውያን ልዩነት ግን አደገኛ ልዩነት እየሆነ ነው። የልዕልና ልዩነት ሳይሆን የጥላቻ ልዩነት፣ የመሠልጠን ልዩነት ሳይሆን የኋላቀርነት ልዩነት፣ የደግነት ልዩነት ሳይሆን የክፋት ልዩነት… እየሆነ ነው። ልዩነት ውበት የሚሆነው የሌላውን ልዩነት (መብት ማክበር ሲኖረው ነው። እነዚህ አደገኛ ልዩነቶች በተለይም የተማረ ነው በሚባለው የህብረተሰብ ክፍል ውስጥ በስፋት እየተንፀባረቁ ነው፡፡

ለምሳሌ፤ የዲጂታል ቴክኖሎጂ አማራጮችን የሚጠቀመው የተማረ የሚባለው ክፍል ነው። ዲጂታል ሚዲያዎች የግለሰብ ነፃነት የሚንጸባረቅባቸው ናቸው። አንድ ሰው በውስጡ የሚሰማውን ነገር ያለምንም ገደብ የሚናገርበት ነው። ስለዚህ የእነዚያ ሰዎች የውስጥ እምነት ያ የሚያንፀባርቁት ነገር ነው ማለት ነው። በሌላ ቦታ (በዋናዎቹ ሚዲያዎች፣ በስብሰባ፣ በመድረኮች…) እንደዚያ ማለት ስለማይችሉ እንጂ የልባቸው እምነት ያ ነው ማለት ነው። ልዩነት በጣም ሲሰፋ ይከራል፣ ሲከር ደግሞ ይበጠሳል ማለት ነው፡፡

ብዙ ጊዜ ልብ ብላችሁ ከሆነ ሁለት የኢትዮጵያ መሪዎችን ፎቶ ይደረግና ‹‹ማን ይሻላል?›› የሚል ጥያቄ ይጠየቃል። ነገርየው ለቀልድና ጨዋታ ተብሎ የሚደረግ ተራ እና ቀላል ጥያቄ ቢሆንም ግብረ መልሶች ግን የተማረ የሚባለውን ክፍል አስተሳሰብ ያንፀባርቃሉ። ይህን ለማስተዋል የግድ በሆነ ፋውንዴሽን ወይም በዓለም አቀፍ ተቋም የሚሠራ ጥናት መጠበቅ አያስፈልግም። ብዙዎች የውስጥ አስተሳሰባቸው በእነዚህ ቀላል ነገሮች ውስጥ ይንፀባረቃል።

መለስ ዜናዊን የሚያደንቅ ሰው ዐቢይን (ዶ/ር) ‹‹እንዴት ከዚህ ሰይጣን ጋር ታነፃፅራለህ?›› ይላል። ዐቢይን (ዶ/ር) የሚያደንቅ ደግሞ መለስ ዜናዊን ‹‹እንዴት ከዚህ ሰይጣን ጋር ታነፃፅራለህ?›› ይላል። ከሳይንስም ከሃይማኖትም፣ ከሞራልም የተጣላ የጥላቻ ሃሳብ ነው። እንዲህ አይነት ሰው የአቶ መለስ ዜናዊን ብቃት ወይም ድክመት ከ ዐቢይ (ዶ/ር) ብቃት ወይም ድክመት ጋር ማነፃፀር ስለማይችል ያለው አማራጭ ከሳይንስም ከሃይማኖትም የተጣላ የጥላቻ ስድብ መሳደብ ብቻ ነው።

ሃጫሉ እና ቴዲ አፍሮን በሙዚቃ ሥራዎቻቸው እያነፃፀረ የሃጫሉ ዜማው እንዲህ ነው፣ ግጥሙ እንዲህ ነው፤ የቴዲ አፍሮ ዜማው እንዲህ ነው፣ ግጥሙ እንዲህ ነው… ቅንብሩ ምናምን እያለ ማወዳደር አይችልም። የሚችለው የአንደኛው አድናቂ የዚያኛውን አድናቂዎች መሳደብ ነው። እሱ የሚያደንቀውን ቅዱስ ያኛውን ሰይጣን ማድረግ ነው። ታዲያ ይህ ልዩነት ‹‹ውበት›› የሚባል ነው?

ይህ የትንንሽ ነገሮች የሰፋ ልዩነት ወደ ፖለቲካውም አደገ። በፖለቲከኞች መካከል ያለው ልዩነት የሰማይና ምድር ያህል የተራራቀ ነው። ለምሳሌ፤ በትጥቅም ሆነ በሰላማዊ መንገድ መንግሥትን የሚታገሉ ኃይሎች አሉ። የሚገርመው ግን ከመንግሥት ጋር ካላቸው ልዩነት ይልቅ እርስ በእርሳቸው ያላቸው ልዩነት ይበልጣል። አንደኛው ታጋይ ኃይል ቢያሸንፍ ታግሎ ከጣለው መንግሥት የከፋ ተቃዋሚና ታጋይ ያጋጥመዋል። አንዱ ተቃዋሚ ከሌላኛው ተቃዋሚ ጋር ወደ ጦርነት የሚወስድ ልዩነት ያላቸው ናቸው። ይህ ሁሉ ለምን ሆነ ከተባለ፤ እጅግ ኋላቀር የሆነ አመለካከት ስላለን ነው።

በሀገራችን እንደ ዕውቀት የሚታየው የግሪክ ፈላስፎችን ጥቅስ መደርደር፣ እና የተሸመደደ ‹‹ቲዎሪ›› ማነብነብ ነው። ወደ ሥልጣኔ የሚወስደው ግን ቅንነትና የሞራል ልዕልና ነው። አለበለዚያ የዲግሪ መአት መደርደር፣ ከኢንተርኔት የተገለበጡ ጥናቶችን እያሳተሙ መደርደሪያ ማሞቅ ምሁር አያሰኝም።

አንዳንድ ጊዜ የሞራል ልዕልናን ልብ ብላችሁ ታውቃላችሁ? የተማረ ከሚባለው ይልቅ ፊደል ያልቆጠረው የህብረተሰብ ክፍል የተሻለ የሞራል ከፍታ አለው። ለሠለጠነው ዓለም ሥነ ልቦና የሚቀርበው በኢትዮጵያ የተማረ ከሚባለው ይልቅ ምንም ያልተማረው ገበሬ ነው። ለእንስሳት ሕይወት ይቆረቆራል። የቤት እንስሳት ሲታመም ውስጡ ይረበሻል፣ የቤት እንስሳት ሲሞት ያለቅሳል። ይህን የሞራል ልዕልና የምንሰማው የሠለጠኑ ናቸው በሚባሉት ሀገራት ነው። የሰውን መብት አልፈው የእንስሳት መብት ተሟጋች አላቸው። ሕይወትን ማጥፋት ነውር ነገር ነው።

ኢትዮጵያ ውስጥ ግን የተማረ የሚባለው የህብረተሰብ ክፍል ‹‹በለው! ግደለው!›› ሲል ትንሽ አይሰቀጥጠውም። ‹‹የእነ እገሌን ዘር ማጥፋት ነው!›› እያለ የሚናገረው የተማረ የሚባለው ነው። በዚህ ልክ ልዩነታችን ለምን ሰፋ?

የሚገርመው እኮ ደግሞ የሠለጠኑ ናቸው ከሚባሉት ሀገራት በላይ ሠብዓዊነት ያለውም ኢትዮጵያ ውስጥ ነው። ለሞተ አስከሬን ክብር የሚሰጥበት፣ ‹‹ውሃ አይነፈግም›› የሚባልበት፣ ‹‹ቤት ለእንግዳ ነው›› የሚባልበት ባህልና ወግ ያለው ኢትዮጵያ ውስጥ ሳይሆን አይቀርም። በአውሮፕላን አደጋ ወይም በመኪና አደጋ ሕይወታቸው ያለፈ ምንም ለማያውቋቸው ሰዎች ደረታቸውን እየደቁ የሚያለቅሱ እናቶች ያሉት ምናልባትም ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ ሳይሆን አይቀርም። ሶሪያ ውስጥ ለደረሰ ዘግናኝ ጥቃት ‹‹አታሳዩኝ›› እያሉ ፊታቸውን የሚያዞሩት፣ አይናቸውን የሚጨፍኑት ‹‹እርም›› የሚባል የሞራል ልማድ ስላለ ነው። የጋራ የሆነ የሰው ልጅነት ስላለ ነው። ምንም ሰው የሌለበት አንድ ሕንጻ ቢደረመስ ምናልባትም ሳቅ ነው የሚሳቀው። ምክንያቱም ሰው አይደለም። ችግሩ ግን ለማያውቁት ሰው በሰውነት ብቻ የሚያለቅሱ እንዳሉ ሁሉ በሰው ሞት የሚስቁና የሚደሰቱም አሉን። ለምን ይሆን ልዩነታችን እንዲህ የሰፋው?

በየትኛውም የሠለጠነ ዓለም ቢሆን በሰዎች መካከል ልዩነት አለ። ልዩነቱ ግን የኢትዮጵያን ያህል የተራራቀ ነው ማለት አያስደፍርም። ልዩነታቸው ግለሰባዊ መብትና ነፃነት ላይ፣ ግለሰባዊ ፍላጎት ላይ እንጂ ሰዋዊ ሞራል ላይ አይደለም። በአንድ ዘፋኝና በሌላ ዘፋኝ መካከል ያለው ልዩነት ሙያዊ ልዩነት እንጂ የሰይጣንና የቅዱስነት ልዩነት አይኖራቸውም። የግል ፍላጎታቸው የፈቀደውን ነገር ያደርጋሉ እንጂ ሌሎች ላይ ጉዳት የሚያደርስን ነገር እንደ መብት ሊያዩ አይችሉም። ልዩነታቸው የማስተካከል እንጂ ቀዶ የመጣል ወይም ጫፉ አይነካም የሚል አይደለም። ራሳችንን የሠለጠኑ ናቸው ከሚባሉት ሀገራት አንፃር እንየው ከተባለ በጣም የሰፋ ነው።

ልድገመውና፤ ልዩነት አይኑር አላልኩም። ልዩነት ተፈጥሯዊ ነው። ልዩነት ሲባል የግድ ከባህል፣ ቋንቋና ማንነት ጋር ያለውን ማለት አይደለም። ሞራል ባለው እና ሞራለ ቢስ በሆነው መካከል ያለውን ልዩነት ማለቴ ነው። ነውር በሚያውቅና ሀፍረተ ቢስ በሆነው መካከል ያለው ልዩነት ማለቴ ነው። አዛኝ እና ጨካኝ በሆነው መካከል ያለው ልዩነት ማለቴ ነው። በአጠቃላይ ሞራል ባለውና በሌለው መካከል ያለው ልዩነት ለምን ሰፋ?

ዋለልኝ አየለ

አዲስ ዘመን ረቡዕ ግንቦት 6 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You