የመብት አብዮት

ነገርየው ሲጀምር ዓለም አቀፍ ፖለቲካዊ መልክ የነበረው ነው። ምንም እንኳን የተጀመረው በአሜሪካና አውሮፓ ሀገራት እንደነበር ቢነገርም እየቆየ ሲሄድ ግን የሶሻሊስት አገራት ንቅናቄ መስሏል። በእርግጥ ነገሩን ያጧጧፉትም የሶሻሊስት ሀገራት ናቸው። ብዙ ዝርዝር ምክንያቶች ያሉት ቢሆንም በጥቅሉ ሲታይ ግን፤ የፊውዳል ሥርዓት የድሃ ጉልበት ይበዘብዛል የሚል ነው። በሀገራችን ዓውድ ስናየው፤ የባላባት ሥርዓት ጭሰኛውን ‹‹እርቦ›› እና ‹‹ሲሶ›› እያሳረሰ ይበዘብዝ ነበር፤ ሰራተኛው የልፋቱን ያህል አያገኝም እንደማለት ነው። ለእዚህም ነው የተማሪዎች ንቅናቄ አስጀማሪዎች የ60ዎቹ አብዮተኞች ‹‹መሬት ለአራሹ›› የሚል መፈክር ማንሳታቸው። የላብ አደሮች ቀንም መከበር የጀመረው ንጉሣዊ ሥርዓቱን ባስወገደው የደርግ መንግሥት ነው።

በዓለም አቀፍ ደረጃ ሲታይ ግን የረጅም ጊዜ ታሪክ ያለው ነው። በአውሮፓ የኢንዱስትሪ መስፋፋትን ተከትሎ የተከሰተ ነው። ይህ ቀን በአሜሪካ ‹‹የሠራተኛ ቀን (Labor day) በሚል ሲከበር በዓለም አቀፍ ደረጃ ደግሞ ‹‹ሜይ ዴይ (May day›› በሚል ይታወቃል። ይህም በአውሮፓውያኑ የዘመን ቀመር ግንቦት 1 መሆኑ ነው። በተለያዩ ፋብሪካዎችና ኢንዱስትሪዎች ውስጥ ያሉ ሠራተኞች መብታቸውን ለማስከበር ያስጀመሩት ንቅናቄ ነው። በመላው አሜሪካም በመስከረም ወር ይከበራል። እነሆ በኢትዮጵያ ደግሞ በደርግ ዘመነ መንግሥት በደማቁ፣ ከዚያ ወዲህ ደግሞ ቀዝቀዝ ባለ ሁኔታም ቢሆን ይታሰባል። ሙሉ ታሪኩን ለታሪክ ዓምዳችን እንተወውና ለመሆኑ በሀገራችን የሠራተኛ መብት ምን ይመስላል? የሚለውን እንታዘብ።

ምንም እንኳን የላብ አደሮች ቀን መከበር ያመጣው ነው ለማለት ባያስደፍርም አሁን ባለው ሁኔታ በኢትዮጵያ ውስጥ የሠራተኛ መብት አይከበርም ለማለት አያስችልም። ችግሩ ግን በመንግሥት ተቋም ውስጥ ያለው እና በግል የንግድ ቤቶች ውስጥ ያለው ሁኔታ እጅግ የተራራቀ መሆኑ ነው። በመንግሥት ተቋም ውስጥ ሠራተኛው በሕዝብ በጀት ሲቀልድ፣ በግል የንግድ ተቋማት ውስጥ ደግሞ ባለሀብቶች በድሃ ጉልበት ይጫወታሉ። በተለይ እንደ አነስተኛ ሆቴሎችና ሬስቶራንቶች፣ መጠጥ ቤቶችና ሌሎች ንግድ ቤቶች ሠራተኞቻቸውን እንዴት እንደሚያደናብሩ በቀላሉ ማንም ሰው የሚታዘበው ነው።

መጀመሪያ በመንግሥት ተቋማት በኩል ያለውን እንመልከት። የተደራጀ የአሰራር ህግና ደንብ አለው። ተቋማቱ የየራሳቸው የሠራተኛ ህግና ደንብ አላቸው። ለሁሉም ሠራተኛ የወጣውን የአሠሪና ሠራተኛ አዋጅም ያከብራሉ። በጣም አልፎ አልፎ ህግና ደንቡን የተላለፈ የመንግሥት ተቋም ካለ መክሰስ ይቻላል፤ ከክሱ በላይ የመንግሥት ተቋም ሆኖ ህግና ደንብን አለማክበሩ ስለሚያስወቅሰው አስቀድሞ ለስሙ ሲል ይጠነቀቃል። በዋናነት ግን የሠራተኛው መብት በህግና ደንቡ መሰረት ይከበርለታል። ለምሳሌ፤ አንዲት ሴት ስትወልድ የሚሰጣት የወሊድ ፈቃድ በመንግሥት ተቋም ውስጥ እና በግል የንግድ ድርጅት ውስጥ እኩል አይደለም። ይህ መንግሥት ካለበት ሀገራዊ ኃላፊነት አንፃር የሚገርምም ሆነ የሚደነቅ ሊሆን አይገባም፡፡

በመንግሥት ተቋም ውስጥ ያለው ልክ ያልሆነ ነገር ግን የሠራተኛ አያያዝ ዝርክርክነት ነው። መብትን ማክበር እንዳለ ሆኖ፤ የመንግሥትና ሕዝብ ጊዜና ንብረት የሚባክንበት ዝርክርክ አሰራር ግን መብት ማስበር ሳይሆን ብዝበዛ ነው ሊባል የሚገባው! ለምሳሌ፤ የንብረት አያያዝ ላይ አደገኛ ችግር አለ። የመንግሥት ንብረት ሲባል የሆነ የባዕድ ንብረት አይነት ተደርጎ ነው የሚታየው። ይህ የሰራተኛውም የአስተዳዳሪዎችም ችግር ነው። በእንዲህ አይነት አሰራር የሰዎች የዓመት እረፍትና የወሊድ ፈቃድ ቢከበርም በሕዝብ በጀት የሚገዛ ዕቃ ግን ይባክናል። በሕዝብ በጀት የሚሰራ የመገልገያ ቦታ (ለምሳሌ መጸዳጃ) በግዴለሽነት ስለሚያዝ በተደጋጋሚ ይበላሻል፣ በተደጋጋሚ ይጠገናል፡፡

በእዚህ ሁሉ ውስጥ ለዚያውም የሚዘረፈውን ገንዘብ (ሙስና) ሳንቆጥር ነው። ከህግና ደንብ አሰራር ውጭ የሆኑ ወጪዎች ይደረጋሉ። የሚባለው ወቀሳ በየመድረኮች የምንሰማው ነው። ለንብረት መግዣ ወጪ የተደረገ ገንዘብ ተገቢውን ጥራት ያለው ዕቃ ሳይገዛ ገንዘቡን በመቀሸብ (መቀነስ) ለግል ጥቅም ማዋል እና በቀላሉ የሚበላሽ ዕቃ መግዛት በተደጋጋሚ የሚሰማ ወቀሳ ነው። በዚህ ሁኔታ የዘራፊው ሰራተኛ መብት ሲከበር የሕዝብ መብት ግን ተጣሰ ማለት ነው። ዘራፊው ይህን ስለዘረፍኩ ብሎ ተጨማሪ ሰዓት አይሰራም።

ሌላው በመንግሥት ተቋም ውስጥ ያለው ትልቁ አገራዊ ክስረት ‹‹የኔ›› ብሎ የመሥራት ሞራል የሌለ መሆኑ ነው። በሠለጠኑት አገራት የመንግሥት ሠራተኛ በአገሪቱ ትልቁ የኃላፊነት ስሜት የሚሰማው እና ለሥልጣኔ አርዓያ የሆነ ነው። በአገራችን ዓውድ ካየነው ግን የመንግሥት ተቋም ውስጥ መቀጠር ‹‹የአርባ ቀን ዕድሌ›› የሚባልባት እየሆነ ነው። እንደ አገራዊ አገልጋይነት አይታይም። በኃላፊነት ላይ ያሉትም በግል ጥቅም የሚታሙ ናቸው። መብቱን ብቻ ሲያሳድድ ግዴታዎቹን ግን አይወጣም። ለመብቱ የሚታገለውን ያህል ግዴታዎቹን ሲጥስ ግን ልብ አይለውም። ስለዚህ መብትም ይከበር፣ ግዴታም ይከበር።

የሠራተኛ መብት በከፍተና ሁኔታ የሚጣሰው እና ኢ-ሰብዓዊ የሆነ ድርጊት የሚፈጸመው በግል ንግድ ቤቶች ነው። የግል ንግድ ቤት ባለቤቶች ‹‹በገዛ ንብረቴ!›› የሚሉት የስግብግብነት ሞራለ ቢስ ባህሪ አላቸው። በጣም ሲከፋ አሰርተው ገንዘብ የሚከለክሉ ሁሉ አሉ። የእሱ ንብረት መግዣ አንድ ሳንቲም እንዳይጎድል ወር ሙሉ ሲለፋ የነበረ ሠራተኛ የዕለት ጉርሱን የሚያጋኝበትን ገንዘብ እንዳያገኝ ይራዘምበታል፤ ሲከፋ ደግሞ ጭራሹንም ይከለከላል። የሁለትና ሦስት ወር አዘግይቶ መክፈል በተደጋጋሚ ከብዙ ሠራተኞች የምንሰማው ቅሬታ ነው። ባለሀብቱ ለተሻለ ትርፍ የዕቃ መግዣ ካጠረው የዕለት ጉርስ የሌላቸው ሠራተኞች እርሱ ‹‹አሁን ተርፎኛል›› እስከሚል ድረስ መጠበቅ አለባቸው። ህሊና እና ይሉኝታ፣ ሰብዓዊነት ከሌለ ደግሞ መቼም ቢሆን ገንዘብ ‹‹አሁን ተርፎኛል›› ሊባል አይችልም፡፡

የሠራተኛን ጉልበት ስለሚበዘብዙት እያወራን ስለሆነ እንጂ ከደሞዙ በላይ ትርፍ ጨምረው (ጉርሻ ይሉታል) የሚሰጡ መኖራቸውን አልዘነጋነውም። ሠራተኛው ከተቀጠረበት ውል ውጭ ሌሎች ወጪዎቹን የሚሸፍኑለት አሰሪዎች እንዳሉ እናምናለን። በቅርበት የማውቀው አንድ ምሳሌ ብቻ ልጥቀስ። በአንድ የግል ባለሀብት ንግድ ቤት ውስጥ ተቀጥሮ ይሰራ የነበረ አብሮ አደግ ጓደኛዬ ከዓመታት በፊት ሲያገባ ያሰራው የነበረው ባለሀብት 30 ሺህ ብር ሰጥቶት በወቅቱ ብዙ አመስገነናል። ደሞዝ የሚከለክሉ እንዳሉ ሁሉ እንዲህ አይነቶችም አሉ ለካ ብለን ተገርመናል። ያንን ብር የሰጠው ብድር አይደለም! ‹‹ለዚህ ቁም ነገር ከበቃህ!›› ብሎ በሰዋዊነት ነው። ይህ አንድ ነጠላ ምሳሌ ነው፤ የዚህ አይነት ብዙዎች አሉ።

እንደዚህ ማገዙ ቢቀር እንኳን (የሕግ አስገዳጅነት ስለሌለው) ሕግ እየጣሱ የሠራተኛ ደመወዝ የሚከለክሉ፣ የደመወዝ ቀን ሲደርስ ሰበብ አስባብ ፈልገው የሚያባርሩ ህግንም፣ ሞራልንም ሊፈሩ ይገባል!

ዋለልኝ አየለ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሚያዝያ 25 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You