ኢትዮጵያውያን ጀግኖች አርበኞች ሀገራቸውን ለአምስት ዓመታት በኃይል የወረረውን ፋሽስት ጣሊያንን በዱር በገድል ተዋድቀው በማሸነፍ ሃገራቸውን ነጻ ያደረጉበት 82ኛው የድል በዓል ዛሬ በመላ ኢትዮጵያ እየተከበረ ይገኛል:: ኢትዮጵያን ቅኝ ለመግዛት ያሰፈሰፉት ጣሊያኖች በዓድዋው ጦርነት በኢትዮጵያውያን የደረሰባቸውን ውርደት ለመበቀል አርባ ዓመታት ተዘጋጅተው በዘመናዊ መሣሪያ ተደራጅተው ተመልሰው በመምጣት ኢትዮጵያን ቢወሩም እቅዳቸው ግን አልተሳካም::
ፋሽስቶቹ ሀገሪቱን በመውረር በኢትዮጵያውያን ላይ ያልፈጸሙት የግፍ ዓይነት አልነበረም:: በዚህ ወረራም ማይጨው ላይ የገጠማቸውን የኢትዮጵያ ጦር በዓለም አቀፍ ደረጃ የተከለከለ የጦር መሣሪያ /የመርዝ ጋዝ/ ጭምር በመጠቀም በግፍ ጨፍጭፈዋል:: ግራዚያኒ የካቲት 12 ቀን 1929 ዓ.ም በአዲስ አበባ ነዋሪዎች ላይ ዘግናኝ ጭፍጨፋ እንዲፈጸም አድርጓል:: በዚህ ግፍ የተሞላበት ድርጊት ከ30 ሺ በላይ ኢትዮጵያውያን በአካፋ፣ በዶማና በመሳሰሉት ጭምር በግፍ ተጨፍጭፈዋል:: ጭፍጨፋው ከአዲስ አበባም ወጥቶም ደብረ ሊባኖስ ድረስ በመዝለቅ የበርካታ ኢትዮጵያውያን ሕይወት ነጥቋል::
ኢትዮጵያውያን ግን የቱንም ያህል የፋሽስቶች በትር ቢጸናባቸውም፣ የቱንም ያህል ወገኖቻቸው በግፍ ቢገደሉባቸውም ፋሽቶችን መውጫ መግቢያ መንሳታቸውን አጠናክረው ቀጥለውበታል:: እምቢኝ ለሀገሬ ብለው በዱር በገደሉ ሆነው ፋሽስቶችን ለአምስት ዓመታት በመፈተን ፋሽስቶቹ ተደላድለው እንዳይቆዩ ከማድረግ ባለፈ ሽንፈትን እንዲከናነቡ በማድረግ በ1933 ዓ/ም በዚህ ቀን ከሀገራቸው ጠራርገው አስወጥተዋቸዋል:: የዛሬው የድል በዓልም ይህንን የጀግኖች ኢትዮጵያውያንን ታላቅ ጀግንነት የሚዘከር ነው::
ኢትዮጵያውያን ታላቅ ድል ያስመዘገቡት ዘመናዊ የጦር መሣሪያ ታጥቀው አልነበረም፤ ከሃገር በላይ ምንም የሚቀድም እንደሌለ በመገንዘብ በአንድነት ሆነው በወኔ ተሞልተው ባደረጉት እልህ አስጨራሽ ተጋድሎ ነው:: ይደርስባቸው የነበረው ጭፍጨፋና ስቃይ ጠንክረው እንዲዋጉ አበረታታቸው፣ አንድ አደረጋቸው እንጂ ሸብረክ እንዲሉ አላደረጋቸውም:: በዱር በገድል እየተዘዋወሩ ፋሽስት ጣሊያንን መቆሚያ መቀመጫ ነስተውታል፤ ቁም ስቅሉን አሳይተውታል፤ በመጨረሻም ጠራርገው በማስወጣት ጀግኖች አባቶቻቸው በዓድዋ የተጎናጸፉትን ድል እነሱም ደግመውታል::
ይህን ታላቅ ገድል በመጻፍ እንደ ዓድዋ አባቶቻቸው ሁሉ ሀገራቸው በፋሽስቶች መዳፍ ውስጥ እንዳትገባ በማድረግ ታሪክ ደግመው ጽፈዋል:: ይህ ድል ፊቱንም በዓድዋው ድል የሚታወቁትን ኢትዮጵያውያንን ጀግንነት ድርብ ድርብርብ እንዲሆን አድርጎታል:: የኢትዮጵያውያን ጀግንነት ሌላ ከፍታ እንዲላበስ አድርጓል::
ኢትዮጵያውያን የሀገር ሉዓላዊነትን የሚደፍሩ ድርጊቶች ከውጭ ኃይሎች ሊሰነዘሩ በተሞከሩም ሆነ በተሰነዘሩ ቁጥር ለጠላትም ለወዳጅም በሚል እነዚህ የጦር ሜዳ ገድሎቻቸው ይጠቀሳሉ:: ኢትዮጵያውያን የውጪ ኃይሎች ሀገራቸውን በወረሩበትም ሆነ ሊወሩ ባሰቡበት ወቅት ሁሉ እነዚህ ታሪኮች ይጠቀሳሉ፤ በእነዚህ ታሪኮች ልክ ጠላቶቻቸውን እንደሚያሸንፉም በሚገባ ያምናሉ:: ኢትዮጵያውያን እያንዳንዱን ሙከራ በቀደመው የአያት ቅድመ አያቶቻቸውና አባቶቻቸው የጀግንነት ታሪክ አክሸፈዋል::
በልማቱም መስክ ይህንኑ ጀግንነት ለመድገም ይተባበራሉ:: በዓለምም በአፍሪካም ጭምር ታላቅ የተባለውን የዓባይ ግድብ አሁን ለደረሰበት ወሳኝ ምዕራፍ ያበቁት በዚህ ጀግንነትና ጀግንነቱን በወለደው የአንድነትና የመተባበር ወኔ በመነሳሳት ነው:: ወደፊትም ይሄው ነው የሚሆነው:: ኢትዮጵያውያን ድህነትና ድርቅ ለመቋቋም የሚያስችል ሥራ ለመሥራት ሞክረዋል፤ ከድህነት በላይ ጠላት የለንም ብለው በድህነት ላይ ዘምተዋል::
ኢትዮጵያውያን የዜጎችን ተጠቃሚነት ለማሳደግና የሀገሪቱን ብልጽግና ለማረጋገጥ አሁንም በአንድነትና በመተባበር መሥራት አለባቸው:: እነዚህ ላይ ለመድረስ በመንግሥት በሚከናወኑ ተግባሮች ብቻ ብዙ ርቀት መጓዝ አይቻልም:: የዜጎች በግል መሮጥ አንድ ነገር ሆኖ ባስፈለገ ጊዜ ተባብሮ መሥራትና በአንድነት መቆም ያስፈልጋል::
ትላልቅ ፕሮጀክቶችን አብሮ መፈጸም እንደሚቻል ከዓባይ ግድብ መረዳት ተችሏል:: በቀጣይም መንግሥት ለግዙፍ ፕሮጀክቶቹ እውን መሆን የሚያደርጋቸውን ጥሪዎች በመቀበል በልማት ላይ በንቃት በመሳተፍ ለዜጎችና ለሀገር የበለጠ ተጠቃሚነት መሥራት ዘመኑ የሚጠይቀው ጀግንነት መሆኑን መገንዘብ ይገባል:: በዚህም ጀግኖች አርበኞች በፋሽስቶች ላይ የተጎናጸፉትን ድል ይህ ትውልድ በልማቱ ለመድገም የተጀመሩ ጥረቶችን በመደገፍ የራሱን ታሪክ መጻፍ ይጠበቅበታል::
በልማቱ ድልን ለመጎናጸፍ ልክ ጀግኖች አርበኞች ብዙ ፈተናዎችን አልፈው ድል እንደተጎናጸፉት ሁሉ ይህ ትውልድም በልማቱ ነገሮች አልጋ በአልጋ ላይሆኑ እንደማይችሉ በመገንዘብ ከፈተና መውጫ መንገዶችን በማዘጋጀት በልማቱ ሀገርና ሕዝብን የሚያሻግር ድል ለማስመዝገብ ርብርብ ሊያደርግ ይገባል!
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 28/2015