በሀገራችን ከፍተኛ መጠን ያለው ሀብት እየተመደበ የመንገድ መሰረተ ልማት ግንባታ እየተካሄደ ይገኛል። የመንገዶች ደረጃ እየተሻሻለ ሲሆን፣በዓይነቱ ልዩ የሆነም የአዲስ አዳማ ፈጣን መንገድ ተገንብቶ ወደ ሥራ ገብቷል።መንገዱ ሥራ የሚጀምረው በ2007 ዓ.ም መስከረም ወር መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ። በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በምስራቅ አፍሪካ ደረጃም የመጀመሪያው የፍጥነት መንገድ ነበር ።
መንገዱ በነባሩ መንገድ ከአዲስ አበባ አዳማ ለመድረስ ይታይ የነበረውን የትራፊክ መጨናነቅ እና የወስድ የነበረውን ጊዜ በመቀነስ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎችን እያስገኘ ነው።የነዳጅ ወጪን ይቆጥባል፤የትራፊክ አደጋን ይቀንሳል፤መንገደኞችንና እቃዎች ለማጓጓዝ የተመቻቸም ነው።
ከ24 ሺ በላይ ተሽከርካሪዎች በመንገዱ እየተገለገሉ ይገኛሉ።ወደ ሥራ ከገባ አንስቶም ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ አስገኝቷል።ይህ ገቢ በቀጣይ እያደገ እንደሚሄድ ይጠበቃል።የአዲስ አዳማ መንገድ እያስገኘ ስላለው ፋይዳና አገልግሎቱን ይበልጥ ዘመናዊ ለማድረግ እየተከናወኑ ስላሉ ተግባሮች ከኢትዮጵያ የክፍያ መንገዶች ኢንተርፕራይዝ ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ዓቢይ ወረታው ጋር ያደረግነውን ቃለ ምልልስ እንደሚከተለው አቅርበነዋል።
የፍጥነት መንገዱ ፋይዳዎች
የመንገድ መሠረተ ልማትን ለማስፋፋት የሚያስፈልገው መዋዕለ ንዋይ ሠፊ እንደሆነ ይታወቃል።መንገዱ በክፍያ የሚሰራ እንደመሆኑ ሀገራችን ያለባትን የካፒታል ውስንነት በመፍታት በኩል የራሱን ሚና ይጫወታል።
መንገዱ ከአዲስ አበባ ወደ ጅቡቲ ወደብና ወደ ምስራቁ ክፍል የተለያዩ ክልሎች የሚወስደው የመንገድ ኮሪደር አካል መሆኑ ይታወቃል።ይህ መንገድ ከፍተኛ መጠን ያለው ተሽከርካሪ የሚገለገልበትም፣እያደገ የመጣውን የትራፊክ ፍሰት ነባሩ መንገድ ብቻውን የሚሸከመው አልነበረም።የአዲስ አዳማ የክፍያ መንገድ የትራፊክ መጨናነቅ ከመቀነስ አንፃር አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው።
ፈጣን መንገዱ በተለይ የገቢ ወጪ ንግድ የሚሳለጥበት መንገድ በመሆኑ ከዚህ አኳያ ከፍተኛ የኢኮኖሚ አስተዋፅዖ እያደረገ ይገኛል።አንደኛ በተለይ የጊዜ ቅናሽ አለው።በዚህም ጊዜ ከመቆጠብ ጎን ለጎን የነዳጅ ወጪንም ይቀንሳል።ከነዳጅ በተጨማሪ ሌሎች የተሽከርካሪ ማንቀሳቀሻ
ወጪዎችንም እንዲሁ ይቀንሳል። የካርበን ልቀቱን ይቀንሳል ማለት ነው ስለዚህ ለአካባቢ የሚያበረክተው አስተዋጽኦም አለ ማለት ነው።
እነዚህ ጥቅሞች አጠቃላይ ኢንቨስትመንቱም ባለው ተሽከርካሪው አሽከርካሪው ማክሮ ኢኮኖሚው ላይ አዎንታዊ አስተዋፅዖ ይኖራቸዋል።በተለይ በሎጂስቲክ ስርዓቱ ላይ የወጪ ቅናሽ በማድረግ ኢኮኖሚው ተወዳዳሪ እንዲሆን አስተዋፅዖ አድርጓል ብለን እናምናለን ።
የትራንስፖርት ዘርፉ ብቁና ወጪ ቆጣቢ ሲሆን ኢንቨስተሮች አምራቾች ላኪዎች አስመጪዎች እነዚህ ሁሉ ተወዳዳሪ ይሆናሉ። ከዚህ ጋር በተገናኘ በእኛ በኩል እነዚህ አሁን የፈጣን መንገድ ሆነው እየተገነቡ ያሉ ኮሪደሮች በተለይ የገቢ እና ወጪ ንግድ መስመሩን ታሳቢ ያደረጉ ናቸው።
በመንገዱ የሚገለገሉ ተሽከርካሪዎች
መንገዱ 24 ሰዓት አገልግሎት ይሰጣል።መንገዱ ሥራ ሲጀምር (ከአራት ዓመት በፊት) ተጠቃሚዎቹ 8ሺ ያህል ነበሩ። ይህ አሀዝ በአሁኑ ወቅት በእጅጉ አድጓል።በቀን በአማካይ 24ሺ ተጠቃሚዎች ይመላለሱበታል።
በተያዘው በጀት ዓመት በቀን 24ሺ 301 ተሽከርካሪ ለማስተናገድ ታቅዶ በዘጠኝ ወራት ውስጥ በቀን 23ሺ 294 ተሽከርካሪዎች ተስተናግደዋል ።አፈፃፀሙ የእቅዱ 95ነጥብ 86 በመቶ ነው።
በዘጠኝ ወራት ውስጥ 6ሚሊዮን 658ሺ474 ተሽከርካሪ ለማስተናገድ ታቅዶ 6ሚሊዮን 382ሺ800 ተሽከርካሪዎችን ማስተናገድ ተችሏል።በእነዚህ ወራት 191 ሚሊዮን 470 ሺ 903 ብር ተሰብስቧል። በአማካይ በቀን 728ሺ23 ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ 698ሺ798 ብር በቀን መሰብሰብ ተችሏል።
የሚያስተናግዳቸው ተጠቃሚዎች ብዛት እየጨመረ እንደሚሄድ ይጠበቃል።መንገዱም ከፍተኛ የማስተናገድ አቅም ያለው ስለሆነ ለበርካታ ዓመታት ይሄ ነው የሚባል መጨናነቅ ሳይኖር ማስተናገድ ይችላል።
ገቢ
የገቢው መጠን ከትራፊክ ፍሰቱ ጋር ይያያዛል።ሥራ በጀመረበት ዓመት 96ሚሊዮን ብር አስገኝቷል ።ይህ ገቢ እያደገ ነው የመጣው።በዚህ በጀት ዓመትም 280 ሚሊዮን ብር እንሰበስባለን ብለን እንገምታለን። በቀጣይ በጀት ዓመት ደግሞ ከ300ሚለዮን ብር በላይ የመሰብስብ አቅም ይኖረናል። በአጠቃላይ ሥራ ከጀመረ አንስቶም እስካሁን ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ መሰብሰብ ተችሏል ።
ከታሪፍ ጭማሪው በፊት በበጀት ዓመቱ 265ሚሊዮን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ የእቅዱን 95በመቶ ያህልማሳካት ተችሏል።ከታሪፍ ጭማሪው ጋር ተያይዞ ይህ ገቢ ከመጋቢት ጀምሮ ትንሽ ከፍ እንደሚል ይጠበቃል ። እስከ 280 ሚሊዮን ብር ይጠበቃል። በሚቀጥለው ዓመት ደግሞ አሁን የታሪፍ ማሻሻያ ያደረግን በመሆኑ በዓመት 300ሚሊዮን ብርና ከዚያ በላይ ለመሰብሰብ ታቅዷል።
የሥራ ዕድል
መንገዱ ሠፊ የሥራ ዕድል ፈጥሯል።በአሁኑ ወቅት 500 ያህል ቋሚ እንዲሁም ከ150 የማያንሱ ጊዜያዊ ሠራተኞች አሉት።በሌሎች የሥራ መደቦች በርካታ የሥራ ዕድሎችን የፈጠረ ሲሆን፣ በአጠቃላይ እስከ 1ሺ ያህል ለሚሆኑ ሰዎች የሥራ ዕድል ፈጥሯል ።
ማኅበራዊ ኃላፊነታችንን በመወጣት ከአካባቢው ማኅበረሰብ ጋር የምንሠራው ሥራ መልካም ሊባል የሚችል ነው።በመንገድ ኮሪደሩ ያለው ማህበረሰብ የተለያዩ ድጋፎችን ይጠይቀናል። ለምሳሌ የኤሌክትሪክ እና የውሃ የመሳሰሉት አገልግሎቶች እንዲኖሩት ይፈልጋል።ተቋማችን ብድር ከፋይ ተቋም ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የአቅም ውስንነት ቢኖርበትም፣በየዓመቱ የተወሰኑ ሥራዎችን ለመሥራት እንሞክራለን ።
ከዚህ ይልቅ ተቋሙ ሰፋፊ ኢኮኖሚያዊ
ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ጠቀሜታዎች አሉት። በሀገራችን የመጀመሪያው ፈጣን መንገድ እንደመሆኑ የውጭ ሀገርና የሀገር ውስጥ ብዙ ጎብኚዎች ይሄን መንገድ ይጎበኙታል ።መንገዱን የቴክኖሎጂ ግብዓት ያለው የተሻለ ክብካቤ የሚደረግለት እሴት የታከለበት መንገድ እንደመሆኑ ከዚህ ጋር በተገናኘ ለገፅታ ግንባታ የራሱን ሀገራዊ አስተዋፅዖ እያበረከተም ነው
ከክፍያ ጋር በተያያዘ ሥራ ስንጀምር ከባድ ተግዳሮት አልገጠመንም ምክንያቱም ነባሩ መንገድ ብዙ ችግር የነበረበት ነው ።የተጨናነቀና ጊዜ የሚፈጅ በመሆኑ የመንገዱ ተጠቃሚዎች በፈጣን መንገዱ በመጠቀማቸው የሚያገኙትን ጥቅም በግልፅ ተረድተዋል። ስለዚህ ለሚያገኙት ጥቅም የተወሰነ መጠነኛ ክፍያ ለመክፈል ፍቃደኛ ናቸው።
በአሁኑ ወቅት ለመጀመሪያ ጊዜ መጠነኛ የሆነ የታሪፍ ጭማሪ አድርገናል። አሁንም የመንገድ ተጠቃሚው አቀባበል አዎንታዊ ነው ። የእኛ የክፍያ ታሪፍ ከአፍሪካም ሆነ ከሌሎች ሀገሮች ጋር ሲነፃፀር በጣም ዝቅተኛ ነው ፤ ስለዚህ ከዚህ አንፃርም ሊሆን ይችላል ከክፍያ ጋር በተያያዘ ያጋጠመን የጎላ ተግዳሮት የለም ።መንገዱ ለመንገደኞቻችን ከሚያስገኘው ጥቅም አንፃር ተቀባይነት አግኝቷል ማለት ይቻላል ።
የትራፊክ አደጋ ከመቀነስ አንጻር
በነባሩ መንገድ ይደርስ የነበረውን የትራፊክ አደጋ በፍጥነት መንገዱ መቀነስ ተችሏል። ሆኖም የትራፊክ አደጋው አሁንም የፍጥነት መንገዱ አንዱ ጥያቄ ሆኗል። መንገዱ የፍጥነት በሚል ተጠቃሚዎች ከልክ በላይ በፍጥነት የሚያሽከረክሩበት ሁኔታ እያጋጠመ ነው። በዚህም ዘግናኝ የሚባሉ አደጋዎች ጭምር እየደረሱ ናቸው ።የመንገዱ ተጠቃሚዎች የፍጥነት ወሰኑን አክብረው ሥነ ምግባር በተላበሰ መልኩ ሊያሽከረክሩ ይገባል።ይህ ካልሆነ የሚደርሰው አደጋም ከባድ ይሆናል።
ፈጣን መንገዱ ለጥንቃቄ የሚረዱ አሰራሮች (ሴፍቲ ፋሲሊቲዎች) አሉት። ለምሳሌ የመንገድ አካል አካፋይና ዳር የግጭት መከለያ ብረት አለው ። በእዚህ ፋሲሊቲ አደጋ ቢደርስ ጉዳት መቀነስ ይቻላል።ከአቅም በላይ ፍጥነት ተጠቅመው ተሽከርካሪዎች አደጋ ከደረሰባቸው በዚያው ልክ ጉዳቱም የከፋ ሊሆን ስለሚችል በጥንቃቄ ማሽከርከር ይገባል።
ስለሌሎቾ የፍጥነት /የክፍያ መንገዶች
የድሬዳዋ ደወሌ መንገድን የክፍያ ለማድረግ እየተሰራ ነው።መንገዱ በኤክስፕረስ ወይም ፈጣን
አንዳንድ በግልና በመንግሥት ሽርክና በሚባለው ትስስር ወደፊት የሚገነቡ የፍጥነት መንገዶችን የማስተዳደር ሁኔታ ምን ይሆናል የሚለው ወደፊት የሚወሰን ይሆናል።ዞሮ ዞሮ ግን የፌዴራል የክፍያ መንገዶችን የማስተዳደር ኃላፊነት የክፍያ መንገዶች ኢንተርፕራይዝ ነው፡፡
የመንገድ ጥገና
ኢንተርፕራይዙ መንገዱን የማስተዳደር አንድ ቁልፍ ዋና ተግባር ብቻ አይደለም ያለው፡፡መጠገንም ሌላው ሥራው ነው።ከዚህ ጋር በተገናኘ መንገዱ በአሁኑ ወቅት በጥራት ዋስትና (ዋራንቲ ፔሬድ) ውስጥ ስለሆነ የታዩ ክፍተቶችን ተቋራጩ እያስተካከለ ይገኛል።
ከአንድ ዓመት በኋላ ይሄ ሥራው ያበቃል፡፡በመሆኑም ኢንተርፕራይዙ የጥገና ክህሎቱን ማስፋት ይኖርበታል።ለዚህም የጥገና ስትራቴጂ እያዘጋጀ ነው ፡፡ሙሉ ለሙሉ መንገዱን የማስተዳደር እንዲሁም የመጠገን፣ የማስጠገንም አቅም ለማዳበር አቅዶ እየሰራ ይገኛል። ስለዚህ የጥገና ስትራቴጂ እያዘጋጀን እንገኛለን። ጥገናውን እንዴት እንመራዋለን የሚለውን ይዘን እየሰራን ነው፡፡ የአቅም ግንባታችን አንድ
ክፍል የጥገና አቅምን ማሳደግ ነው፡፡
መንገዱን በማስተዳደር ሂደት ያጋጠሙ ተግዳሮቶች
መንገዱን በማስተዳደር ሂደት ችግሮችም አጋጥመዋል። አንደኛውና ዋናው ችግር የአሽከርካሪዎች የሥነምግባር ክፍተት ነው። ፈጣን መንገዱ የሚፈልገውን የአሽከርካሪ ሥነምግባር አሟልቶ ይዞ አለመገኘት አለ። ለምሳሌ በተለይ አንዳንድ የንግድ አሽከርካሪዎችና የትናንሽ የግል ተሽከርካሪ አሽከርካሪዎች ከፍጥነት በላይ ሲያሽከረክሩ ይታያል፡፡ይህ ትልቅ ተግዳሮት ነው። ይህን ለመግታት የሚያስችል የቁጥጥር ሥርዓት ለመተግበር እየተዘጋጀን እንገኛለን።
ሁለተኛ ከጭነት ተሽከርካሪዎች ጋር ብቻ የተያያዘው ችግር ነው፡፡ እነዚህ ተሽከርካሪዎች ከክብደት በላይ ጭነው ወደ ፈጣን መንገድ ለመግባት ይሞክራሉ።በሁሉም በሮቻችን ላይ ከክብደት በላይ የሚጭኑትን እንቆጣጠራለን። ሲመጡም እንመልሳን፡፡
ከክብደት በላይ ጭነው የሚመጡ ተሽከርካሪዎች የሚያልፉበት ሁኔታ ከተፈጠረ አንደኛ መንገዱ ይጎዳል፡፡ሁለተኛ የአደጋ መንስዔ ይሆናሉ። ሦስተኛ ፈጣን መንገዱ የተከለለበትን አጥር እየሰበሩ ወይም እየቀደዱ በመግባት ዝርፊያ የመፈጸም ምልክቶች ይታያሉ።ይህን በመጠቀም እንስሳት ወደ ፈጣን መንገዱ ይገባሉ፡፡ ደንበኛው በፍጥነት በሚጓዝበት ጊዜ ለአደጋ የሚጋለጥበት ሁኔታ እያጋጠመ ነው። በተረፈ የጎላ የሚባል ችግር የለም ፡፡
የመንግሥትና የግሉ ዘርፍ አጋርነት በፍጥነት መንገድ ግንባታ ፍላጎት
በግልና የመንግሥት አጋርነት በቀጣይ እንዲሰሩ ከታሰቡት የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች አንዱ የፈጣን መንገድ ልማትና አስተዳደር ሥራ ነው፡፡ኢንቨስትመንቱ ተጨማሪ የፋይናንስ እቅም የሚፈጠርበት እንደሚሆን ይታመናል፡፡አንዱ ጠቀሜ ታውም ይሄ ይመስለኛል።ሁለተኛው ደግሞ መንገድ የማስተዳደር ክህሎትና ብቃት እንዲጨምርም ያደርጋል ።
የግሉ ዘርፍ ምናልባት ከመንግሥት ዘርፍ የተሻለ ብቃት ይዞ ሊመጣ ይችላል፡ ፡ ከምንም በላይ ግን የመንገድ ድረግብር (Road network) ከማስፋት አንፃር ተጨማሪ ፋይናንስ የመሳብ ዕድል ይኖረዋል፡፡
መንግሥትም ይሄን አስመልክቶ ቦርድ አቋቁሟል፡፡ሥራው ግን በዝርዝር ጥናት ላይ ተመስርቶ መከናወን ይኖርበታል።በቅርብ ይፀድቃል ብለን በምንጠብቀው የመንገድ ክፍያ ፖሊሲ ውስጥም ይህ የመንግሥትና የግል አጋርነት አሠራር የሚካተት ይሆናል ።
ጥናትና ግምገማ
ኢንተርፕራይዙ በየዓመቱ የደንበኞች እርካታ ዳሰሳ ጥናት ይሠራል፡፡በዚህም መሻሻል መኖሩን ተገንዝበናል፡፡በጥናቱ 76በመቶው ተጠቃሚ መርካቱን መረዳት ተችሏል፡፡
የተወሰኑ ቅሬታዎችም አሉ፡፡እነዚህን ለመፍታትም እየተንቀሳቀስን ነው። በተለይ ክፍያ ሰብሳቢዎች አካባቢ ክፍተቶች እንዳሉ ተጠቁሟል፡፡የሠራተኞቹን አቅም መገንባት የሚያስችል የደንበኛ አገልግሎት ወይም የደንበኛ አያያዝ ስልጠና ልምድ ካለው ከአቪየሽን አካዳሚ ልምድ እንዲቀስሙ ተደርጓል።በዚህም ከሠራተኞቻችን የተሻለ የደንበኞች አገልግሎት እንጠብቃለን ።
የክፍያ ሥርዓት የማዘመን ሥራዎች
በቅርቡ የምንተገብራቸው ማሻሻያዎች አሉ ፡፡ለምሳሌ የክፍያ አሰባሰብ ሥርዓቱን የማዘመን ስርዓት አለ፡፡ ኤሌክትሮኒክስ ተኮር የክፍያ ሥርዓት እንዘረጋለን፡፡
የፍጥነት ቁጥጥር አሠራር ለመተግበር አቅደናል፡፡ወደፊት ሞጆ ሐዋሳ የፍጥነት መንገድ የመሳሰሉ ሲመጡ የተቀናጀ የክፍያ አሰባሰብ ስርዓት፣ የትራፊክ አስተዳደር ፣ወዘተ ይኖረናል፡፡ ስለዚህ ተጨማሪ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን በመጠቀም የደንበኞችን እርካታ ለማሳደግ ኢንተርፕራይዙ እየሰራ ነው ።
መልዕክት
ለአሽከርካሪዎች መልዕክት ማስተላለፍ እንፈልጋለን፡፡ መንገዱን ሲጠቀሙ በዋናነት የትራፊክ ደንቦችን እና ፈጣን መንገዱ ላይ በግልጽ የተቀመጡ ምልክቶችን አክብረው ማሽከርከር ይኖርባቸዋል፡፡የፍጥነት ወሰናቸውን ማክበር እና ለሠራተኞቻችን ተባባሪ መሆንም ይጠበቅባቸዋል፡፡ የመንገዶችንና አካባቢያቸውን ንጽህና አለመጠበቅ አንድ ተግዳሮት ሆኗል፡፡ መንገዱን የማፅዳት ሥራ ከባድ ሥራ ሆኖብናል፤ በተለይ ፕላስቲክ ጠርሙሶችንና ሌሎችም ነገሮች መንገዱ ላይ ይጥላሉ ፡፡
ተጠቃሚዎች ደረቅ ቆሻሻ ወዘተ መንገዱ ላይ መቆጠብ አለባቸው፡፡ መንገዱ ዘመናዊ መንገድ ከመሆኑም አንፃር ስልጡን መንገድ ተጠቃሚን ይጠይቃል ፡፡ሌሎች መንገዶች ላይ የሚታዩ ጉድለቶችን ወደ ዘመናዊ ፈጣን መንገድ አምጥቶ የመንገዱን የሥራ ሂደት ማወክና ማሰናከል አይገባም፡፡ ስለዚህ ተጠቃሚዎች በዚህ ደረጃ እንዲተባበሩን እንጠብቃለን ፡፡
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 22/2011
በኃይለማርያም ወንድሙ