የቀቤና ብሔረሰብ ‹‹ወማ›› በሚባል የማዕረግ ስም በሚታወቁ ባህላዊ መሪዎች ይተዳደራል:: ብሔረሰቡ 39 ጎሳዎች አሉት፤ በባህላዊ አስተዳደር ውስጥ አስተዳደራዊ ጉዳዮችን የማየት ስልጣን ያላቸው ሁሉም ጎሳዎች በሚወከሉበት ጉባኤ የሚመርጡ 39 ዳኞችም አሉት:: ዳኞቹም በህዝብ መካከል የሚነሱ ግጭቶችን የሚፈቱት የእስልምና ሃይማኖት እና የብሄረሰቡ ባህላዊ አስተዳደር ህግን መሰረት በማድረግ ነው:: ይህ ባህላዊ ህግ ‹‹ቦበኒ አደታ›› ወይም ‹‹ቦበኒ›› በመባል ይታወቃል::
የቀቤና ወረዳ የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ፅ/ቤት ኃላፊ አቶ አብድልናስር ሚፍታ እንደሚሉት፤ ምንም እንኳን የብሔረሰቡ ሃይማኖታዊ /የእስልምና እምነት/ አስተዳደር መቼ እና እንዴት እንደ ተመሰረተ የሚገልጽ ተጨባጭ ማስረጃ እስካሁን ማግኘት ባይቻልም ለ‹‹ቦበኒ›› ስርዓት መሰረቱ ቁርዓን እንደሆነ ይታመናል::
በ‹‹ ቦበኔ ገልቲታ›› የቀቤና ብሄረሰብ መተዳደሪያ ደንብ ላይ እንደተመለከተው፤ የባህላዊ መተዳደሪያ ደንቡ ሀይማኖትን መነሻ አድርጎ የተዘጋጀ ቢሆንም፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተቀየረ የራሱ የሆነ መተዳደሪያ ደንብ እንዲኖረው በማድረግ የቦበኒ መተዳደሪያ ደንብ በማለት በአጠቃላይ የቀቤና ብሄረሰብ ተሰብስቦ ደንቡን የሚያጸድቅበት፣ የሚያሻሽልበት የተለያዩ ደንቦችና መመሪያዎች የሚያስተላልፍበት ስብሰባ ‹‹ኦገት›› ተብሎ ይጠራል::
በብሄረሰቡ ውስጥ ግጭት ሲከሰት ለመፍታት ውሳኔ የሚሰጥበት መንገድ እንደ ግጭቱ ክብደትና ቅለት ይለያያል:: በብሔረሰቡ ውስጥ ቀላል ግጭት ሲፈጠር ግጭቱ በተፈጠረበት አካባቢ ካሉ ታዋቂ ሽማግሌዎች መካከል የተወሰኑት ተመርጠው ጉዳዩን እንዲመለከቱት ከተደረገ በኋላ ባለጉዳዮቹን ‹‹ሩባቱ›› ተብሎ በብሄረሰቡ የሚታወቀውን ዋስ በማስጠራት ጉዳዩን በጥልቀት ይመረምራሉ:: የአካባቢው ሽማግሌዎች ጉዳዩን በጥልቀት በመመርመር ጥፋተኛው ላይ ቅጣት በመወሰን በሁለቱም ወገን እርቅ እንዲፈጠር እንደሚደረግ የብሔረሰቡ መተዳደሪያ ደንብ ‹‹ቦበኔ ገልቲታ›› ያብራራል::
በሌላ በኩል በብሄረሰቡ ጎሳ አባላት መካከል ግጭት ሲፈጠር በራሱ ጎሳ ዳኛ አማካኝነት ይዳኛል:: ይህ ማለት ከቤተሰብ ወጣ ባለ በአንድ አይነት ጎሳ ውስጥ ግጭት የሚፈጠር ከሆነ ጉዳዩ ወደ ብሄረሰቡ ሽማግሌ ወይም ወደ ሰፈር ሽማግሌዎች ሳይደርስ በጎሳ ዳኛ አማካኝነት የጎሳው አባላት ተሰብስበው በጥፋተኛው ላይ ቅጣት በመወሰን እንዲታረም ያደርጋሉ::
በዚሁ አሰራር የጎሳው ዳኞች ከቀላል የገንዘብ ቅጣት እስከ ግርፋትና ከጎሳ አባልነት የማግለል ቅጣት ሲጥሉ ዘመናትን መቆየታቸውን ይኸው መተዳደሪያ ደንቡ ያስረዳል:: ግጭቶቹም እርስ በርስ የድንበር ግጭት፣ በውርስ ሀብት ክፍፍል ላይ የሚከሰት አለመስማማት፣ ልጅ አባቱን እና እናቱን ያለመጦር እና ልጅ ለቤተሰቦቹና ለዘመዶቹ ማድረግ ያለበትን ያለማድረግና የመሳሰሉት አይነት ናቸው:: ለእነዚህ ጥፋቶች ቅጣቱም በዳይ ወገን ለተበዳይ ወገን ማር፣ ቅቤ ጋቢ፣ ወዘተ እንዲሰጥ የሚያደርግ ሲሆን፣ ለሽማግሌዎቹ ደግሞ በግ፣ ወይፈን ወይም በሬ አርዶ ያበላል፤ በሽማግሌዎች በኩል ደግሞ ምረቃ ተደርጎ እርቅ እንዲፈጠር ሲደረግ ኖሯል::
መተዳደሪያ ደንቡ በጎሳዎች መካከል የሚፈጠሩ ግጭቶች የሚፈቱበትን አኳኋንም ያሳያል:: በቀቤና ብሄረሰብ ውስጥ ባሉት ጎሳዎች መካከል የሚፈጠሩ ግጭቶችን የከሳሽና የተከሳሽ ወይም የበዳይና የተበዳይ ጎሳ መሪዎች በመገናኘት ይፈታሉ:: ግጭቱ ቀለል ያለ ከሆነ በሰፈራቸው ባሉ ሽማግሌዎች አማካኝነት እንዲዳኙ ይደረጋል፤ ከበድ ያለ ግጭት ከሆነ ደግሞ የሁለቱ ጎሳ መሪዎች ሁለቱም ቡድኖች ዋስ እንዲጠሩ በማድረግ በብሄረሰቡ ውስጥ ታዋቂ ችግር ፈቺ ሰዎችን ወይም ዳኝነት የሚችሉ ሰዎችን በማስቆጠር እንዲዳኙ ይደረጋል::
የግጭት አፈታት ስርዓቱ ለብዙ ዘመናት መዋቅራዊ ይዘት ሳይኖረው ግጭቶች ሲፈጠሩ ብቻ ችግር ፈቺ ሰዎች እየተፈለጉ ሲያስታርቁ የኖሩበት መሆኑን የሚገልጹት አቶ አብድልናስር፣ ከ19ኛው ክፍለ ዘመን ወዲህ ግን የግጭት አፈታቱ መዋቅራዊ ይዘት እንዲይዝ መደረጉን ይገልጻሉ:: በብሄረሰቡ ውስጥ የሚፈጠር ቀላል ግጭትን በሰፈር ውስጥ እንዲፈታ ይደረጋል፤ ከበድ ያሉ ግጭቶች ደግሞ በመላ ቀቤና ጉባኤ ‹‹ኦገት››በተመረጡ ሽማግሌዎች ዘንድ በማቅረብ እንዲዳኝ ሲደረግ መቆየቱን ያብራራሉ::
የዚህ አይነት ግጭት በብሄረሰቡ መካከል ብቻ ሳይሆን ቀቤና ብሄረሰብ ከሌሎች አጎራባች ብሄረሰቦች ጋርም በድንበር፣ በግጦሽ መሬት እና በሌሎች ምክንያቶች ግጭት ውስጥ ሲገባ ለመፍታት ጥቅም ላይ የሚውልበት ሁኔታ እንዳለም ገልጸዋል:: በዚህ ግጭት የመፍቻ ባህላዊ መንገድ የተለያዩ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች በነዚሁ ታዋቂ ሽማግሌዎች ሲፈታ ቆይቷል::
አቶ አብድልናስር እንደሚሉት፤ ‹‹ቦበኒ›› በብሄረሰቡ ውስጥ ወይም ከአጎራባች ህዝቦች ጋር የሚከሰት የነፍስ መጥፋት ወንጀሎችን በሶስት ዋና ዋና ክፍሎች ይከፍላል:: እነሱም ‹‹ሙሉ ደም››፣ ‹‹መዳላ›› እና የ‹‹መዳላ መዳላ›› ይባላሉ::
በሁለት ደመኞች መካከል ታስቦ እና ታቅዶ ጭካኔ በተሞላበት ሁኔታ የሚፈጸም ከባድ የግድያ ወንጀል ሙሉ ደም ይባላል:: በድንገተኛ አጋጣሚ በሁለቱም ወገኖች መካከል በተፈጠረ እለታዊ ግጭት ምክንያት የሚፈጸም የግድያ ወንጀል ‹‹መዳላ›› ሲባል፣ የመጨረሻው እና ዝቅተኛ ደረጃ የተሰጠው የግድያ ወንጀል ደግሞ የ‹‹መዳላ መዳላ›› ይባላል:: የመዳላ መዳላ በሁለቱም ወገኖች ባልታሰበ አጋጣሚ የሚፈጸም የነፍስ ማጥፋት ወንጀልን ያጠቃልላል::
በማንኛውም ሁኔታ በብሄረሰቡ ውስጥ የነፍስ ማጥፋት ወንጀል ከተከሰተ ችግሩን የሚፈቱት ከሁለቱም ወገኖች ማለትም ከሟች እና ከገዳይ ወገኖች ጋር ዝምድና ወይም የደም ትስስር የሌላቸው የአገር ሽማግሌዎች መሆናቸውን የሚያብራሩት አቶ አብድልናስር፤ በአጥፊው ወገን ላይ የቅጣት ውሳኔ የሚተላለፈውም በባህላዊ ህግ ወይም ‹‹ ቦበኒ›› መሰረት መሆኑን ይናገራሉ::
ግጭቶች ወደ ከፋ ግጭት እንዳያመሩና ግጭቱንም ከምንጩ ለማድረቅ ችግሩ ከተፈጠረበት ሰዓት ጀምሮ የአገር ሽማግሌዎች ያለሰለሰ ጥረት ያደርጋሉ:: ወዲያው ድርጊቱ እንደተፈጸመ የአገር ሽማግሌዎች ወደ ሟች ወገን በመሄድ የሞተው ነፍስ ፈጣሪ ለጀነት ያድርገው፣ ለናንተም ፈጣሪ ጽናቱን ይስጣችሁ ብለው ካጽናኑ በኋላ ‹‹ደም ስጡን›› ጉዳዩን በሽምግልና እንድናየው ፍቀዱልን በማለት የተበዳይ ወገንን ይማጸናሉ::
እንደ አቶ አብዱልናስር ማብራሪያ፤ የአገር ሽማግሌዎቹ ተማጽኖና ልመና በሟች ወገን ተቀባይነት ካገኘ የገዳይ ቤተሰብ ‹‹እንጂጃታ ሹንሻ›› (የእንባ ማበሻ) ተብሎ የገዳይ ወገን ወይም ቤተሰብ ጉዳዩን በያዙት ሽማግሌዎች እጅ የተወሰነ ገንዘብ በማስያዣነት ያስቀምጣል:: ሽማግሌዎቹም ከተበዳይ ወገን ይሁንታን ካገኙበት ሰዓት ጀምሮ ለግድያ ያበቀውን የጸቡን መንስኤ ደከመን ሰለቸን ሳይሉ ቀን ከሌት መመርመር ይጀምራሉ::
የአገር ሽማግሌዎቹ የጸቡን መንስኤ ከመመርመር ጎን ለጎን ተጨማሪ ግጭቶች እንዳይከሰቱ የጥንቃቄ እርምጃዎችንም ይወስዳሉ የሚሉት አቶ አብድልናስር፤ ከሚወሰዱ እርምጃዎች መካከል የገዳይ የቅርብ ዘመዶች የሚኖሩበትን ቀዬ ለቀው እንዲሄዱ፤ የሟች ወገኖች በሚዘዋወሩባቸው አካባቢዎች እንዳይዘዋወሩና እንዳይገበያዩ በሽማግሌዎቹ አማካኝነት ጥብቅ ማስጠንቀቂያ ይሰጣል ሲሉ ያብራራሉ::
ማስጠንቀቂያ የሚሰጠው ለገዳይ ቤተሰብ ብቻ አይደለም:: ለሟች ቤተሰብም የሚሰጥ ማስጠንቀቂያ አለ:: የሟች ወገኖች ጉዳዩን ወደ መደበኛ ፍርድ ቤት እንዳይወስዱና ክስ እንዳይመሰርቱ ትዕዛዝ ይሰጣቸዋል:: ለገዳይ እና ለሟች ቤተሰብ በአገር ሽማግሌዎች የሚተላለፈው ትዕዛዝ ‹‹ከተራ›› ተብሎ ይጠራል:: የሽማግሌዎቹን ትዕዛዝ ተላልፎ የተገኘ ወገን በ‹‹ቦበኒ›› ስርዓት እንደሚቀጣ አቶ አብድልናስር ይናገራሉ::
ገዳይ በሽማግሌዎች ፊት ቀርቦ የእምነት ክህደት ቃሉን የሚሰጥበት የብሄረሰቡ የወንጀል ምርመራ ሂደት ‹‹ጉዳ›› ተብሎ ይጠራል፤ ገዳዩ በሽማግሌዎች ፊት ቀርቦ የእምነት ክህደት ቃሉን ከሰጠ በኋላ ቀዬያቸውን ጥለው እንዲሄዱ የተደረጉት ገዳይና የገዳይ የቅርብ ዘመዶች ወደ ቀዬያቸው እንዲመለሱ ይፈቀድላቸዋል::
አቶ አብድልናስር እንደሚሉት፤ በጉዳ ስርዓት ላይ ገዳይ ቢዋሽ ወይም የተሳሳተ መረጃ ቢሰጥ በርሱና በዘሩ ላይ ከባድ ችግር ይፈጠራል ተብሎ ስለሚታመን ገዳዩ ፈጽሞ አይዋሽም:: የተፈጸመውን ክስተትም ሳይዋሽ አንድ በአንድ ይናገራል:: ሽማግሌዎቹ ሁሉንም ነገር አጣርተው ከመረመሩ በኋላ ለወንጀሉ አፈጻጸም ደረጃ ይሰጡታል::
እንደ አቶ አብድልናስር ማብራሪያ፤ እንደ ወንጀሉ አይነትም የ‹‹ቦበኒ›› ህግን መሰረት በማድረግ ቅጣት ይሰጣል:: የተፈጸመው ወንጀል ከፍተኛ ወይም ሙሉ ደም ከሆነ በበ‹‹ቦበኒ›› ደንብ መሰረት ሙሉ ካሳ በገንዘብ ይከፈላል:: ገንዘብ ከሌለው ያለው ከብት ተገምቶ እንዲከፍል ይደረጋል:: ካሳ ከመክፈልና ከመቀበል ባሻገር ሁለቱም ወገኖች ዳግም ለጸብ እንዳይፈላለጉ ማሰሪያ ተበጅቶ የእርቁ ስነ ስርዓት ይጠናቀቃል:: የእርቁ ስነ ስርዓት ከተጠናቀቀ በኋላ ሁለቱ ወገኖች እንደ ጠላት አይተያዩም::
የቦበኔ ገልቲታ ባህላዊ የዳኝነት ስርዓት ለብሄረሰቡ ከፍ ያለ ጠቀሜታ እያስገኘ መሆኑ ይነገርለታል:: በተለይም ማህበራዊ ጠቃሜታው የላቀ ነው:: በብሄረሰቡ አባላት መካከልና ከአጎራባች ብሄረሰቦች ጋር ተባብሮ ተቻችሎ እንዲኖር ይረዳል:: አቅም ያለው አቅም የሌለውን እንዳይጎዳ፣ ሀብታም ድሃውን እንዳይበድል፣ ጉልበተኛው አቅመ ደካማውን እንዳይጎዳው፣ ባለብዙ ዘመድ ዘመድ አልባውን እንዳይበድል፣ ሌሎችም ማህበራዊ ግንኙነትን የሚያሻክሩ ችግሮች እንዳይፈጠሩ በማድረግ እገዛው የላቀ ነው::
መሰል ችግሮች ቢፈጠሩ ሳይባባሱ በአጭሩ እንዲቀጩ በማድረግ በብሄረሰቡ መካከል እና ከአጎራባች ህዝቦች ጋር ማህበራዊ ትስስር እንዲጠናከር ከፍተኛ አስተዋጽኦ ሲያበርክት መቆየቱን ‹‹ቦበኔ ገልቲታ›› በተሰኘው የቀቤና ብሄረሰብ ባህላዊ መተዳደሪያ ደንብ ላይ ሰፍሮ ይገኛል::
የቀቤና ብሔረሰብ ሽማግሌዎች ግጭቶችን በባህላዊ መንገድ በመፍታት ዘመናትን የተሻገረ ስርአት አላቸው
መላኩ ኤሮሴ
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 27/2015