የትምህርት ተደራሽነትና ጥራት – በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል

እንደ ሀገር የትምህርት ተደራሽነትና ጥራትን ለማረጋገጥ በመንግሥት በኩል በርካታ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑ ይታወቃል። እነዚህ ተግባራት እውን ለማድረግ ግን ከበጀት ማነስ ባለፈ በተለያዩ ጊዜያት የሚከሰቱ ግጭቶች ተጨማሪ ፈተና ሆነው ቆይተዋል። የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የዚህ ችግር ተቋዳሽ ከሆኑት አካባቢዎች አንዱ ነው። ከዓመታት በፊት በክልሉ ተከስቶ የነበረው ግጭት በርካታ ትምህርት ቤቶችን ለውድመት የዳረገ ሲሆን፣ ጥቂት ለማይባል ጊዜ ተማሪዎችም ከትምህርት ገበታቸው ተፈናቅለው እንዲቆዩ ተገደዋል። ያለፉት ዓመታት ግን በክልሉ ያለው ሰላም እየተጠናከረ በመምጣቱ የመማር ማስተማር ሂደቱ ወደ ነበረበት እየተመለሰ ይገኛል።

ለመሆኑ በክልሉ ያለው አጠቃላይ የትምህርት ዘርፍ እንቅስቃሴ ምን ይመስላል ስንል የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ተመስገን ዲሳሳ (ዶ/ር) አነጋግረናቸዋል። እርሳቸው እንደሚያብራሩት ከሆነ፤ በበጀት ዓመቱ የተማሪ ተሳትፎን በተመለከተ 294ሺ426 ተማሪዎችን በትምህርት ገበታ ላይ ማሳተፍ የተቻለበት ነው፡፡ ይህ ደግሞ የእቅዱን 94 በመቶ ማሳካት አስችሏል። መቶ በመቶ ተማሪዎች በትምህርት ገበታ ላይ እንዲገኙ ለማድረግ ያልተቻለው ከዓመታት በፊት በክልሉ ተከስቶ በነበረው ችግር የተነሳ ሲሆን፣ ይህም 17 የሚደርሱ ትምህርት ቤቶች እስካሁን አገልግሎት እንዳይጀምሩ የሆኑበት ነው። በተለይ በጠረፍ አካባቢ የሚገኙ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የዚህ ችግር ሰለባ ናቸው። ስለሆነም በተወሰነ ደረጃ በዚህ አካባቢ የሚገኙ ተማሪዎችን በአቅራቢያ ወደሚገኙ የትምህርት ተቋማት ሄደው እንዲማሩ እየተሠራ ይገኛል።

የትምህርት ጥራትንም በተመለከተ ክልሉ በ2017 የትምህርት ዘመን ወደ ሥራ የተገባው በከፍተኛ ደረጃ የሕዝብ ንቅናቄ በማካሄድ ነበር። የትምህርት ጥራትን ለማረጋጋጥ በቅድሚያ በቁጥርም ሆነ በጥራት በቂ የሆነ መምህር እንዲኖር ይጠበቃል። በዚህ ረገድ በአሁኑ ወቅት በክልሉ ሰባት ሺህ 317 የአንደኛና መካከለኛ ደረጃ ሁለት ሺህ 206 የከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ መምህራን፤ እንዲሁም 512 የአንደኛና መካከለኛ ደረጃ፤ 91 የከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ርዕሳነ መምህራንና 124 የክላስተር ሱፐር ቫይዘሮች አሉ። ይህ በቁጥር ደረጃ በቂ የሚባል ነው። ነገር ግን እነዚህ መምህራን፤ ርእሳነ መምህራንና ሱፐር ቫይዘሮች ለተመደቡበት የሥራ መጠን የሚመጥን የትምህርት ዝግጅት ያላቸው ቢሆንም በብቃት ረገድ ክፍተት እንዳለባቸው ተለይቷል ብለዋልም።

ክፍተቶቹን ለመሙላት በማሰብ እየተሠራ ሲሆን፣ በዚህ ዓመት ብቻ በትምህርት ሚኒስቴር አስተባባሪነት 136 ርእሳነ መምህራን 668 መምህራን በየሚያስተምሩት የትምህርት አይነቶች ለ15 ቀን በአሶሳ ዩኒቨርሲቲ ልዩ ስልጠና ተሰጥቷቸዋል። ይህ በክልሉ አቅም በተለያዩ ደረጃዎች ሲሰጡ ከነበሩ ስልጠናዎች በተጨማሪ ሲሆን፣ ከዚህም በኋላ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አስረድተዋል። ከመማሪያ ክፍሎች ምቹነት አንጻርም ባለፉት ዓመታት በክልሉ በነበሩት ግጭቶች ምክንያት በርካታ ትምህርት ቤቶች ሙሉ ለሙሉ የወደሙ ሲሆን፣ ጥቂት የማይባሉም በከፊል የንብረት ውድመት አጋጥሟቸዋልና እነዚህን ትምህርት ቤቶች የሚጠግነውን ጠግኖ፤ የሚገነባውን ገንብቶ ለአገልግሎት ማዋል ተችሏል። ለዚህ ደግሞ በወቅቱ የነበሩት አመራሮችና የሕብረተሰብ ተሳትፎ ትልቅ አስተዋዕጾ ነበረው። በዚህም በተደረገው ከፍተኛ ርብርብ ዛሬ ላይ ሁሉም ሊባል በሚያስችል ደረጃ በቋሚነትና በግዚያዊነት አገልግሎት እንዲሰጡ ሆነዋል። በጊዜያዊነት አገልግሎት እንዲሰጡ እየተደረጉ ያሉትም በቀጣይ በሚጠበቀው ደረጃ እድሳትና ግንባታ ተካሂዶላቸው በሙሉ አቅማቸው ለአገልግሎት አንዲበቁ ይደረጋል።

ከትምህርት ቤት ሕንጻ ግንባታ ባለፈ ለመማር ማስተማር የሚረዱ የወደሙና የጠፉ ቁሳቁሶችን ማሟላትም የክልሉ ሌላው ፈተና እንደነበር የሚያነሱት ኃላፊው፣ የክልሉ ከፍተኛ ባለስልጣናት በልዩ ትኩረት እየሠሩ ቢሆንም ከሚጠበቀው አኳያ ብዙ የሚቀሩ ነገሮች ስለመኖራቸው ያነሳሉ። የቁሳቁስ ማሟላት ሥራ ሲባል ከተለመዱት ግብአቶች ባለፈ ዘመኑ የኢንፎርሜሽንና ቴክኖሎጂ በመሆኑ በዚያ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን ማብቃት ይጠበቃል። ቢያንስ እያንዳንዱ ተማሪ ሌሎቹን የትምህርት አይነቶች የሚከተታልበት የቴክኖሎጂ አቅም መፍጠር ባይቻል የአይ ቲ ትምህርት በተግባር የሚማርበት እና የኦን ላይን ትምህርት መከታተያ ቴክኖሎጂዎች ያስፈልጋቸዋል። እናም ከአይቲ መሰረተ ልማት ግንባታ ጀምሮ እንደ ክልል አሁንም ቢሆን ሰፊ ከፍተቶች እንዳሉም አብራርተዋል።

ከኮምፒውተር አቅርቦት ባለፈ የአይ ቲ እና የኤሌክትሪክ ኃይል መሰረተ ልማት በማይደርስባቸው አካባቢዎች የሶላር ኃይል ማመንጫ በመጠቀም ተማሪዎች ከሌሎች እኩል በቴክኖሎጂ የታገዘ ትምህርት እንዲያገኙ እየተሠራ ይገኛል። ይህ ግን ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቅ በመሆኑና በክልሉ አቅም ብቻ ተደራሽ ማድረግ ስለማይቻል ከአጋር አካላት ጋር የሚደረገው ትብብር ቅድሚያ ተሰጥቶታል። በዚህ አካሄድ በተሠራው ሥራም በዚህ ዓመት ብቻ 22 ትምህርት ቤቶች ከ15 እስከ 35 ዴስክ ቶፕ ኮምፒውተሮችን እንዲያገኙ ተደርጓል። ከዚህ ውስጥ ሁለቱ ትምህርት ቤቶች በቀዳማዊት እመቤት ወይዘሮ ዝናሽ ታያቸው ድጋፍ፤ 14 ትምህርት ቤቶች በመልሶ ማቋቋም ሲሆን፣ ቀሪዎቹ ሰባት ትምህርት ቤቶች ‹‹ኩሶ›› በሚባል ዓለም አቀፍ የበጎ አድራጎት ድርጅት ተጠቃሚ መሆን እንደቻሉም አመላክተዋል።

ተመስገን (ዶ/ር) እንደሚናገሩት፣ ከግብአት አኳያ ሌላው መሰረታዊ ነገር የመማሪያ መጻህፍቶች አቅርቦት ነው። በዚህ ረገድም መምህሩ የሚመራበትን የመማሪያ መጽሀፍ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ ለማሳተም ከባለፈው ዓመት ጀምሮ እንደ ክልል ዝግጅት እየተደረገ ይገኛል። በተጨማሪም በዚህ ዓመት ትምህርት ሚኒስቴር 234 ሺህ የከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መጽሀፍት ልኮልናል። በዚህም ከዘጠነኛ እስከ 12ኛ ክፍል ያለው ተማሪ ከሁለት የትምህርት አይነቶች ውጪ አንድ ለአንድ መጽሀፍ ሊደርሰው ችሏል። የሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ለሚወስዱ ተማሪዎች ሙሉ ለሙሉ ማዳረስ ተችሏል። በቀጣዩ በጀት ዓመት ያለውን ችግር ሙሉ ለሙሉ ለመቅረፍ የምንሠራ ይሆናል።

የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ ከትምህርት ቤቶችና ከትምህርት ቢሮ ብዙ የሚጠበቅ ቢሆንም በአንጻሩ የበርካታ ባለድርሻ አካላትንም ተሳትፎ ያስፈልጋል። ጥራቱን የጠበቀ ትምህርት ተደራሽ ለማድረግና ብቁ ተማሪዎች ለማውጣት በቀዳሚነት የግብአት እና ለደረጃው ብቁ የሆነ መምህር መኖርንም ይጠይቃል። በመሆኑም በዚህ ዓመት የተማሪዎችን ውጤትና ሥነ ምግባር ለማሻሻል የንቅናቄ ሥራዎች እየተሠሩ ናቸው። ከዚህም ውስጥ በሀገር አቀፍ ደረጃ እየተተገበረ ያለውም አጠቃላይ ፈተና ለሚቀመጡ ተማሪዎች የማጠናከሪያ ትምህርት መስጠት እየተተገበረ ሲሆን፣ በዚህ እድል በርካታ ተማሪዎች እየተጠቀሙ ይገኛል። ይህንን የማጠናከሪያ ትምህርት ለመስጠትም በብቃታቸው የተመሰከረላቸው መምህራን ተለይተው እያስተማሩ ነው። የትምህርት ጥራት ማስጠበቅ በየወቅቱ እየተስተካካለና እያደገ መምጣት ያለበት አንደመሆኑ መጠን ብዙ የሚቀሩ ሥራዎች ስለመኖራቸውም ተመስገን (ዶ/ር) ተናግረዋል።

የትምህርት ዋነኛ ዓላማ ልጆችን በእውቀት ማበልጸግና ማብቃት ብቻ ሳይሆን በሥነ ምግባርም የታነጹ ሆነው ሀገር ተረካቢ ትውልድ እንዲሆኑ ማድረግም ነው። ተማሪዎች አጠቃላይ የሀገራቸውን ሁኔታ እና ማኅበረሰባቸውንም እየተገነዘቡ እንዲያድጉ ያስፈልጋል። ለዚህ ደግሞ ከትምህርት ተቋማትም የሚጠበቅ ኃላፊነት አለ። ስለዚህም ክልሉም ለመደበኛ ትምህርት ከሚሰጠው ትኩረት ባልተናነሰ ለተማሪዎች ሥነምግባር መስተካካልም ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ይገኛል። ተማሪዎች መምህራኖቻቸውንና ታላላቆቻቸውን እንዲያከብሩ የትምህርት ሰዓት እንዲያከብሩ ትምህርታቸውን በአግባቡ እንዲከታተሉ ለማድረግ እቅድ ተዘጋጅቶ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመጣመር እየተሠራም ነው።

ተማሪዎች የተስተካከለ እና በማኅበረሰቡ ዘንድ ቅቡልነት ያለው ሥነ ምግባር እንዲኖራቸው የመምህራን ሥነምግባርም መስተካካል አለበት። ተማሪዎች ልጆች ከሚነገራቸውና አድርጉ ተብለው ከሚታዘዙት በላይ ታላላቆቻቸውና መምህራኑ በተግባር የሚያሳዩዋቸውን የመተግበርና የመሆን እድላቸው ሰፊ ነው። በዚህ መነሻነትም የክልሉ ትምህርት ቢሮ የመምህራን እና የርእሳነ መምህራን ሥነምግባር፣ አርአያ እንዲሆኑ ለማድረግ፣ ቤተሰብ በቤት ውስጥ ማኅበረሰቡም ተማሪዎች በሚንቀሳቀሱባቸው ቦታዎች በጎ ተጽእኖ እንዲያሳድሩባቸው በንቅናቄ ሲሠራ ቆይቷል። በተጨማሪም እንደ ሀገር በሥርዓተ ትምህርት ወስጥ የተካተተ ግብረ ገብ ትምህርት ተማሪዎች በትምህርት ቤት እያሉና ትምህርታቸውን ጨርሰው ከወጡ በኋላ በማኅበረሰቡ ውስጥ ምን ሚና ይኖራቸዋል የሚለው ይሰራበታል። በተጨማሪ በተማሪዎች መማክርት ክበባት በመተግበር የሥነ ምግባር ጉድለት የታየባቸውን ተማሪዎች ለማስተካከል እየተሠራ ነው።

ተመስገን (ዶ/ር) ስለትምህርት ውጤታማነትም እንዲህ ይላሉ። እንዳጠቃለይ የሴቶችና የልዩ ፍላጎት ተማሪዎች ተሳትፎ ማጠናከርና መጠነ ማቋረጥ እንዲሁም ክፍል መድገምን መቀነስ የትምህርት ዘርፉ ትልቁ ሥራ ነው። ከዚህ አንጻር አሁን ያለው አሀዝ የሴቶች ተሳትፎ ከወንዶች እኩል እየሆነ ነው። ነገር ግን እንደ ትምህርት ቢሮ ዋናው የሚፈለገው ትምህርት ቤት መምጣታቸው ብቻ ሳይሆን በተሳትፎ ሁሉም እኩል ብቁ ተወዳዳሪ ሆኖ መገኘቱ ነው። ይህንን ለማሳካት ደግሞ ሰባት በሚደርሱ ትምህርት ቤቶች ፕሮጀከት ተዘጋጅቶ እየተተገበረ ይገኛል። ለዚህም ‹‹ኮንሶ›› የሚባለው ዓለም አቀፍ ድርጅት ብዙ ድጋፎችን እያደረገ ይገኛል። በተለይም ሴቶችን በሚመለከት የተለየ የማጠናከሪያ ትምህርትና ሌሎች ድጋፎች እያደረገላቸው ነው። ድጋፎቹ በዩኒሴፍ ከሚቀርበው የንጽህና መጠበቂያ ጀምሮ ሌሎች ቁሳቁሶች ከማሟላትና ማበረታቻ መስጠት ባለፈ ቤተሰብንም የሚያካትት ነው።

በ‹‹ፋሮ ፋውንዴሽን›› የተቋቋመ 44 ሴቶችን ብቻ የሚያስተምር አዳሪ ትምህርት ቤትም አለ። ይህ ትምህርት ቤት ባለፈው ዓመት ያስፈተናቸው የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች በሙሉ አልፈዋል። ይህም ሆኖ እንደ ክልል የሴቶችን ተሳትፎ ከማረጋገጥ አኳያ በቂ ባለመሆኑ እነዚህ ድጋፎች ተጠናክረው ቢቀጥሉ መልካም እንደሆነ አስረድተዋል። በመጠነ ማቋረጥንም በተመለከተ ሴቶች እድሜያቸው ከፍ እያለ ስሄድ ከትምህርት ገበታ የመቅረት ነገር ይታያል። ወንዶችም ቢሆኑ 15 እና 16 ዓመት አካባቢ ሲሆናቸው ወደ እርሻና የወርቅ ቁፋሮ የሚሄዱበት አጋጣሚ አለ። ለትምህርት የደረሱ ትንንሽ ልጆችም ወላጆቻቸው ወደ ወርቅ ቁፋሮ ሲሄዱ ይዘዋቸው ስለሚሄዱ ከትምህርት ይስተጓጎሉ። ማኅበረሰቡ ራሱ በየአካባቢው ባለው መተዳደሪያ ደንብ እንዲቀጣ ሕግ አውጥቷል። ስምምነታቸው የትኛውም ወላጅ ለእርሻ ሥራም ሆነ ለወርቅ ቁፋሮ በሚንቀሳቀስበት ወቅት ልጁን ከትምህርት ገበታው እንዳይለይ አድርጎ መሆን ይጠበቅበታል ይላልም። በዚህም ብዙ መሻሻሎች መምጣታቸውን አስረድተዋል።

መጠነ መድገም ግን ከሌላው ችግር ባለፈ ከትምህርት አሰጣጥ ጥራትና ከመምህራን ጋር የሚያያዝ በመሆኑ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሠራ ስለመሆኑ የሚያነሱት ኃላፊው፣ በተለይም ከ12ኛ፣ ከስምተኛና ስድስተኛ ክፍል ጋር በተያያዘ የሚሰጠውን የማጠናከሪያ ትምህርት ከሌሎቹ የተለየ እንዲሆን በማድረግ ዙሪያ እየተሠራ እንደሆነም አጫውተውናል። አክለውም የተሻሉ መምህራንና ተማሪዎች ድጋፍ የሚየደርጉበትን መንገድ ዘላቂ ለማድረግም ከሌሎች ክልሎች የልምድ ተሞክሮ እየተወሰደ እየተሠራ ስለመሆኑም አብራርተዋል።

ሌላው ተመስገን (ዶ/ር) ያነሱት ጉዳይ ለመማር ማስተማር ሂደት የማኅበረሰብ ሚናን ነው። እንደእርሳቸው አገላለጽ፣ በቤኒ ሻንጉል ጉሙዝ ክልል እንደ ማኅበረሰብ ለትምህርት ቤት መስፋፋት ሰፊ ፍላጎት አለ። በየቦታው ትምህርት ቤት እንዲገነባ ብቻ ሳይሆን በሌሎች አካባቢ ባሉ ትምህርት ቤቶች ያዩዋቸውን ነገሮች ጥሩ መምህራን ከመምረጥ ጀምሮ ለእነሱም እንዲሟሉ ይጠይቃሉ። ይህ ከአንድ ለውጥ ከሚፈልግ ማኅበረሰብ የሚጠበቅ ነው። ትምህርት ቤቶች ሲመሰረቱም ማኅበረሰቡ እንደ ራሱ ሀብት ንብረት እየተንከባከባቸው ይገኛል። ባለፉት ዘጠኝ ወራት ብቻ በጸጥታ ምክንያት የፈረሱ ትምህርት ቤቶችን ለመጠገንና ተጨማሪ ክፍል ለመገንባት ማኅበረሰቡ ከ67 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት ድጋፍ አድርጓል። ይህ ካበለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጻር በ11 በመቶ ብልጫ አለው። የዛሬ 30 ዓመት በክልሉ የነበሩትን 189 አንደኛና መካከለኛ ትምህርት ቤቶች ዛሬ ላይ 625 ማድረስ ተችሏል። ሁለት ብቻ የነበሩትን ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችንም ዛሬ ላይ 94 ማድረስ የተቻለበት ሁኔታ ተፈጥሯል። እንዳጠቃላይ ሲታይ የትምህርት ተደራሽነትን በተመለከተ ክልሉ አበረታች ውጤት ማስመዝገብ ችሏል።

ራስወርቅ ሙሉጌታ

አዲስ ዘመን ሰኞ ሰኔ 9 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You