ነገረ መሐንዲሶቹ

እኤአ በ1919 ከማሳቹሴትስ የቴክኖሎጂ ተቋም (ኤምቲ) ስትመረቅ በዩናይትድ ስቴትስ የመጀመሪያዋ ሴት የኤሌክትሪክ መሐንዲስ ነች። የኤሌክትሪክ ምሕንድስና ችግሮችን በብዙ መልኩ መፍትሔ እንዲቸራቸው ያደረገች እውቅ መሐንዲስ ነች። ዛሬ ድረስ በኤሌክትሪካል ኢንጂነሪንግ ዘርፍ ያበረከተችው አስተዋፅኦ ዘላቂ ተጽእኖ ያሳደረ እና በSTEM ውስጥ ለሚኖሩ ሴቶች አርአያና ማርሽ ቀያሪም እንደሆነች ይነገርላታል ኤዲት ክላርክ።

በ1985 በካምብሪጅ ዩኒቨርሲቲ የምሕንድስና ዲፓርትመንት መምህር ሆና የተሾመች የመጀመሪያዋ ሴት ዶክተር ሂልዳ ሃልካርድ-ሃርላንድ ሌላዋ አበረታች ሴት መሐንዲስ ነች። አስደናቂ ምርምሮችን በማድረግ ትታወቃለች። ባዮ ሜዲካል ምሕንድስና እንዲለወጥ እና አዳዲስ በዘርፉ ፈጠራዎችን በመሥራትም ዘርፉ ተወዳጅ እንዲሆን አድርጋለች። ከሁሉም በላይ ደግሞ በአርቴፊሻል መገጣጠሚያዎች እና ሌሎች የሕክምና ተከላዎች ውስጥ ለመጠቀም የሚያስችሉ ቁሳቁሶችን በመሥራት ዓለም የተደነቀባት ሴት ነች።

እነዚህን ሴቶች ስንጠቅስ ያለ ምክንያት አይደለም። ትናንትም ሆነ ዛሬ ፈተናዎች ቢደራረቡባቸውም ሥራው የወንዶች ብቻ ተደርጎ ቢታሰብም በመከራ ውስጥ ነጥረውና ልቀው የሚወጡ ሴቶች እንዳሉ ለመጥቀስ ነው። ግን እንዲህ ዓይነቶቹ መሐንዲሶች ምን ያህል ቦታ ይይዛሉ፤ ምን ያህል ትኩረት ይሰጣቸዋል ስንል ልዩነቱ ገዝፎ እናየዋለን። በተለይም እንደ እኛ በማደግ ላይ ያሉ ሀገራት ውስጥ በብዙ ገዝፈው ይታያሉ። ማነቆዎቻቸውም ቀላል የማይባሉ እንደሆኑ በተለያየ ጊዜ የሚወጡ መረጃዎች ያመላክታሉ።

በእኛ ሀገር ነባራዊ ሁኔታ ሥራ ከአቅም፣ ከባሕልና መሰል ነገሮች አንጻር ተለይቶ ይታያል። ወጥቶ መሥራትም ለወንድ እንጂ ለሴት ሲበረታታ አይታይም። ዛሬ ዛሬ ነገሮች እየተቀየሩ መጡ እንጂ ቀደም ባሉት ጊዜያት አይደለም ምሕንድስና ዘርፉን እንዲቀላቀሉ ወጥተው ቀለል ያሉ የሚባሉ ሥራዎችን እንዲያከናውኑ እንኳን አይፈቀድላቸውም። ፈቃድ ደግሞ በቃል ብቻ ሳይሆን በአባባል ጭምር የተደገፈ ነው። ሴት ወደማጀት ወንድ ወደ ችሎት ይባል የለ። እናም ፍርዱም ውሳኔውም የወንዱ ብቻ በሆነበት ዓለም ውስጥ የምሕንድስና ዘርፉን ሴቶች እንዲቀላቀሉት አይታሰብም።

በትምህርት ደረጃ እና በክህሎት የተሻለች እንኳን ብትሆን የሚሰጣት ቦታ ሁሌ ከወንዶች በታች ያደርጋታል። ይህ ደግሞ የሴቶች የኮንስትራክሽን ዘርፍ ተሳትፎ በ2021 በተጠናው ጥናት በዓለም ደረጃ እስከ 15 በመቶ ብቻ ነው፣ በሀገራችን ሲታይ ደግሞ የኮሊዶር ልማቱን ጨምሮ በመደበኛው ሥራ ተሳታፊ የሆኑ ሴቶች ዘጠኝ በመቶ ብቻ ናቸው። ከሰሞኑ በሀገር ደረጃ ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን አዘጋጅነት “እርሷ ኢትዮጵያን ትገነባለች” በሚል መሪ ሃሳብ ይህንን በስፋት የሚያትት መድረክ ተዘጋጅቷልና ከተወያዮች አንደበትና ከጥናቱ ጋር በማዋቀር ለዛሬው የሴቶች አምዳችን ልናስነብባችሁ ወደናል።

ጥናቶቹ እንደሚያስረዱት፤ ይህ ዘርፍ በአስተው ሎትና በትዕግስት ከመሥራት አኳያ ከወንዶች ይልቅ የተሻለ ውጤታማ ሊሆኑበት የሚችሉት ሴቶች በስፋት ሲሳተፉበት ነው። ለእዚህ ደግሞ በዘርፉ ተሠማርተው ተቋማትን የመሩና የለወጡ ሴት መሐንዲሶች ምስክሮች ናቸው።

ውይይቱን በይፋ ያስጀመሩት የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ቤዛዊት ግርማ(ዶ/ር) በወቅቱ እንደገለጹት፤ ሴቶች በተለያዩ የግንባታ ፕሮጀክቶችና መሠረተ ልማት ዝርጋታ ሥራዎች ጉልህ ሚና እየተወጡ ይገኛሉ። በተለይም በአሁኑ ወቅት ዘርፉ በቴክኖሎጂ እያደገ በመምጣቱ በዓለም ላይ ባለው የልማት ጉዞ ላይ ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ነው። በኢትዮጵያም ቢሆን እየታዩ ያሉ ውጤታማ ተግባራት አሉ። ተሳታፊነታቸው በቂ ነው ባይባልም በኮሊዶር ልማቱ የተነሳ ጥሩ መሻሻሎች እየታዩበት ይገኛል። በእዚያው ልክ ግን ብዙ መሥራት የሚጠበቁብን ነገሮች አሉ።

ሴቶች በግንባታ ዘርፍ ያለውን እድልና ቴክኖሎጂ በመጠቀም እውቀታቸውንና ክህሎታቸውን በማዳበር ወደ ዘርፉ በስፋት እንዲገቡ በማድረጉ ዙሪያ ከማህበረሰቡ እስከ መንግሥት ድረስ ያላሰለሰ ጥረት ማድረግ ይጠይቃል። ሴቶችን በዘርፉ እድል ስንሰጣቸው ሀገር ስኬታማነቷን እንድታፋጥን ትሆናለች፤ ለውጦች በአጭር ጊዜ እንዲታዩ ይሆናሉ፤ አዳዲስ የሥራ አማራጮች ይሰፋሉ። ሴቶች በምሕንድስናው ኢንዱስትሪ ላይ ገቡ ማለት 51 በመቶ የሚሆነው ሕዝብ ሥራ የማግኘትና ራሱን በራሱ የማስተዳደር እድልን እንዳገኘ የሚወሰድም ነው። በተለይ ደግሞ በኮንስትራክሽኑ ዘርፍ ላይ መግባት ሲችሉ ሀገር ብዙ ምቹ የሆኑ የኢኮኖሚ አማራጮችን እንድታገኝ ያደርጋታል ሲሉ ያብራራሉ።

ኮርፖሬሽኑ ሴቶችን በአመራሩ ዘርፍ ብቻ የማብቃት ሥራው ላይ ከአራት በመቶ ወደ 20 ከፍ ቢያደርግም ይህ በቂ አይደለም ብሎ እንዲሠራ የሚያስችለው እንደሆነ የጠቆሙት ኃላፊዋ፤ በኮንስትራክሽኑ ዘርፍ እንዲህ ዓይነት መድረኮች መዘጋጀታቸው ሌሎች ተቋማትም በዘርፉ ላይ ትኩረት ሰጥተው እንዲሠሩ ያደርጋቸዋል። በመድረኩ ባለሙያዎችን፣ ፖሊሲ አውጪዎችን፣ ኃላፊዎችንና መሰል የሚመለከታቸው አካላት የተሳተፉ በመሆኑም እንደ ሀገር ሥር ነቀል ለውጥ ለማምጣት ወሳኝነት አለው። ከሁሉም በላይ ደግሞ ሁሉም የሚመለከተውን ጉዳይ ይዞ እንዲሄድ፤ በጥናቱ የተመላከተውን ችግር ለይቶ እንዲሠራበትና ልማቱን በስፋት የሚመለከተው ማነው የሚለውን እንዲለይ ያስችለዋልም ብለዋል።

የሴቶች አመለካከቶች ለኢንጂነሪንግ ፕሮጀክቶች እና እድገቶች ልዩና ምስጢራዊ ጥበብን የሚያላብስ ነው፤ መልከ ብዙ አስተውሎት ያላቸው ስለመሆናቸው ያነሱት ደግሞ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በመንግሥት ልማት ድርጅቶች ውስጥ ቋሚ ኮሚቴ አባልና የሴቶች ኮከስ ውስጥ ፈንድ አፈላላጊ ሰብሳቢ እንዲሁም የተለያዩ ኮንፈረንሶች ላይ የምርምር አዘጋጅ ኮሚቴና ጥናት አቅራቢዋ ወይዘሮ ደጅይጥኑ አለነ ናቸው።

እርሳቸው እንደሚሉት፤ ዘርፉ እንደ ሀገር በርካታ የሰው ኃይልን የሚያቅፍ ነው፣ ትልቁን የኢኮኖሚ ድርሻ ይዞ የሚያንቀሳቅስም ነው። በእዚህም ትኩረትን፣ ጥበብንና ነገን አልሞ መሥራትን ይጠይቃል። እነዚህ ተግባራቶቹ ደግሞ ለሴቶች በተፈጥሮ የተቸሯቸው ናቸው። ሆኖም ዘርፉ እነርሱን ያገለለ በመሆኑ በርካታ ችግሮች ሲገጥሙት ይስተዋላል። በእኛ ሀገር ነባራዊ ሁኔታ ብቻ ብናነሳ በእዚህ ዘርፍ ውስጥ ለመግባት ሴቶች ከባሕል እስከ ማህበራዊ ኃላፊነት፤ ከፖሊሲ እስከ ኃላፊዎች ጫና እና ጾታዊ ጥቃት ከፍተኛ ጫና ይደርስባቸዋል።

በማንኛውም ዘርፍ ሀገር ለውጥ ማምጣት የምት ችለው ሁሉንም የማህበረሰብ ክፍሎች በእኩል ስታሳትፍ ነው። በተለይ ሴቶች ደግሞ ከሚሸፍኑት ቁጥር አንጻር በእውቀታቸውና ባላቸው የተፈጥሮ ሀብት እንዲሠሩ ማድረግ የውዴታ ግዴታ መሆን ይጠበቅበታል። ገበያው ላይ ጭምር እያሉ እድሉን አለመስጠት ግን ዋጋ ያስከፍላል። ምክንያቱም ዘርፉ በሴቶች ከመመራትና ከመሠራቱ አንጻር የመጡ ለውጦች በርካታ መሆናቸውን በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኮሊዶር ልማት ብቻ ማየት ይቻላል።

የሴቶች እይታ ፕሮጀክቶችን ከመንደፍ ጀምሮ እንደ ሀገር ብቻ ሳይሆን እንደ ዓለምም ከፍተኛ እድገት የሚያመጣ ነው። ሆኖም ልዩ የሆኑና የተዛቡ አመለካከቶች ይህንን እድል ዘግተውታል። በተጨማሪም ለሴቶች ሁሉን አቀፍ ድጋፍ አለመደረጉም ሴቶች በዘርፉ ላይ ገብተው እንዳይሳተፉ እንቅፋት ሆኖባቸዋል። ከሁሉም በላይ ደግሞ በማህበረሰቡ ዘንድ ያለው የተዛባ አመለካከት ከትምህርት ምርጫቸው ጀምሮ ዘርፉን እንዳይቀላቀሉ ገድቧቸዋል። ስለሆነም ምቹ አካባቢን መፍጠር፣ የሥርዓተ-ፆታ እኩልነትን ማሳደግና ማህበራዊ ጫናዎቻቸውን መቀነስ እንዲሁም በተዛቡት ባሕሎች ዙሪያ ግንዛቤ መፍጠር ለተሳትፏቸው መጨመር ወሳኝነት እንዳለው አስረድተዋል።

በኮንስትራክሽኑ ዘርፍ ውስጥ ሴቶችን በብዛት ማሳተፍ ማለት ሀገርን በዘርፉ የተሻለ እድል እንድታገኝ ማስቻል ነው። ምክንያቱም ከ50 በመቶ በላይ የሚሆነውን ሕዝብ ስንይዝ ሀገርን ከመያዝ አይተናነስም። በእዚያ ላይ የኅብረተሰብ ፍላጎቶችን በሚገባ የመረዳቱ አቅም ከወንዶች ይልቅ ሴቶች የሚያዩት ጉዳይ ነውና ችግሩን ለመፍታት ቅርብ የሆነውን ሰው እናገኝበታለንም ይላሉ።

በእዚህ ዘርፍ ውስጥ በአንድ እጅ ማጨብጨብ ብሎ ነገር የለም። የመደመር ባሕል መፍጠር የግድ አስፈላጊ ነው። ከእዚህ አንጻር ሴቶች በተግባራቸው ውስጥ ከፍ ያለ ግምት እንዲሰጣቸው ማድረግ ይገባል። ፖሊሲዎችን በማሻሻል የሥራ እድሎችን መፍጠር፣ ማበረታታት እና በሥራ ቦታ የሚደርስባቸውን አድልዎ እና ትንኮሳ ለመፍታት ግልጽ መንገዶችን ማመቻቸት፤ እንዲሁም እነዚህን አሠራሮች በመተግበር የሚደግፍ፣ የሚቀበል እና የሚደግፍ አካባቢ መፍጠር ያስፈልጋልም ባይ ናቸው።

በሀገሪቱ እየተከናወኑ በሚገኙ የኮሪዶር ልማት የሴቶች ተሳትፎ የተሻለ በመሆኑ ይህም ለሌሎች ዘርፎች ተሞክሮ የሚሆን ነው። ከእዚህ አንጻርም ወደፊት በምሕንድስና የሴቶች አመለካከት በእጅጉ እየተለወጠ እንደሚመጣ እምነት እንዳላቸውም አስረድተዋል።

ኅብረተሰቡ ወደ ላቀ የፆታ እኩልነት ሲሸጋገር የሴቶችን አመለካከቶች በዘርፉ ውስጥ የማካተት ፋይዳው እየጨመረ ይሄዳል። በኢንጂነሪንግ ዲዛይን እና ችግር መፍታት ላይ የተለያዩ አመለካከቶችን መቀበል በሌላ መልኩ ወደማይቻሉ እድገቶች እና ፈጠራዎች ሊመራ ይችላል። ይህም ሴቶችን ለኢንጂነሪንግ ቡድኖች በዋጋ ሊተመን የማይችል አስተዋጽኦ ያላቸው ያደርጋቸዋል ስትል የጠቀሰችው ደግሞ ሌላኛዋ ጥናት አቅራቢ አርክቴክት ቦንቱ በቃና ነች።

እርሷ እንደምታነሳው፤ ሴቶች በገቡበት የሥራ ዘርፍ ሁሉ ልዩ ችሎታዎች እና ልምዶችን በቀላሉ ያዳብራሉ። ችግር ፈቺ አካሄዶቻቸውም በአዲስ እይታ የተቃኙ ናቸው። ነገር ግን ቴክኖሎጂውን ለመቀላቀል በብዙ መልኩ ፍራቻ ያድርባቸዋል። ቴክኖሎጂውን ተጠቅመው የፈለጉትን ነገር ለማድረግም በርካታ ፈተናዎች ይገጥሟቸዋል። አንዱና ዋነኛው የትምህርት እድል አለማግኘታቸውና የባሕል ጫናው ነው። እነዚህን አልፈው ዘርፉን የሚቀላቀሉበት እድል ካገኙ ግን ብዙ ችግሮችን እንደ ሀገር መፍታት ይችላሉ። ለአብነት ቀደም ሲል ችላ የተባሉ የማህበረሰብ ችግሮችን ለመፍታት ከእነርሱ በላይ ቅርብ የለም። በዲዛይን ሥራ ውስጥም አስተውሎትንና ትዕግስትን በተፈጥሮ የተቸሩ በመሆናቸው ከእነርሱ የተሻለ ሰው ሊመጣ አይችልም።

ሴቶች ከኮንስትራክሽን ዘርፉ ጋር ተያይዞ በተለይም በቴክኖሎጂው ዘርፍ የበለጠ ተሳታፊ ማድረግ የሥርዓተ-ፆታ ልዩነቶችን ለመቀበል፣ በዘርፉ ውስብስብ የሆኑ ችግሮችን ለመፍታት፣ የሥራ ልዩነትን ለማጥበብ፣ የሴቶችን አስተዋጽኦ ለማጉላት፣ አርአያ የሚሆኑ ሴቶችን በዘርፉ ለመፍጠርና ተተኪዎች ፍላጎታቸውን አውቀው እንዲሰማሩ፣ እንዲሁም እንዲማሩ ለማድረግ ወሳኝ ሚና አለው የምትለው አርክቴክቷ፣ የሴቶች መሐንዲሶች ልዩ ችሎታዎች ናቸው ከሚባሉት ውስጥ አንዱ የተሻሉ ሃሳቦችን እና አመለካከቶችን ወደ ጠረጴዛው ማምጣት እንደሆነ ታነሳለች።

አክላም ለተለያዩ የምሕንድስና ፕሮጀክቶች እና እድገቶች ስኬት አስተዋጽኦ ያደርጋል። በንድፍ እና በውሳኔ አሰጣጥ ሂደቶች ውስጥ ወሳኝ ግብአትን ይፈጥራል። እኔ ሳይሆን እኛ የሚለው ሃሳብ ቅድሚያ እንዲሰጠው ያደርጋል። ከሁሉም በላይ ሁሉን አቀፍ ሥራና የሥራ እድልን ለመፍጠር ያስችላልም ትላለች። አዎ አርክቴክቷ እንዳለችው፤ የሴቶች ተሳትፎ መኖር ተዘርዝሮ የማያልቅ ሀብትን ለሀገር የሚያበረክት ነውና ዘርፉ የተሻለ አቅም ኖሮት በኢኮኖሚው ሀገርን ከአለችበት ወደ ብልፅግና ጎዳና እንዲያሸጋግራት ልዩ አቅማችንን ተጠቅመን መሥራት ይኖርብናል። ያሉባቸውን ችግሮች እየፈታንም መሐንዲሶቹ የሀገር መብራቶች እንዲሆኑ፣ ሀገራቸው ላይ አሻራቸውን እንዲያሳርፉ ማድረግ ይገባናል። ሰላም!!

በጽጌረዳ ጫንያለው

አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሰኔ 10 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You