መነጋገር፣ መወያየት፣ መመካከር፣ የሃሳብ ልውውጥ ማድረግ የሚሉ ጉዳዮች፤ በሰው ልጆች መስተጋብሮች ውስጥ ለሚፈጠሩ የሃሳብ ልዩነቶች፣ አለመግባባቶች፣ ችግሮችና ሌሎች መሰል ጥርጣሬን የሚፈጥሩ ነገሮች አድገው ወደ ግጭት ከማም ራታቸው በፊት መፍትሄ ማፍለ ቂያ አውዶች ናቸው::
በዚህ ረገድ በችግሮቻቸው ዙሪያ ቁጭ ብለው የተነጋገሩ እና የአለመግባባታቸው ምክንያት የሆኑ ጉዳዮችን በነቂስ አውጥተው የተወያዩና የተመካከሩ አካላት፣ ከችግሮቻቸው ልቀው በመውጣት ለሌሎች የሚተርፍ ሥራን ሲከውኑ ማየት የተለመደ ተግባር ነው:: በአንጻሩ በችግሮቻቸው ዙሪያ ቁጭ ብለው መነጋገር ባለመቻላቸው ምክንያት ልዩነቶቻቸውን ማጥበብና በጋራ መቆም ባለመቻላቸው ዛሬ ላይ የውድቀት ማሳያ ሆነው የሚነሱ በርካታ የማህበረሰብ ክፍሎችም፣ አገሮችም አሉ::
በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ በዘመናት ሂደት ውስጥ በበርካታ ችግሮች ተፈትናለች:: አንዳንዴም ችግሮቿን ፈትታ የአሸናፊነት ምሳሌ ተደርጋ ስትገለጽ፤ ሌላ ገጿም ልጆቿ በችግሮቻቸው ዙሪያ ቁጭ ብለው መምከርና ልዩነቶቻቸውን አጥብበው ለሰላማዊ ጉዞ ራሳቸውን ባለማዘጋጀታቸው ምክንያት ከፍ ያለ ሰብዓዊና ቁሳዊ ኪሳራን ያስተናገደችባቸው ሁነቶች አሉ:: የሃሳብ ልዩነት ሳይበግራቸው በአንድ ተሰልፈው የልዕልናቸውን ታሪክ የከተቡ ሕዝቦች፤ በአንድም በሌላ ምክንያት ልዩነታቸውን ቁጭ ብለው በመነጋገር መፍታት ባለመቻላቸው እርስ በእርሳቸው ጦር ተማዝዘው የጥቁር ጠባሳ የታሪክ ምዕራፍ ገጾችንም ፈጥረዋል::
የሩቁ ቀርቶ የቅርቡን መመልከት ቢቻል እንኳን፤ ራስን ለንግግር ዝግጁ ባለማድረግ ትንሿ አለመግባባት አድጋ ወደ ጦርነት አምርታለች፤ ችግሩን ቀድሞ ማስቀረት ቢቻልም ይሄ ባለመሆኑ ለከፋ ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ኪሳራም ዳርጋለች:: ይሁን እንጂ በመንግሥት በኩል በነበረው ብርቱ ጥረት በችግሮች ዙሪያ መነጋገር፤ ጦርነቱንም በሰላም ለመቋጨት ተችሏል:: በዚህም በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ከሁለት ዓመታት በላይ የቆየው ጦርነት በሰላም አየር ተተክቷል፤ የሕዝቦች ወንድማማችነት ወደቀደመ ሁኔታው ተመልሷል::
ይሁን እንጂ ዛሬም በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች የሚስተዋሉ ችግሮች አሉ:: እነዚህ ችግሮች በዋናነት የጽንፈኝነት አመለካከት የወለዳቸው ቢሆኑም፤ አገርንም ሆነ ሕዝብን ዋጋ እያስከፈሉ ያሉ ናቸው:: ለዚህ ደግሞ፣ ቀደም ሲል በኦሮሚያ፣ አሁንም በአማራ ክልሎች የሚስተዋሉ ችግሮችን ማንሳት ይቻላል:: እነዚህን ችግሮች ለመፍታትም በመንግሥት በኩል ትናንትም ሆነ ዛሬ ያላሰለሰ ጥረት እየተደረገ ይገኛል:: በመሆኑም በኦሮሚያ ክልል በሸኔ አማካኝነት ሲፈጠሩ የነበሩ ዘርፈ ብዙ ችግር እልባት እንዲያገኙ ያስችል ዘንድ ሰሞኑን በታንዛኒያ የሰላም ውይይት ሲከናወን ቆይቷል::
ይሄ ውይይት ቀደም ሲል መንግሥት ከሕወሓት ጋር እንዳደረገው የሰላም ውይይት ሁሉ ለሕዝቦች ሰላምና ደህንነት፣ ለአገር ሁለንተናዊ ሰላምና ብልጽግና እውን መሆን ከፍ ያለ ፋይዳ ያለው ነው:: ከዚህ አኳያ በመንግሥት እና በሸኔ ኃይል መካከል ሲደረግ የቆየው የሰላም ውይይት የመጀመሪያ ምዕራፍ የተጠናቀቀ ሲሆን፤ ውይይቱም በአብዛኛው በአዎንታዊ የተከናወነ ስለመሆኑም ነው የመንግሥት ኮሙኒኬሽን መግለጫ ያመለከተው:: በተለይም ግጭትን በዘላቂነት ሰላማዊ በሆነ መንገድ ማቆም መቻል ተገቢ እንደመሆኑ ሁለቱም ወገኖች በውይይቱ አስፈላጊነት ላይ ተግባብተዋል::
ይሄን መሰል ግጭትን በዘላቂነትና ሰላማዊ በሆነ መልኩ መፍታት ምን ያህል ከፍ ያለ ዋጋም ፋይዳም እንዳለው መንግሥት ከሕወሓት ጋር ባደረገው የሰላም ውይይት የተፈጠረው ሰላም ከፍ ያለ እማኝ ነው:: ምክንያቱም መነጋገርና መወያየት ባልተቻለበት ጊዜ በሰሜኑ የአገራችን ክፍል ከፍ ያለ ቀውስና ኪሳራ ደርሷል፤ አገርንም ዋጋ አስከፍሏል:: ልዩነቶችን በውይይት ለመፍታት እና ችግሮችን በመነጋገር በሰላማዊ መንገድ መከወን ሲቻል ደግሞ አካባቢው ላይ የሰፈነውን ሰላምና መረጋጋት፤ አገር ላይ የተፈጠረውን አዎንታዊ የማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ እና ዲፕሎማሲያዊ ከፍታ መመልከት ተገቢነት ይኖረዋል::
ዛሬም በሰሜኑ የአገራችን ክፍል የተገኘው እፎይታ፣ ሰላምና መረጋጋት፤ በኦሮሚያም ሆነ በአማራ ክልል ላሉ ወገኖች እውን ሊሆን ያስፈልጋል:: ይሄ የሚሆነው ደግሞ ልዩነቶችን ለማጥበብ የሚያስችሉ ንግግሮችና ምክክሮችን፤ ሰላምን ማምጣት የሚያስችሉ ሰላማዊ ውይይቶችን ማድረግ ሲቻል ነው:: በዚህ ረገድ ከሕወሓት ጋር የተደረገው የሰላም ውይይት ብዙ ያስተማረ ሲሆን፤ ከሸኔ ጋር እየተደረገ የነበረው የሰላም ውይይትም ችግሮችን ለመፍታትና ጦርነትን በሰላማዊ መንገድ በዘላቂነት ለማስቆም ይቻል ዘንድ ጥሩ ጅምር የታየበት ነው:: በመሆኑም በአንድ በኩል ይሄ መልካም ጅምር ተጠናክሮ ሊቀጥል፤ በሌላ በኩልም ይሄው ችግሮችን ቁጭ ብሎ በሰላማዊ መንገድ የመነጋገር ልምድ ሌሎችም ሊወስዱት የሚገባ ነው:: ይሄን ማድረግ ደግሞ ከራስ በላይ ለሕዝብ፤ ከቡድን በላይ ለአገር የማሰብና የመኖር ሰብዕና መገለጫ መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል:: ስለሆነም ችግሮችን በውይይት የመፍታት ጅምሮች ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል!
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 27/2015