ጽንፈኝነት ከሚገለጽባቸው መንገዶች አንዱና ዋነኛው ሕዝብን ከእውነተኛ ማንነቱ ሊያፋቱ የሚችሉ የጥፋት ትርክቶችን በመፍጠር በተቻለው መጠን ሕዝባዊ መሰረት እንዲኖራቸው በሁለንተናዊ መልኩ የተጠናከረ የፕሮፓጋንዳ ዘመቻዎችን ማካሄድ ነው።
ዘመቻዎቹ ጭፍን ጥላቻዎችን መሰረት ያደረጉ ፤ ሕዝቦችን ያልተገቡ ሥጋቶች ውስጥ በመክተትና ተጨባጭ በሆኑ ነባራዊ እውነታዎች ላይ ያላቸውን መታመን በመስረቅ ከስጋታቸው አትራፊ መሆን ላይ የተንጠላጠሉ ናቸው።
ጽንፈኞች የሕዝብን የዕለት ተዕለት ሕይወት የሚፈታተኑ ” እንዲህና እንዲህ ሊደረግብህ ነው፤ እንዲህም ሆኖብሀል ” የሚሉ የፈጠራና የስጋት ትርክቶችን ጨምሮ ነገዎችን የሚያጨልሙና ሕዝብን ለጸለምተኛ አስተሳሰቦች ሰላባ ለማድረግ የሚተጉ ናቸው።
በተለይም ኅብረ ብሄራዊነት፤ መገለጫቸው በሆኑ አገራት ፤ ለአገራቱ ሕዝቦች ውበት የሆነውን ኅብረብሄራዊ ማንነት ለጥፋት ተልእኳቸው እንደ አንድ ትልቅ እድል በመውሰድ፤ በሕዝቦች መካከል አለመተማመንና ጥርጣሪዎችን መፍጠርን የተልዕኳቸው ማዕከል ያደርጋሉ።
ሕዝብን በሕዝብ ላይ፤ ሀይማኖትን በሀይማኖት ላይ በማነሳሳት፤ በአገር ያለመረጋጋትና ሁከት እንዲፈጠር ከዚያም ባለፈ የለየለት የጦርነት አውድማ እንድትሆን በማድረግ ከሕዝቦች መከራና ስቃይ አትራፊ ለመሆን ይሰራሉ።
በማኅበረሰብ ውስጥ በተለያዩ ምክንያት የሚፈጠሩ ግጭቶችን ከአቅማቸው በላይ በማግዘፍ ያለመረጋጋትና የውጥረት ምክንያት እንዲሆኑ ከመስራት ባለፈም፤ ግጭቶቹ ሊፈቱ የሚችሉበትን ማኅበራዊ እሴቶች በማሳነስ ከግጭቶች ተጠቃሚ አስካልሆኑ ድረስ ግጭቶች ዘላቂነት እንዲላበሱ ያደርጋሉ።
በእኛም አገር ጽንፈኛ ኃይሎች መሽቶ እስኪነጋ በሚፈጥሯቸው የጥፋት ትርክቶች እያደረጉት ያለው ከዚህ የተለየ አይደለም። በተለይም ከለውጡ ማግስት ጀምሮ መንግስት አዲስ የፖለቲካ ስርአት ለመፍጠር እየሄደበት ያለው የፖለቲካ መንገድ ስጋት የሆነባቸው ኃይሎች ጽንፈኝነትን ዋነኛ የፖለቲካ ስትራቴጂ አድርገው እየተንቀሳቀሱ ነው።
በአንድ በኩል ቀደም ሲል የመጣንበት የፖለቲካ መንገድ ከውድቀት ባለፈ ያተረፈልን የለም በሚል በመንግስት በኩል የተፈጠረው ችግሮችን በውይይት በሆደ ሰፊነት ለመፍታት የመሞከር ሂደት ፤ በሌላ በኩል እነዚህ ኃይሎች ይህን የመንግስት ሆደ ሰፊነት እንደ አቅም ማጣት የማይታቸው እውነታ የሽግግር ወቅት ፈተናውን አክብዶታል።
ባለፉት አምስት ዓመታት በእነዚህ ጽንፈኛ ኃይሎች የተፈበረኩ የጥፋት ትርክቶች ሰሚ ቢያገኙ ኖሮ አገሪቱ እንደ አገር ስንት ጊዜ በአደባባይ ፈርሳ እንደነበርና አንድ ብሄር በአንዱ ላይ ተነስቶ የተፈጠሩ እልቂቶችም ብዛታቸው ምን ያህል ሊሆን እንደሚችል ለየትኛውም ዜጋ የሚሰወር አይደለም።
ሕዝብ በምርጫ ካርዱ ወዶና ፈቅዶ ወደ ስልጣን ያመጣውን መንግስት በሁከትና በግርግር ከዚያም ባለፈ በጦርነት ከስልጣን ለማስወገድ የተደረጉ አንድ ሺ አንድ የክተት ጥሪዎች እነማንን በቦታው ለማምጣት ተስፋ አድርገው እንደነበርና የቱን ያህል ዋጋ እንዳስከፈሉን ለማስታወስ የሚከብድ አይደለም።
በጽንፈኞች የተሞከረው ሕዝባችንን ከእውነትና ማንነቱ የማፋታት የተጠናከረ የፕሮፓጋንዳ ዘመቻም ቢሆን እንደታሰበው ሕዝባችንን ወደ አልተገባ ባህሪ ከመውሰድ ይልቅ ፤ ዋጋ እየከፈለ ዘመናት ያሻገረውን ማህበራዊ ስብዕናውን አጥብቆ እንዲይዘው አቅም ሆኖታል።
እነዚህ ኃይሎች ዛሬ ላይ የአማራ ክልልን የግጭትና የሁከት ማዕከል ለማድረግ ከቀደመው ሰፊ የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ ባለፈ በህቡዕ ተደራጅተው እየተንቀሳቀሱ ስለመሆናቸው መረጃዎች እያሳዩና ከዚያም ባለፈ ተጨባጭ የጽንፈኝነት ተግባራዊ እንቅስቃሴዎች እየተስተዋሉ ነው። ከዚህም አልፎ በክልሉ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት ለማስፈን በክልሉ ባለው የመከላከያ ኃይል ላይ ሰፊ የጥላቻ ፕሮፓጋንዳ ከፍተዋል።
የአማራ ሕዝብ ከወንድም እህቶቹ ኢትዮጵያውያን ጋር በአገረ መንግስት ምስረታ ባለቤት እንደመሆኑ በጽንፈኞች አስተሳሰብ መሰረት ላይ ሊዋቀር የሚችል አገረ መንግስት ይኖራል ብሎ አያምንም። አገር እንደአገር ልትመሰረትም ሆነ ጸንታ ልትቆምና ልትቀጥል የምትችለው ፤ እንደአገር የተመሰረተችበትንና ዘመናት ተሻግራ ዛሬ ላይ ፀንታ እንድትቆም ያደረጓትን መንፈሳዊ፤ ባህላዊ እና ማህበራዊ እሴቶቿን ጠብቃ ማቆየት ስትችል ብቻ እንደሆነም ይረዳል።
በርግጥም የዛሬ ሰላማችንና ክብራችን በመከላከያ ሰራዊቱ ከፍ ያለ የተጋድሎ ታሪክ ደምቆ የተጻፈ፣ የነገ ሰላምና መረጋጋታችንና የመልማት መሻታችንም ከምንም በላይ በመከላከያ ሰራዊቱ ቀጣይ ተልእኮ ላይ የተመሰረተ መሆኑን ኢትዮጵያውያን ጠንቅቀው የሚያውቁት እውነት ነው!
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 26/2015