የጽንፈኝነት አስተሳሰብ ሰለባ የሆኑ ግለሰቦች እና ቡድኖች የኖሩበትን ማኅበረሰብ ፣ ሀገራቸውን ፣ ከዚያም ባለፈ ዓለምን ብዙ ዋጋ አስከፍለዋል። በቀደሙት ዘመናትም ሆነ ዛሬ ላይ ዓለማችን ያስተናገደቻቸውም ሆነ እያስተናገደቻቸው ያሉ አውዳሚ ጦርነቶች እና ግጭቶች በአንድም ይሁን በሌላ በዚህ የአስተሳሰብ ስንኩልነት የተፈጠሩ ናቸው።
ሁለቱን ዓለም አቀፍ ጦርነቶች ጨምሮ ባለፉት መቶ ዓመታት ዓለም ያስተናገደቻቸው ጦርነቶች ፤ በአብዛኛው የአስተሳሰብ መዛነፍ ባጋጠማቸው ጽንፈኛ ግለሰቦች ተጀምረው፣ የቡድን መንፈስ ተላብሰው ፣ በተዛቡ ትርክቶች ታጅበው የሰደድ እሳት ያህል በማኅበረሰብ ውስጥ ፈጥነው በመሰራጨት ዓለምን ብዙ ያልተገቡ ዋጋዎችን ያስከፈሉ ናቸው።
የአስተሳሰቡ ባለቤቶች /ጽንፈኞች/ አስተሳሰባቸው ማኅበራዊ መሰረት እንዲኖረው ለማድረግ፣ በተለይም ለስሜት ቅርብ የሆነውን ወጣቱን ትውልድ ከጎናቸው ለማሰለፍ የተለያዩ ማኅበራዊ ፣ ፖለቲካዊ ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ታሪካዊ የተዛቡ /የጥፋት ትርክቶችን በመፍጠር ፣ ለራሱና ለሀገሩ ነገዎች ተስፋ የሆነውን ትውልድ ባልተገባ መልኩ ለጥፋት ዳርገው እነሱም አስተሳሰቡ በወለደው እሳት ተበልተው አልፈዋል።
ይህ ዓለምን ከቀደመው ዘመን ጀምሮ እየተፈታተነ ያለ ስንኩል አስተሳሰብ ዛሬም ቢሆን ለሀገራት ፣ ከዚያም አልፎ ለዓለም ሰላም ትልቁ ስጋት ሆኗል። ኢኮኖሚያዊ ፣ ፖለቲካዊና ሃይማኖታዊ መሰረት ተላብሶ ዓለምን እየተፈታታነ ያለው ጽንፈኝነት፣ አሁን ባለንበትም ዘመን በመካከለኛው ምስራቅ የተቀጣጠለው የጸደይ አብዮት መልኩን እንዲቀይር በማድረግ ሀገራትን እንደሀገር እንዳይቆሙ አድርጓቸዋል።
ዜጎቻቸው ተረጋግተው የተሻለ ሕይወት ይመሩ የነበሩ እንደ ሊቢያ፣ ሶሪያ እና ኢራቅን የመሳሰሉ ሀገራት እስከዛሬ ሊወጡት ወደማይችሉት ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ አዘቅት ጨምሯቸዋል፤ ዜጎቻቸውም ከስደት ባለፈ ጠባቂ እንዲሆኑ በማድረግ ብሄራዊ ክብራቸውን እንዲያጡ አድርጓቸዋል። ለችግሮቻቸው ዘላቂ መፍትሄ እንዳያገኙም እስከዛሬ ዋነኛ ተግዳሮት ሆኖባቸዋል።
በኛም ሀገር ከለውጡ ማግስት ጀምሮ ዘርን እና ሃይማኖትን ሽፋን አድርጎ እየተስተዋለ ያለው ጽንፈኝነት ሕዝባችንን በሁለንተናዊ መልኩ ዋጋ እያስከፈለ ይገኛል። የህዝባችንን ተቻችሎና ተከባብሮ የመኖር እሴቶችን ከመሸርሸር ባለፈ፣ በየዕለቱ በሚፈበረኩ አዳዲስ የጥፋት ትርክቶች እየታጀበ ሀገራዊ የስጋት ምንጭ ከሆነ ውሎ አድሯል።
ሀገራችንንና ሕዝባችንን እየተፈታተኑ ካሉ አጀንዳዎች በስተጀርባ ገዝፎ የሚገኝው ጽንፈኝነት ፤ አሁን አሁን ወደ ከፋ ደረጃ ለመሸጋገር እየዳሀ ስለመሆኑ ምልክቶች እየተስተዋሉ ነው። ቀደም ሲል በአማራ ክልልና በመከላከያ አመራሮች ላይ ፤ ሰሞኑን ደግሞ በአቶ ግርማ የሺጥላ ላይ ጽንፈኞች ያደረሱት ግድያን ጨምሮ ፤ በኃይልና በሽብር ወደ ስልጣን ለመምጣት እየተጓዙበት ያለው የጨለማ መንገድ ለዚህ ተጨባጭ ማሳያ ነው።
ሕዝባችን ከተገነባበት መንፈሳዊ ፣ ባህላዊና ማኅበራዊ እሴቶች አኳያ ለጽንፈኝነት የተሰጠ ልብና አእምሮ ባይኖረውም ፤ አስተሳሰቡ በባህሪው የተለያዩ ማኅበራዊ ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጥያቄዎችን ጠልፎ በመውሰድ የጥፋቱ አቅም መገንቢያ አድርጎ የሚወስድ በመሆኑ፣ ሕዝባችንየዚህ ባህሪው ሰለባ እንዳይሆን ነቅቶ መጠበቅ ይኖርበታል።
በሃገራችን ካለው የብሔር ብሔረሰቦች እና የሀይማኖት ብዝሃነት አንጻር ፤በየትኛውም መንገድና መልክ የሚገለፅ ጽንፈኝነት ሊያስከፍለን የሚችለውን ያልተገባ ዋጋ ዛሬ ላይ ቆም ብለን ፣ በተረጋጋ አእምሮና በሰከነ መንፈስ ማየት ካልቻልን ፤የጥፋቱ አድማስ ሊሎች ሀገራት ለመክፈል ከተገደዱት የከፋ እንጂ ያነሰ እንደማይሆን ለማሰብ የሚከብድ አይሆንም ።
እንደ ጥላ ከሚከተሉን ታሪካዊ ጠላቶቻችን ጀምሮ በየጊዜውመልካቸውን እየቀያየሩ ለውድቀታችን የሚተጉ ኃይሎች ፤ የዘመናት ምኞታቸው ውጤታማ ሊሆን የሚችለው ከሁሉም በላይ ጽንፈኛ አስተሳሰቦች ማኅበራዊ መሰረት ሲይዙ መሆኑን ተረድተው በተቻላቸው ሁሉ እየሰሩ ነው።በዚህም ትናንት እና ዛሬ ላይ ያስከፈሉንና እያስከፈሉን ያለው ዋጋ ቀላል አይደለም።
ጽንፈኝነትን ይብቃ ብለን በቁርጠኝነት መነሳት ከቻልን ዛሬ ላይ የምናከብራቸውን መንድሞቻችንን ነፍስ ከመቅጠፍ አልፎ፤ነገ ላይ አባቶቻችን ከፍ ያለ የህይወት ዋጋ ከፍለው በብዙ ተጋድሎ ያቆዩልንን ሀገራችንን እንደሀገር ሊያሳጣን እንደሚችል ለአፍታ እንኳን ልንጠራጠር አይገባም። ስለሆነም ይህንን የሕዝብና የሃገር ጠላት ለማስወገድ መረባረብ ከሁሉም ኢትዮጵዊ የሚጠበቅ ሃገራዊ ግዴታ ይሆናል!
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 25/2015