ለአንድ አገር ልማትና ዕድገት ሰላም ከምንም በላይ የገዘፈ ዋጋ አለው። ሰላም የሁሉም ነገር መሰረት ነው፣ የሰላም ዋጋ በምንም አይነት ምድራዊ ዋጋ አይሰላም፤ ተመንም ሆነ መስፈሪያ እንዲሁም ማንፀሪያ የለውም። የአገርና የሕዝብ ሰላም ትልቅ ዋጋ አለው፣ ሰላም ለአገር ልማትና እድገት ዋነኛው ምሰሶና መሰረት ነው።
ሰላም የሰውን ልጅ የአዕምሮ እና የልብ መረጋጋት፤ ከሚያስጨንቁ ነገሮች ነፃ መሆን ብሎም በአጠቃላይ የሰው ልጅ ውስጣዊና ውጫዊ እረፍት ማግኘት ነው። ለዚህም ነው ሰላማችን ይበዛ ዘንድ ሁላችንም ለአገራችን ሰላም ዘብ መቆም አለብን የሚባለው። የኢትዮጵያ መንግሥት በተደጋጋሚ ለሰላም ሲል ብዙ ነገሮችን ሲያልፍ እና በይቅርታ ለመሻገር ሲደክም እና ረጅም ርቀት ሲጓዝ እንደነበር የማይካድ ሃቅ ነው። ዛሬም ይሄን ጥረቱን አጠናክሮ እንደቀጠለ ለማንም የተደበቀ አይደለም።
ላለፉት ሁለት ዓመታት በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል የተፈጠረው ችግር እልባት ያገኘው በድርድር ሂደት መሆኑ ከግጭት በኋላ የሚገኘው ሰላም ዘለቄታ እንዲኖረው አድርጓል። በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ በመንግስት እና በሕወሓት መካከል የተደረሰው የሰላም ስምምነት ባለፉት ሁለት ዓመታት የተፈጠሩትን ጫናዎች የሚያስወግድ ስምምነት መሆን ችሏል።
ከስምምነቱ ኢትዮጵያ ብዙ አትርፋለች። በስምምነቱ የሠላም ወጋገን መፈንጠቅ ጀምሯል። የሰላም ስምምነቱ ትሩፋት ግን በዚህ ብቻ የሚገለጽ አይደለም። በስምምነቱ ማግስት ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያውያን ማትረፍ የቻሉባቸው በርካታ መስኮች ተስተውለዋልና። መንግስት የነበረው ደም አፋሳሽ ጦርነት እንዲቆም በማድረግ ሕዝብ የሰላም አየር እንዲተነፍስ ሆደ ሰፊ ሆኖ የተጓዘበት ርቀት የሚደነቅ ነው።
ሰሞኑን ከሸኔ ጋር በታንዛኒያ የጀመረው የሰላም ውይይትም የሕዝብን ሰላም ከመመለስ ባሻገር ችግሮችን በጠረጴዛ ዙሪያ ተቀምጦ የመፍታት ዘላቂ የሆነ የመወያየት ባህል መሰረት እንደሚሆን አርቆ ማሰብ ያስፈልጋል። እውነተኛ እና ዘላቂነት ያለው ሰላም የሚገኘው ክፉውን በመልካም አሸንፈን እንጂ በክፉ መልሰን አይደለም። በአገራችን ተከስቶ ሕዝባችንን ዋጋ ያስከፈለውን ግጭት በሰላም መንገድ በአግባቡ አርመን ወደ ዘላቂ ሰላም ካልተመለስን የኢትዮጵያን የብልጽግና ጉዞ ማሳካት አንችልም።
“እርቅ ደም ያድርቅ” እንዲሉ የእርቅን ጥቅም በመቀበል ወደ ተሻለ ነገር ለመራመድ ሕዝቡን ከሚከፋፍሉ ነገሮች መቆጠብ ለኢትዮጵያ ከምን ጊዜውም በላይ አስፈላጊ ነው። ማንኛውም ግለሰብ ከማናቸውም አደረጃጀት ነፃ አድርጎ የሰላም ጥሪን በማሰማት ለሁሉም ኢትዮጵያውያን ሰላም መረጋገጥ ለሰላም በሰላም መስራት መጣር እና ለውጥ ማምጣት ለነገ የሚቆይ የቤት ስራ አይደለም።
ማንኛውም ዜጋ ሰላም እና አንድነትን ለማረጋገጥ ጉልበትን ሀብትን እንዲሁም ስልጣንም ሆነ ነጠላ እውቀትን እንደ አማራጭ መውሰድን አቁሞ የተከሰቱብንን ችግሮች በውይይት እና በድርድር በመፍታት በጦርነት በረሃብና በድርቅ የተጎዱ ወገኖቻችንን የምንታደግበት ትልቅ እድል በእጃችን ይገኛልና እንጠቀምበት። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ “በጦርነት የረጅም ዘመን ታሪክ ያላት ኢትዮጵያ የጦርነትን አውዳሚነት ሩቅ ሳትሄድ ካለፉት ሁለት ዓመታት ብዙ ተምራለች” ብለዋል።
ግጭት በህይወት የመኖር የተቃርኖ ዕውነታ ቢሆንም ለሰው ልጆች ሰላም ሲባል በአዎንታ የሚደገፍ አይደለም። ዓለማችን በተለያዩ ዘመናት በርካታ ግጭቶችን አስተናግዳለች እያስተናገደችም ትገኛለች። እንዲያም ሆኖ ከግጭቶች በኋላ የሚገኘው ሰላም ዘለቄታ እንዲኖረው ለማድረግ ሲባል ግጭቶችን በሰላማዊ ንግግር እና ድርድር መፍታት አዋጭ ስለመሆኑ ተደጋግሞ የታየ ሀቅ ነው። በርካታ የታሪክ ድርሳናት የሚነግሩንም በዓለማችን ላይ የተከሰቱ አብዛኞቹ ግጭቶች እና አለመግባባቶች መቋጫ መንገድ ንግግር እና ድርድር ላይ የተመሰረቱ መሆናቸውን ነው።
በመሆኑ መንግስት ለየትኛውም አካል የሚዘረጋው የሰላም እጅ ትርፍ እንጂ ኪሳራ የለውምና ከሕዝብ ድጋፍ ሊቸረው ይገባል። መንግስት ለሰላም እጁን የዘረጋው የኢትዮጵያንና የሕዝቧን ዘላቂ ጥቅም ለማስከበር መሆኑንንም በሚገባ መገንዘብ ይገባል። የአገርን ብሔራዊ ጥቅም ሰላምና ደኅንነት መጠበቅ፣ የተጀመሩ የልማት ስራዎችን ማስቀጠልና ለውጤት ማብቃትም የመንግስት ብቻ ሳይሆን የሕዝቡም የጋራ አገራዊ ኃላፊነትና ግዴታ ነው። ለዚህም ሲባል ከአገር ሰላም በፊት የሚቀድም ሌላ ምንም ጉዳይ አይኖርም!
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሚያዝያ 24 ቀን 2015 ዓ.ም