በኢትዮጵያ ለነዳጅ በሚደረገው ድጎማ ምክንያት ከዓለም አቀፍ ዋጋ ጋር ሲነፃፃር በአነስተኛ ዋጋ መሸጡ ለኮንትሮባንድ ንግድ ተጋላጭ አድርጎታል። ወደ ውጭ አገራት በመውጣቱ በነዳጅ ግብይት ላይ ያለውን ክፍተት ለመቅረፍ የነዳጅ ግብይት በኤሌክትሮኒክስ የክፍያ ስርዓት እንዲሆን ማድረግ አስፈላጊ ሆኗል። ይህንን ተከትሎ የንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ከግንቦት ወር ጀምሮ በመላ አገሪቱ የነዳጅ ግብይት በኤሌክትሮኒክስ የክፍያ ስርዓት ተፈፃሚ እንደሚሆን አስታውቋል።
በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ፤ ምንም እንኳ ጊዜው አጭር ቢሆንም የነዳጅ ግብይት ሪፎርም ከተደረገ ወዲህ መሻሻሎች መኖራቸውም አመልክቷል። የነዳጅ ግብይት ባለፉት ሃያ ዓመታት የዋጋ አሰራሩ ክፍተት የነበረበት በመሆኑ፤ ለነዳጅ ዋጋ ማረጋጊያ የሚሰጠው ፈንድ አገሪቱን ለእዳ እየዳረጋት ቆይቷል። በዚህም የነዳጅ ግብይቱን ስርዓት ለማስያዝ የኤሌክትሮኒክስ የክፍያ ስርዓት ተዘርግቶ ፍትሃዊ የነዳጅ ስርጭትና አጠቃቀም እውን እንዲሆን የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ተጠቁሟል።
በሌላ በኩል በሙከራ ደረጃ እየተተገበረ የቆየው ይህ የአሰራር ስርዓት ከሚያዚያ 16 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ በአዲስ አበባ ውስጥ በሚገኙ የነዳጅ ማደያዎች ግብይቱ ሙሉ በሙሉ በኤሌክትሮኒክስ የክፍያ መንገዶች ብቻ እንደሚፈጸም ያስታወቀው ደግሞ የነዳጅና ኢነርጂ ቁጥጥር ባለስልጣን ነው። ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በአዲስ አበባ የኤሌክትሮኒክስ የክፍያ ስርዓቱ በአማራጭነት በሙከራ ደረጃ እየተተገበረ መቆየቱን ገልጾ፤ ከሚያዚያ 16 2015 ዓ.ም ጀምሮ የነዳጅ ግብይቱ በአስገዳጅ ሁኔታ ሙሉ በሙሉ በኤሌክትሮኒክስ ክፍያ መንገዶች ብቻ እንደሚፈጸም አሳውቋል። በመሆኑም ህብረተሰቡ ማንኛውም የነዳጅ ግብይት በኤሌክትሮኒክስ ብቻ የሚፈጸም መሆኑን ተገንዝቦ ከወዲሁ አስፈላጊውን ዝግጅት ሊያደርግ እንደሚገባ ማሳሰቢያ አስተላልፏል።
ኢትዮ ቴሌኮም በበኩሉ የነዳጅ ግብይትን በኤሌክትሮኒክስ ክፍያ መንገዶች በማድረግ ረገድ በ “ቴሌ ብር” ውጤታማ ስራ ሲሰራ መቆየቱን ገልጿል። በሙከራ ትግበራ በቆየባቸው ባለፉት ዘጠኝ ወራት በ “ ቴሌ ብር “ ብቻ ከ30 ቢሊዮን ብር በላይ የነዳጅ ግብይት መፈጸሙን አመልክቶ። በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኙ 153ቱም የነዳጅ ማደያዎች የነዳጅ ግብይቱ በቴሌብር በተሳለጠ መልኩ እንዲከናወን እና ለደንበኞች በፍጥነት የተሳለጠ አገልግሎት ለመስጠት እንዲቻል አስፈላጊውን ድጋፍ እያደረገ መሆኑን በተጨማሪም የነዳጅ ግብይቱን በአግባቡ በኤሌክትሮኒክስ የክፍያ መንገዶች ለማከናወን የሚያስችል ዘመናዊ ቴክኖሎጂ መገንባቱንም አስረድቷል።
አሰራሩ መንግስት የነዳጅ ምርት ከመነሻው እስከ መድረሻው በሚኖረው የስርጭት ሂደት መረጃ እንዲኖረው እና ነጋዴዎችም ግብርና ታክስ እንዳያጭበረብሩ በማድረግ ቴክኖሎጂው ትልቅ ሚና እንዳለው ደግሞ የተለያዩ ባለሙያዎች ይገልፃሉ። ይህንን ጉዳይ በተመለከተ የዘርፉ ምሁራን የሚሉት አላቸው። የኢኮኖሚ እና የምጣኔ ሃብት ባለሙያው አቶ ወሰንሰገድ አሰፋ እንደሚናገሩት፤ የእቃ ግብይት የክፍያ አሰራር ዘዴ ከኢኮኖሚ መስኮች አንዱ ነው። ግብይት ሄዶ ሄዶ እቃ መሸጥ በመሆኑ፤ ዋነኛው የታችኛው የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ የሚሳለጥበትን መንገድ በቀጥታ (በኦንለይን) ማድረግ ትልቅ ጠቀሜታ አለው።
አሁን በነዳጅ ላይ ብቻ የተፈፀመ ቢሆንም፤ ወደ ፊት ግብርና ላይ ገበሬውን ማዳረስ ቢቻል እንዲሁም ደግሞ ሌላ አገልግሎት የሚሰጡ አካላት አምራቾች እና ሸማቾች በአካል መገናኘት ሳይጠበቅባቸው የኦንለይን ግብይት መፈፀም መቻል እንደ አገር በብዙ መልኩ ከፍ ያለ ኢኮኖሚያዊ ጠቃሜታ አለው። ጥሬ ገንዘብ በኪስ ይዞ መዞርን ያስቀራል። ይሄ ደግሞ ፋይዳው ብዙ መሆኑን ያስረዳሉ። እያንዳንዱ ብር ሲያረጅ እንደ አዲስ በብሔራዊ ባንክ መታተም ይኖርበታል። ብር ለማሳተም ተጨማሪ ወጪ ይወጣል።
በተለይ በነዳጅ ግብይት አካባቢ ላይ የብር ዝውውሩ በጣም ከፍተኛ በሆነበት ሁኔታ የብሮች መበላሸት እና ብሮች በተበላሹ ቁጥር ደግሞ መንግስት የተበላሹትን ብሮች ለመተካት የሚያወጣውን የውጭ ምንዛሬ በከፍተኛ ደረጃ ያስቀራል። ስለዚህ ከጥሬ ብር ንክኪ መውጣት ከተቻለ መልካም ስለመሆኑ ያብራራሉ። እንደ አቶ ወሰንሰገድ ገለፃ፤ የነዳጅ ማደያዎች ላይ በቢሊየኖች ገንዘብ ይዘዋወራል። ይህ ሁሉ እስከ አሁን የሚዘዋወረው በካሽ ነበር። በካሽ አለመሆኑ የመበላሸት ፍጥነቱን ይቀንሳል። ይህ ደግሞ የውጪ ምንዛሬ ወጪን ይቀንሳል።
በሁለተኛ ደረጃ በገቢዎች የግብር አከፋፈል በኩል በማየት አቶ ወሰንሰገድ ለአብነት ሲያነሱ ለድርጅቶች የነዳጅ ወጪ ይወራረዳል። ከዚህ አኳያ ከተመለከትነው ጥሬ ደረሰኝ ሳያስፈልግ በቴሌ ብር ወይም በሌላ የክፍያ አማራጭ አንድ ግለሰብ በትክክል ለነዳጅ ያወጣውን ወጪ በቀላሉ ድርጅቱም ሆነ መንግስት ማወቅ ይችላሉ። ስለዚህ ከታክስ ጋር ተያይዞ ያሉ ነገሮችን በቀላሉ መፍታት ይቻላል። ሌላኛው ደግሞ እያንዳንዱ ሰው በግል ለነዳጅ የሚያወጣውን ፍጆታ መጠን ያውቃል። የሁለት ሺህ ብር እና የሶስት ሺህ ብር ነዳጅ ሲሞላ ምን ያህል ኪሎ ሜትር መጓዝ እንደሚቻል በማረጋገጥ፤ በቀላሉ የግል የነዳጅ ፍጆታን ማወቅ ቀላል ይሆናል ይላሉ።
የግብይት ሂደቱን በጣም ስለሚያቀላጥፈው በትክክል ከነዳጅ ሽያጭ የሚሰበሰበውን ገቢ ማወቅ እንዲቻል ያደርገል፤ ነዳጅ የሚያከፋፍሉ ድርጅቶችም ዕለታዊ ገቢያቸው ስንት እንደሆነ ቁጭ ብለው በአካል ብር ቆጥረው መረከብ ሳይኖርባቸው ባሉበት ቦታ ድርጅታቸው ስንት እንደሸጣ፤ ስንት ሊትር ነዳጅ እንደቀረው፤ በሞባይላቸው መከታተል እንዲችሉ ያደርጋቸዋል ብለዋል።
ቴክኖሎጂ በመጣ ቁጥር የቴክኖሎጂ ዕድገት ከኢኮኖሚ ዕድገት ጋር ቀጥተኛ ተያያዥነት አለው የሚሉት አቶ ወሰንሰገድ፤ ቴክኖሎጂ ባደገ ቁጥር ታክስ ማጭበርበር አይቻልም። ገንዘብ ይቆጥባል፤ ጊዜ ይቆጥባል፤ በተጨማሪ ለትራንስፖርት ይወጣ የነበረውን ወጪ መቆጠብ ያስችላል። እነኝህ ሁሉ ነገሮች ሰይባክኑ መቅረታቸው የኢኮኖሚ እድገቱ ላይ ቀጥተኛ አስተዋፅኦ ይኖራቸዋል ብለዋል።
ከዚህ ጋር ተያይዞ የአሰራር ለውጥ ሲመጣ በለውጡ የሚጠቀም አካል ይኖራል። የሚጎዳ አካል ሊኖርም ይችላል የሚሉት የኢኮኖሚ ባለሙያው፤ አንዳንድ ጊዜ ነዳጅ ለቀዱ አካላት ተጨማሪ ጉርሻ መስጠት ወይም ደግሞ በማጭበርበር ዋጋ ከፍ እና ዝቅ ማድረግ መኖሩ ሲነገር ነበር። አሁን ግን ቀጥታ ወደ ባንክ ሒሳብ ስለሚገባ እጃቸው ላይ ምንም አይነት የጥሬ ገንዘብ ዝውውር አይኖርም። ተንጠባጥቦ የሚቀር ገንዘብ የመገኘት እድላቸው በጣም ያንሳል፤ በዚህ ምቾት የማይሰማቸው አካላት ሊኖሩ ይችላሉ፤ ይሄ ደግሞ የሚጠበቅ እና ተፈጥሯዊ እንደሆነ ነው የተነገሩት።
የቴክኖሎጂ ባለሙያው አቶ አበበ በቀለ በበኩላቸው፤ ሁሉም ነገር አልጋ በአልጋ አይሆንም። አንድ ነገር ሲመጣ ጥቅም እንዳለው ሁሉ ጉዳትም ሊኖረው ይችላል፤ የሞባይል ገንዘብ ዋና አላማው የግብይት ሂደቱን ጥሬ ገንዘብ አልባ ማድረግ ነው። ሰው ገንዘብ በእጁ መያዝ ሳይጠበቅበት የሚፈልገውን ግብይት ይፈፅመል። ይህ የግለሰብን ደህንነትንም ያስጠብቃል፤ የግዴታ ምርጥ ስልክ ሳያስፈልግ በማንኛውም ስልክ አገልግሎት ማግኘት የሚቻል በመሆኑ ብዙ የሚያስጨንቅ አይደለም ይላሉ።
እንደ ኢኮኖሚስቶች አቶ ወሰንሰገድ ሁሉ፤ አቶ አበበም በቴክኖሎጂው መጠቀም ከተቻለ አንድ ነዳጅ ማደያ በቀን ውስጥ ያከናወነውን የግብይት መጠን ማወቅ ይቻላል። የመጣው ነዳጅ በትክክል ተጠቀሚ ጋር ደርሷል የሚለውን ሁሉ በመረዳት፤ ከብልሹ አሰራር የፀዳ አገልግሎት እንዲኖር ያደርጋል። ወደ ፊት ይሄንን አሰራር ከአቅጣጫ ጠቋሚ ቴክሎጂ ጋር፣ ከኪሎ ሜትር ጋር ማገናኘት ከተቻለ ደግሞ የበለጠ ተጠቃሚ ሊያደርግ ይችላል ይላሉ። የተጀመረው አሰራር እጅግ በጣም ጠቃሚ እና ውጤታማ እንደሚሆን ጥርጥር እንደሌላቸውም ነው የተናገሩት።
አዳዲስ ነገር ሲጀመር ለጊዜው ፍራቻ ይኖራል። በሂደት ግን አሰራሩን ሁሉም ሲለመድ በጣም ቀላል እንደሆነ ይታወቃል። ወደ ፊት ውጤታማ እንደሚሆን አያጠያይቅም ብለዋል። በዓለም ዙርያ በቢሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች የሞባይል ገንዘብ አገልግሎት ይጠቀማሉ። ባደጉ አገራት ብቻ ሳይሆን፤ ጎረቤት አገራት ከኢትዮጵያ በተሻለ ሁኔታ ገንዘብን በሞባይል ያዘዋውራሉ። በከተማ ብቻ ሳይሆን ገጠር ውስጥ ሳይቀር፤ የግድ ባንክ ሄዶ ገንዘብ አውጥቶ አገልግሎት ወደሚገኝበት ቦታ መሄድ አይጠበቅም። ካሉበት በእጄ ስልካቸው ይጠቀማሉ። በኢትዮጵያም በተመሳሳይ መልኩ የትም ቦታ ሆኖ የሚፈልገውን አገልግሎት ማግኘት መቻል አለበት።
ዜጎች ከነዳጅ ባለፈ በሌሎች ግብይቶች ላይም ቢጠቀሙት መልካም ነው። ምክንያቱም ለአገር ያለው አስተዋፅኦው ትልቅ ነው። ጅምር ላይ ያለ አሰራር በመሆኑ የተለያዩ ችግሮች ሊያጋጥሙ ይችላሉ የሚሉት አቶ አበበ፤ የኢንተርኔት አቅርቦት ክፍያ፣ የኃይል አቅርቦት ክፍያ ብቻ ሳይሆን በሌሎች ተቋማት ላይም በመተግበር አገራዊ ተቋማት በመተጋገዝ እና ኃላፊነታቸውን በአግባቡ በመወጣት ቴክኖሎጂው በአግባቡ ሥራ ላይ እንዲውል መስራት አለባቸው። በዚህ መልኩ ከተሰራ ምንም የማይቀረፍ ችግር አይኖርም። ይሄ የሞባይል የክፍያ ስርዓት በአዲስ መልክ እንደመጣ ሁሉ ለሚያጋጥሙ ችግሮች ፈጠራ የታከለበት መንገድ ተጠቅመን ከሰራን ውጤታማ እንሆናለን ብለዋል።
ቴክኖሎጂው በኢትዮጵያ ሲተገበር ገና አዲስ ከመሆኑ አንፃር ምን ምን ችግር ያጋጥማል? ማወቅ የሚቻለው የሚለውን በሂደት ነው፤ ከአሁኑ ሁሉንም ችግር ዘርዝሮ እንዲህ እና እንዲያ ነው ማለት አይቻልም። ጥቅም እና ጉዳት አለው። ግን የትኛው ይበልጣል ወይም ሚዛን ይደፋል የሚለው ትልቁ ነገር በመሆኑ ጠቃሜታው ከፍተኛ መሆኑን አምኖ እና ቴክሎጂውን ተቀብሎ ችግሮችን እየተቋቋሙ መስራት ተገቢ እንደሆነ ተናግረዋል።
በአጠቃለይ የቴክኖሎጂ እድገት በጨመረ ቁጥር የኢኮኖሚ እድገት በዛው መጠን ይጨምራል። ስለዚህ ይህንን የኦንላይን የግብይት ስርዓት ወደ ሁሉም የገበያ መስኮች ማስፋት መቻል አገራዊ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳው ከፍተኛ እንደሆነ ባለሙያዎቹ ገልፀዋል።
ክብረአብ በላቸው
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሚያዝያ 24 ቀን 2015 ዓ.ም