. ከበልግ ወቅት 24 ሚሊዮን ኩንታል ሰብል ለማምረት ታቅዶ እየተሠራ ነው
. የበጋ ስንዴ መስኖ ልማት አዝመራ የመሰብሰቡ ሥራ ተጠናክሯል
የኢትዮጵያ የሰብል ልማት በዋናነት በመኸርና በበልግ ወቅቶች ይከናወናል፤ ከቅርብ አመታት ወዲህ ደግሞ የበጋ ስንዴ መስኖ ልማት ሥራም እነዚህን ወቅቶች ተቀላቅሏል:: መንግሥት የግብርናውን ዘርፍ ምርትና ምርታማነት ይበልጥ ለማሳደግ በሦስቱም የግብርና ወቅቶች ላይ ሰፋፊ እቅዶችን ይዞ በትኩረት ይሠራል::
ዘመናዊ ቴክኖሎጂ በመታገዝ ጭምር መካሄድ በጀመረው በዚህ የግብርና ሥራ ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ እየታቸለ ነው:: በግብርና ሚኒስቴር የ2015 በጀት ዓመት የዘጠኝ ወራት ዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርት ላይ የተመለከተውም ይህንኑ ይጠቁማል::
በሪፖርቱ ላይ እንደተጠቆመው፤ በበጀት ዓመቱ በ2014/2015 የምርት ዘመን በሰብል ልማት በአነስተኛ አርሶ አደሮች በመኸር 13 ነጥብ 8 ሚሊዮን ሄክታር በማልማት 472 ሚሊዮን ኩንታል ለማምረት ታቅዶ 14 ነጥብ 7 ሚሊዮን ሄክታር (ከመቶ ፐርሰንት በላይ) መሬት በሰብል መሸፈን ተችሏል:: አዝመራው ከተሰበሰበው 14 ነጥብ 43 ሚሊዮን ሄክታር መሬትም 480 ሚሊዮን ኩንታል (ከመቶ ፐርሰንት በላይ) ምርት ተገኝቷል:: ከዚህ ውስጥ የአነስተኛ አርሶ አደሮች የአዝርዕት ሰብል 13.4 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ለማልማት ታቅዶ 14 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በዘር ተሸፍኗል:: ከዚህም 393.3 ሚሊዮን ኩንታል (99.9 በመቶ) ምርት ማግኘት ተችሏል::
ግብርናው የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ብቻ የሚሠራበት አይደለም፤ ለአገሪቱ የውጭ ምንዛሬ ማግኘት አስተዋጽኦ በማድረግም ይታወቃል፤ ከግብርናው ዘርፍ በርካታ ምርቶች ለውጭ ገበያ እየቀረቡ ሲሆን፣ ዘንድሮ ደግሞ የስንዴ ምርትም የውጭ ገበያውን ተቀላቅሎታል:: ከውጭ የሚገባ የስንዴ ምርት በአገር ውስጥ መተካትም ተችሏል::
እንደሚታወቀው ያለንበት ወቅት የበልግ እርሻ የሚካሄድበት ነው:: የበልጉ ዝናብ ወራትን ለዘለቀ ጊዜ እየጣለ ይገኛል:: የበልግ አብቃይ አካባቢ አርሶ አደሮችና ሌሎች የግብርናው ዘርፍ ተዋንያንም በመኸር እና በበጋ መስኖ ወቅት እየተደረገ እንዳለው ሁሉ በዚህ የምርት ወቅትም ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ሰፊ ርብርብ እያደረጉ ናቸው::
በልግ አብቃይ የሆኑት የአማራ፣ ኦሮሚያ፣ ሲዳማ፣ ደቡብና ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ አካባቢዎች በአሁኑ ወቅት በሰፊ የግብርና ሥራ ላይ ተጠምደዋል፤ እንደ አገርም በእነዚህ አካባቢዎች ለሚደረገው የበልግ እርሻ ሥራ ሰፊ ዝግጅት ተደርጎ ነው ወደ ሥራ የተገባው::
በሌላ በኩል ደግሞ ወቅቱ የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት የሚካሄድበትና አዝመራ መሰብሰብ የተጀመረበትም ነው:: የመኸር እርሻ የሚጀመርበትም ወቅት ነው:: በተለይ እየጣለ ያለው ዝናብ ለበልጉ ወቅት ብቻ ሳይሆን የመኸር እርሻውን ለመጀመር ምቹ ሁኔታ የተፈጠረ ሊባል የሚችል ነው:: የግብርና ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነትና ኮሚኒኬሽን ሥራ አስፈጻሚ አቶ ከበደ ላቀው በሰጡን ማብራሪያ እንደ አገር በእነዚህ ሦስት የግብርና ሥራዎች ላይ ሰፊ ርብርብ እየተደረገ ይገኛል::
የበልግ ወቅት
እንደ አቶ ከበደ ገለጻ፤ እንደ ግብርና ሚኒስቴር በእዚህ የበልግ ወቅት የታቀደው ሁለት ነጥብ አራት ሚሊዮን ሄክታር መሬት ለማልማት ነው:: እስከ መጋቢት 30 ቀን 2015 ዓ.ም ድረስ ሁለት ነጥብ ሦስት ሚሊዮን ሄክታር መሬት ታርሷል:: ከዚህ ውስጥም አንድ ነጥብ አራት ሚሊዮን ሄክታሩ በዘር ተሸፍኗል:: ቀሪዎቹ ደግሞ በዚህና በቀጣዩ ወራት ይሸፈናሉ::
በእቅድ ለማልማት ከተያዘው መሬትም ወደ 24 ሚሊዮን ኩንታል ምርት እንደሚጠበቅ ሥራ አስፈጻሚው ይገልጻሉ:: በእነዚህ በልግ አብቃይ አካባቢዎች በዋናነት የሚመረቱት በቆሎ፣ ማሽላ ስንዴና ጤፍ መሆናቸውን አስታውቀው፣ ማሳዎቹም በእነዚህ የእህል ዘሮች እየተሸፈኑ መሆናቸውን ነው ያመለከቱት::
እሳቸው እንዳሉት፤ በተያዘው እቅድ መሠረት ሁለት ነጥብ አራት ሚሊዮን ሄክታር በዘር ለመሸፈን ከተያዘው እቅድ፣ እስከ አሁን ባለው አፈጻጸም ወደ 64 በመቶውን በመዘር መሸፈን ተችሏል:: በቀሪዎቹ ወራትም (በሚያዝያ እና ግንቦት) የግብርና ሥራው ተጠናክሮ ይቀጥላል፤ ምክንያቱም የግብርና ሥራ ከወቅት እና ከዝናብም ጋር የሚሄድ ስለሆነ በቀጣይ ደግሞ የቀረውን በእቅድ የተያዘ መሬት አርሶ፣ አለስልሶ በዘር ሸፍኖ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ይሠራል::
ይህን ለማድረግ ደግሞ ከክልል እስከ ዞን ወረዳ ድረስ ያለው ሠራተኛና አመራሩ ሁሉም በአገር ደረጃ በበልግ ወቅት የታቀደውን ምርት ለማግኘት በቅንጅት ርብርብ እያደረጉ ናቸው:: ይህ ሥራ በመኸርም በበጋ መስኖ ስንዴ ልማቱም ተጠናክሮ ይቀጥላል:: የእነዚህ ሦስቱ የእርሻ ወቅቶች በተቀናጀ መልኩ መፈጸም የአገሪቱን ምርትና ምርታማነት በማሳደግ በምጣኔ ሀብቱ ላይ የሚኖረው ድርሻ ወሳኝ ይሆናል::
በአገሪቱ የበልግ ዝናብ ተጠናክሮ ቀጥሏል:: በበልግ ዝናብ መዘግየትና መጥፋት የተነሳ ለድርቅ ተጋልጠው በቆዩ አካባቢዎች ሁሉ ጥሩ ዝናብ እንዳለ ተረድተናል ያሉት አቶ ከበደ፣ አርሶ አደሮቹን የመደገፍና የማቋቋም ሥራዎች በግብርና ሚኒስቴር በኩል በስፋት እየተካሄዱ ናቸው ሲሉም ጠቁመዋል:: ለሰዎች የቁሳቁስ፣ የምግብ፣ ለእንስሳትም የመኖ፣ የመድኃኒት አቅርቦት እየተደረገ ነው:: ከ300 ሚሊዮን ብር በላይ በአጠቃላይ በሶማሌ፣ በኦሮሚያና ደቡብ ክልል በድርቁ የተነሳ ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች ግብርና ሚኒስቴር ከልማት አጋሮች ጋር በመሆን ድጋፍ አድርጓል ሲሉም አብራርተው፣ የባለሙያ ድጋፍ በማድረግ ላይም በስፋት እየተሠራ መሆኑን ጠቁመዋል::
ምክንያቱም ከዝናቡ ጋር ተያይዞ በሽታ እንዳይሰከትና የበለጠ ጉዳት እንዳያደርስ የግብርና የአንስሳት ባለሙያዎች እዚያው በቅርበት ሆነው ይህን ድጋፍ የሚያደርጉ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ በቀጣይም ዝናቡ የሚጠናከር ከሆነ በዚህም ላይ በሰፊው ይሠራል ብለዋል::
የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት
በሚኒስቴሩ የዘጠኝ ወራት የሥራ አፈጻጸም ላይ እንደተመለከተው 2014/15 ምርት ዘመን በመስኖ አንድ ነጥብ ሰባት ሦስት ሚሊዮን ሄክታር መሬት ላይ ሰብል ለማልማት ታቅዶ ሁለት ነጥብ ሁለት ሰባት ሚሊዮን ሄክታር (ከእቅድ በላይ) በዘር መሸፈን ተችሏል::
ከዚህ ውስጥ ከውጭ የሚገባውን የስንዴ ምርት በአገር ውስጥ ለመተካት የተቀመጠውን አገራዊ ግብ ለማሳካት የመስኖ ስንዴ ልማቱ /በአማራ፣ በኦሮሚያ፣ በደቡብ፣ ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ፣ በሲዳማ፣ በሶማሌ፣ በጋምቤላ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝና በአፋር ክልሎች/ እየተካሄደ ይገኛል:: በዚህም በአጠቃላይ አንድ ነጥብ ሦስት ሁለት ሚሊዮን ሄክታር መሬት በዘር በመሸፈን 52 ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ ለማግኘት ታቅዶ አንድ ነጥብ ሦስት ስድስት ሚሊዮን ሄክታር /ከመቶ ፐርሰንት በላይ/ መሬት በዘር መሸፈን ተችሏል::
ይህም አዝመራ በባህላዊና ዘመናዊ መንገድ እየተሰበሰበ ነው፤ በባህላዊ ዘዴ 274 ሺ 853 ሄክታር በዘመናዊ ዘዴ ደግሞ 62 ሺ 852 ሄክታር በድምሩ 337 ሺ 705 ሄክታር መሬት ላይ በበጋ መስኖ የለማ የስንዴ አዝመራ ተሰብስቧል፤ በዚህም 7 ሚሊዮን 849 ሺ441 ኩንታል ምርት ተገኝቷል:: በባህላዊ ዘዴ ከተሰበሰበው 274 ሺ 853 ሄክታር መሬት ላይ የተሰበሰበው ስንዴ ገና እንዳልተወቃ ሪፖርቱ ጠቁሟል:: የምርት መሰብሰቡ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ሥራ አስፈጻሚው ጠቁመዋል::
ከበልግ ዝናብ ጋር በተያያዘ በአንዳንድ አካባቢዎች በደረሰ የበጋ መስኖ ስንዴ አዝመራ ላይ ትንሽ ጉዳት የደረሰበት ሁኔታ ቢኖርም፣ ዝናቡ አዝመራውን እንዳያበላሽ የመሰብሰቡን ሥራ አጠናክረን እንቀጥላለን ያሉት አቶ ከበደ፣ ስለዚህ በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት 52 ሚሊዮን ኩንታል እናገኛለን ብለን ያቀድነው ላይ ለመድረስ ሰፊ ሥራ እየተሠራ ነው ብለዋል::
በደረሰ የበጋ መስኖ አዝመራ ላይ ዝናቡ ጉዳት እንዳያደርስ አርሶ አደሩ ቶሎ ቶሎ እንዲሰበስብ የማድረግ ሥራ እየተሠራ መሆኑንም አቶ ከበደ አስታውቀዋል:: ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱም የደረሰ የበጋ መስኖ ስንዴ አዝመራ በዝናቡ እንዳይበላሽ አርሶ አደሩ በአስቸኳይ እንዲሰብሰብ እንዲደረግ በማህበራዊ ሚዲያ ገጾቹ እያሳሰበ ይገኛል ነው ያሉት::
ዝናቡ ወቅቱን ያልጠበቀ አይባልም፤ ወቅቱ የበልግ ወቅት ነው:: እኛ ደግሞ በመስኖ የዘራነው የበጋ መስኖ ስንዴ አዝመራ አለ:: በእሱ ላይ የከፋ ጉዳት እንዳይደርስ የደረሰውን ቶሎ ቶሎ የመሰብሰብ ሥራ እንዲሠራ ምክረ ሀሳብ እየተሰጠ ነው ሰሉ ገልጸዋል::
የአፈር ማዳበሪያ አቅርቦት
ከግብርና ሥራዎቹ ጋር በተያያዘ መነሳት ያለበት ትልቁ ጉዳይ የግብአት አቅርቦት ነው:: አቅርቦቱን በሁለቱም የምርት ወቅቶች አርሶ አደሩ የአፈር ማዳበሪያ እንዲጠቀም ተደርጓል:: በዚሁ መሠረት ለበልግ 533 ሺ 681 ነጥብ ሰባት ኩንታል ማዳበሪያ ለአርሶ አደሩ ቀርቧል:: ለበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ደግሞ አንድ ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ኩንታል ጥቅም ላይ እንዲውል ተደርጓል:: በድምሩ ሁለት ነጥብ ሦስት ሚሊዮን ኩንታል ጥቅም ላይ ውሏል::
በልጉን ስንጨርስ ወደ መኸር እንገባለን:: ወደ መኸር ስንገባ ምርታማነትን ለማሳደግ የሚያስፈልገን ትልቅ ግብአት ማዳበሪያ መሆኑ ይታወቃል ያሉት ሥራ አስፈጻሚው፣ በዚህ መሠረት 12 ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ግዥ ተፈጽሟል:: የከረመ/ አገር ውስጥ የነበረ/ ወደ ሁለት ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ኩንታል አለ:: በድምሩ 15 ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ለምርት ዘመኑ ጥቅም ላይ እንዲውል እየተሠራ ነው ሲሉ አብራርተዋል::
እንደ እሳቸው ገለጻ፤ ከውጭ አገር የተገዛው 12 ነጥብ ስምንት ሚሊዮን የአፈር ማዳበሪያ ወደ አገር ውስጥ የማጓጓዝ ሥራዎች በስፋት እየተሠሩ ናቸው:: በዚሁ መሠረት ከአምስት ነጥብ አንድ ሚሊዮን በላይ የአፈር ማዳበሪያ ወደ አገር ውስጥ ማእከላዊ መጋዘን ገብቷል፤ ከዚያም ወደ ክልሎች፣ ክልሎች ደግሞ በማህበራትና ዩኒየኖች በኩል ወደ አርሶ አደሩ እንዲደርስ የማድረግ ሥራ እየተከናወነ ይገኛል:: ይህም ተጠናክሮ እንዲቀጥል በማድረግ ወደ አርሶ አደሩ ተደራሽ የማድረግ ሥራዎች ይሠራሉ::
በ2015/16 የምርት ዘመን ለየት የሚለው ነገር በማዳበሪያ ግዥው ላይ መንግሥት የ21 ቢሊዮን ብር ድጎማ ማድረጉ ነው:: በዚህም የማዳበሪያ ዋጋ በአንድ ኩንታል የአንድ ሺ አምስት መቶ ስልሳ ብር ቅናሽ ይኖረዋል ማለት ነው:: ስለዚህ አርሶ አደሩ በአፈር ማዳበሪያ ግዥ በኩል ጫና እንዳይፈጠርበት በሚል መንግሥት የተወሰነ ኃላፊነቱን በመውሰድ ድጎማ አድርጓል:: ለማዳበሪያ የተደረገው ድጎማም ካለፈው አመት ድጎማ የስድስት ቢሊዮን ብር ብልጫ አለው ሲሉ አብራርተዋል::
ይህ እንግዲህ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ በሚደረገው እንቅስቃሴ መንግሥት እያደረገ ያለው ድጋፍ ተጠናክሮ መቀጠሉን ያመለክታል:: በየደረጃው ያለው አመራርና መላ አርሶአደር ይህን ግንዛቤ ውስጥ በማስገባ ሰፊ እንቅስቃሴ ውሰጥ መግባት ይኖርበታል ብለዋል::
የግብርና ሜካናይዜሽንና ኩታ ገጠም
በመኸር ላይ የሚታየው የግብርና ሜካናይዜሽን አጠቃቀም በበልጉም ይሠራበታል:: በሜካናይዜሽን የማረሱ፣ የማለስለሱ፣ የመዝራቱ፣ የመሰብሰቡ ሁኔታዎች ልክ እንደ መኸሩ ሁሉ በበልጉም በተጠናከረ መልኩ ይሠራበታል::
የኩታ ገጠም እርሻም በመኸሩ፣ በበጋ መስኖ ስንዴ ልማቱም የሚሠራበት እንደመሆኑ በበልጉም ወቅት ይሠራበታል:: ሜካናይዜሽንን እያሰፋን ነው የምንሄደው:: ግብርናውን የማዘመን፣ ሜካናይዝድ የማድረግ እንቅስቃሴ በስፋት እየተሠራበት እንደመሆኑ በዚህም ላይ በትኩረት ይሠራል ሲሉም ሥራ አስፈጻሚው አስታውቀዋል:: በመኸርም፣ በበልግም በበጋ መስኖም ላይ በስፋት ይሠራበታል:: ሜካናይዜሽኑ እየጨመረ ነው የመጣው:: በቴክኖሎጂ በኩል የአርሶ አደሩም የባለሙያውም ፍላጎት እየጨመረ መጥቷል:: መንግሥትም በተቻለው አቅም አርሶ አደሩ የዘመናዊ ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ እንዲሆን በቅርበት እየሠራ ነው ሲሉ አስታውቀዋል›::
ኃይሉ ሣህለድንግል
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 23/2015