ለምርት ዘመኑ የግብርናው ዘርፍ ዕቅድ ስኬት

መንግሥት በሀገሪቱ ምጣኔ ሀብት ላይ ከፍተኛ ለውጥ እንደሚጣ በትኩረት ከሚሠራባቸው ዘርፎች መካከል ግብርናው በዋናነት ይጠቀሳል:: ዘርፉ የምግብ ዋስትና ማረጋገጫ፣ የውጭ ምንዛሬ ምንጭ፣ የሥራ እድል የአርሶ አደሩ የኑሮ መሰረት፣ ወዘተ መሆኑም ይታወቃል::

ሀገሪቱ ለምትልገው ዘላቂ ልማት እምቅ አቅም አሏቸው ከሚባሉት ዘርፎች መካከልም ይሄው ግብርና በዋናነት ይጠቀሳል:: ለእርሻ ሊውል በሚችል መሬት፣ ለመስኖኖ ለመሳሰሉት ሊውል በሚችል የውሃ ሀብት፣ በአየር ጠባይ፣ በሰው ሀብት ወዘተ፣ በኩል ሲታሰብም እንዲሁ ግብርና ትልቅ አቅም ያለው ነው::

የሀገሪቱ የምጣኔ ሀብት መሰረት ሆኖ የኖረው ግብርና ባለው በእዚህ ሁሉ እምቅ አቅም በቀጣይም ለምጣኔ ሀብቱ መዋቅራዊ ሽግግር እውን መሆን ትልቅ ፋይዳ እንደሚኖረውም ታምኖ በትኩረት እየተሠራበት ይገኛል::

መንግሥት ይህን ሁሉ ታሳቢ በማድረግ ባለፉት ዓመታት በዘርፉ ላይ በትኩረት ሰርቶ እምርታዊ ለውጦችንም ማስመዝገብ ተችሏል:: ማሳ እንዲሁም ኩታ ገጠም እርሻን በማስፋፋት፣ ማዳበሪያ በድጎማ በማቅረብ፣ ሜካናይዜሽንን በማስፋፋት፣ ለሜካናይዜሽንና ለመሳሰሉት አገልግሎት የሚውል የፋይናንስ አቅርቦት እንዲመቻች በማድረግ፣ በስንዴ ልማት አተኩሮ በመሥራት ለውጥ ለማምጣት በሰፊው ተንቀሳቅሷል::

እነዚህ ሥራዎች ውጤታማ ሆነዋል:: የእርሻ ማሳ ተስፋፍቷል:: መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፤ የእርሻ ማሳው ከነበረበት ከ17 ሚሊየን ሄክታር ወደ 20 ሚሊየን አድጓል:: የኩታ ገጠም እርሻም እንዲሁ በየዓመቱ እየተስፋፋ ይገኛል::

ለሜካናይዜሽን የተሰጠውን ትኩረት ተከትሎ በትራክተር የማረስ ምጣኔን 25 በመቶ ማድረስ ተችሏል፤ ይህም በቅርቡ ለአርሶ አደሩ የቀረቡ የሜካናይዜሽን ማሽነሪዎችን አይጨምርም/በኦሮሚያ ክልል ብቻ ከ1400 በላይ ትራክተሮችና ተቀጥላዎቻቸው በቅርቡ ተሰራጭተዋል/ በሌሎችም ክልሎች ተመሳሳይ ሥራዎች ተሠርተዋል:: ይህም ምጣኔው ከፍ እንዲል ሊያደርገው ይችላል::

በስንዴ ልማት እምርታዊ ለውጦች እየተመዘገቡ ናቸው:: በሀገሪቱ የስንዴ መስኖ ልማት ወደ ሥራ ከገባ ወዲህ አርሶ አደሩ ዓመቱን በሙሉ የሚሠራበት ሁኔታም ተፈጥሯል:: ውጤቱም ይህንን ሁሉ ተከትሎ የመጣ ነው::

መረጃዎች እንደጠቆሙት፤ ባለፈው ዓመት ብቻ በበጋ፣ በመስኖና በበልግ እርሻ 300 ሚሊየን ኩንታል ስንዴ ማምረት ተችሏል:: ይህም ሀገሪቱን በአፍሪካ ግንባር ቀደሟ ስንዴ አምራች እስከ መሆን አድርሷታል::

በየዓመቱ የሚመረተው የስንዴ መጠንም እየጨመረ ይገኛል:: በ2016 የምርት ዘመን በስንዴ ልማት ከቀደመው ዓመት የተሻለ ምርት ተገኝቷል:: አምና በመኸር ወቅት 122 ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ የተመረተ ሲሆን፤ ዘንድሮ ወደ 152 ሚሊዮን ኩንታል ተመርቷል:: ይህም የ30 ሚሊዮን ኩንታል ብልጫ እንዳለው ያሳያል::

ሀገሪቱ በአጠቃላይ በሰብል ምርትና ምርታማነት ዕድገት በየዓመቱ ከፍተኛ ለውጥ እያስመዘገበች ትገኛለች:: ባለፈው የምርት ዘመን 505 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ነበር የተሰበሰበው፤ ዘንድሮ ከዚህ የሚልቅ 610 ሚሊየን ኩንታል ምርት መሰብሰብ ተችሏል::

በቡና ልማትና ግብይትም እምርታዊ ለውጥ ማስመዝገብ ተችሏል፤ በቡና ተከላ ጉንደላና ግብይት ላይ በተከናወኑ ሥራዎች በዓመት ከ700 ቢሊየን ዶላር በላይ ያልነበረው ወደ ውጪ ከተላከ ቡና የሚገኘው የውጭ ምንዛሬ በ2017 በጀት ዓመት ዘጠኝ ወራት ብቻ ከሁለት ቢሊየን ዶላር በላይ ደርሷል:: እነዚህ ለማሳያ የቀረቡ ናቸው፤ የዘርፉን ስኬት እዚህ ዘርዝሮ መጨረስ አይቻልም::

በተያዘው 2017 በጀት ዓመትም ይህን ስኬትና ሥራ አጠናክሮ ለማስቀጠል በትኩረት ተሠርቷል፤ እየተሠራም ይገኛል::

ሰሞኑን የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ‹‹ሰላምን በዘላቂነት ለማጽናት›› በሚል ባወጣው መግለጫ ላይ እንደተጠቆመው፤ በ2017 በጀት ዓመት በግብርናው ዘርፍ እምርታዊ ለውጥ ለማስመዝገብ ሲሠራ ቆይቷል፤ እየተሠራም ነው::

በመግለጫ እንደተመላከተው፤ መንግሥት ኢኮኖሚያዊ እመርታ እንዲመጣ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ ከሚሠራባቸው ተግባራት አንዱ ግብርና ነው። በዚህም የበጋና በልግ ወቅት የግብርና ሥራዎች፣ የስንዴ ምርታማነትን ማሳደግ፣ የአካባቢ ጥበቃ፣ የግብዓት አቅርቦትና የሌማት ትሩፋት ኢንሼቲቮች እና ሌሎችም በርካታ መርሐግብሮች በትግበራ ላይ ይገኛሉ። በዚህም እምርታዎች እየተመዘገቡ እንደሚገኙ መግለጫ ጠቁሟል::

መግለጫው እንዳብራራው፤ በ2017 ዓ.ም የምርት ዘመን መንግሥት የምግብ ሉዐላዊነትን ለማረጋጋጥ በትኩረት በተሠራበት የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት የተሻለ እምርታ አሳይቷል፤ በተለይ የውሃ አማራጮችን አሟጦ በመጠቀም የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ ባለፈ ስንዴን ከራስ አልፎ ለውጭ ገበያ ለማቅረብ የሚያስችል ዕድል ፈጥሯል።

በበጀት ዓመቱ አራት ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ሄክታር መሬት በበጋ ስንዴ ለማልማት ታቅዶ፣ ከዚህ ውስጥ ሶስት ነጥብ አራት ሚሊዮን ሄክታር መሬት በዘር በመሸፈን ከ 66 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት መሰብሰብ ተችሏል ብሏል።

በ2017 የበልግ አዝመራ ወቅትም እንዲሁ በልግ አብቃይ በሆኑ አካባቢዎች ሁለት ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ሄክታር መሬት በዘር መሸፈን የተቻለ መሆኑን ገልጾ፣ ከዚህም ውስጥ 235 ሺህ ሄክታር በክላስተር (ኩታ-ገጠም) የአስተራረስ ዘዴ የተሸፈነ መሬት መሆኑን ጠቅሷል።

ኩታ ገጠም እርሻ ለምርታማነትና ገበያ ትስስር የሚኖረው ድርሻ ከፍተኛ መሆኑን አመልክቶ፣ እና በልግ አምራች በሆኑ የሀገሪቱ አካባቢዎች በዚህ ዓመት የተሻለ የዝናብ ሁኔታ በመኖሩ ጥሩ ምርት ይገኛል ተብሎ ይጠበቃል ብሏል። በቀሪው የበልግ ወቅት በሚከናወኑ ሥራዎች ላይ ልዩ ትኩረት መስጠትና መረባረብ እንደሚጠበቅም አስገንዝቧል።

መግለጫው እንዳመለከተው፤ ባለፉት ወራት የነበረው የዝናብ መጠንና ስርጭት የበልግ የግብርና ሥራዎችን ለማከናወን፤ ተፋሰሶች በቂ ውሃ እንዲይዙ፤ የአርብቶ አደሩና ከፊል አርብቶ አደሩ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት እንዲሻሻልና የእንስሳት መኖ አቅርቦትም እንዲኖር ከፍተኛ ፋይዳ ነበረው።

በቀጣይም የበልግ ወቅት የመጨረሻ ወር የዝናብ ስርጭትን በአግባቡ መጠቀም ያስፈልጋል። በተለይ የበልግ ወቅት የመጨረሻ ጊዜያት የዝናብ ስርጭት ሊዋዥቅና ሊለዋወጥ ስለሚችል የደረሰ ሰብልን ቀድሞ በመሰብሰብ ጥቅም ላይ ማዋል ያስፈልጋል። በሌላ መልኩ ይህ የአየር ጸባይ ለወባ ትንኝ መራባት ምቹ ሁኔታ ሊፈጥር ስለሚችል ማኅበረሰቡ አካባቢውን የማጽዳት እና የታቆሩ ውሃዎችን የማፋሰስ ተግባር ማከናወን ይጠበቅበታል።

የአርሶ አደሩን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግና በምግብ እህል ራስን ለመቻል፣ የሀገሪቱን የግብርና ምርት በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ ለማድረግ እና ለሀገር ውስጥ ኢንዱስትሪዎች በቂ ምርት ማቅረብ እንዲቻል የምርት ማሳደጊያ ግብዓቶችን በተደራጀ ሁኔታ ማቅረብ፣ ማሰራጨትና መጠቀም እንደሚገባ አስገንዝቧል:: ከዚህ አንጻር መንግሥት የአፈር ማዳበሪያ አቅርቦትንና የምርጥ ዘርን ስርጭት ለማሻሻል በትኩረት እየሥራ ይገኛል ብሏል።

የማዳበሪያ አቅርቦትን አስተማማኝ ለማድረግ ዘንድሮ ለማዳበሪያ ግዥ ብቻ አንድ ነጥብ ሶስት ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር መመደቡን ያስታወቀው መግለጫው፣ ለዘንድሮ የምርት ዘመን (2017/18) የሚገዛው የማዳበሪያ መጠን ካለፈው የምርት ዘመን የማዳበሪያ ግዥ ጋር ሲነጻጸር የአራት ነጥብ ስድስት ሚሊየን ኩንታል ብልጫ እንዳለው አብራርቷል።

አገልግሎቱ በመግለጫው እንዳስታወቀው፣ ለዘንድሮ የምርት ዘመን በማዳበሪያ ዋጋ ላይ የ84 ቢሊየን ብር ድጎማ ተደርጓል። ይህም በአንድ ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ መንግሥት ከአምስት ሺ ብር በላይ ድጎማ እንደሚያደረግ ያሳያል። ለቀጣይ ምርት ዘመን እስካሁን 10 ነጥብ ሚሊዮን ተጓጉዞ መድረሱን አስታውቆ፣ ከዚህም ውስጥ 39 ሚሊዮን ኩንታሉ ወደ ክልሎች በማሠራጨት ቀሪውንም በቀጣይ የማጓጓዙ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አመልክቷል።

ምርታማነትን ለማሳደግ ከማዳበሪያ በተጨማሪ የምርጥ ዘር አቅርቦት ወሳኝ ሚና ያለው መሆኑን ገልጾ፣ በዚህም ላይ መንግሥት በልዩ ትኩረት እየሠራበት እንደሚገኝም አስታውቋል። በ2017 በጀት ዓመት እስከ አሁን አንድ ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ኩንታል ምርጥ ዘር ተሰብስቦ አራት መቶ ሺህ ኩንታል ለአርሶ አደሩ ተሠራጭቷል ብሏል። ….

የግብርና ሚኒስትሩ ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) ሰሞኑን ከኢትዮጵያ ብሮድካቲንግ ኮርፖሬሽን ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ የበልግ ዘር ወቅት ተጠናቆ ሰብል የመንከባከብ ሥራ እየተካሄደ እንደሚገኝ ጠቅሰው፤ በልግን ያጠናቀቁና የመኸር ወቅት ተጠቃሚዎች ወደ መኸር እርሻ ዝግጅት መግባታቸውን ገልጸዋል::

እሳቸው እንዳሉት፤ በ2017/18 የመኸር ወቅት በአነስተኛ ማሳ ያላቸው አርሶ አደሮች ማሳ ላይ በአብዛኛው ይሠራል:: ወደ 20 ነጥብ ሶስት ሚሊየን ሄክታር ማሳ በዘር ይሸፈናል:: ከዚህ በተጨማሪ በሰፋፊ እርሻና በኢንቨስመንት የሚከናወኑ የመኸር ወቅት ሥራዎች ይኖራሉ:: እነዚህ ሲደማመሩ 21 ሚሊየን ሄክታር ማሳ በሰብል ዘር የሚሸፈን ይሆናል ብለዋል::

ከእዚህ ውስጥ ወደ 13 ሚሊየን ሄክታር በክላስተር ማሳ የሚሸፈን ይሆናል ሲሉ ጠቅሰው፣ የክለስተር እርሻ እየጨመረ ነው፤ ባለፈው ዓመት 11 ነጥብ ስምንት ሚሊየን ሄክታር ላይ ነበር፤ ዘንድሮ ወደ 13 ሚሊየን ሄክታር ከፍ ብሏል ብለዋል:: አርሶ አደሮች በኩታገጠም ሲደራጁ የቴክኖሎጂ ተጠቃሚነታቸው ምን ያህል እንደሚጭምር ተመልክተናል ሲሉም ገልጸዋል::

ሚኒስትሩ አንዳንድ አካባቢዎች በመኸር ብቻ ሁለቴ እንደሚጠቀሙ ጠቅሰው፣ ያለውን የመሬት እርጥበት በመጠቀም በቆሎ አንስተው ሌላ ሰብል የሚዘሩበት ሁኔታ እንዳለ ተናግረዋል:: በዚህም ወደ አንድ ነጥብ አራት ሚሊየን ሄክታር መሬት በዳግም እርሻ እንደሚለማ አስታውቀዋል::

በዘንድሮ የመኸር ወቅት 690 ሚሊየን ኩንታል ለማምረት እንደሚጠበቅ ጠቁመው፣ ይህም ባለፈው መኸር ከተገኘው 610 ሚሊየን ኩንታል ወደ 80 ሚሊየን ኩንታል ብልጫ ይኖረዋል ብለዋል::

ለእዚህ ምርታማነት መጨመር ምክንያት የሚሆኑትንም አያይዘው ገልጸዋል:: የኩታ ገጠም እርሻ ከአንድ ሚሊዮን ሄክታር በላይ መጨመሩን አንዱ ምክንያት መሆኑን ጠቅሰው::

በማዳበሪያ አቅርቦትም እንዲሁ ጭማሪ እንዳለው ተናግረዋል:: አሳቸው እንዳሉት፤ ባለፈው ዓመት 20 ሚሊየን ኩንታል ማዳበሪያ ነበር ጥቅም ላይ የዋለው፤ ዘንድሮ 24 ሚሊየን ኩንታል ማዳበሪያ ይቀርባል፤ እስከ አሁን 11 ሚሊየን ኩንታሉ ቀርቧል:: ሌላውም እንደየአካባቢው ሥነ ምኅዳር እየታየ የሚቀርብ ይሆናል::

ምርጥ ዘርን በተመለተከተም ሲያብራሩ ከዚህ በፊት ወደ አንድ ሚሊየን ኩንታል ነበር የምናቀርበው ሲሉ ጠቅሰው፣ ከዚህ ዓመት ጀምሮ ወደ ሁለት ሚሊየን ኩንታል ዘር ለማቅረብ ታቅዶ እየተሠራ ነው ብለዋል:: በኩታ ገጠም በማዳበሪያ በምርጥ ዘር የሚከናወኑትን አቀናጅቶ በመሥራት የተያዘውን እቅድ ለመፈጸም ርብርብ እንደሚደረግ አስታውቀዋል::

ኃይሉ ሣህለድንግል

አዲስ ዘመን ሰኞ ግንቦት 11 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You