የኢትዮጵያ ግብርና በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ከ90 በመቶ በላይ የዝናብ ጥገኛ ስለመሆኑ መረጃዎች ያመላክታሉ። ለእዚህም ግብርናውን ከዝናብ ጥገኝነት ለማላቀቅ የመስኖ አውታሮችን ለመገንባቱ ሥራ ትኩረት ተሰጥቶት ሲሠራ ቆይቷል። በዚህም በርካታ የመስኖ መሠረተ ልማቶች ተገንብተዋል። እየተገነቡም ይገኛሉ።
በአነስተኛም ሆነ በከፍተኛ ደረጃ በተገነቡ በእነዚህ የመስኖ አውታሮች ብዙ ሄክታር መሬት ለማልማት ጥረት እየተደረገ ይገኛል። ይሁን እንጂ ከፍተኛ የውሃ ክምችት የመያዝ አቅም ባላቸው የመስኖ አውታሮች ለማልማት የታሰበውና እያለማ ያለው መሬት ሲታስብ ሃሳቡና መሬት ላይ ያለው እውነታ አራምባና ቆቦ መሆኑን መረጃዎች አመላክተዋል።
በቅርቡም የኢትዮጵያ ፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት የመስኖ ልማት አውታሮችን አስመልክቶ ይፋ ያደረገው የጥናት ውጤትም ይህንኑ ያጠናክራል። በጥናቱ እንደተጠቆመው፤ በስኳር መስኖ ልማት ፕሮጀክቶች እንዲለማ ከታሰበው መሬት በታች ነው እያለማ የሚገኘው፣ ይባስ ብሎም ሥራ ያቆሙም ፕሮጀክቶች ተገኝተዋል።
ኢንስቲትዩቱ በቅርቡ መስኖ ልማት ፕሮጀክቶችን የልማት አቅምንና ፖሊሲን አስመልክቶ ያቀረቡ ይሄው ጥናት የከሰምና ተንዳሆ የስኳር መስኖ ልማት ፕሮጀክቶች ከታቀደው በታች እያለሙ መሆናቸውን ጠቁሟል።
በኢትዮጵያ ፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት የግብርናና የገጠር ልማት ተመራማሪው የጥናቱ አቅራቢ መኮንን በቀለ (ዶ/ር) እንዳሉት፤ ጥናቱ መንግሥት ብዙ ሀብት አውጥቶ የገነባቸው የመስኖ አውታሮች በምን ያህል ብቃት አገልግሎት እየሰጡ ነው። አገልግሎት የማይሰጡት ምን ያህል ናቸው የሚለውን ያሳያል፡፡፡
እሳቸው እንደሚሉት፤ ጥናቱ በከሰምና ተንዳሆ የስኳር መስኖ ግድቦች ላይ ትኩረት አድርጓል። እነዚህ ግድቦች በጣም ሰፊ አካባቢዎች ማልማት እንዲችሉ ብዙ ሀብት ወጥቶባቸው የተገነቡ ናቸው፤ ይሁንና በግድቦቹ የተያዘው ውሃ አገልግሎት እየሰጠ አይደለም።
የከሰም የስኳር መስኖ ግድብ ከስድስት ዓመታት ወዲህ በተወሰነ መልኩ በጣም መጠነኛ በሆነ ደረጃ ስኳር እያመረተ ቆይቷል። ግድቡ 20ሺ ሄክታር መሬት ለማልማት ታስቦ የተገነባ ቢሆንም፣ ሁለት ሺ 750 ሄክታር መሬት ብቻ እያለማ የነበረው። በአሁኑ ወቅት በቅርቡ ከተከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥ ጋር በተያያዘ ሙሉ ለሙሉ ሥራ አቁማል። በዚህ ሊለማ የታሰበው መሬት ባለመልማቱም ሀገሪቱ በዓመት 10 ቢሊዮን ብር ገቢ እንድታጣ ተደርጋለች።
የተንዳሆ የስኳር መስኖ ልማት ፕሮጀክት 60 ሺህ ሄክታር መሬት በመስኖ ለማልማት ታስቦ የተገነባ ነው፤ ይህ ግድብ ላለፉት ዘጠኝ ዓመታት በተወሰነ መልኩ ሲያመርት ቆይቶ ነበር። በዚህ የመስኖ ፕሮጀክት መሠረተ ልማትም እንዲሁ መልማት ያለበት መሬት አለመልማቱ ሀገሪቱ በዓመት 33 ቢሊዮን ብር ገቢ እንድታጣ የሚያደርግ ነው ሲሉ አመልክተዋል።
እነዚህ ሁለት የስኳር ፋብሪካ የመስኖ ፕሮጀክቶች መንግሥት ከፍተኛ ወጪ አውጥቶባቸው የተሠሩ መሆናቸውን ተመራማሪው ጠቅሰው፣ ከፍተኛ ምርት በማምረት ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን ሊተኩና ብዙ የሥራ ዕድል ሊፈጥሩ የሚችሉ ከመሆናቸው ባሻገርም ከኢኮኖሚው ትስስር አኳያ የጎላ ሚና ሊኖራቸው የሚችል ኢንቨስትመንቶች እንደሆኑም ያስረዳሉ።
የመስኖ ሥራ ከፍተኛ የውሃ ክምችትን የሚጠይቅና ለእዚህም ከፍተኛ ወጪ ወጥቶበት የሚሠራ መሆኑን ተመራማሪው ገልጸው፣ መንግሥት አሁንም ትኩረት ሰጥቶ ኢንቨስት እያደረገባቸው ካሉት መሠረተ ልማቶች ዋነኛው የመስኖ መሠረተ ልማት ነው ብለዋል።
ጥናቱ የመስኖ ልማት ፕሮጀክቶቹ ከመነሻው ሊቆሙ የቻሉበትን ምክንያት በማጥናት ችግሮቹን በመለየት ከአካባቢው ኅብረተሰብ፣ ከክልሉ እና ከሌሎች ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋርም በመወያየት ችግሩን ለመፍታት ታሰቦ መካሄዱን ይገልጻሉ። እነዚህ ፕሮጀክቶች ኅብረተሰቡ በሥራ ዕድል ፈጠራ፣ በሚገኘው ተረፈ ምርት እና በሌሎች መንገዶች በብዙ መልኩ ሊጠቀም የሚችል ሆኖ ሳለ አሁን ላይ ሥራ ማቆማቸው ኅብረተሰቡን በእጅጉ እንደሚጎዳም አስታውቀዋል።
ተመራማሪው እንዳብራሩት፤ በጥናቱ በስኳር መስኖ ፕሮጀክቱ ከተለዩት ተግዳሮቶች መካከል አንዱ የመስኖ ውሃ ተጠቃሚዎች ማህበራት በፋይናንስ፣ በሥልጠናና በሌሎችም ተያያዥ ችግሮች ምክንያት ጠንክረው አለመገኘታቸው ነው።
የፋይናንስ ችግር ሌላኛው ተግዳሮት ነው። ከአየር ንብረት ለውጥና ከአካባቢ ጋር የተያያዙ ተጽዕኖዎችም አሉ። ዲዛይኑና ኮንስትራክሽኑም የራሱ የሆነ ችግር ያለው ሲሆን፤ አስተዳደሩና ተቋማዊ ሁኔታው ሊፈተሹ ይገባል። እነዚህ በመስኖ ፕሮጀክቶቹ ቀጣይነት ላይ ችግር የሚፈጥሩ ማነቆዎች ናቸው።
የመስኖ ተጠቃሚ በተለይ የስኳር ፋብሪካዎች የሚፈጽሙት ክፍያ በጣም አነስተኛ መሆኑም ተጠቁሟል። አርሶ አደሮች የተወሰነ ክፍያ ቢፈጽሙም፣ ክፍያው የሚጠቀሙበትን የውሃ መጠን ከግምት ውስጥ ያስገባ እንዳልሆነም ተመላክቷል። ከእነዚህ አካላት አንዳንዶቹ ለሚጠቀሙት የውሃ መጠን የተወሰነ ክፍያ ቢፈጽሙም፣ ክፍያውን ፍራቻ ብለው ውሃ የሚቆጥቡበት ሁኔታ እንዳለም አመላክተዋል።
በፖሊሲው በተቀመጠው መሠረት የውሃ ታሪፍ እየተተገበረ አለመሆኑም ሌላኛው የመስኖ ተግዳሮት እንደሆነ ያመላክታሉ። በእነዚህ ተግዳሮቶች ላይ ተወያይቶ ሌሎች የፖሊሲ ሃሳቦች ማምጣት እንደሚያስፈልግም ጠቁመዋል።
ጥናቱ ሀገሪቷ ያሉትን ሁሉንም የመስኖ ፕሮጀክቶች ያካተተ አይደለም ያሉት ተመራማሪው፤ በተለይ የመስኖ ውሃ በሚገባ እያገኙ ባሉ የመስኖ ፕሮጀክቶች ቀጣይነት፣ የውሃ ታሪፍ ጉዳይ እንዲሁም መስኖ የሚያስተዳድሩ ተቋማት ትርፋማነት ላይ ትኩረት ማድረጉን አመላክተዋል።
በቀጣይ በሀገሪቱ በሚገኙ የመስኖ ልማት ፕሮጀክቶች (አገልግሎት እየሰጡ ባሉትም ሆነ በማይሰጡት) ዙሪያ ጥናት ለማድረግ መታቀዱን ገልጸው፤ የተገነቡትንና ሥራ ላይ ያሉትን በሚገባ ማየትና መለየት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።
በሌላ በኩል በጣም አነስተኛ የመስኖ ዓይነቶች በ2000 ዓ.ም አካባቢ በሁሉም አካባቢ በአንድ ጊዜ እንዲተገበሩ መደረጉን አስታውሰው፣ የዚህም የመጀመሪያው አፈጻጸም የራሱ ችግር እንዳለበት ይገልጻሉ። ከእነዚህ ውስጥ በጥሩ ሁኔታ ጥቅም ላይ የዋሉ እንደነበሩም አንስተው፤ እነዚህም ቢሆኑ ቀስ በቀስ በጣም የመቀነስ ሁኔታዎች እንደታየባቸው ይገልጻሉ።
በእነዚህ አነስተኛ የመስኖ ዓይነቶች አንዳንድ አካባቢዎች በግብርና ሚኒስቴር በኩል የማበረታታ ሥራ መሠራቱን ጠቅሰው፣ ይህን ተከትሎም ጥሩ ውጤት እንደመጣና ሥራው ሊበረታታ እንደሚገባም አስታውቀዋል።
በመስኖ ቴክኖሎጂዎች አቅርቦት በኩልም ችግሮች እንዳሉ ተጠቁሟል። በተለይ ፕላስቲክ ጆሞፕሬን፣ ሞተር ፓምፕና የመሳሰሉት በሚፈለገው መጠን እየተሰራጩ እንዳልሆነም ገልጸዋል።
በአንድ ወቅት መንግሥት እንደ ውሃ ፓምፕ ያሉትን ከቀረጥ ነፃ በሆነ መንገድ ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገቡ በማድረግ እያበረታታ እንደነበር አስታውሰው፣ አሁንም አንዳንድ አካባቢዎች ላይ ሥራው በጥሩ ሁኔታ እየተፈጸመ መሆኑን ተናግረዋል። በአብዛኛው ግን እንደተጠበቀው አለመሆኑን ገልጸዋል።
የውሃ ታሪፍ መሬት ላይ እንዲወርድ ሲደረግ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል ያሉት ጥናት አቅራቢው፤ የሚከፈለው ከፍተኛ ዋጋ ለሥራው ፍላጎት እንዲያጡ የሚያደርግ መሆን የለበትም ብለዋል። ከውሃ ታሪፍ የሚገኘው ፋይናንስ ለጥገና አገልግሎት የሚውል መሆን አለበት ሲሉም አስገንዝበዋል፡፡
የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር የአነስተኛ መስኖ ልማት ዳይሬክተር አቶ አሸናፊ ሊካሳ በበኩላቸው ጥናቱ ያስገኛቸውን ውጤቶችና ምክረ ሃሳቦች በግብዓትነት መጠቀም እንደሚቻል ይገልጻሉ። አንዳንዶች ደግሞ ቀደም ሲል የታዩና እየተሠራባቸው ያሉ መሆናቸውን ተናግረው፣ የጥናቱ ውጤቶች በከፍተኛ ደረጃ ግብዓት ሊሆኑ እንደሚችሉ ጠቁመዋል።
እሳቸው እንዳሉት፤ መስኖ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ግብርናውን ያግዛል። ግብርናው በቀጥታ ሆነ በተዘዋዋሪ ከ90 በመቶ በላይ የዝናብ ውሃ ጥገኛ ነው። ዝናብን ጠበቆ የግብርናን ሥራ መሥራት እምብዛም አያስኬድም፤ መስኖ መጠቀም የግድ ነው፡፡
መስኖ ከብዙ ነገሮች ጋር የተያያዘና በጣም ወሳኝ የሆነ ዘርፍ ነው ሲሉም አመልክተው፣ ውሃ በአግባቡ በማከማቸት በምንፈልገው ጊዜና መጠን ለመጠቀም፣ የዝናብ ጥገኝነትን ለመቀነስ ያስችላል፣ ምርትና ምርታማነትን ይጨምራል፤ የሥራ ዕድል ይፈጥራል። የሕዝቡን የኑሮ ደረጃም ያሻሽላል ብለዋል፡፡
የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር ከዓለም ባንክ ጋር በመተባበር ያካሄደው ጥናት እንዳለ ጠቁመው፤ ይህም ከዚህኛው ጥናት ጋር ተመሳሳይ ግኝቶችን የያዘ መሆኑን አመላክተዋል።
በቅድሚያ ያለን ሀብት ምን ያህል ነው የሚለው መታየት እንዳለበት ዳይሬክተሩ ጠቅሰው፣ እንደ ሀገር ከ30 እስከ 43 ሚሊዮን ሄክታር የሚሆን ለመስኖ ምቹ የሆነ መሬት አለ ተብሎ እንደሚገመት ተናግረዋል። ይህንን በሙሉ መጠቀም እንችላለን ማለት ላይሆን ይችላል ሲሉ አብራርተዋል፡፡
ዳይሬክተሩ፤ ያለን የውሃ መጠን ብንመለከት በምድር ላይ ያለው ውሃ 124 ቢሊዮን ሜትሪክ ኪዮብ ነው፤ ይህ ትልቅ አቅም ነው። ከዚህ ውስጥ ወደ 61 ቢሊዮን ሜትሪክ ለመስኖ ብንጠቀምበት ተብሎ የተለየ ነው። የከርሰ ምድር ውሃም ተጠንቶ ያላለቀበት ቢሆንም እምቅ አቅም እንዳለ አመላካቾች አሉ።
በአጠቃላይ አሁን ባለው መረጃ እስከ 10 ሚሊዮን ሄክታር (በምድር ውሃ 9 ሚሊዮንና በከርሰ ምድር ውሃ አንድ ሚሊዮን ) ማልማት የሚያስችል አቅም እንዳለ አመላካቾች ያሳያሉ ሲሉ ጠቁመዋል።
የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር በአዋጅ ሲቋቋም ፖሊሲ ማሻሻልና አዳዲስ ፖሊሲዎች የማዘጋጀት እንዲሁም እንደ ሀገር ቴክኖሎጂዎች በመጠቀም በመስኖ ማስፋፋት፣ ጥናቶችና ዲዛይኖች በመሥራት ግንባታ በመካሄድ እና ሌሎች በርከት ያሉ ተግባራት እንዲያከናውን ኃላፊነት እንደተሰጠው ያመላክታል። በተለይ በፌዴራል መንግሥት የሚሠሩ ትላልቅ የመስኖ ተቋማት መገንባትና የተገነቡትን የማስተዳደር ኃላፊነት እንዳለበትም ይጠቁማል፡፡
ዳይሬክተሩ፤ በአሁኑ ወቅት በሚኒስቴሩ 12 የሚሆኑ በጣም ትላልቅ የመስኖ ዲዛይን ፕሮጀክቶች እንዳሉ ተናግረው፣ 287ሺ ሄክታር የሚሆን መሬት የሚያለማ የጥናት ዲዛይን እንዳለም አመላክተዋል። በተጨማሪም 22 ኮንስትራክሽን ፕሮጀክቶች እንዳሉ ጠቅሰው፣ ፕሮጀክቶቹ ሲጠናቀቁ ከ280ሺ ሄክታር በላይ መሬት ማልማት ያስችላሉ ብለዋል፡፡
የኦፕሬሽንና ጥገና ሥራ እየተሠራ መሆኑን ገልጸው፤ በቀጣይም በተለያዩ የሀገሪቷ ክፍሎች የጥገና ማዕከላት በማቋቋም ማዕከላቱ በአካባቢያቸው ያሉትን የመስኖ አውታሮችን መጠገንና ክልሎችን ለማገዝ እንዲችሉ ለማድረግ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።
እሳቸው እንዳሉት፤ የመስኖ አዋጁ ሦስት ተቋማትን ታሳቢ ያደረገ ነው። ተቋማቱና የሚያከናውኗቸው ተግባሮችም የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር፣ የውሃ ሀብቱን ያስተዳድራል፤ ሁለተኛው የመስኖና ቆላማ ልማት ሚኒስቴር ሲሆን፣ እሱም የመስኖ መሠረተ ልማቶችን ይሠራል። ሶስተኛው የግብርና ሚኒስቴር ደግሞ የተገነቡትን የመስኖ አውታሮች ተቀብሎ ተግባር ላይ እንዲያውል ያደርጋል፡፡
እነዚህ ሦስት ተቋማት በቅንጅት እንዲሠሩ ይጠበቃል፤ መስኖ በቅንጅት የማይሠራ ከሆነ ውጤታማ መሆን አይችልም፤ ተቀራርቦ በጋራ መሥራቱ በጥናቱ የተገለጹ ችግሮችንም ለመፍታት ያግዛል።
ቀደም ሲል የመስኖ ፕሮጀክት አሠራር ከላይ ወደታች የተገናኘ እንዳልነበረ አስታውሰው፣ በዚህ የተነሳም ብዙ ተግዳሮቶች ሲገጥሙ መቆየታቸውን ጠቁመዋል። አሁን ላይ መስኖ በእያንዳንዱ ክልል የራሱ ቢሮዎች እንዲኖሩት መደረጉንም ይገልጻሉ። ፖሊሲው ላይ ያሉ ክፍተቶችን በመሙላትና ተጨማሪም መካተት ያለበትን በማካተት ለመሥራት የሚያስችሉ አስቻይ ሁኔታዎች እንዳሉም ያመላክታሉ።
ዳይሬክተሩ እንዳብራሩት፤ በመስኖ አውታሮች ከሚታዩ ተግዳሮቶች መካከል አንዱ ከተጠበቁት በታች ሆነው መገኘታቸው ነው። ለዚህም የቴክኒካል፣ የእቅድ፣ የዕውቀት ክፍተት፣ የፖሊሲ ፍሬም ወርክ እና የመሳሰሉት ምክንያቶች ይጠቀሳሉ። ሌሎቹ የቴክኒክ ተግዳሮቶች ናቸው፤ ዲዛይን ሲደረግ ጥራቱን የጠበቀ መሆን አለመሆን፣ ተቋማዊና አስተዳደራዊ፤ የፋይናንስ፤ አካባቢዊ እና የመሳሰሉት ከተግዳሮቶች መካከል ይጠቀሳሉ፡፡
ተግዳሮቶቹን ለመፍታት በመንግሥት የሚሠሩ ሥራዎች መኖራቸውን የጠቆሙት ዳይሬክተሩ፤ መልካም አጋጣሚዎች እንዳሉም ዳይሬክተሩ አመልክተዋል። መስኖን ለማስፋፋት የሚያስችል የውሃ ሀብትና መንግሥት ለመስኖ ልማት ቁርጠኛ ሆኖ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መሆኑንም አንስተዋል። አጋር አካላት ለመስኖ የሚያደርጉት ድጋፍ ከፍተኛ መሆኑንም አስታውቀዋል።
ከፖሊሲ ስትራቴጂ አንጻር ሀገር አቀፍ የመስኖ ስትራቴጂ ፕሮግራም ለመጀመር በሂደት ላይ መሆኑን ያመላክታሉ። ከተጠበቀው በታች የሆኑትን የመስኖ አውታሮች በመጠገን ውጤታማ እንዲሆኑ ለማድረግ ስትራቴጂ ተይዞ እየተሠራ መሆኑን ይገልጻሉ። የተቀናጀና ቀጣይነት ያለው የተቋማት አቅም ግንባታ ለመሥራት መታቀዱንም አስታውቀዋል። ቴክኒካል ኮድና ስታንዳርድ እንዲኖር ለማድረግ እንደሚሠራም አመላክተዋል፡፡
ውጤታማ ከሆኑት የመስኖ አውታሮች የተገኙትን ተሞክሮዎች ሌሎች ላይ ተግባራዊ ለማድረግ መታቀዱንም ገልጸዋል። የመስኖ አውታሮች መገንባት ብቻ ሳይሆን የኦፕሬሽን ጥገና መስጠትንም አብሮ ለማስኬድ ታቅዶ እየተሠራ እንደሚገኝም አስታውቀዋል።
ወርቅነሽ ደምሰው
አዲስ ዘመን ሰኞ ግንቦት 18 ቀን 2017 ዓ.ም