
ኢትዮጵያ ከእንስሳት ሃብት ተገቢውን ጥቅም እያገኘች አይደለም። አሁን ደግሞ በእንስሳት ገበያ ላይ መሠረታዊ ጥያቄ ተነስቷል። ሀገራት የእንስሳት ልየታና ክትትል ሥርዓት ምዝገባ ያልተካሔደበትን እንስሳም ሆነ የእንሰሳ ምርት እንደማይገዙ እያሳወቁ ናቸው። ለእዚህ ዋነኛው ምክንያት ልየታ እና ምዝገባው የእንስሳት ምርት ግብይት ላይ ለሚያጋጥሙ ችግሮች ሁነኛ መፍትሔ ያመጣል ብለው በማመናቸው ነው።
ይህንኑ በተመለከተ የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ወጪ አስተዳደር እና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በኢትዮጵያ የግብርና ባለስልጣን የእንስሳት ቄራዎች አደረጃጀት እና የስጋ ምርት አገልግሎት አሰጣጥ ውጤታማነት በተመለከተ የተከናወነ ክዋኔ ኦዲት ሪፖርትን መነሻ በማድረግ ጥያቄ አቅርቧል።
ለገበያ የሚቀርበውን የእንስሳት ምርት ጥራትና ጤንነት ለመከታተልና ለመቆጣጠር የሚያስችል አሠራር ሥርዓትን በተመለከተ በቋሚ ኮሚቴዋ አባል አያንቱ ጉተታ ጥያቄ ቀርቧል። የእንስሳት ልየታና ክትትል ሥርዓት ምዝገባ ማካሔድ ላይ ክፍተት መኖሩ በክዋኔ ኦዲት ለማወቅ ተችሏል። በተጨማሪ ከዛው ጋር በተያያዘ እንደ ሀገር ከበሽታ ነፃ የሆነ ቀጠና መፍጠር አለመቻሉ መታወቁን በማስታወስ፤ በተለይም አፈተግር (foot and mouth disease) የተባለ በሽታ መኖሩ ታውቋል። የርቢ ጣቢያ /commercial ranch/ አለመኖሩም እንደተረጋገጠ አስታውሰው፤ በእነዚህ ላይ ለምን መሥራት አልተቻለም የሚል ጥያቄ አቅርበዋል። አለመሠራቱ በገበያ ላይ የመዳረሻ ገበያን ማስፋት እንዳይቻል ምክንያት መሆኑ፤ የኦዲት ግኝቱ አመላክቷል ሲሉ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ግብርና ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አምባሳደር ድሪባ ኩማ በበኩላቸው በሰጡት ምላሽ፤ በእንስሳት ምርት እና ግብይት ላይ ያለውን ችግር አስመልክቶ እንደተናገሩት፤ አሁን ላይ ከብት ታርዶ ምኑም ሳይታወቅ ስጋው ወደ ውጪ መላክ አይቻልም። ሆኖም እስከ አሁን የተለመደው አካሔድ ይሔ ነበር። አሁን ገበያው ላይ ለመሳተፍ የእንስሳት አረባብ ሥርዓቱ ከዝርያ ጀምሮ መታወቅ አለበት። ሀገሮች የሚፈልጉት የእንስሳት ዝርያ እና የስጋ ዓይነት የተለየ ነው።
በተጨማሪ ብዙ አይነት የከብት በሽታዎች በመኖራቸው፤ በዓለም ደረጃ ተቀባይነት ለማግኘት ሥጋውም ሆነ የቁም እንስሳው ከበሽታ ነፃ መሆናቸውን ማረጋገጥ ግዴታ ነው። እንደተገለፀው የአፍ እና የእግር በሽታ አለ። ስለዚህ ክትባት የሚፈልጉ ከብቶች አሉ። የተከተቡት መታወቅ አለባቸው ሲሉ ገልፀዋል።
በሽታው ላይ ብቻ ሳይሆን የአመጋገብ ሥርዓትን ጨምሮ በኢትዮጵያ በደንብ አልተሠራም። የሚሉት አምባባሳደር ድሪባ፤ ከናሚቢያ፣ ከሞንጎሊያ እና ከብራዚል የተገኘው ተሞክሮ እንደሚያመለክተው አንድ እንስሳ ከተወለደ ጀምሮ ይመዘገባል። ጆሮዋ ላይ ምልክት ይደረግባታል። ምን ዓይነት ምግብ እንደተመገበ እና ታሞ ከታከመ፤ ከምን ዓይነት በሽታ እንደዳነ ሁሉ ይታወቃል። ኢትዮጵያ ውስጥ ግን በዘፈቀደ በየሠፈሩ እንስሳቱ ስለሚያድጉ ይህ ሳይደረግ መቆየቱን አመልክተዋል።
የእንስሳትን የኋላ ታሪክ አለመመዝገብ ብቻ ሳይሆን ከበሽታ ነፃ ዞን መመሥረት እንዲሁም የእንስሳት ማዕከላት እንዲኖሩ ማደለቢያዎችን ማስፋት እና ወደ ውጪ ከመላክ ጋር እንዲተሳሰሩ ሌሎች ሀገሮች አድርገዋል ብለዋል። በኢትዮጵያ ግን የእንስሳት ግብይት ብዙ ተሳታፊዎችን የያዘ ነው። አምራች፤ እንስሳውን አጓጓዥ አለ። ንግድ ሚኒስቴር፣ ግብርና ሚኒስቴር እና ግብርና ባለስልጣንም ያለቡት ነው። ያሉት አምባሳደር ድሪባ፤ በቅድሚያ በግብርና ሚኒስትሩ የሚመራ ብሔራዊ ኮሚቴ ተቋቁሞ የአቅርቦት እና የጥራት ችግርን በተመለከተ ሰፊ ሥራ ለመሥራት ያጋጠሙ ችግሮችን ለማየት ተሞክሯል ብለዋል።
ማን ምን ችግር ይፍታ? አንዴት ይፍታ? ምን ሃብት እና ምን እገዛ ያስፈልጋል? በሚል ባለድርሻ አካላት ሶስት ጊዜ ስብሰባ አካሂደው ዕቅድ አውጥተዋል። ይህንን ተከትሎ ከእንስሳት ሃብት ጋር ተያይዞ ያለውን ችግር ለመፍታት ብዙ ጥረት እየተደረገ ይገኛል። ችግሩን ለመፍታት በጋራ ከሚወሰደው ሃላፊነት በተጨማሪ እያንዳንዱ ድርሻውን ለመወጣት እየሠራ ነው ብለዋል።
አምባሳደር ድሪባ እንደገለፁት፤ በተካሔደው ውይይት ቀደም ሲል የነበሩት የግብርና አዋጆች አሁን ዓለም የሚፈልገውን የዘርፉን ቁጥጥር ለመሥራት እና ለመመዝገብ የሚያመቹ አልነበሩም። በሕግ የማይደገፍ ቁጥጥር ጥርስ እንደሌለው አንበሳ ነው። መገፋፋት ብቻ ሳይሆን ማስገደድ ያስፈልጋል። ለምሳሌ የጥራት ሁኔታውን የሚፈትሹ አሉ። ጥራት ከሌለ ማስገደድ እንዲችሉ አዋጁ አይደግፋቸውም ነበር። አሁን ግን ፍተሻውን አረጋግጦ ለመሥራት አዋጅ ፀድቋል። ይህ ሕግን መሠረት ያደረገ የቁጥጥር ሥራን ለማከናወን ያስችላል።
ደንብ እና መመሪያው ላይ እየተሠራ ነው። የደረጃ ሥርዓትም ተዘጋጅቷል። ከዚሁ ጋር ተያይዞ የእንስሳቱ ልየታ፣ ምዝገባ፣ የደህንነት እና የፋይናንስ ጉዳዩ የሚሠራው በግብርና ሚኒስቴር ነው። ግብርና እስከ ወረዳ መዋቅር አለው። እንስሳትን ይለያል፤ ይመዘግባል፤ የፋይናንስ ሁኔታን ያረጋግጣል። ማለትም አርብቶ አደሩ እንስሳቱን አስይዞ ብድር ያገኛል። ይህ ከኢንሹራንስ ጋር ይያያዛል። ግብርና ሚኒስቴር ከመዘገበ በኋላ የኢትዮጵያ ግብርና ባለስልጣን የኋልዮሽ ታሪኩን መረጃ በሲስተም ውስጥ ይከታል ብለዋል።
ሥራው የሚከናወነው በቅብብሎሽ በመሆኑ ቅንጅት እንደሚያስፈልገው ጠቁመው፤ አንዱ ወደ ሌላ መወርወር ሳይሆን ሁሉም ድርሻ አለው። ይህንን በተመለከተ ሥራው አዲስ በመሆኑ መረጃ በተቆጣጣሪ ተቋም ውስጥ እንዲሆን ብዙ ጥናቶች ተሰርተዋል። ስለዚህ ሁሉም የድርሻውን በመሥራት ኃላፊነቱን መወጣት አለበት ሲሉም እምነታቸውን ገልፀዋል።
ባለስልጣኑ ይህን ለመሥራት ሥራውን ከሲቪል ሰርቪስ ጋር ለይቷል። ተቆጣጣሪ በመሆኑ በኢትዮጵያ የእንስሳት ገበያ ላይ ቅሬታ ቢነሳ ባለስልጣን መሥሪያ ቤቱ ሀገሪቱን ወክሎ ይከራከራል። ተባይ ነገር ቢገኝ ገዢዎች ይጠይቃሉ። እንስሳው የት ተወለደ? የእንስሳው ዘር ምንድን ነው? ከየት መጣ? ከብቱ የወሰደው ምግብ እና መድሃኒት ምንድን ነው? ምን በሽታ አጋጥሞት ነበር? ምን መድሃኒት ወስዶ ነበር? የተበከለው የት ነው? የበሽታው መሠረታዊ ምክንያት ምንድን ነው? የሚሉ ጥያቄዎች ለመመለስ ባለስልጣኑ ሥራውን በአደረጃጀት እና በአሠራር ለይቷል። ምዝገባውንም ለማካሔድ በየወረዳው ሥልጠናዎች እየተሰጡ ናቸው ብለዋል። እነዚህን ጥያቄዎች ለመመለስ ከመጀመሪያው ጀምሮ ታሽጎ እስከሚላክ ድረስ ባለው ሁኔታ ላይ ጥናት በማድረግ ምላሽ ይሠጣል። በተጨማሪ በሽታ የተገኘባቸው የእንስሳት ምርቶችም እንዲቃጠሉ ወይም በሌላ መልኩ እንዲወገዱ እንደሚያደርግ አመላክተዋል።
ምዝገባው ለፋይናንስ አገልግሎትም መፍጠን አለበት እየተባለ በመሆኑ፤ በባለስልጣኑ መረጃ ሥርዓት ውስጥ የተመዘገበ እንስሳ ብቻ ወደ ቄራ እንዲገባ ለማድረግ በጋራ ይሠራል ብለዋል። እስከ አሁን የምዝገባ ሥራ አለመጀመሩ ጥናቶቹ ባለመጠናቀቃቸው እና አደረጃጀቱ ባለመጥራቱ ቢሆንም፤ አሁን ሥራው እየተጀመረ መሆኑን አመላክተዋል።
አምባሳደር ድሪባ፤ የኋልዮሽ ታሪክን መመዝገብ ከተጀመረ ምናልባትም የቁጥጥር ሥርዓቱ የበለጠ ሳይንሳዊ ይሆናል። ከመጀመሪያው እንስሳቶቹ ከበሽታ ነፃ መሆናቸውን፤ እንዲሁም የምርቶቹን ጥራት እና ደህንነት ማረጋገጥ ይቻላል ሲሉ ተናግረዋል። ምዝገባው ሙሉ ለሙሉ ከተጠናቀቀ በኋላ የተሟላ የዓለም ገበያ የሚፈልገውን ዓይነት የእንስሳት ንግድ ይኖራል የሚል እምነት እንዳላቸውም አክለዋል።
ሆኖም በ2017 የዘጠኝ ወር ዕቅድ አፈፃፀማቸው 96 ከመቶ መሥራታቸውን ተናግረዋል። ይህንኑ ሲያብራሩ ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡትንም የግብርና ምርቶች እንደሚከታተሉ ጠቁመው፤ 66 አገልግሎቶችን ባለስልጣኑ ይሠጣል ብለዋል። ሁሉም ዲጂታላይዝድ በሆነ መንገድ በቀጥታ (ኦን ላይን) የሚሰጡ ሲሆኑ፤ ወደ ዓለም ገበያ የሚላኩት የእንስሳት ምርቶች ከበሽታ ነፃ መሆናቸውን እና ጥራታቸው የተረጋገጡ እንዲሁም የተቀባይ ሀገር መስፈርትን ያሟሉ መሆናቸውን የማረጋገጥ ሥራ ከተሠራ በኋላ የፋይቶ ሰርተፍኬት ይሠጣቸዋል ሲሉ ገልፀዋል።
በኢትዮጵያ ታሪክ ከ110 ዓመት በፊት የፋይቶ ማዕከል ተጀምሮ እንደነበር አስታውሰው፤ ፋይቶ ማዕከል ማለት አንድ ምርት ከአንድ ሀገር ተነስቶ ወደ ሌላ ሀገር ሲሔድ ሰው ፓስፖርት ይዞ ውጪ እንደሚሔደው ሁሉ፤ ‹‹ ምርቱ ጥራቱን የጠበቀ ነው፤ ከበሽታ ነፃ ነው›› የሚለው ማረጋገጫ ሰርተፍኬት መስጠት ነው ብለዋል። በዚህ ላይ ባለስልጣኑ እየሠራ መሆኑንም አመልክተዋል።
ባለስልጣኑ ከሠራቸው ሥራዎች መካከል ላብራቶሪ አንደኛው መሆኑን በማመላከት፤ በ13 ደረጃዎች በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና ማግኘት ተችሏል ሲሉ ተናግረዋል። ይህ በኢትዮጵያ የተመረመረው እንስሳ እና የእንስሳ ምርት በሁሉም ሀገር ተቀባይነት አለው ማለት ነው። ጎን ለጎን የተለያዩ ሥራዎች እየተሠሩ መሆናቸውን አመልክተው፤ በቅርቡ የስጋ ምርቶችን በስፋት ወደ ቻይና ገበያ እንደሚላክ እና ብዙ መቶ ሚሊየን ዶላር የማግኘት ዕድል እንደሚኖር አመላክተዋል።
በእርግጥ አሁን ያሉት አስራ አንድ ቄራዎች ብቻ መሆናቸው ኢትዮጵያ ካላት አቅም እና መላክ ከምትችለው አንፃር አነስተኛ ናቸው። ስለዚህ በዓለም ገበያም ሆነ በቻይና ገበያ በስፋት ለመሳተፍ፤ በብዛት ለመላክ በመቶ የሚቆጠሩ ቄራዎች መገንባት አለባቸው ብለዋል።
ዘንድሮ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከግማሽ ሚሊየን እንስሳት በላይ ተልኳል። ከቁም እንስሳት ከ48 ሚሊየን ዶላር በላይ ገቢ ተገኝቷል። ግብይቱን ግብርና ሚኒስቴር የሚከታተል ሲሆን፤ የግብርና ባለስልጣን ደግሞ ይቆጣጠራል። ዘንድሮ ግን ገቢው ካለፈው ዓመት በእጥፍ አድጓል። በአጠቃላይ ከኢኮኖሚክ ሪፎርሙ በኋላ ትልቅ ለውጥ መጥቷል ሲሉ፤ ምዝገባው ባይካሄድም ውጤቶች መምጣት መጀመራቸውን አመላክተዋል ።
በፊት የነበረው የኢኮኖሚ ፖሊሲ ዶላር ይዞ ከሀገር መውጣት ይከለክል እንደነበር አስታውሰው፤ የፖሊሲ ለውጥ መፈፀሙ እና ሙሉ ለሙሉ የነፃ ገበያ ፖሊሲ ተግባራዊ መደረጉ ባለሃብቶች ላይ ፍላጎትን ፈጥሯል ብለዋል። የእንስሳት ልየታና ክትትል ሥርዓት ምዝገባ ትልቅ ለውጥ ያመጣል ተብሎ ተስፋ እንደተጣለበት በመጠቆም፤ በተለይ ገበያው ላይ ውጪ ያሉ ባለሃቶች በስፋት ከመጡ ከዘርፉ ብዙ ይገኛል ብለው እንደሚያምኑም ጠቁመዋል።
ይሁንና ዘርፉን ውጤታማ ለማድረግ፤ ፋይናንስን በተመለከተ ገበሬው በሬውን አስይዞ ብድር እንዲያገኝ፤ እንስሳቶቹ ተለይተው ጆሯቸው ላይ መለያ እንዲኖራቸው ከተመዘገቡ በኋላ መረጃው ወደ ግብርና ባለስልጣን መላክ ያስፈልጋል። ይህ እንስሳው ወይም የእንሰሳው ምርት ወደ ውጪ ከተላከ በኋላ በእንስሳው ላይ በሽታ ከተገኘ መረጃ ለማግኘት እና ችግሩን ቶሎ ለመለየት ያመቻል። በዚህ ላይ አሁንም በፍጥነት እና ቅልጥፍናን በተላበሰ መልኩ መሠራት አለበት ሲሉ ያላቸውን ሃሳብ ገልፀዋል።
የውይይቱ ተሳታፊዎች የእንስሳ ምዝገባ እና የኋልዮሽ ክትትል ሥርዓት ከቁጥጥር ተቋም ወጥቶ ወደ ግል በማዞር ለሕብረተሰቡ ጠቃሚነቱን አስረድቶ በዛ መልክ ወደ ቄራ እንዲገባ ማድረግ እንደሚያስፈልግ አመላክተዋል።
ምሕረት ሞገስ
አዲስ ዘመን ሰኞ ግንቦት 25 ቀን 2017 ዓ.ም