አቶ ግርማ የሺጥላ ወ/ጻዲቅ ከእናታቸው ከወ/ሮ ዘውዴ ስመኝ ከአባታቸው ከአቶ የሺጥላ ወልደጻዲቅ በቀድሞው ሸዋ ክፍለ ሃገር በመንዝና ግሼ አውራጃ በጌራ ምድር ወረዳ መሐል ሜዳ ከተማ ኅዳር 17 ቀን 1967 ዓ.ም ተወለዱ።
ዕድሜያቸው ለትምህርት እንደደረሰ የአንደኛና መለስተኛ 2ኛ ደረጃ ትምህርታቸውን እንዲሁም የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በመሐል ሜዳ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እና አጠቃላይ 2ኛ ደረጃ ት/ቤት ማጠናቀቅ ችለዋል።
ገና በአፍላ ወጣትነት ዕድሜያቸው ከሰኔ 1986 ዓ.ም ጀምሮ በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን በአንጾኪያ ወረዳ የተፈጥሮ ሃብት ጽ/ቤት የስራ ባልደረባ በመሆን የመንግሥትን ሥራ አሀዱ ብለው ጀምረዋል።
አቶ ግርማ የሺጥላ በወጣትነታቸው ባሳዩት ትጋትና ታታሪነት ምክንያት ለኃላፊነት የታጩ ሲሆን ከ1989 ዓ.ም እስከ 1990 ዓ.ም ድረስ በአማራ ብሔራዊ ክልል መንግሥት በሰሜን ሸዋ ዞን የአንጾኪያ ወረዳ የኢኮኖሚ ዘርፍ ሥራ አስፈጻሚ በመሆን ሕዝባቸውና መንግሥት የጣለባቸውን ኃላፊነት ተወጥተዋል።
አቶ ግርማ የሺጥላ ለትምህርት በነበራቸው ልዩ ጉጉትና ፍላጎት ምክንያት የትምህርት ዕድል እንዲመቻችላቸው ዘወትር ጥያቄ ያቀርቡ ስለነበረ የተሰጣቸውን የመንግሥትና የሕዝብ ኃላፊነት ከማከናወን ጎን ለጎን ከግል ኮሌጅ በማኔጅመንት በዲፕሎማ ተመርቀዋል።
የተከበሩ አቶ ግርማ የሺጥላ በነበራቸው የሥራ ታታሪነትና አስተዋይነት እንዲሁም ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ በሚያገለግሉት ማኅበረሰብ ከፍ ያለ ተቀባይነት ስለነበራቸው ከ1990 ዓ.ም እስከ መስከረም ወር 1995 ዓ.ም ድረስ የአንጾኪያ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ በመሆንም አገልግለዋል።
አቶ ግርማ የሺጥላ በታችኛው እርከን በነበራቸው የአመራር ብቃትና ልዩ ተሰጥዖና ልምድ ምክንያት ለዞን ከፍተኛ ኃላፊነት ተመርጠው ወደ ሰሜን ሽዋ ዞን በመዛወር ከፍ ያሉ ኃላፊነቶችን ሲወጡ ኖረዋል።
ከጥቅምት ወር 1995 ዓ.ም ጀምሮ የሰሜን ሸዋ ዞን ብአዴን ጽ/ቤት ኃላፊ በመሆን ቀጥለውም ከመስከረም 1997 ዓ.ም እስከ ኅዳር 30 ቀን 1998 ዓ.ም ድረስ በሰሜን ሸዋ ዞን የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባና የማስታወቂያ ጽ/ቤት ኃላፊ በመሆን የከተማውን ሕዝብ አገልግለዋል።
በኋላም ከታኅሳስ 01 ቀን 1998 ዓ.ም ጀምሮ በሰሜን ሸዋ ዞን የባሶና ወራና ወረዳ ማስታወቂያ ጽ/ቤት ኃለፊ በመሆን በየደረጃው የተሰጣቸውን ኃላፊነት በብቃት፣ በብስለት እና በትጋት ከተወጡ በኋላ እንደገና ተመልሰው ከሚያዚያ 1 ቀን 1999 ዓ.ም እስከ መስከረም 2000 ዓ.ም ድረስ የሰሜን ሸዋ ዞን የሕዝብ ግንኙነት አማካሪ በመሆን አገልግለዋል።
አቶ ግርማ የሺጥላ በደብረብረሃን ዩኒቨርሲቲ በኢኮኖሚክስ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን አግኝተዋል። የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ካገኙ በኋላ ወደ ሥራ በመመለስ የሰሜን ሸዋ ዞን ብአዴን አደረጃጀት እንዲሁም እስከ መስከረም 30 ቀን 2008 ዓ.ም ድረስ የሰሜን ሸዋ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ በመሆን የተሰጣቸውን የሥራ ኀኃላፊነት በብቃት ተወጥተዋል።
አቶ ግርማ የሺጥላ ከጥቅምት 1 ቀን 2008 ዓ.ም ጀምሮ የሰሜን ሸዋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ በመሆን ካገለገሉ በኋላ ለከፍተኛ ትምህርት ወደአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በመሄድ ትምህርታቸውን ጀምረዋል። በአዲስ አባባ ዩኒቨርሲቲ ማለትም በኮተቤ ሜትሮ ፖሊቲያን ዩኒቨርሲቲ የሁለተኛ ዲግሪያቸውን ሲማሩ ቆይተው በኢኮኖሚክስ ተመርቀዋል።
የሁለተኛ ዲግሪ ትምህርቸውን እንዳጠናቀቁ ከመስከረም 2013 ዓ.ም ጀምሮ በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ በመሆን የክልሉን ሕዝብና መንግሥት በትጋት አገልግለዋል።
አቶ ግርማ የሺጥላ ከመስከረም 2014 ዓ.ም. ጀምሮ ሕይወታቸውን በድንገተኛ አደጋ እስከተነጠቁበት ሚያዝያ 19 ቀን 2015 ዓ.ም ድረስ የብልጽግና ማዕከላዊ ኮሚቴ ሥራ አስፈጻሚና የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ በመሆን አገልግለዋል።
አቶ ግርማ የሺጥላ በስድስተኛው አገር አቀፍ ምርጫ በባሶና ወራና ወረዳ የቀይት ምርጫ ጣቢያ የክልል ምክር ቤት ዕጩ በመሆን ተወዳድረው ሕዝቡ የሰጣቸውን ውክልና በኃላፊነት ስሜት ሲወጡ ቆይተዋል።
የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥትንና የክልሉን ሕዝብ ወክለው የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የፌደሬሽን ምክር ቤት አባል በመሆን የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት ሲወጡ የቆዩ ወሳኝ አመራር ነበሩ።
አቶ ግርማ የሺጥላ ከመደበኛ ሥራ በተጓዳኝ የደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ ሥራ አመራር ቦርድ አባል ሆነው ያገለገሉ ሲሆን የደብረ ብርሃን ሪፈራል ሆስፒታል ሥራ አመራር ቦርድን እና የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ሥራ አመራር ቦርድን በሰብሳቢነት መርተዋል።
አቶ ግርማ የሺጥላ ከልጅነት እስከ እውቀት በተለያዩ የሥራ ኃላፊነቶች ተመድበው ሲሠሩ መቆየታቸው እንደተጠበቀ ሆኖ ከጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም. ወዲህ በተደጋጋሚ የተከፈተብንን ጦርነት ለመቀልበስ ጉልህ ድርሻ ነበራቸው።
በተለይም በሁለተኛውና በሦስተኛው ጦርነት ወቅት የሀገር ሉዓላዊነትን ለማስከበር ግንባር ቀደም መሪ በመሆን እስከ ውጊያ ወረዳ ድረስ በመግባት የክልሉ ሕዝብ የተቃጣበትን የሕልውና አደጋ ለመቀልበስ ራሳቸውን ለመስዋዕትነት አዘጋጅተው ከፍተኛ አሰተዋፅዖ ያበረከቱ ቅንና አስተዋይ መሪ ነበሩ።
አቶ ግርማ የሺጥላ ከ25 ዓመታት በላይ የክልሉን መንግሥትና ሕዝብ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ ያለመታከት ማገልገላቸው የሚዘነጋ አይደለም። ከወጣትነት እድሜያቸው ጀምሮ ሕይወታቸውን በግፍ እስከተነጠቁበት ቀን ድረስ ራሳቸውን ለክልሉ ሕዝብ ጥቅም በግንባር ቀደምነት አሰልፈው ደፋር አመራር አረጋግጠዋል።
አቶ ግርማ የሺጥላ ብርቱ፣ ታታሪና ለቆሙለት ዓላማ ግንባራቸውን የማያጥፉ፣ የተሰጣቸውን ኃላፊነት የሚያከብሩ፣ ለአማራ ሕዝብም ሆነ በአጠቃላይ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ሳይታክቱ የደከሙና ብልህና አዋቂ የሕዝብ መሪ እንደሆኑ አብረዋቸው የሠሩ የሥራ ባልደረቦቻቸው ሁሉ የሚመሰክሩላቸው ሐቅ ነው።
አቶ ግርማ የሺጥላ ለሥራ በወጡበት ወቅት የክልሉን ሕዝብ ጥቅም ዛሬም ሆነ ዘወትር የማምከን ሕልምና ትልም አንግበው ከሚንቀሳቀሱ ፀረ ሕዝብ ኃይሎች ድንገት በተተኮሰባቸው ጥይት ሚያዚያ 19 ቀን 2015 ዓ.ም በተወለዱ በ48 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል።
አቶ ግርማ የሺጥላ ባለትዳር ሲሆኑ የሶስት ሴት እና የአራት ወንድ ልጆች አባት ነበሩ።
አቶ ግርማ የሺጥላ በደረሰባቸው አስደንጋጭና ድንገተኛ ህልፈተ ሕይወት ለመላው ቤተሰቦቻቸው፣ ለወዳጅ ዘመዶቻቸው፣ ለሥራ ባልደረቦቻቸው፣ ለትግል አጋሮቻቸው እና ለመላው የአማራ ክልል ሕዝብ መፅናናትን እንመኛለን።
ፈጣሪ ነፍሳቸውን በአፀደ ገነት ያኑርልን ።
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 23/2015