ጥላቻ የሚጠላውን ብቻ ሳይሆን ጠይውንም ራሱን ቀስ በቀስ የሚበላ ክፋት ነው። በጥላቻ ላይ የተገነባ የትኛውም ዓይነት አስተሳሰብ ፍጻሜው ጥፋትና ኪሳራ ብቻ ነው። ለዚህም በጥላቻ ተጀምረው በከፍተኛ ውድቀት የተፈጸሙ ታሪኮችን ዓለማችን በየዘመኑ አስተናግዳለች፤ ዛሬም ቢሆን ከዚህ የአስተሳሰብ እርግማን መሻገር የሚያስችላትን የተሟላ አቅም ማግኘት ባለመቻሏ ተጨማሪ ዋጋ ለመክፈል ተገዳለች።
በተለይም ጥላቻን እንደ አንድ የፖለቲካ መሣሪያ አድርገው የሚጠቀሙ ግለሰቦችና ቡድኖች፤ በተደራጀና በተጠና መንገድ በማኅበረሰብ ውስጥ የሚዘሯቸው የጥላቻ ዘሮች ወቅቱን ጠብቀው የሚያፈሯቸው ፍሬዎች የሚኖሩባቸውን ማኅበረሰቦች እያስከፈሉ ያለው ዋጋ ከግምት በላይ እየሆነ ነው። ዓለምንም በብዙ መልኩ መረጋጋት እያሳጣት ይገኛል።
እንዲህ ዓይነቱ የአስተሳሰብ ርግማን የሩዋንዳ፣ የብሩንዲ ፣ የሶማሊያ ፣ የሱዳን … ወዘተ ሕዝቦችን የቱን ያህል ዋጋ እንዳስከፈላቸው፣ እነዚህን አገራት አለመረጋጋት አሳጥቶ ሕዝቦቻቸው የተሻሉ ነገዎችን ተስፋ አድርገው እንዳይንቀሳቀሱ ትልቅ ተግዳሮት እንደሆነባቸው የአደባባይ ምስጢር ነው። ከጠባቂነት ወጥተው ራሳቸውን አሸንፈው ቀና ብለው መጓዝ እንዳይችሉም አድርጓቸዋል።
ዘመኑ የደረሰበት የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ እድገት በራሱ፤ ይህ የጥፋት አስተሳሰብ በቀላሉ ወደ የማኅበረሰቡ እንዲሰራጭ አስቻይ ሁኔታዎችን ፈጥሯል። በዚህም ችግሩን ለመቆጣጠር የሚደረጉ አገራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ጥረቶችን የሚጠበቀውን ያህል ውጤታማ እንዳይሆን፤ ብዙዎች ዛሬ ላይም በየዋህነት የአስተሳሰቡ ሰለባ እንዲሆኑም አድርጓል።
በእኛም አገር ቢሆን አንዳንድ ግለሰቦችና ቡድኖች ጥላቻን መሠረት ባደረገ ትርክት የፖለቲካውን መድረኩን የመደባለቃቸው እውነታ፤ አገር እንደአገር የዚህ የአስተሳሰብ ሰለባ እንድትሆን እያደረጋት ይገኛል። ላለፉት አስርት ዓመታት ጥላቻን መሠረት አድርገው የተዘሩ ትርክቶች በተለይም ባለፉት አምስት ዓመታት ክፉ ፍሬ አፍርተው ዜጎችን ብዙ ዋጋ አስከፍለዋል።
ሕዝቦቿ በመቻቻልና በመከባበር በዓለም አቀፍ ደረጃ በሚታወቁባት አገራችን ፤ የጥላቻ ትርክቶች በፈጠሯቸው ውዥንብሮች ብዙ ሺዎች ለሞት፤ ሚሊዮኖች ለስደት ተዳርገዋል። ጥቂት የማይባሉ የትውልዱ ተስፋዎች በዚህ የአስተሳሰብ ህመም ተይዘው፤ ለራሳቸውና ለአገራቸው ነገዎች ተስፋ ከመሆን ይልቅ ስጋት ሆነዋል።
እውነታው ከለውጡ ዋዜማ ጀምሮ እንደአገር አገር ይዛ በተነሳችው የበለጸገች የጋራ አገር ምስረታ ራዕይ ላይ የፈጠረው አሉታዊ ተጽእኖ ለውጡን ወደኋላ ከመጎተት አልፎ፤ ዜጎች በለውጡ ላይ የነበራቸውን ተስፋ በማጨለም ትናንቶችን ናፋቂ እንዲሆኑ አስገድዷቸዋል። ይህንን ለመቀልበስ የለውጡ ኃይል ለመሄድ የተገደደበት ርቀትና ያስከፈለው ዋጋ ቀለል ተደርጎ የሚታይ አይደለም።
አሁን ላይ እነዚህ የጥላቻ ትርክቶች እንደ አገር የፈጠሩብንን ተግዳሮቶች ለዘለቄታው ችግር በማይሆኑበት ደረጃ አክመን መሻገር የሚያስችለንን የአስተሳሰብ አቅም መገንባት ካልቻልን፤ ችግሩ ካለው ክፉ ባህሪ አንጻር መጪውንም ትውልድ ያልተገባ ተጨማሪ ዋጋ ማስከፈሉ የማይቀር ነው። ለዚህም ደግሞ እንደ ትውልድ የተጠያቂነት ደረጃው ከፍያለ ነው።
ጥላቻ ማኅበረሰብ ከተገነባበበት መንፈሳዊ፣ ባህላዊና ማህበራዊ እሴቶች አንጻር የማንነት ግራ መጋባት ከመፍጠር፣ በብዙ የጥፋተኝነት መንፈስ እራስን እንዲኮንን ከማድረግ እና ሰላሙን ከመናጠቅ የዘለለ የሚያተርፍለት ነገር አይኖርም፤ እስከዛሬ ባለውም ያተረፈለት ነገር የለም።
የጥላቻ ሳባኪዎችም ቢሆን ከስብከታቸው የተነሳ በሚፈጠር ጥፋት ከመፈንጠዝ ፤ በዚህም ሕዝባችንን ያልተገባ ዋጋ ከማስከፈል ባለፈ ጥፋትና ጽንፈኝነት ወደመሻታቸው መቼም ቢሆን ሊያደርሳቸው አይችልም። የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር የተሸከሙት የጥላቻ ካንሰር እነሱን በልቶ መጨረሱ የማይቀር ነው።
መላው ሕዝባችን ይህንን እውነታ ዘመናትን ካሻገሩት መንፈሳዊ ፣ ባህላዊና ማኅበራዊ እሴቶች አንጻር በሰከነ መንፈስ በመመርመር፤ አሁን የተጀመረውና ፍሬው እየታየ ያለው የሰላም መንገድ የበለጠ ፍሬ እንዲያፈራ በቁርጠኝነትና በኃላፊነት መንፈስ መንቀሳቀስ ይጠበቅበታል። የመጪውን ትውልድ ዕጣ ፈንታ የሚወስነው ዛሬ ላይ እንደአገር እየጣልነው ያለው የሰላም መሠረት እንደሆነም ሊያስተውለው ይገባል!
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 23/2015