ሰላም ልጆች እንደምን ሰነበታችሁ !ሳምንቱን እንዴት አሳለፋችሁ? በጥናት እንዳሳለፋችሁት ተስፋ አደርጋለሁ። ልጆች ለዛሬ አንድ የ10ኛ ክፍል ተማሪና ነዋሪነቷ ጅማ ዞን የሆነ ታዳጊ አስተዋውቃችኋለሁ። ኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በየጊዜው ስለ ኢትዮጵያ በሚል በሚያዘጋጀው መድረክ ላይ ነው ያገኘናት
ስምረት አብዩ ትባላለች። ዕድሜዋ 15 ዓመት ሲሆን በዚህ ጊዜ ውስጥ 10ኛ ክፍል መድረሷ በራሱ የሚደነቅ ነው። 1ኛ ክፍል በአምስት ዓመቷ ገብታ አሁን ላይ 10ኛ ክፍል መድረሷ ብቻ ሳይሆን የተለያየ ተሰጥኦ ያላት ልጅ መሆኗም የተለየች ያደርጋታል። በትምህርቷም በየዓመቱ አንደኛ የምትወጣ ጎበዝ የደረጃ ተማሪና ተሸላሚ ናት። ኢትዮጵያን አብዝታ ትወዳለች። ኢትዮጵያዊ በመሆኗም እንደምትኮራና እንደምትደሰት ደጋግማ ትናገራለች። በዚህ ዕድሜዋ የብዙ ተቋም አምባሳደርም ለመሆን ችላለች። ደስ አይልም ልጆች ስምረት በጣም ዕድለኛና ጎበዝ ልጅ ናት አይደል? ላስተዋውቃችሁ የወደድኩትም ለዚህ ነው።
ስምረት ኦሮሚኛ፤አማርኛና እንግሊዝኛ ቋንቋዎችን ጥሩ አድርጋ ትናገራለች። መናገር ብቻ ሳይሆን በቋንቋዎቹ ግጥሞችን፤ሙዚቃዊ ድራማዎችንና የተለያዩ ስነ ጽሁፎችን ትጽፋለች። ጽፎቿን ብዙ ሕዝብ በተሰበሰበበት በአደባባይ ስታቀርብም በሰው ብዛት አትፈራም፣አትደናገጥም። በተደጋጋሚ በእንደዚህ ዓይነት መድረኮች የተለያዩ ግጥሞችን የማቅረብ ልምድ ስላዳበረች ምንም ችግር ሳይገጥማት ለታዳሚው መድረስ ያለበትን የግጥሟን መልዕክት ያለ አንዳች መደናገርና ፍርሃት በጽሞና ማስተላለፍ ትችላለች። የተለያዩ ብሄር ቤሄረሰቦችን ባህላዊ ውዝዋዜና ዘፈኖች ዳንስና ጨዋታ፤ጭፈራ ትችላለች።
የግጥምና ዜማ ደራሲ ናት። በሁሉም ጎበዝና ውጤታማ ሥራ መሥራት በተለይ በዜማና ግጥም የተዋጣላት ልጅ ናት።
የአባቶች አገር
የደጋጎች መንደር
ባለ ወርቃማ መሬት
አንቺ ነሽ የእኛ እናት
ኢትዮጵያ እኛ ነን ልጆችሽ
ሁሌ የምንወድሽ
የሚለው ሙዚቃዊ ግጥሟ ተጠቃሽ ነው። ልጆች ስምረት ይሄን ሙዚቃዊ ዘፈን በአንደበቷ ስታቀርበው ለዛው ልዩ ቅላፄ ያለውና ደስ የሚል ነው።
ስምረት እንደምትለው ባህላዊ ነገሮች በሙሉ ይማርኳታል፣ ደስም ይሏታል። የአገር ውስጥ ምርቶችን እንጂ ከውጭ ወደ አገር ውስጥ የሚገቡትን አታደንቅም። መጠቀምና መኩራት ያለብን በራሳችን ሀገር ምርት ነው የሚል ጽኑ አቋም አላት። ልጆች ስምረት ሁለገብ ተሰጥኦ ያላት እንደመሆኗ እነዚህ አገር በቀል ምርቶች ባህላዊ ይዘታቸውን ሳይለቁ አዘምኖ መጠቀም በሚያስችል የፋሽን ዲዛይንም መሥራት እንደሚቻል ትናገራለች። ወደፊት እዚህ ላይም የመሥራት ዕቅድ አላት። ልጆች ተማሪ ስምረት እንደምትናገረው አገራዊ ፋይዳ የሚያስገኙ ጉዳዮች ላይ መሳተፍ በጣም ያስደስታታል።
በክልሉ የገቢዎች ቢሮ ሕብረተሰቡ ግብር የመክፈል ግዴታውን እንዲወጣ በስነ ጽሑፍና በተለያየ መንገድ ግንዛቤ ታስጨብጣለች። በተለይ ገቢዎች ቢሮ በሚያካሂዳቸው የተለያዩ መርሐ ግብሮች ንቅናቄ ላይ ትሳተፋለች። ገቢዎችና ግምሩክ ባዘጋጀው ፈተና ላይ ከትምህርት ቤት ተወክለው የመሳተፍ ዕድል ማግኘታቸውና እንደ ጅማ ዞን እሷ በኦሮሚያ ክልል አንደኛ መውጣት መቻሏ እንድትመረጥ እንዳደረጋት ትናገራለች። በዚህ አጋጣሚ ባገኘችው ዕድል በቢሮውና በክልሉ ገቢን የተመለከተ ጉዳይ በንቃት እንድትሳተፍ አስችሏታል። በተለይ ግብር የመክፈል ንቅናቄ መርሐ ግብር ስምረት በንቃት ከምትሳተፍበት አገራዊ ፋይዳ ያለው ጉዳይ አንዱ ነው። በዚህም የኦሮሚያ ክልል ገቢዎች ቢሮ የታክስ የክብር አምባሳደር አድርጎ ሾሟታል። በተጨማሪም ስምረት እንደዚሁ የተለያዩ ተቋማት በሚያዘጋጁት መርሐ ግብሮች በመሳተፏ በዚህ ዕድሜዋ የክብር አምባሳደርነት ሹመት ዕድሎች ማግኘት ችላለች።
ለአብነት የሰላም ሚኒስትር በጎነት ለሰላም የክብር አምባሳደር
የጅማ ዩኒቨርሲቲ የክብር አምባሳደር
የጅማ ዞን እና ከተማ አስተዳደር የታክስ ቢሮ የክብር አምባሳደር
የጅማ ዞን ሴቶች እና ህፃናት ቢሮ የክብር አምባሳደር ሆና የተሾመችባቸው ይጠቀሳሉ።
ልጆች ታዳጊ ስምረትን ጅማ ዩኒቨርሲቲ በአምባሳደርነት መሾም ብቻ ሳይሆን ጎበዝና ውጤታማ ተማሪ እንዲሁም ሁለገብ ተሳትፎና ችሎታ ያላት ተማሪ በመሆኗ ነፃ የትምህርት ዕድልም ተጠቃሚ እንድትሆን አድርጓታል። ዕድሉ በዕድሜ ዘመኗ በሙሉ ተመቻችታ መማር የሚያስችላት ነው። ልጆች ስምረት ጎበዝ ባትሆን ኖሮ ይሄን ዕድል ማግኘት አትችልም ነበር አይደል? እንዲህ ዓይነት ጥቅም ማግኘት እንድትችሉ እናንተም ጎበዝ ሁኑ እሺ።
ስምረት አብዛኛውን ጊዜዋን የምታሳልፈው መጽሐፍ በማንበብ ነው። ከዚሁ ጎን ለጎንም የሰፈር ልጆችን አሰባስባ ታስጠናለች። ሙዚቃ ታደምጣለች። ንፁህ ከባቢ አየር ባለበት ሥፍራ ተቀምጦ ራስን መመሰጥ፤ስለ ነገና ስለ አገሯ ጠቃሚና አዳዲስ ሀሳቦችን ማመንጨት ደስ ይላታል። ይሄ ሁኔታ ያዝናናኛል ስትልም ትገልፀዋለች። በዚህ መልኩ እንድታድግ ያደረጋት አካባቢዋና ቤተሰቧ እንደሆነም ነግራናለች። ‹‹ከአካባቢዬ ብዙ የተገነዘብኩትና ለስነጽሑፍ ሥራዬ የተጠቀምኩት አለ››ትላለች። ቤተሰቦቼ በተለይም እናትና አባቴ እንዲሁም አክስትና አጎቶቼ አሁን ለደረስኩበት ደረጃ እንድደርስ ከፍተኛ እገዛ አድርገውልኛል ትላለች። በነፃነት ሀሳቧን እንድትገልጽ ዕድል መስጠታቸው አንዱና በከፍተኛ ደረጃ የጠቀማት መሆኑንም ትናገራለች። ጥሩ ስትሰራ ያበረታቷትና በተለያየ መንገድ እንደሚደግፏትም ትጠቅሳለች። ለእሷ የማይጠቅማት ነገር ሲያዩባት ደግሞ እንደሚያርሟትና ጎጂነቱን በአግባቡ እንደሚያስረዷትም አጫውታናለች። ልጆች ከስምረት ብዙ እንደተማራችሁ ተስፋ አደርጋለሁ። ሳምንት በሌላ ጽሑፍ እስክንገናኝ ሰላም ሁኑ።
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 22/2015