ኢያሴ.. ኢያሴ… ኢያሴ በማለት በስርቅርቅ ድምጹ ሲያቀነቅን ውስጣዊ ስሜቱ እየተነካ የልብ ትርታው የማይጨምር ሰው የለም። ሙዚቃ ቋንቋ አያሻውም፤ ምክንያቱም ሙዚቃ ራሱ ቋንቋ ነውና።
ከጊቤ ወንዝ ባሻገር ቁልቁል የሚፈስ የወንዝ ጅረት ብቻ ሳይሆን ረዥምና ግዙፍ የጥበብ ባህር አለ። ከዚህ የጠጣ ሁሉ በጥበብ በረከት እንደመጠመቅ ያህል፣ እልፍ ጠቢባን ሳሎን ጓዳዋን ሞልተውታል። ከእነዚህም የጥበብ ሰዎች መካከል አንደኛው ድምጻዊ ዘሪሁን ወዳጆ ነው። የእውነትም ሙዚቃን ከነብሱ ጋር ያወዳጀ የአፋን ኦሮሞ ሙዚቃ አቀንቃኝ ነበር። ነበር ብለን ብቻ እንዳንተወው ዛሬም ስራዎቹ እንደመስታወት ቁልጭ አድርገው እሱነቱን ያሳዩናል። ከሰሞኑ “ዘሪሁን ወዳጆ ከዚህ አለም በሞት ተለየ” የሚለው አረፍተ ነገር ከየሚዲያው ሲሰማ ቅስምን የሚሰብር ልብን ለሁለት የሚከፍል አሳዛኝ የዜና አርዕስት ነበር።
ሞት ለማንም የማትቀር የሰው ልጆች የመጨረሻ የሕይወት ምዕራፍ ብትሆንም የሁሉም ሞት ግን አንድ አይደለም። ልክ እንደ ዘሪሁን ያሉ ታላቅ ሰዎችን ስንመለከት ከሞት በላይ፣ ከመቃብር አናት ላይ ባስቀመጡት ስራዎቻቸው ሞትን አሸንፈውታል ለማለት ያስደፍራል። ስራዎቹ አልሞቱምና ሞት የሚሉት ነገር ካበጀው የማይወጣበት ግዙፍ ዋሻ አምልጦ በስራዎቹ መካከል ተደብቋል። ሃያል ከሆነው ከእዚህ የጥበብ ግዛት ውስጥ ሞት ደፍሮ ለመግባት አይችልምና ሞት በጥበብ ይረታል። እርሱ የዚህችን አለም ተልዕኮውን ጨርሶ በድል ወደ እረፍት አለም ተመልሷል፤ እኛ ግን በጥቂቱም ቢሆን ስለግላዊ ሕይወቱና ስለ ስራዎቹ ልናወሳ እንወዳለን።
አርቲስት ዘሪሁን ወዳጆ 1949 ዓ.ም በነቀምቴ ከተማ ተወለደ። ተወልዶ ባደገባት በዚህች የጥበብ ሰዎች መፍለቂያ ምንጭ በሆነችው ከተማ ውስጥ ከልጅነት ሕይወቱ ጀምሮ ይሄ ነው ብሎ ለመግለጽ የሚያዳግቱ የጥበብ ስራዎቹን ለማህበረሰቡ እያበረከተ የኖረ ሰው ነው። ከዚያው የልጅነት ሕይወቱ አንድ ብሎ፤ ኪነ ጥበባዊ እንቅስቃሴውን በመጀመር ለ48 አመታት ያህል ያለምንም መታከት ላይ ታች ሲል ለእራሱ ሳይሆን ለጥበብ ብሎም ለሙዚቃ ኖሮላታል። ለእኔ ብሎ እምብዛም ስለ እራሱ ሳይጨነቅ አላማውን ለማሳካት እድሜውን ሙሉ ያሳለፈው በትግልና ፈተና በበዛበት በብዙ የችግር አረንቋ ውስጥ ነበር።
ሙዚቃ የነጻነት፣ የሰላም ትግል እንዲሁም የድል ብስራት ማብሰሪያ መሳሪያ እንደመሆኑ ከምንም በላይ በሙዚቃዎቹ ውስጥ ለዘመናት ስለማህበረሰቡ ነጻነት በጀግንነት ሲታገል የኖረ የኪነ ጥበቡ አለም የነጻነት ታጋይም ጭምር ነው። 1962 ዓ.ም የኦሮሞ የባህል ባንድ ሲመሰረት የያኔው ወጣቱ አርቲስት ዘሪሁን ወዳጆ ከእነ ኢታና ቶሎሳ፣ እልፍነሽ ቀኖና፣ አቢቶ ከበደ፣ ሰለሞን ደነቀ፣ አመንቴ ዶጃ እና ከሌሎች አርቲስቶች ጋር ባንዱን በመቀላቀል የሚደረገውን ሕዝባዊ የነጻነት ትግል አፋፍመውታል።
በዚህ ሕዝባዊነቱም በአብዛኛው የኦሮሞ ማህበረሰብ ተወዳጅነትን ከማግኘቱም በላይ ስራዎቹም በሕዝቡ ልብ ውስጥ እንደ ነጻነት ባንዲራ ናቸው። በ1969 ዓ.ም በተደረገው ሀገር አቀፍ የቲያትርና የባህል መድረክ ላይ በመሳተፍ የኦሮሞ ሕዝብን እውነተኛ ባህል በስራዎቹ ፍንትው አድርጎ ማሳየት በመቻሉ በኦሮሞ ማህበረሰብ ብቻ ሳይሆን በብዙ ኢትዮጵያዊያን ዘንድ ተወዳጅነትን ለማግኘት ችሏል። የእርሱ ሙዚቃዎች ድንገት ከጆሮው ውስጥ የገባ ማንኛውም ሰው ቢሆን እንዲሁ ሰምቶ ብቻ አያልፈውም፡፡ ትርጉሙ የገባው እያደነቀው፣ ያልገባውም ለጆሮ ጥኡም ከሆነው ድምጹና ውብ ሙዚቃው በስተጀርባ ያለውን ትርጉም ለማወቅ ሳይነሽጠው በቀላሉ አያልፈውም።
ይህ ድንቅ ድምጻዊ የአድማጩን ልብ በስሜት ማዕበል እየናጠ በብዙ ሙዚቃዎቹ አድማጩን አዘልሏል፤ አስፈንድቋል፤ አስለቅሷል ብቻ በሙዚቃ ችሎታው በርካቶችን አስደምሟል። ከዚህ ሁሉ መሃል ግን ሁሉም እርሱን የሚያስታውስበትና ሌላኛው የመጠሪያ ስሙ እስከመሆን የደረሰው ‘ኢያሴ’ በተሰኘው ስራው ነበር። ኢያሴ በወለጋ አካባቢ የሚዘወተር ባህላዊ ጨዋታ ሲሆን፤ ዘሪሁን ደግሞ ያለውን የሙዚቃ ጥበብ በመጠቀም ከሽኖና መጥኖ በሙዚቃ መልክ ለአድማጭ ጆሮ አበቃው። እንግዲህ ከመሃሉ ‘ሲርባ ሞርማ’ የሚለውን ሌላ ዜማ እንደ ጨው ነስነስ አድርጎ ያዘጋጀውን ይህን ጣፋጭ ሙዚቃ አድምጦ በስሜት የማይዘል አሊያም ጆሮው በዜማው ስበት የማይማረክ ማነው…
ያኔ በወርቃማው የሙዚቃ ዘመን የወርቃማ ሙዚቃዎችን ወርቃማ ድምጾች ወደ ሕዝቡ ጆሮ በራዲዮ ሞገድ ሲስተጋቡ፣ በኢትዮጵያ ራዲዮ ብሄራዊ አገልግሎት ስር የነበሩት የሐረርና የመቱ የራዲዮ ጣቢያዎች የዘሪሁን ወዳጆን ሙዚቃዎች ከፍ አድርጎ በማስደመጥ የዚያን ዘመን አንደኛው ትውስታ እንዲሆን አድርገውታል። የሙዚቃዎቹ መልዕክት ደግሞ ሌላኛው አይረሴ የትዝታ ቋት ናቸው። የዘሪሁን ሙዚቃዎች እንዲሁ የሙዚቃ ጥምን ለማርካት ብቻ የሚደመጡ አልነበሩም። ስለ ፍቅር፣ ስለ ሰላም፣ ስለ እኩልነት፣ ስለ ፍትህ፣ ስለ አንድነት፣ የመዝጊያ በሩን የሃገር ፍቅር እያደረገ በርካታ ዜማዎችን ለአድማጮች አድርሷል።
በዚያ አስቸጋሪ በነበረበት ወቅት እንኳን ከተለያዩ አካላትና ግለሰቦች በሚደርስበት ዛቻና ማስፈራሪያዎች ሳይሸበር እራሱን ከጥበብ ስር ደብቆ ድንቅ የሆኑ የጥበብ ስራዎችን ለማበርከት ችሏል። ሁሌም በየትኛውም ጊዜና ሰዓት፣ እንዲሁም ሁኔታ ውስጥ ስለተሰጠው ድንቅ ተሰጥኦና ያለምንም ስስት እራሱን አሳልፎ ስለ ሰጠለት አላማው ወደ ኋላ ብሎ ነገር አይወድም። የፖለቲካው ዳፋ ሙዚቀኞችን ጨምሮ በርካታ የጥበብ ሰዎችን እንደ ጎርፍ በሚጠርግበት አስቸጋሪ ጊዜያት ውስጥ ለዘሪሁን ወዳጆ ከስራዎቹ ማግስት እንደ ሽልማት የሚበረከትለት እስርና እንግልት ነበር። የቁሳቁስና የዝነኝነት አባዜ ለማያናውዘውና ለአላማው በጀግንነት መቆም ለሚያስደስተው ዘሪሁንም በስራዎቹ መታሰር ጭንቁ አልነበረም።
ይልቁንስ ፈተናዎቹን ሁሉ ለስኬቶቹ እንደ መሰላል እየተጠቀማቸው በድል ለማለፍ ችሏል። በማራኪ ዜማዎቹ፣ በተስረቅራቂ ድምጹና ስሜትን በሚቀሰቅሱ ግጥሞቹ ሙዚቃውን እያዋዛ በነጻነትና በእኩልነት ሰገነት ላይ ከመቆሙም በላይ ብዙዎች የእርሱን መንገድ እንዲከተሉም አርአያነቱን አሳይቷል። ለስራዎቹ አድናቂዎችን ከመሰብሰብ ይልቅ የእርሱን ፈለግ የሚከተሉ እውነተኛ ባለ ራዕዮችን ማፍራት ለውስጡ እርካታን፣ለልቡም ደስታን ይፈጥርለታል።
ዘሪሁን ወዳጆ ለረዥም ዘመናት ከገጠመው የህመም ስንክሳር ጋር እየታገለ ቢኖርም አንድም ቀን ግን ደከመኝ ብሎ ከሙዚቃ ሕይወቱ ተነጥሎ እረፍት ለማድረግ አልፈቀደም ነበር። ከጥቂት አመታት በፊት ከሀገሩ ኢትዮጵያ በመውጣት ለብዙ ዘመናት በጉጉት ሲጠባበቁት የነበሩትን አድናቂዎቹን ለማግኘትና የሙዚቃ ስራዎቹን ለማቅረብ የመድረክ ላይ ኮንሰርት ተሰናድቶለት ወደ አሜሪካን ሀገር አቀና። ቀድሞውኑ በስራዎቹ አብዝተው የሚወዱት የዋሽንግተን ዲሲ እና የሚኒሶታ አድናቂዎቹ ከመድረኩ በኋላ አሁን አሁን ወደ ኢትዮጵያ መመለስ የለብህም ከዚሁ ሆነህ የተሻለ ህክምና ማግኘት አለብህ ቢሉትም፣ እርሱ ግን ወይ ፍንክች ከሀገሬ ወጥቼስ ለመኖር አይቻለኝም አለ።
ከሰው ሀገር ሕይወት የሀገሬ ሞት ይሻለኛል ሲል ተመልሶ ወደ ኢትዮጵያ መጣ። ወደ ሀገሩ ለመመለስ ሲያስብ ዘሪሁን አንዳች ነገር አልነበረውም። ከዚያ ሀገር ለመኖር ቢፈቅድ ኖሮ ምናልባትም የተደላደለና ምቹ የሆነ ኑሮ ለመኖር ይችል ነበር። እርሱ ግን በችግር አለንጋ እየተገረፈም ቢሆን ለመኖር የሀገሩን አፈርና ውሃ መርጦ መጣ። ለስራዎቹ እንጂ ምድራዊ ኑሮን አደላድሎ ለመኖር የማያስብ ስለነበረ የእኔ የሚለው ምንም አይነት ነገር አነበረውም።
በአንድ ወቅት ግን ይህን የተመለከቱ በሀገር ውስጥና በውጭ የሚኖሩ አድናቂዎቹ ገንዘብ በማሰባሰብ፣ የሚኖርበትን ማረፊያ ቤት ሰሩለት። እርሱ በጥበብ ውስጥ ስለ እነርሱ እየኖረ መሆኑን ስለተረዱ ያላቸውን እያሰባሰቡም በተለያዩ ጊዜያት ህክምና እንዲያገኝ በማድረግ አለኝታነታቸውን አሳይተውታል። ከህመሙ ስቃይ ይልቅ በዚህ የሚያገኘው ደስታ እያሸነፈ፣ እድሜውን አርዝሞለት በተስፋ ብርሃን እየታጀበ ለሌላ ስራ የተዘጋጀባቸው ጊዜያት ጥቂት የሚባሉ አልነበሩም።
ከህመሙ ለመዳንና በሕይወት ሰንብቶ እልፍ የዘመን ስጦታዎችን ለማበርከት ሲውተረተር ቆይቶ በመጨረሻ ግን እጁን ሰጠ፡፡ ከጥቂት ጊዜያት በፊት ህክምና ለማድረግ ወደ ህንድ ሀገር አቅንቶ በጤና የመመለስን ተስፋ ከውስጡ ቢሞላም የማይሆን ሆነና ያልታሰበው ሆነ፡፡ ባሳለፍነው እሁድ ሚያዚያ 14 ቀን 2015 ዓ.ም አስደንጋጩ ዜና ከየአቅጣጫው መሰማት ጀመረ፡፡ “እውቁ የአፋን ኦሮሞ አቀንቃኝ ዘሪሁን ወዳጆ በህክምና ሲረዳ ቆይቶ በዛሬው ዕለት አረፈ” የሁሉም የኢትዮጵያ ሚዲያዎች ሰበር ዜና ነበር፡፡ ዘሪሁን ወዳጆ ታሞ ከሀገሩ እንደወጣው፣ ድኖ ወደሀገሩ ለመመለስ አልቻለም፡፡
እንኳንስ እሱ አስክሬኑም የሀገሩን አፈር ትናፍቃለችና የሀገሬ አፈር ይብላኝ እንዳለው አስክሬኑ ከህንድ ወደ ኢትየጵያ በአውሮፕላን ተጭኖ ሚያዚያ 17 ቀን 2015 ዓ.ም በአዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ጣቢያ ገባ፡፡ ብዙዎች ከስፈራው ተገኝተው በእንባ እየተራጩ አቀባበልም አደረጉለት፡፡ እርሱ ግን ከእንግዲህ ከሞት ወዲያ ከሞት ሸሽቶ ከጥበብ መዝገብ ውስጥ ስሙን ሸሽጎታልና ሁሌም እንደነበር ይኖራል፡፡
ሚያዚያ 18 ቀን 2015 ዓ.ም ስጋው ከአፈር በታች ስሙም ከመቃብር በላይ ሆነ፡፡ ዘመን ተሻጋሪ የሆነ የጥበብን ማዕድ በሙዚቃ ውስጥ ሰንጎ፣ ለትውልዱ ሁሉ ይሆን ዘንድ ዘሪሁን ወዳጆ ‘ኢያሴ’ በሚለው ስሙ ከመቃብር በላይ አስቀምጦታል። ትውልዱም ይህንን ስጦታውን ተቃምሶ እያጣጣመ የእውነትም ከመቃብር በላይ ስለመኖሩ ይመሰክራል። ሞት ስጋና ደምን ቢነጥቅም በጥበብ ሙዳይ ውስጥ ያለችን እንቁ የመስረቅ ኃይል ግን የለውም። ዳሩ እኛ ባንወድም ለስጋው የዘላለም እረፍት ሆኗልና ነብሱም እንደ አበባ በአጸደ ገነቱ ትፍካ!
ሙሉጌታ ብርሃኑ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 22/2015