ጦርነት ሕይወት ነጣቂ፣ አካል የሚያጎድል በመሆኑም አሸማቃቂ ነው። ሰው በተፈጥሮ የተሰጠውን በነጻነት የመኖር ሕልውና የሚቀማም ጭምር ነው። በጦርነት ለዓመታት የዘለቁ ሀገራት መጨረሻቸው አምራቹን ዜጋ ማጣት፣ አካለ ጎዶሎነትን መታቀፍ፣ መሰረተ ልማታቸው መውደም ብሎም ዜጎቻቸው ከሀገር መሰደድ በመሆኑ ተንኮታኩተው ይቀራሉ። ከዚያ በኋላ ምናልባትም ሀገራቱ ቀድሞ የነበራቸውን ስልጣኔያቸውና ኢኮኖሚያቸው ላቅ ያለ ስለመሆኑ የሚዘክራቸው ቢኖር ታሪክ ብቻ ይሆናል።
በዛሬው ጽሑፌ በመግቢያዬ የጦርነትን አስከፊ ገጽታ የማስቀደሜ ምስጢር በጎረቤታችን ሱዳን በተቀሰቀሰው የእርስ በእርስ ግጭት ሳቢያ ነው። ምክንያቱም እንዲያው ደፍሬ ‹‹አፍንጫ ሲመታ…›› የሚለውን የአበውን አባባል ሙሉ ለሙሉ መጠቀም ባልሻም መቼም ሱዳን የኢትዮጵያ ጎረቤት ሀገር ናትና ጉዳዩ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ይነካናል በሚል ነው። በክፉም ሆነ በደግ በርካታ ጉዳዮችን ከዚህች ጎረቤት ሀገር ጋር ኢትዮጵያ መልካም ጎረቤት በመሆን አሳልፋለች፤ ዛሬም እያሳለፈች ትገኛለች።
ብዙዎቻችን እንደምንረዳው የጎረቤት ሰላም ውሎ ማደር ለራስም ትልቅ እፎይታ ነው፤ የጎረቤት ከልክ በላይ ፈንጠዚያም ሆነ ከልክ ያለፈ ሀዘን በራስ ላይ የሚያመጣው ጉዳት የሚናቅም እንዲያው በምን አገባኝ የሚተውም አይደለም፤ አይሆንምም። እኛ ሰላም ለመሆናችን የራሳችን መልካምነትና ብቃት ብቻ በቂ አይሆንም፤ አሊያም እኛ ሰላም ለመሆናችን መልካም ባህሪያችን ወይም ደግሞ ዳጎስ ያለ ኢኮኖሚያችንም የሚያስመካ መሆን አይችልም።
ሰላም የጋራ ነው፤ በተለይ ደግሞ በሰፈር አጥር የሚሊዮን ጎረቤትም ሆነ በርቀት ድንበር ከሚሊዮን ጎረቤት ሀገር ጋር በሰላም መኖሩ የግዴታ ውዴታም ጭምር ነው። ጎረቤት ሀገራት በሌላ በራሳቸው ምክንያት የተነሳ በሚመጣባቸው ግጭት ሰላም አለማደር የእኛም ትልቅ ራስ ምታት ስለመሆኑ አጠያያቂ አይደለም።
ታድያ የኢትዮጵያ ጎረቤት የሆነችው ሱዳን ሰላም ከራቃት ሳምንት አልፏታል። ይህች ጎረቤት ሀገር ሱዳን እርስ በእርስ በሚባሉ ልጆቿ ድርጊት ታማለች፤ ቆስላለችም። የልጆቿ የጀነራል አል-ቡርሃንና የጀነራል ዳጋሎ ውዝግብ ሀገሪቱን እያመሰቃቀላት ይገኛል። ግጭቱ በቦንብ ድብደባና በአየር ጥቃትም የታገዘ በመሆኑ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ለኅልፈተ ሕይወት ተዳርገዋል፤ በሺዎች የሚቆጠሩ ደግሞ ቆስለዋል።
ሀገሪቱ እየታመሰች ያለችው በሱዳን መደበኛ ጦር አባላት እና አር.ኤስ.ኤፍ በሚል ምህጻረ ቃል በሚጠራ በፈጥኖ ደራሽ ልዩ ኃይል አባላት መካከል እንደሆነ ይታወቃል። እነዚህ ሁለት ኃይሎች የየራሳቸውን ፍላጎት ለማድረስ ሲሉ እያካሄዱ ያለው ጦርነት ሀገሪቱን እያወደማት ነው። በቀናት ውስጥ እንኳ ምን ያህል ውድመት እንደደረሰ በተለያዩ የሚዲያ አውታሮች እየተነገሩ በመሆኑ ጉዳቱ ምን ያህል የከፋ ስለመሆኑ ከብዙዎቻችን የተሰወረ አይደለም።
በሀገሪቱ እየተካሄደ ያለው ጦርነት ደግሞ በሱዳን ውስጥ ብቻ የሚያበቃ አይሆንም። በጣም ከቀላሉ ብንነሳ እንኳ በሀገሪቱ እየተካሄደ ባለው የእርስ በእርስ ግጭት ሰላም በመታጣቱና መሰረተ ልማት በመውደሙ ዜጎች ተሰደው ወደኢትዮጵያ ሊመጡ ይችላሉ። ቀጣናው በራሱ የራሱ ራስምታት ያለበትና የማይበርድ በመሆኑ ይኸኛው ሲታከልበት በዳር ሆነው ምስራቅ አፍሪካ ሰላም ውሎ እንዳያድር የሚቋምጡ እንደ እድል ሊቆጥሩት ይችላሉና በኢትዮጵያ በኩል ጉዳዩን በትኩረት መከታተሉ ተገቢ ነው።
እርግጥ ነው የእኛን ዜጎች ለመታደግ እየተደረገ ያለ ጥረት መኖሩን በሱዳን የኢትዮጵያ ኤምባሲ ጉዳዩን እየተከታተለውና ለኢትዮጵያውያኑም መልዕክት እያደረሰ ስለመሆኑ ተሰምቷል። ኢትዮጵያውያኑም ከዋና ከተማዋ ካርቱም ለመውጣት በመፈለጋቸው ለኤምባሲያችን ጥሪ ማቅረባቸውም ይታወቃል። ምክንያቱም ጥይት መርጦ አይመታም፤ ቦንብም መርጦ አይደበድብምና ጦርነቱ ከራሷ ከሱዳን ዜጎች አልፎ የእኛን ጨምሮ ሌሎችንም ዜጎች የሚያጠቃ እንደሚሆን ይታወቃል። ይህ በእንዲህ ከቀጠለ ደግሞ ስደተኛውም ድንበር ተሻግሮ ላለመምጣቱ ማረጋጋጫ የለምና በኢትዮጵያ መንግስት በኩል ቀድሞ ለመጠንቅ ከወዲሁ ብልህ መሆንን ይጠይቃል።
ጦርነቱን ተከትሎም የኢትዮጵያን ሰላም መሆን የማይወዱ አካላት ከወዲሁ የየራሳቸውን ሴራ ለመሸረብ እንቀልፍ አጥተው ማደር ጀምረዋል፤ ጅማሬያቸውም አንድ ያለው የሐሰት ፕሮፓጋንዳ ከመንዛት ነው። በተለይም በሱዳን ከተቀሰቀሰው ግጭት ጀርባ ኢትዮጵያም አለችበት መባሉ አንዱ የ‹‹በሬ ወለደ›› ትርክት በመሆኑ እንዲህ አይነቱን ቅጥፈት በመንዛት የኢትዮጵያን ስም ለማጠልሸት ብዙ ርቀት መሄድ አይቻልም። አጅሪትም ብትሆን ‹‹ለጋራ ወታደራዊ ልምምድ›› እያለች በሱዳን ሰማይ ላይ አየሩን የምትቀዝፈው ለአዝርዕት የሚሆን ማሳ ለማበጃጀት እንዳልሆነ ልብ ይሏል።
እንደ እኔ መረዳት የአፍሪካ ኅብረት ለ‹‹አፍሪካዊ ችግር አፍሪካዊ መፍትሔ›› የሚለውን ግሩም መርህ ዛሬም ቀድሞ መተግበር ይኖርበታል እላለሁ። በጎረቤታችን ሀገር ሱዳን፣ የፖለቲካ ትርፍና ጦርነቱን እንዲራዘም በማድረግ ዳጎስ ያለ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ለማግኘት ሲሉ ረጃጅም እጆች ገብተው ችግሩ እጅ እጅ ከማለቱ በፊት የእኛ የኢትዮጵያውያን ግጭት የተፈታበትን ዘዴ በመጠቀምም ሆነ ሌሎች ስልቶችን በማከል የአህጉራችንን ጉዳት ከወዲሁ ለማከም መድኃኒቱ ላይ በመወያየት ፈውሱን ማፋጠን ተገቢ ነው።
በአፋጣኝም ችግሩ የበለጠ እንዲፋፋምና እንዲጋጋል የተዘረጉ እጆችን መቀልበስ ያሻል፤ መፍትሔ አመንጪ በመምሰል በሱዳን ሁለት ተፋላሚ ኃይሎች ጎን የተኮለኮሉትን አስመሳይ ኃይሎችን የተራበ ማንነት ማምከን ከአፍሪካውያኑ ይጠበቃል። ሁሌም የሚዋጥ ከርፋፋ አካል ካገኙ ለመሰልቀጥ ዝግጁ ሆነው የሚጠባበቁ ላንቃዎችን ኢትዮጵያም ከወዲሁ የሚዘጉበትን መንገድ ልትከተል ግድ ይላታልና ሁለመናዋ አይንና ጆሮ ሊሆን ይገባል።
በእርግጥም የኢትዮጵያ መንግስት በጉዳዩ ዙሪያ ለሚናፈሱ አሉባልታዎችም ሆነ ሌሎች ወሬዎች ዙሪያ የሚሰጠው የራሱ የሆነ መረጃ እንዳለው ይታወቃል፤ ሁኔታዎችንም በትኩረት እንደሚከታተልም እሙን ነው። እንዲያም ሆኖ ቀጣናውን ለማተራመስ ምቹ አጋጣሚን የሚጠብቁ መኖራቸው የማይታበል ሐቅ እንደመሆኑ ከወዲሁ የኢትዮጵያ መንግስት ተገቢውን ሁሉ እንደሚያደርግ አምናለሁ። ከአሁን ቀደምም ያለው ልምድ የሚያመላክተው በቀጣናው ሰላም በማስጠበቅ ረገድ ግንባር ቀደም መሆኑ ነውና የሰላም ተምሳሌትነቱ የማይነጥፍ እንደሆነም እተማመናለሁ። ለሰው ልጆች ሁሉ ሰላም ይሁን!!!
ወጋሶ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 22ቀን 2015 ዓ.ም