ኢትዮጵያ ለኢንቨስትመንት የሚውል ሰፊ የተፈጥሮ ሀብት፣ እንግዳ ተቀባይ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሕዝብ፣ ለኢንቨስትመንት አመች የሆነ የአየር ንብረት ያላት ጥንታዊ/ታሪካዊ ሀገር ነች። በአሁኑ ወቅትም በአፍሪካ ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት ከሚያስመዘግቡ እና ለኢንቨስትመንት ምቹ ከሆኑ አገራት መካከል በግንባር ቀደምትነት ተጠቃሽ ነች።
መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፤ ሀገሪቱ በግብርና፣ በማዕድን፣ በቱሪዝም፣ በማኑፋክቸሪንግ ፣ በኢነርጂ እና በአይሲቲ ዘርፎች ኢንቨስት ለሚያደርጉ ባለሀብቶች ትልቅ አቅም አላት ፤ በመሰረተ ልማት እና በኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታ እያሳየችው ያለው እመርታም እነዚህን የኢንቨስትመንት አማራጮች በቀላሉ ወደ ስራ ለማስገባት እንደሚያስችሉ ይታመናል።
ሀገሪቱ በግብርናው ዘርፍ ከፍተኛ አቅም እንዳላት መረጃዎች ያመለክታሉ፤ በአፍሪካ ቀንድ በከብት ሀብቷ በመሪነት ደረጃ ላይ የምትገኝ ፤ የሚታረስ ሰፊ መሬት ባለቤት ነች። በዓለም አቀፍ ደረጃ ተፈላጊነት ያላቸውን አትክልትና ፍራፍሬዎች በጥራትና በስፋት ማምረት የሚያስችል ተስማሚ የአየር ንብረትም አላት።
በማዕድን ዘርፉም በጥናት የተረጋገጡ ብዛት ያላቸው የተለያዩ ማእድኖች በስፋት የሚገኙባት ሀገር ነች። ከወርቅ ጀምሮ ከፍተኛ የነዳጅ ክምችት በሀገሪቱ ይገኛል። በአሁኑ ወቅት ማዕድናት በዓለም አቀፍ ገበያ ካላቸው ተፈላጊነት አንጻር በዘርፉ ኢንቨስት ማድረግ አስተማማኝ ተጠቃሚነትን እውን ማድረግ የሚያስችል እንደሆነ ይታመናል።
በቱሪዝም ዘርፉም፤ ሀገሪቱ ጥንታዊ ከመሆኗ አኳያ ብዛት ያላቸው የቱሪዝም መስህቦች ባለቤት ነች። በአነስተኛ ኢንቨስትመንት ወደ ከፍተኛ የቱሪስት መስህብነት ሊቀየሩ የሚችሉ የተፈጥሮ አካባቢዎችም አሏት። አዲስ አበባ የአፍሪካውያን ዋና ከተማ ፤ ዓለም አቀፍ የዲፕሎማቲክ ማእከል መሆኗም በተለይ በሆቴሎች እና ቱሪዝም ዘርፍ መሰማራት ለሚፈልጉ ባለሀብቶች አዋጭ የኢንቨስትመንት አማራጭ ነው።
በማኑፋክቸሪንግ ፣ በኢነርጂ እና በአይሲቲ ዘርፎችም ያለው የኢንቨስትመንት እድል ሰፊ እና አዋጭ ነው። በተለይም በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ያለው ሠፊ ዕድል ፣ ከውጭ በስፋት የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ከማምረት ጀምሮ፤ የግብርና ምርቶች ላይ በአነስተኛ ኢንቨስትመንት እሴቶችን በመጨመር ተጠቃሚነትን አስተማማኝ የሚያደርግ ነው።
መንግስት እነዚህን ሀገራዊ የኢንቨስትመንት አቅሞች ወደ ተጨባጭ ሀብት በመለወጥ ቀጣይነት ያለውና የተረጋጋ ማክሮ ኢኮኖሚ ለመገንባት የሚያስችል የሃገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ተግባራዊ አድርጓል ፤ማሻሻያው ሀገር በአስቸጋሪ ወቅት በነበረችባቸው ባለፉት አምስት ዓመታት ስኬታማ ውጤቶችን በማስመዝገብ ሀገርን ከጥፋት መታደግ ችሏል። ሀገራዊ ኢኮኖሚው ተስፋ ሰጪ እንዲሆን በማድረግ የውጪ ኢንቨስትመንትን ፍሰት እንዲጨምር ረድቷል።
በተለይም ብዛት ያላቸው የውጪ ሀገር ባለሀብቶች በሀገሪቱ ኢንቨስት እንዲያደርጉ ፖሊሲዎችንና መመሪያዎችን ቀጣይነት ባለው ሁኔታ ከማሻሻል ጀምሮ፤ የተለያዩ የኢንቨስትመንት ማበረታቻዎችን በመስጠት እነዚህን ሀገራዊ አቅሞች ወደ ስራ በመቀየር የሀገሪቱን ነገዎች ብሩህ ለማድረግ እያሳየ ያለው ቁርጠኝነት ፤ የሀገሪቱን ነገዎች ለተሻለ ኢንቨስትመንት የሚያዘጋጁ ናቸው።
በአሁኑ ወቅት በሀገሪቱ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን በመንግስት ደረጃ እየተደረገ ያለው ጥረት እና እየተመዘገበ ያለው ስኬትም፤የኢንቨስትመንት አቅሞችን በተጨባጭ ወደ ተግባር በመለወጥ ዘላቂነት ያለው ልማት በማስፈን ሀገሪቱ ተስፋ አድርጋ ለጀመረችው የብልጽግና ጉዞ ስኬት ትልቅ አቅም እንደሚሆን ይታመናል።
ይህን ትልቅ አቅም አሁነኛ የተሻለ ዓለም አቀፍ የኢንቨስትመንት እድል በመሆኑ፤ የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች ፣ ዲያስፖራዎችና የውጪ ኢንቨስተሮች የዕድሉ ተጠቃሚ በመሆን ራሳቸውን በመጥቀም ለሀገር ባለውለታ መሆን ወቅቱ የሚፈልገው እውነታ ነው!
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 22ቀን 2015 ዓ.ም