አንድ ማለዳ ነው፤ ከእነአቶ ሸለመ ማስረሻ ቤት እልልታ ተሰማ። እልልል….. እልልልልል……. እልልልልል…ገና ጎህ ሲቀድ መንደሯን የሚያናጋ እልልታ መሰማቱ ያልተለመደ ነበር፡፡ ሁሉም ከየቤቱ ብቅ ብቅ እያለ የሆነውን ለማየትና ለመሰማት ይጣደፍ ጀመር። ለዘመናት የልጅ ጠረን ሸቶበት የማያውቀው የአቶ ሸለመ ቤት የበኩር ልጅ የሆነችው ጽጌ ሸለመ ያለምንም ጭንቀት በቀላል ምጥ ከእናቷ ማህፀን ወጥታ መሬት ስትረግጥ ነበር፡፡ ጎረቤቶች ደስታቸውን ለመግለፅ እልልታቸውን አቀለጡት። የፅጌ ወላጆች ለአመታት ልጅ ለማግኘት ያልሄዱበት ሀኪም ቤት ያልረገጡት ደጀ ሰላም አልነበረም፡፡ ይህችን ብርቅዬ የፈጣሪ ስጦታቸውን ተቀብለው በደስታ ማሳደግ ጀመሩ።
ፅጌ ለቤቱ ብቸኛ ልጅ ነበረች። የብርቅ ልጅ፤ አፈር አይንካሽ ተብላ ያደገችው ልጅ ሁሉንም ማግኘት መብቷ እንደሆነ እስኪሰማት ድረስ የጠየቀችው ሁሉ ተደርጎላት አደገች። ምንም እንኳን ገቢያቸው አነስተኛ ከሆኑ ቤተሰቦች ቤት ብትወለድም ከአካባቢው ልጆች በተለይ ተሞላቃ ቀብጣ አደገች።
ልጅቱ ዕድሜዋ እየጨመረ ሲሄድ፤ የምትፈልጋቸው ነገሮች በወላጆቿ አቅም የማይሆን በመሆኑ ያቺ አፈር አይንካሽ ተብላ ያደገችው ልጅ ጭቅጭቅ ጀመረች። ፍላጎቷ ሳይገደብ ያደገችው ወጣት በልክ ስትባል እምቢኝ አሻፈረኝ በማለት ከቤት ወጥታ ውሎ አዳሯ ሁሉ ከምታውቃቸው ከዱርዬዎች እና ከሱሰኞች ጋር ሆነ። ወጣቷ ለለመደቻቸው አጉል ሱሶች ገንዘብ ያስገኛል ብላ ያሰበችውን ነገር በሙሉ መሞከር ጀመረች።
በእዚህ ተግባሯም እንደዛ በደስታ እያነቡ የተቀበሏትን ቤተሰቦቿን በኀዘን አስነባቻቸው። በእልልታ ያወጁትን የልጅ ማግኘትን ብስራት፤ አንገት በመድፋት እንዲታዩ አደረገቻቸው። የለየላት ሌባ ሆነች። ነጋ ጠባ ስሞታ ቤት ድረስ ይመጣ ጀመር። ይህ ባህሪዋ አድጎ ከወንጀለኞች ቡድን ጋር አስተዋወቃት። በዚህም የበርካቶችን ንብረት ቀምታ ላልተገደበው ፍላጎቷ ማስፈፀሚያ አደረገችው። የበርካቶችን የወዝ ውጤት ምንም ሳትሳቀቅ የራሷ አደረገች። ለእዚህ እኩይ ተግባሯ ሌላ ምቹ ሁኔታ ተፈጠረላት። በአገሪቱ የነበረውን ወቅታዊ ሁኔታ ግምት ውስጥ በማስገባት ለዘረፋ የሚሆን ምቹ ሁኔታ ታመቻች ጀመር።
የደከሙበትን የተነጠቁት አባት
አቶ ፍፁም ሐጎስ ገብሩ ይባላሉ። ከተወለዱባት ትግራይ ክልል ልዩ ስሙ ሙጉላት ከተባለ አካባቢ የወጡት በልጅነት ዕድሜያቸው ነው። ገና በአፍላው የወጣትነት ዘመናቸው፤ በአስመራ ከተማ ከጉልበት ሥራ ጀምረው የተለያዩ ሥራዎችን ሠርተዋል። አስመራ በጋራ ተከራይተው በኖሩባት ክፍል ውስጥ የሠሩበትን ገንዘብ ማስቀመጫ ቦታ ስላልነበራቸው ልብሳቸው ውስጥ ሰፍተው በመያዝ ገንዘብ አጠራቀመው ነበር፡፡ የያዙትን ይዘው ከአስመራ ወደ አዲስ አበባ መጡ።
ያየኔው ወጣት ፍፁም ያጠራቀሟትን ጥሪት ይዘው ሥራ እስከሚለምዱ ድረስ አንድ ልብስ ሰፊ ዘመዳቸው ጋር ተጠግተው ይሠሩ ጀመር። አገሩንም ሥራውንም በደንብ ሲለምዱ የስፌት መኪና ገዝተው ልብስ ጥገና ጀመሩ። ከጥገና ተነሰተው ዘመናዊ የሴቶች አልባሳትን አሳምሮ የሚሰፋ ስመጥር ልብስ ሰፊ ሆኑ።
እኚህ ሰው ሀብትን በሥራ ካገኙ በኋላ ሚስት አገብተው ልጆች ወልደው አሁን እስከ የደረሱበት የእርጅና ዕድሜ ድረስ አዲስ አበባ ሲኖሩ፤ የጀመሩትን ሥራ አስፋፍተው ሀብት ለማፍራት በቅተዋል። በደስታና በሰላም ይኖሩ የነበሩት አባት፤ በአገራችን በተከሰተው የእርስ በእርስ ጦርነት ወቅት ሥራ ቀዝቅዞ ቤት መወላቸው ያስከፋቸው ጀመር።
ብዙም ወደ ሱቅ መለስ ቀለሰ ባይሉም ከመወለድ ያለፈ ብዙም የማያሰታወሷት የትወልድ ቀዬቸው ጦርነት ላይ መሆኗ እንቅልፍ ነስቷቸዋል። በወቅቱ የሚሰሙት የተለያዩ አስፈሪ አሉባልታዎችም ዘመናቸውን ሙሉ ከኖሩባት አዲስ አበባ እንዳያስወጣቸው ሰግተዋል።
በዚህ መሀል ግን አንድ ምሽት በርከት ያሉ ግለሰቦች ወደ መኖሪያ ቤታቸው መጥተው ቤቱን ለፍተሻ እንደሚፈልጉት ነገሯቸው። በወቅቱ የፖሊስ የደንብ ልብስ የለበሱ ሰዎች አብረው በመኖራቸው ሕጋዊ የሆነ ፍተሻ እንጂ ሌላ አላማ አንግበው የመጡ አልመሰላቸውም ነበር። ለፍተሻ ሲጠየቁ ያለምንም ማንገራገር ቤታቸውን ከፍተው እንዲገቡ ጋበዟቸው።
ሰዎቹ ዘጠኝ የአዲስ አበባ ፖሊስ ደንብ ልብስን የለበሱና ሁለት የሲቪል ሰው አለባበስ የለበሱ በድምሩ አስራ ኣንድ ሰዎች ነበሩ፡፡ አቶ ፍፁም ሐጎስ ገብሩ ቤት ሲገቡ ‹‹ፖሊሶች ነን ተጠቁመን ነው፤ ቤቱን እንፈትሻለን›› ብለው ገብተው ዝርፊያ ፈፅሙ። የሕግ ሰው መስለው በሕገ ወጥነት ከልጅነት እስከ እውቀት ያጠራቀሙትን ጥሪያቸውን ዘርፈው አመለጡ።
የተቀነባበረው ዘረፋ
ነገሩ እንዲህ ነው፤ ጽጌ ሸለመ የተባለችው ወጣት ለሕገ ወጥ ሥራዋ የሚሆኗትን ሰዎች አደራጅታ መንቀሳቀሰ ከጀመረች ሰነባብታለች። በዚህ ተግባሯ ጥሩ ገቢ በማግኘቷ፤ የተጠናና የማያስጠረጥሩ የዘራፋ ሁኔታዎችን ለማካሄድ አስፈላጊ ዕቃዎችን አሟልታለች። ወቅቱ የፈጠረውን ሁኔታ እንደ ጥሩ አጋጣሚ በመጠቀም እውነት የሚመሰል ሁኔታን አቀናብራ፤ ታሪክ ፈጥራ ግብረ አበሮቿን አደራጀች።
ከዚህ በኋላ በጦር መሣሪያ በታገዘና ወንጀልን ለመፈጸም ከተደራጀ የወንበዴ ቡድን ጋር በመሆን በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ወረዳ 10 ዞን 5 መንገድ 9 ተብሎ ከሚጠራው አካባቢ ካልተያዙ 4 ክላሽንኮቭ መሣሪያ ከያዙ 9 የአዲስ አበባ ፖሊስ ደንብ ልብስን የለበሱና 2 የሲቪል ሰው አለባበስ የለበሱ በድምሩ ከሌሎች 11 ሰዎች ጋር ወደ አቶ ፍፁም ሐጎስ ገብሩ ቤት በመሄድ «ፖሊሶች ነን ተጠቁመን ነው ቤቱን እንፈትሻለን» በማለት ወደ ውስጥ ገቡ።
ወንበዴዎቹ የግል ተበዳይ ላይ መሣሪያ በመደቀን «ዶላር አምጣ» በማለትና የተበዳይን ቤት በመበርበር ተከሳሿ በቁጥር ሁለት የሆኑ ዴል ላፕቶፕ ኮምፒዩተሮችን ይዛው በነበረው ቦርሳ ስትከት፣ ሌሎች ግብረ-አበሮቿ ባለ 18 ካራት 23 ግራም ወርቅ እና ስልክ በድምሩ 125 ሺ ብር የሚያወጡ ንብረቶችን በመውሰድ ተሰወሩ።
ፖሊስ ስለሆነው ነገር ጥቆማ ከደረሰው በኋላ በሕጋዊነት አምሳል የተፈፀመ ወንጀል መሆኑን ተረድቶ ጉዳዩን ይከታተል ጀመር።
የፖሊስ ምርመራ
ፖሊስ የግል ተበዳዮችን አነጋግሮ መረጃ በመውሰድ ጉዳዩን መከታተል ይጀምራል። ወንጀሉ የተፈፀመው በተጠና መልኩ መሆኑ ደግሞ ምርመራውን ፈታኝ አድርጎታል። ወንጀለኞቹ የፖሊስ ደንብ ልብስ በመልበስ መሣሪያ ይዘው ቤት እንፈትሻለን በማለት፤ ከባድ ውንብድና ወንጀል ከፈጸሙት ሰዎች መካከል ጽጌ ሸለመን በቁጥጥር ስር አውሏት።
የእሷ መያዝም ሌሎቹ እንዲያዙ መንገድ የጠረገ ሲሆን፤ አንዱ አንዱ ላይ እየጠቆመ አስራ አንድ ሰዎች በቁጥጥር ስር በመዋላቸው፤ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፍትህ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ የልዩ ልዩ ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ ክስ እንዲመሰርት ማስረጃዎችን አጠናቀሮ ላከ።
የዐቃቤ ሕግ የክስ መዝገብ እንደሚያስረዳው ጽጌ ሸለመ የተባለችው ተከሳሽ በጦር መሣሪያ በታገዘና ወንጀልን ለመፈጸም ከተደራጀ የወንበዴ ቡድን ጋር በመሆን ታኅሣሥ 22 ቀን 2014 ዓ.ም ወንጀል ፈፅመዋል፡፡ በለሚኩራ ክፍለ ከተማ ወረዳ 10 ዞን 5 መንገድ 9 ተብሎ ከሚጠራው አካባቢ ካልተያዙ 4 ክላሽንኮቭ መሣሪያ ከያዙ 9 የአዲስ አበባ ፖሊስ ደንብ ልብስን የለበሱና 2 የሲቪል ሰው አለባበስ የለበሱ በድምሩ ከሌሎች 11 ሰዎች ጋር በመሆን የግል ተበዳይ ቤት ገብተዋል፡፡ በግል ተበዳይ አቶ ፍፁም ሐጎስ ገብሩ ቤት በመሄድ «ፖሊሶች ነን ተጠቁመን ነው ቤቱን እንፈትሻለን» በማለት፤ ከግብረ-አበሯ ጋር በመሆን ተበዳይን «ዶላር አምጣ» በማለት የያዙትን መሳሪያ ተበዳይ ላይ በመደገን አንገቱን አንቀው በመያዝ ተከሳሿና ሌሎች ያልተያዙት የወንጀሉ ፈፃሚዎች የተበዳይን ቤት በመበርበር ተከሳሿ በቁጥር ሁለት የሆኑ ዴል ላፕቶፕ ኮምፒዩተሮችን ይዛው በነበረው ቦርሳ ስትከት፣ ሌሎች ግብረ-አበሮቿ ባለ 18 ካራት 23 ግራም ወርቅ እና ስልክ በድምሩ 125 ሺ ብር የሚያወጡ ንብረቶችን በመውሰድ የተሰወሩ በመሆኑ፤ ተከሳሿ በዋና ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ በመሆን በፈፀመችው የከባድ ውንብድና ወንጀል ዐቃቤ ሕግ ክስ መስርቶባታል፡፡
ውሳኔ
በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የልደታ ምድብ 1ኛ ሰው ግድያና ከባድ ውንብድና ወንጀል ችሎት የቀረበችው ተከሳሽ የተከሰሰችበት ክስ በችሎት ተነቦላት የወንጀል ድርጊቱን አልፈፀምኩም ብላለች፡፡ ዐቃቤ ሕግም ማስረጃዎችን በማቅረብ በበቂ ሁኔታ ወንጀሉን ስለመፈጸሟ በማስረዳቱ ፍርድ ቤቱ እንድትከላከል በሰጠው ብይን መሠረት ቀጠሮ ቢሰጣትም ቀጠሮዋን አክብራ ችሎት ያልቀረበች፣ የመከላከያ ምስክርም ያላቀረበች በመሆኑ ተከሳሽ የመከላከል መብቷን መጠቀም እንዳልፈለገች ተቆጥሮ ትከላከል በተባለችበት ድንጋጌ ስር የጥፋተኝነት ፍርድ በመስጠት በሌለችበት በ12 ዓመት እስራት እንድትቀጣ፣ እንዲሁም ለ3 ዓመት ከሕዝባዊ መብቷ እንድትታገድ ሲል ወስኖበታል፡፡
ማስታወሻ
ተከሳሽ በሕግ በተፈቀደላት መብት መሠረት በዋስትና ወጥታ ክርክር ስታደርግ ብትቆይም የዐቃቤ ሕግ ማስረጃ ከተሰማ በኋላ እንደሚፈረድባት ስታውቅ የመከላከያ ማስረጃ እንድታቀርብ በተቀጠረ ቀጠሮ ሳትገኝ የቀረች በመሆኑ ፍርድ ቤቱ የመከላከል መብቷን አልፎ የጥፋተኝነት ፍርድ በመስጠት በ12 ዓመት እስራት እንድትቀጣ የወሰነባት ሲሆን የወንጀል ሕጉ ስለ ቅጣት ይርጋ በሚደነግገው አንቀጽ 224 ስር ከ10 ዓመት በላይ ለሆነ ነፃነትን ለሚያሳጣ ወንጀል የቅጣት ይርጋው 20 ዓመት በመሆኑ ተከሳሿ/ፍርደኛዋ የቅጣት ፍርዱ ተፈጻሚ ከሚደረግበት የካቲት 22/2015 ዓ.ም ጀምሮ ባሉ 20 ዓመታት ውስጥ በተገኘች በማንኛውም ጊዜ ቅጣቱ የሚፈጸምባት ይሆናል። በመሆኑም ተከሳሽ 20 ዓመታትን ከፍትህ በመሸሽ በድብብቆሽ በመሳቀቅ ከማሳለፍ ቀርባ ተገቢውን ቅጣት እንድትቀበል ጥሪ እያቀረብን ተከሳሽን በማንኛውም አጋጣሚ ያየ ወይም የሚያውቅ ለቦሌ ክፍለ-ከተማ ፖሊስ ወይም በአቅራቢያው ለሚገኝ ፖሊስ እንዲያሳውቅ በማክበር እንጠይቃለን።
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 21/2015