
በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ በድምቀት የሚከበረው የትንሳኤ በዓል ዋዜማ ላይ እንገኛለን:: የትንሳኤ በዓል ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ምድር ወርዶ ሕዝቡን ያስተማረበት እና በተግባር ፍቅሩን የገለጸበት ሲሆን ለሰው ልጆች ያሳየውን ፍቅር ራሱን በመስጠት ጭምር ዝቅ በማለት በመስቀል ላይ በመዋል ገልፀዋል:: በመስቀል ላይ ውሎም በሶስተኛው ቀን ሞትን ድል አድርጎ ተነስቷል::
ይህ የትንሳኤ በዓልም በተለያዩ ሃይማኖታዊ ክንዋኔዎች በእምነት ተቋማት ክርስቶስ ለሰው ልጆች ያሳየውን ፍቅርና ትህትና እንዲኖሩት በማስተማር ይከበራል:: በዛሬው የትንሣዔ በዓል ዋዜማችን በዚሁ የዘመን እንግዳ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል የስብከተ ወንጌል ክፍል አገልግሎት አካል የሆኑትን መጋቢ ሀዲስ አባ ወልደገብርኤል ገብረእየሱስ ቆሞስ በዓሉን አስመልክቶ የሚከበርበትን መንገድ እና ሰዎች ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰው ልጆች በተግባር ያሳየውን ፍቅር እንዴት ሊተግብሩት ይገባል በሚል ያደረግነውን ቆይታ እንደሚከተለው አሰናድተንላችኋል:: መልካም ንባብ::
አዲስ ዘመን፡- የትንሣዔ በዓል ሲታሰብ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ትልቅ ስፍራ የሚሰጠውን ዐብይ ጾም እናገኛለን:: ይህ የጾም ወቅት ምን ለየት ያደርገዋል?
መጋቢ ሀዲስ አባ ወልደገብርኤል፡- የዐብይ ጾም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ውስጥ ካሉ ሰባት አጽዋማት በስርዓትም፣ በትውፊትም በአምልኮትም ከጸኑትና አባቶችና ሊቃውንት ከደነገጉት አንዱ ነው:: ዐብይ የተባለበት ምክንያት ከሁሉ ትልቅ ማለት ሲሆን ጌታችንና መድሀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የጾመው ነው:: የጾመበትም ቦታ በእደ ዩሀንስ ፈለገ ዮርዳኖስ ከተጠመቀ በኋላ የማቲዎስ ወንጌል ምዕራፍ አራት ላይ ‹‹ ወምዝ ወሰዶ መንፈስ ውስተ ክዳም ወጾመ ኣርባ መዓልተ ወኣርባ ለሊት ›› በማለት ኢየሱስ ክርስቶስ ዐርባ ቀን እና ዐርባ ለሊት የጾመበትን ያስቀምጣል:: ይህ የዐብይ ጾም ስምንት ሳምንታት ያሉት ሲሆን ከመጀመርያው ሳምንት ዘወረደ፣ ቅድስት፣ ምኩራብ፣ መጻጉ፣ ገብርኄር፣ ኒቆዲሞስ፣ ሆሳዕና በመባል እስከ ትንሳኤው እለት ድረስ የየራሳቸው ስያሜ እና የሚያስተላልፉት መልዕክት አላቸው::
አዲስ ዘመን፡- የዐብይ ጾም ተጀምሮ እስከሚጠናቀቅ ድረስ እያንዳንዱ ሳምንታት የየራሳቸው ስያሜና መልዕክት አላቸው :: በመጨረሻው ሳምንት ሰሙነ ሕማማት ላይ እያንዳንዱ ቀናት እንዲሁ ያላቸው ስያሜ መነሻ እና ትርጓሜያቸው ምን ይመስላል?
መጋቢ ሀዲስ አባ ወልደገብርኤል፡- ባለፈው ታሪክ ስንመለከተው ሰሙነ ሕማማትና ዐብይ ጾም የሶስት ዓመት ከሶስት ወር ርቀት አላቸው:: ነገር ግን ሊቃውንት ይህንን በጋራ በማምጣት እንዲታሰብ አድርገውታል:: ሰሙነ ሕማማት ጌታችንና መድሀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ 40 ቀን እና 40 ለሊት ከጾመ በኋላ ወደእስራኤል ምድር ገብቶ ሶስት ዓመት ከሶስት ወር ደቀ መዛሙርቱን ካስተማረ፣ የተለያዩ ተዐምራትን ካደረገ በኋላ ለተከታዮቹ እና ደቀመዝሙሮቹ ‹‹ ናሁ ነኣርግ ውስተ እየሩሳሌም ›› ወደእየሩሳሌም እንወጣለን ‹‹ወይሕዝዎ ለወልደጓለ እምሕያው›› በአይሁድ እንደሚያዝ እና እንደሚሰቀል አስቀድሞ በተናገረው ትንቢት መሰረት የተፈጸመ ነው::
የሆሳዕና እለት ከሕማማት ቀደም ብሎ የሚመጣ ሲሆን በማቲዎስ ምዕራፍ 21 ከቁጥር አንድ ጀምሮ እንደተጻፈው ‹‹ጌታችን እና መድሀኒታችን ኢየሱስ ክርሰቶስ አህያዋን ከውርንጭላዋ ታገኛላችሁ፤ ፈትታችሁ አምጡልኝ፤ ለምን ትፈታላችሁ? ብለው ቢጠይቋችሁ፤ ለጌታ ያስፈልጉታል ብላችሁ መልሱላቸው ››በማለት አዘዛቸው:: የሆሳዕና ሚስጥር አምስት ሺህ 500 ዘመን በዲያብሎስ እስራት ውስጥ የነበሩ ምዕመናን እንዲፈቱ ፍቱና አምጡልኝ የሚል የራሱ ሚስጥራዊ ትርጉምን የያዘ ነው::
ጌታችንም በአህያዋ ላይ ሆኖ በሚሄድበት ወቅት አዋቂዎች ሕጻናት አመሰገኑት:: በሚያልፍበት መንገድም ልብሳቸውን አነጠፉለት:: ይህንን ከመስማት ባለፈ ምስጢሩን በመረዳት ምዕመናን ልቦናቸው ለእግዚአብሄር ቅርብ ማድረግ እንዳለብን የሚናገርም ጭምር ነው:: በዚህ እለት ሕጻናትም ጭምር ሆሳዕና በአርያም እያሉ ያመሰግኑት ነበር:: አይሁድም የተከተለውን የሕዝብ ብዛት ባዩ ጊዜ ቁጣቸው በረታ በዚህም በሀሰት ምስክር በመወንጀል እንስቀለው ብለው ተማከሩ::
ሰሞነ ሕማማትን የምናስታውሰው ከዚህ በኋላ ባሉ በተደረጉ ክስተቶች ነው:: ሰኞ በለሰ መርገም ዕለት ሲባል ፍሬ ፈልጎ የሄደባትና በለስ ባጣ ጊዜ ከእንግዲህ ፍሬ አይገኝብሽ ብሎ ረገማት:: ይህም በበለሷ የ5500 ዘመን መርገመ ስጋ መርገመ ነፍስን አስወገደ ዳግም ሀጥያትን ቦታ እንዳያገኝ አደረገ:: አድማ የጀመሩበት ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለመግደል የተማከሩበት እና ይህም ምክራቸው የፈረሰበት ነው::
ሰኞ ዕለት መርገመ በለስ በመባልም ይጠራል፣ ዕለተ ማክሰኞ የጥያቄ ቀን ተብሎ ተሰይሟል፤ በዚህ ቀን ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቤተመቅደስ ሲሸጡ ሲለውጡ የነበሩትን በሚያስወጣ ጊዜ በማን ስልጣን ይህን ታደርጋለህ በማለት በፈሪሳውያን ተጠይቋልና የጥያቄ ቀን ይባላል:: በድጋሚ አይሁድ ጌታችንን ለመያዝ የመከሩበት እና ይህ ምክራቸው የፈረሰበት ነው:: ረቡዕ ዕለት ምክረ አይሁድ ተብሎ የሚጠራበት ሲሆን አይሁድ ሊቀ ካህናትና ጸሀፍት ጌታን እንዴት መያዝ እንዳለባቸው የመከሩበትና ውሳኔ ያሳለፉት ቀን በመሆኑ ምክረ አይሁድ ይባላል:: በዕለተ ሐሙስ ጌታችንና መድሀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከመያዙ በፊት የጌታ እራት ተብሎ የሚጠራውን ምሽት ላይ ከሐዋርያቱ ጋር በመሆን ‹‹ ነገ በመልክተ መስቀል የሚቆረሰው ስጋዬ ይህ ነው እንክሙ ብልኡ፤ የሚጠጣውንም ጽዋ በማንሳት እንካችሁ ንስኡ ስትዩ ነገ ለብዙዎች ቤዛ የሚፈሰው ደሜ ይህ ነው›› ብሎ ሰጣቸው፤ ይህም በማቲዎስ ወንጌል ምዕራፍ 26 ከቁጥር 26 ላይ ተቀምጧል::
ከዚህ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ይሁዳ አራት ጭፍራዎችን አስከትሎ መጣ፤ ጌታችንም ‹‹ከመሳሪቁኑ ተሓዚኑ መጻይክሙ›› ይህን ያህል ዓመት ከእናንተ ጋር ስኖር በምኩራብ ሳስተምር እንደ ሌባ ልትይዙኝ መጣችሁን ብሎ ጠይቋቸዋል:: በዚህም ሰዓት ይሁዳ ጌታችንን ሰላም ላንተ ይሁን ብሎ ቀርቦ በመሳም እንዲይዙት ምልክት በመስጠት አሳልፎ ሰጣቸው:: ይህም በሰሞነ ሕማማት ከሚደረጉት ተግባራት ውስጥ ሰላም አለመባባል አንዱ መነሻ ነው::
ከዚህ በኋላ አይሁድ ጌታችንን ያዙት አስቀድሞ ባስተማራቸው ትምህርቶች በማንሳት ጌታችን ላይ ይሳለቁበት ጀመር ለሊቱንም ከጲላጦስ ወደቀያፋ እያመላለሱ እንዲፈረድበት፣ እንዲሰቃይ አደረጉ:: ወደአደባባይ ባቀረቡት ጊዜም በሀሰት መሰከሩበት:: ንጉስ ጲላጦስ ምንም እንኳን አንድም ሀጥያት አላገኘሁበትም ከደሙ ንጹ ነኝ ብሎ እጁን ታጥቦ አሳልፎ ሰጣቸው:: ይህ በዕለተ ዓርብ የሆነ ሲሆን እንዲሰቀል ከተፈረደበት ከሶስት ሰዓት እስከ ስድስት ሰዓት አንገላቱትም በስድስት ሰዓትም በመስቀል ላይ ሰቀሉት:: ያን ጊዜ ቀኑ ጨለመ ከዋክብት ረገፉ፣ ጨረቃም ደም መሰለች:: ቤተክርስቲያንም ከሰኞ እስከ ዓርብ ያለውን ይህንን መከራ የተቀበለበትን እና ሞትን ድል አድርጎ የተነሳበትን በተለያዩ የጸሎት ጊዜያት እና ተግባራት ጋር በማጣመር ምዕመናን ያሳልፋሉ::
አዲስ ዘመን፡- በሕማማት ወቅት በጸሎተ ሐሙስ ጌታችን የደቀመዝሙሮቹን እግር ዝቅ ብሎ በማጠብ ያሳየው ትህትና ምዕመኑ ከዚህ በምን መልኩ ሊማር ይገባል?
መጋቢ ሀዲስ አባ ወልደገብርኤል፡- ‹‹ ኮኖሙ አበ ውእመ፤ እናትም አባትም ሆናቸው ወመሃሮሙ ጥበብ፤ ጥበብንም አስተማራቸው፣ እግረ አርዳዩ ወሀጸበ፤ የደቀመዛሙርቱን እግር አጠበ ሲል ዩሀንስ ምዕራፍ 13 ላይ ተገልጹዋል::›› የደቀመዛሙርቱን እግር ዝቅ ብሎ ካጠባቸው በኋላም በመካከላቸው ሆኖ ርእክሙኑ ዘገበርክልሙ፤ ያደረግሁላችሁን አስተዋላችሁ እንዘኣነ ሊቅክሙ ወእግዚክሙ፤ እኔ መምህራችሁ ጌታችሁ ስሆን እንዲህ አደረግሁኝ አንቲ እ-ሙሂ ግበሩ ለሐዊክሙ እናንተም ለወንድሞቻችሁ የበላይ ስትሆኑ ለታናናሾቻችሁ ይህንን አድርጉ::
ጸሎተ ሐሙስ ሕጽበተ እግር የሚባል ሲሆን ጌታችን ዝቅ ብሎ እግርን በማጠብ ያሳየውን ትህትና በዚህ በእኛ ዘመን በቤተክርስቲያናችን ቅዱስ ፓትሪያርኩ በጸሎተ ሀሙስ መጥተው የቅዱስ ጳጳሳቱን እግር ዝቅ ብለው ያጥባሉ:: ከኦሪት ጀምሮ እንደሚደረገውም በእኛም ባሕልም እንዲሁ እንግዳ ሲመጣ ዝቅ ብሎ እግርን ማጠብ ትህትና ማሳየት በፍቅር ማስተናገድ የተለመደ ነው:: አሁን ላይ ግን የትህትና ምሳሌያችን የቀረ ይመስላል፤ የትህትና መጓደል ደግሞ እርስ በእርስ እንድንጠፋፋ ያደርጋል::
መጀመርያ ሰውን በሰውነቱ መውደድ፣ ማክበር ክርስቶስ የይሁዳንም እግር ዝቅ ብሎ አጥቧል ወዳጅ ብሎ በመለየት አልያም በጥቅም በመተሳሰር ሳይሆን እንዲሁ ወዷልና ጠላቶቻችሁንም ውደዱ እንደሚል ቃሉ በሰሞነ ሕማማትም ተግባራትም ክርስቶስ ለሰው ልጆች ያሳየው ይህንኑ ነው:: በመሆኑም በጸሎቱ ሐሙስ ጌታችን ያደረገውና ያስተማረውን ትህትናና ፍቅርን፣ ራስን አሳልፎ ለሌሎች መስጠት ነው::
አዲስ ዘመን፡- ከትንሳኤው እለት አስቀድሞ ያለውን በዕለት አርብ (የስቅለተ እለት ጀምሮ እስከ ትንሳኤው እለት ያሉትን ቀናት ቤተክስርቲያኗ በምን መልኩ ታሳልፈዋለች?
መጋቢ ሀዲስ አባ ወልደገብርኤል፡- በዕለተ ዓርብ ጌታችን በሶሰት ሰዓት የተፈረደበት፣ በስድስት ሰዓት በቀራንዮ መስቀል ላይ የዋለበት እንዲሁም በዘጠኝ ሰዓት ነፍሱ ከስጋ የተለየችበት ነው:: በዚህ ቀን ቤተክርስቲያን ምዕመኑ በጾም፣ በጸሎት፣ እንዲሁም በስግደተ የሚያልፍ ሲሆን በእለቱ በክርስቶስ ስቅላት የተፈጸመው በኦሪት የተቀመጡ ሁሉ ይነበባል:: ቤተክርስቲያን ይህን እለት በጊዜው ያለውን የጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስቅለት እንደሆነ አድርጋ ታሳልፈዋለች:: በትንሳኤው እለትም ከምዕመናን
ጋር በመሆን በዓሉን ከነድያን ጋር ታከብረዋለች::
አዲስ ዘመን፡- ጌታችንና መድሀኒታችን ለሰው ልጆች ያለውን ፍቅር የገለጸበት መንገድ እና ትህትና ሰዎች ከዚህ እንዴት ሊማሩ ይችላሉ?
መጋቢ ሀዲስ አባ ወልደገብርኤል፡- በማቲዎስ ወንጌል እንደተጻፈው ሊቃውንት የጌታችንን ደግነት እና ትህትና ሲገልጹት እየገረፉት እንዘይሃምምዎ ኢተቀየመ ትርጓሜውም ሲገርፉት አልተቀየመም ወተለዎም በየዋህ በየዋህነት ተከተላቸው ክፉን በክፉ አትመልሱ እንደተባለው መልካም ማሰብን፣ ክፉ ለሚያስብብንም ጭምር መልካም መመኘትን የሚያስተምር ነው::
ክርስቶስ ራሱን ለሰው ልጆች አሳልፎ እንደሰጠው እኛ ደግሞ ያለንን ለሌሎች ማካፈል ይገባል:: በማቲዎስ ወንጌል ምዕራፍ 25 ከቁጥር 31 ላይ ብራብ አበልታችሁኛል፤ ብጠማ አጠጥታችሁኛል ይላል:: በመሆኑም ካለን ላይ ማካፈል ለተቸገሩ ወገኖች መድረስ የምንሰጠው ባይኖረን እንኳን ከአንደበታችን መልካም ቃላትን በማውጣት ያዘኑ ሰዎችን ማጽናናት ማበርታት ይገባናል::
አዲስ ዘመን፡- የትንሳኤው ዕለት ከተከበረ በኋላ የክርስቶስን መነሳት ቤተክርስቲያን የምታስታውስበት ሥርዓት እንዴት ይገለጻል?
መጋቢ ሀዲስ አባ ወልደገብርኤል፡- የዐብይ ጾምን ካገባደድን በኋላ የክርስቶስን ሕማም በማሰብ የሕማማት ወቅት እንዳበቃ ሞተ ተቀበረ በሶስተኛውም ቀን ሞትን ድል አድርጎ ተነስቷል፡፡ ይህም በጥንት የግዕዝ ቋንቋ ክርስቶስ ተንስኣ ሙታን፤ በዐብይ ኃይል ወስልጣን ፤ አሰሮ ለሰይጣን፤ አጋዕዞ ለአዳም፤ ሰላም እምዝዬሰ፤ ኮነ ፍስሐ ወሰላም በማለት ትንሣዔውን ለ50 ቀን ታበስራለች:: የአይሁድ እንደተራ የያዙት ምራቃቸውን የተፉበት፣ የገረፉት፣ የሰቀሉት የቀበሩት ሞትን ድል አድርጎ ሲነሳ ክርስቶስ ተንስኣ ሙታን – ማንም ይዞ በማያስቀረው ሥልጣኑ ተነሳ፤ የሰው ልጆችን በሀጥያት አስሮ የነበረውን ሰይጣንን አሰረው አዳምንም ከዚህ እስራት ነጻ አወጣው ከእንግዲህ በኋላ ፍጹም ሰላም ለሥጋም ለነፍስም ይሁን እየተባለ ይነገራል::
የጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ትንሳኤ ለሰው ልጆች ሁሉ ነውና እኛም ትንሳኤውን ስናስብ ትንሳኤ ልቡና፣ ትንሳኤ ሕሊናን ማሰብ አለብን:: ሊቃውንቱ እንደሚሉት ሰበሰን ዘክቡር ውዕቱ ዘ-እያይምሮ ሆነ ከመ-እንስሳ ይህም ሰው ክቡር ሳለ አላወቀምና እንደእንስሳ ሆነ የሚል ሲሆን የሰው ልጅ የሰውነት ክብሩን የተፈጠረበትን ዓላማ የሚመጥን ሥራ ለመሥራት በትንሳኤ ልቡና፣ በትንሳኤ ሕሊና ሊነሳ ይገባል::
ይህ ሲሆን ለበጎ ምግባር፣ ለትሩፋት፣ ለመረዳዳት የምንተባበር እንሆናለን:: በትንሳኤውም ፍቅርን፣ የመረዳዳትና አብሮነትን በማሰብ ለጊዜያዊ ጥቅም ሳይሆን ዘላቂ ጥቅምን በማሰብ ትንሳኤው የተራቡትን በማብላት፣ የተጠሙትን በማጠጣት፣ የታመሙትን በመጠየቅ ስናከብረው ያን ጊዜ ትንሳኤው በእኛ ይገለጻል:: በምድርም በሰማይም ዋጋ ይኖረናል::
አዲስ ዘመን፡- ትንሳኤ ከዛሬ ሁለት ሺህ ዓ.ም በፊት ክርስቶስ በምድር ላይ ሳለ ለሰው ልጆች ያሳየውን ፍቅር ባለንበት ዘመን ሰዎች እርስ በእርስ መቻቻል ሲያቅታቸው ይታያል:: ምክንያቱ ምንድ ነው? መፍትሄውስ?
መጋቢ ሀዲስ አባ ወልደገብርኤል፡- እንደ ሀገር በርካታ የምንታወቅባቸው አብሮ የመኖር እሴቶች ያለን ቢሆንም በምንሰማቸው ዜናዎች ይህ ባሕላችንና እሴታችን የቀነሰ ይመስላል:: መጠየቅ ያለብን ትውልዱን ከመተሳሰብ፣ ከፍቅር፣ ከመቻቻልና ከመረዳዳት ከተማ ማነው ያስኮበለለው የሚለው ነው:: ይህን ያደረገ ጠላት ዲብሎስ አብሮነትን የሚጠላ ጠላትን ግን እንዲሁ መዋጋት አይቻልም:: የአባቶቻችን የአብሮነት ፈለግ በመከተል ይህንን ለመወጋት የፍቅር ካምፕ፣ የአብሮነት እና የአንድነት ካምፕ ያስፈልገናል::
ሥልጣኔ በመጠኑ እና እኛነታችንን ማንነታችን፣ ባሕልና ትውፊታችንን ሳይሸረሸር ሲሆን መልካም ነው:: ከአንድነታችን፣ ከአብሮነታችን እንዲሁም ከማንነታችን የሚለየን ከሆነ ግን ይህ ሥልጣኔ ሊባል አይችልም:: ትውልዱ ለወላጅ ማይታዘዝ ከሆነ፤ ወላጅ ደግሞ ለእግዚአብሄር የማይታዘዝ ከሆነ እርስ በእርሳችን የማንስማማ እንሆናለን:: ራስወዳድነት፣ ጊዜያዊ ጥቅምን በማስቀደማችን ለክፉ ሀሳብ የምንጋለጥ ሲሆን፤ ራሱን ለእግዚአብሄር ያላስገዛ ሰው ለመልካም ሀሳብ ተገዢ ሊሆን አይችልም::
በመጽሐፍ ቅዱስ በተለያየ መልኩ እንደተገለጸው ዲያብሎስ በተለያየ መልኩ አለሙን ይዋጋል:: በመሆኑም እንደምዕመን ትንሳኤውን ስናስብ ሰውን ማሰብ ከሰውም አልፎ እንስሳትን ማሰብ ይገባል:: እምነት አለኝ የሚል ግን ሰው ወንድሙን እየገፋ ሌላን ሰው እየጠላ እግዚአብሄርን አውቃለሁ ቢል ሀሰት ነው::
ለዚህ መፍትሄ የሚሆነው ሁሉም የእምነት ተቋማት ምዕመናቸውን ሊመክሩና ሊያስተምሩ ሊቆጣጠሩ ግድ ነው:: የእምነት ተቋማት ምዕመናቸውን በመጠበቅና በማስተማር ካልተወጡ ሕዝብ እንደ ሕዝብ፣ ተቋማት እንደ ተቋም ብሎም ሀገር እንደ ሀገር ለማስቀጠል እንደ ሀይማኖት አባትነቴ ከባድ ይሆናል ብዬ አምናለሁ:: ምክንያቱም ክርስቶስ ሰላምን ፍቅርን የሚሰብክ ዘላለማዊ ትንሳኤውን ስናስብ አጠገባችን ያለውን ወንድማችንን ሳንወድ እንዴት ከሌላው ጋር ሰላም እንሆናለን የሚለውን ራሳችንን መጠየቅ ይገባናል::
አዲስ ዘመን፡- እንደ ሀገር ኢትዮጵያ ከፍተኛ የአማኞች ቁጥር ያለባት መሆኗ ይነገራል:: ነገር ግን ከአማኞች የማይጠበቁ ድርጊቶች ሲፈጸሙ እንመለከታለን:: በዚህ ላይ ምን ይላሉ ?
መጋቢ ሀዲስ አባ ወልደገብርኤል፡- ጥንት ሊቃውንትም ሆኑ ነብያት ስለመጪው ዘመን አስቀድመው ከትበው አስቀምጠዋል:: ይህ ትንቢት አምላካዊ ትንቢት ሲሆን የሃይማኖት አባቶች አስቀድመው በመናገር ያስተምራሉ:: ነገር ግን ይህን ጊዜ ነቅተው መጠበቅን መጠንቀቅን ከትምህርቱ አንዱ ሲሆን የትንቢት መፈጸምያ እንዳንሆን ነቅተን እና ተግተን መጠበቅ እና መጠንቀቅ ያስፈልጋል::
የሰው ልጅ ለፈጠረው አምላኩ ራሱን ካላስገዛ ሰላም ሊሆን አይችልም:: ያለፈው ትውልድ የራሱን ሥራ በጎም ይሁን መጥፎ ሠርቶ አልፏል:: አሁን ያለው ትውልድ ደግሞ የራሱን ሥራ መሥራትና እየተጓዘበት ያለውን መንገድ ማጤን ይገባዋል:: ለዚህም የሃይማኖት ተቋማት ትልቅ ሥራ ይጠበቅባቸዋል:: የሃይማኖት ተቋማት በሕቡዕም ሆነ በገሀድ የምታስተምሩት ትምህርት ተመሳሳይና ሀገርን ትውልድን የሚያንጽ ሊሆን ይገባል:: ከዘረኝነት እና ከጎጠኝነት የጸዳ ሀገርን እንደ ሀገርን ሕዝብን እንደ ሕዝብ የሚያስቀጥል ሊሆን ይገባል:: መንግሥትም ነገሮችን በትዕግስት የማየት፤ እንደዜጋ እንዲሁ መብትና ግዴታችንን ለይተን ማወቅና ለትውልዱ ማሳወቅ ያስፈልጋል::
በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን በማሕበራዊ ሚዲያዎች የሚሰራጩ ሕዝብን ከሕዝብ የሚያጋጩና የሚያለያዩ ርዕስ ይዘው የሚቀርቡትን ርምጃ መውሰድ፣ የማሕበራዊ ሚዲያ ላይም ቁጥጥር ሊደረግባቸው ይገባል:: የማሕበራዊ ሚዲያ ቁጥጥር ካልተደረገበት ሁከት እንዲበዛ የሚያደርግ በመሆኑ ሊታይ ይገባል:: አሁን ላይ የደረስንበት ዘመን ማንኛውም ሰው የራሱን ሀሳብ የሚያንጸባርቅበት፤ እና አስቀድሞ የማይታይበት ነውና የሚተላለፉ አንዳንድ ሀሳቦች ሀገርንም ሕዝብንም ወገንንም ያለውን የእርስ በእርስ አብሮነት እያፈረሰ በመሆኑ ገደብ ሊደረግለት ይገባል:: ሀገር የምትኖረው ሰላም ሲኖር፤ መተባበር ሲኖር ነውና እውቀት አለን የሚሉ በየትኛው ተቋም ያሉ ግለሰቦች ሕዝብን ከሕዝብ የሚነጣጥሉ ንግግራቸው ቢቆጠቡ ሰዎችም ሰከን ቢሉ መልካም ነው::
አዲስ ዘመን ፡- የእምነት ተቋማት መተሳሰብ እና የተቸገሩትን መርዳትን እንደሚገባ ያስተምራሉ:: እርዳታ የሚያስፈልጋቸውን ሰዎች አስመልክቶ የተዛባ አመለካከት ያለ ይመስላል፤ በሃይማኖት ውስጥ መረዳት የሚያስፈልጋቸው ተብለው የተቀመጡት እነማን ናቸው?
መጋቢ ሀዲስ አባ ወልደገብርኤል፡- በቤተክርስቲያን መረዳት የሚያስፈልጋቸው ሰዎች ቅድሚያ የሚሰጣቸው አሉ፤ ተከትለው የሚመጡም አሉ:: ቅድሚያ የሚሰጣቸው አካል ጉዳተኛ የሆኑ ሠርተው ራሳቸውን ለመርዳት የሚቸገሩ በቅድሚያ ተደራሽ የሚደረጉ ሲሆን ይህም ለአንድ ቀን ሳይሆን በቋሚነት መርዳት ይገባል:: ይህንን ስንል የጤና እክል የገጠማቸው ማለት እንደሆነ ሊታሰብ ይገባል:: ሌላው ደግሞ በድንገት እጅ ያጠረው ነገር ግን ቀርቦ ለመጠየቅ ድፍረት ያጣ፤ እክል የገጠመው መርዳት ይገባል:: ከዚህ ውጪ ግን ሙሉ አካልና ጤና ያለውን ግን ቤተክርስቲያንም ትቃወማለች::
በመሆኑም ሙሉ አካል ያለው ይሥራ ዘይፈቅድ ኢትቀነ እይሴሰይ ሊሠራ የማይወድ አይመገብ እንደሚል ቃሉ አሁን ላይ ባይኖርም ሎሌ ከሆነ ወደጌታው ገብቶ ይሥራ፤ ሞግዚትም ከሆነች ወደ እመቤቷ ገብታ ትሥራ ከዚህ የወጣ ግን ሙሉ አካል እያለው ለመሥራት የማይወድ ለቤተክርስቲያንም ለሀገርም ሸክም ነው:: እርዳታም ስናደርግ መልሶ ለሚያደርግልን ሰው ሳይሆን ምንም የሌላቸው ላይ በማተኮር ሊሆን ይገባል:: እንደሀገርም ገጽታችንን ለመገንባት መሥራት ለሚችሉ የሥራ ቦታን ፈጥሮ ማሰማራት ሥራን በመፍጠር ልመናን ማስቀረት ይገባል::
አዲስ ዘመን፡- የትንሳኤ በዓል በተለያዩ ሀገራት በተለያየ መልኩ ይከበራል:: በሀገራችንም ይህ ቀን ሲከበር ምን ለየት ያደርገዋል ?
መጋቢ ሀዲስ አባ ወልደገብርኤል፡- በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የትንሳኤውን በዓል ከዐብይ ጾም ጀምሮ በልዩ ሁኔታ በማሰብ ትንሳኤውን በዚህ መልኩ ታከብረዋለች:: ኢትዮጵያ ከሌሎች ሀገራት ልዩ የሚያደርጋት የራሷ የሆነ ዘመን አቆጣጠር፣ የራሷ ፊደል እንዲሁም ቁጥር ያላት ሀገር ናት:: በዚህም ዓመተ ምሕረት በማለት ዘመንን ትቆጥራለች:: ይህም የምሕረት ዓመት ማለት ሲሆን አዲስ ዓመት በሚውልበት ጊዜ ባህረ ሀሳብ ብለን በምንጠራው የአቆጣጠር ቀመር እያንዳንዱ በዓላት እና አጽዋማት የሚውሉበት ወቅትና ጊዜ አስቀድሞ በባህረ ሀሳብ ይቀመጣል:: በዚህም መሰረት የዘንድሮው የትንሳኤ በዓል ሚያዝያ 12 የሚውል ይሆናል:: የግዕዝ ፊደላችንን ብንመለከት ከጥንት ጀምሮ የምንጠቀምበትና በርካታ ታሪክን የያዘ ሲሆን ዓለም ሁሉ የእኛን ታሪክና ባህል ለማወቅ ለማየት በሚጓጓበት እና ወደ ሀገራችን በሚመጣበት ጊዜ እኛ ግን ያለንን ማቆየት እያቃተን ነው:: ይህንን መጠንቀቅ ይገባናል::
አዲስ ዘመን፡- በመጨረሻም አባታዊና የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክትዎን ያስተላልፉልን፡፡
መጋቢ ሀዲስ አባ ወልደገብርኤል፡- ለመላው የክርስትና እምነት ተከታይ ኢትዮጵያውያን የትንሳኤው በዓል የበረከት፣ የሰላም የሕይወት ትንሳኤ እንዲሆን እመኛለሁ:: የተለያየ የሚገናኝበት፣ የተጣላ የሚታረቅበት፣ የተራበ የሚጠግብበት፣ የታመመ የሚፈወስበት የሰላም በዓል ያድርግልን:: ወ-ኣረቀ ክሌሕዝበ ማዕከሌበ በእኛ መካከል ሆኖ ከአባቱ ጋር አስታረቀን እንደተባለው ትንሳኤው የተለዩትን አንድ የሚያደርግ ነውና በሕሊና የሞትነው እንድንነሳ ለሀገር ፍቅር እድገት ትንሳኤ ሕሊና ልቡና ያስፈልገናል:: ማለትም ሰው ትንሳኤ ስጋ ቢኖረው ነገርን የልቡናና የሕሊና ተነሳሽነት ከሌለው ዋጋ የለውምና ነው::
ሰሚራ በርሀ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሚያዝያ 11 ቀን 2017 ዓ.ም