በማለዳ የገጠር ከተማዋ ላይ ወጣቶች በብዛት ይታያሉ። በርካታ ኮበሌዎችና ኮረዶች የሚበዙባት የአማራ ክልሏ ሲሪንቃ ከተማ። ቆነጃጅቶቹና ጎበዛዝቱ ወላጆቻውን በሥራ ከማገዝ ያለፈ ይህ ነው የሚባል ውጤታማ ሥራ አይሠሩም ነበር። ልባቸው ከሀገር በመውጣት ምኞት ተወጥሮ ትምህርቱም ሥራውም አልያዝ አልጨበጥ ብላቸዋል። ለዚህም ነው ማልደው አደባባይ በመውጣት የደላሎችን ወሬ ማነፍነፍ ምርጫቸው ያደረጉት።
በአካባቢያቸው ሌት ከቀን ሥራ ሳይፈቱ ልብን በሚያሸፈቱ ታሪኮች የሚሞላቸው ደላሎችም በእንፃሩ ሞልተዋል። “እነ እገሌን አታይዋቸውም በሄዱ በዓመታቸው እኮ ነው ለቤተሰቦቻቸው እንዲህ ያደረጉት…. ማነው ስሙ ደግሞ….” በማለት መከራዎች ቢደራረቡባቸውም በለስ ቀንቷቸው የዓረብ ሀገርን መሬት የረገጡት የሀገራቸው ልጆች ተሳክቶላቸው ቤተሰቦቻቸውን ሲደግፉ የሚያሳዩ ምሳሌዎችን በመጥቀስ ይበልጥ መነሳሳታቸው ይጨምሩባቸዋል። ወሬው ጨወታው ሁሉ “አረብ ሀገር ስሄድ….” ብሎ ነው የሚጀመረው።
ከእነዚህ ከሀገር የመውጣት ጉጉት ሰቅዞ ከያዛቸው ወጣቶች መካከል አንዱ ወጣት ተሳክቶለት ጉዞ ጀምሯል። ይህ ወጣት ቤተሰቡንም ሆነ እራሱን የመቀየር ህልምን ይዞ ሀገሩ ቢነሳም ሩቅ አሳቢ ቅርብ አዳሪ ይሉት ነገር ደርሶበታል።
አንደኛው የአጋቾች ሰለባ
ወጣት ወንዴ አድማሱም ውጭ ሀገር ሄዶ ሠርቶ ለመለወጥ ካለው ፍላጎት በውስጣቸው ከሞላው የአካባቢው ነዋሪዎች አንዱ ነው። ወጣቱ የደላሎችን ጉትጎታ ተቀብሎ የአባቱን ጥማድ በሬ አሽጦ ቤተሰቡን ተሰናብቶ ተመርቆ ከቤቱ ወጣ።
ወጣቱ በጥቅምት ወር 2012 ዓ.ም ከሚኖርበት አካባቢ ከአማራ ክልል ሲሪንቃ ከተማ በመነሳት በወልዲያ አድርጎ አፋር ክልል ደረሰ። ከዚያም በእግር አስቸጋሪውን የበረሃ መንገድ ከውሃ ጥምና ከፀሃይ ሀሩር ጋር በመታገል የተወሰነ መንገድ አቋረጡ። በመቀጠል በመኪና በመጓዝ ጂቡቲ ገብቶ በባሕር በጀልባ በመጓዝ የመን ሀገር ደረሰ። ከሁሉም አስከፊው ውሃ ላይ እየሄዱ ውሃ መጠማቱ እንደሆነ የሚናገረው ወጣት ወንዴ ከላይ የፀሀይ ንዳድ በብዛት በአንድ ጀልባ ላይ የተጠቀጠቁትን ወጣቶች ያለርህራሄ ሲቀጠቅጣቸው ከስር ደግሞ የፈላ የጨው ውሃ እየተፈናጠረ ሰውነታቸውን ይልጣቸው ጀመር።
ይህን ሁሉ አልፈው መዳረሻቸው ላይ ከደረሱ በኋላ ያልጠበቁት ፈተና ገጠማቸው። በራሱ ሀገር ቋንቋ የሚናገሩ የእሱ መሳይ ከለር ያላቸው ሰዎች እንደታገቱ ነገሯቸው። ወንዴም ከታጋቾቹ መካከል ነበር። በኋላ አጋቹ ታግቶ 4ሺህ 500 ሪያል አምጣ ካልሆነ በሕይወት አትኖርም አሰቃይቼ እገልሃለሁ በማለት ሲደበድበው ይቆያል።
ወንዴ ግን ምንም ስቃይ ቢበዛበትም ቤተሰቡ ያላቸውን ጥማድ በሬ ሸጠው ለእሱ በመስጠታቸው እነሱን ከማሳቅቅ ብሞት ይሻላል በማለት የተጠየቀውን ገንዘብ ሳይሰጥ ይቀራል።
ሌሎቹ ተበዳዮች
ሻምበል ሁሴን፣ ሁሴን ኢብራሂምና መሀመድ ሁሴን የተባሉ ወጣቶችም ልክ እንደ ወንዴ ውጭ ሀገር ሄዶ ሠርቶ ለመለወጥ ካላቸው ፍላጎት የተነሳ ጀማል ሰኢድ የሚባል ደላላ ጋር ይገናኛሉ። ደላላውም ወጣቶቹ ጉጉት ልባቸውን እንዳነሳሳው ሲያውቅ ወደ ሳዑዲ አረቢያ ለሥራ እልካለሁ በማለት ይነግራቸዋል። ደላላው ወጣቶቹን በአፋር በኩል በየመን በማቋረጥ ሳዑዲ አስገባችኋለሁ በማለት በማሳመን ሳዑዲ አረቢያ ለመሄድ በታህሳስ ወር 2012 ዓ.ም ከሚኖሩበት አካባቢ አማራ ክልል ደቡብ ወሎ ዞን በመነሳት በኮምቦልቻ አድርገው አፋር ክልል ከዚያም በእግር ጉዞ ይጀምራሉ። ከቀናት የእግር ጉዞ በኋላ 8 ቀን የፈጀ የመኪና ጉዞን ያደርጋሉ። ከዛ በጀልባ ወደ የመን ከደረሱ በኋላ አህመድ ሰይድ እና አንዋር በሚባሉ አጋቾች እጅ ላይ ይወድቃሉ::
በኋላም ወጣት ሻምበል ሁሴንን 30 ሺህ ብር አምጣ ብለው በመደብደብና ወደ አባቱ ስልክ በመደወል እኛ በምንሰጥህ የባንክ አካውንት 30 ሺህ ብር የማትልክ ከሆነ ልጅህን በሕይወት አታገኘውም ሲሉት ገንዘቡን በሂሳብ ቁጥሩ ለግብረ-አበሮቻቸው የላከ ሲሆን፣ በተመሳሳይ የግል ተበዳይ ሁሴን ኢብራሂም እና መሀመድ ሁሴንን አግተው 25 ሺህ ብር እንዲያመጡ በማስገደድ እና በመደብደብ እና አግቶ በማቆየት በስተመጨረሻም ወደ አባቶቻቸው ስልክ በመደወል ብሩን አስልከዋል::
የፖሊስ ምርመራ
ይህን እኩይ ተግባራቸውን ያወቀ ፖሊስም ልጆቻችን ታገቱና ጠፉ የሚል ጥቆማን ተከትሎ ምርመራ ይጀምራል። የሰውና የሰነድ ማስረጃን አጠናክሮ የወንጀል ፈፃሚዎቹን ፎቶ በመያዝ ሀገር እስኪገቡ ድረስ ይጠባበቅ ጀመር። መቸም ከሞትና ከሀገር የሚቀር የለምና ሀገራቸው ሲመለሱ አድፍጦ የሚጠባበቀው ፖሊስ በቁጥጥር ስር አውሎ ክስ እንዲመሠርት በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፍትህ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ የተደራጁና ድንበር ተሻጋሪ ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ጄኔራል ዐቃቤ ሕግ አስተላልፎ ይሰጣል።
የክስ አቀራረብ
የዐቃቤ ሕግ የክስ መዝገብ እንደሚያስረዳው 1ኛ መለስ ካህሳይ፣ 2ኛ ሀፍቶም ገ/እየሱስ እና 3ኛ ከማል ይማም የተባሉ ተከሳሾች በ1996 ዓ.ም የወጣውን የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ወንጀል ሕግ አንቀጽ 32/1/ሀ/ እና በሰው መነገድና ሰውን በሕገ-ወጥ መንገድ ድንበር የማሻገር ወንጀልን ለመከታተልና ለመቆጣጠር የወጣ አዋጅ ቁጥር 1178/2012 አንቀጽ 3/1/ ላይ የተመለከተውን በመተላለፍ በዓቃቤ ሕግ 4 ክሶች ቀርቦባቸዋል::
1ኛ ክስ በሶስቱም ተከሳሾች ላይ ሲሆን ተከሳሾች ካልተያዙት ግብረ-አበሮቻቸው ጋር በመሆን ከኢትዮጵያ ክልል ውጪ ሳዑዲ አረቢያ ድንበር ራጓ ተብሎ ከሚጠራው ቦታ ላይ በሕገ-ወጥ መንገድ ሰዎችን ለማዘዋወር በማሰብ የግል ተበዳይ ወንዴ አድማሱ ውጭ ሀገር ሄዶ ሠርቶ ለመለወጥ ካለው ፍላጎት የተነሳ በጥቅምት ወር 2012 ዓ.ም ከሚኖርበት አካባቢ ከአማራ ክልል ሲሪንቃ ከተማ በመነሳት በወልዲያ አድርጎ አፋር ክልል ከዚያም በእግርና በመኪና በመጓዝ ጂቡቲ ገብቶ በባሕር በጀልባ በመጓዝ የመን ሀገር ከደረሰ በኋላ ለጊዜው ያልተያዘው ከንዙ በሚባል አጋች ታግቶ 4ሺህ 500 ሪያል አምጣ ካልሆነ በሕይወት አትኖርም አሰቃይቼ እገልሃለሁ በማለት ሲደበድበው ቢቆይም ተበዳይ የተጠየቀውን ገንዘብ አግኝቶ ሊሰጠው አልቻለም::
በኋላም ለሁለት ሳምንት በእግርና በመኪና ተጉዞ ሳዑዲ ድንበር ራጓ የሚባል ቦታ ለተከሳሾቹ ተላልፎ የተሰጠ ሲሆን ተከሳሾችም ሳዑዲ ላይ የሚኖር የዘመድ ስልክ ስጠን የማትሰጠን ከሆነ አሰቃይተን እንገድልሃለን፣ በሕይወት አትቆይም በማለት እጅና እግሩን በገመድ አስረው በዱላ እና በኤሌክትሪክ ሽቦ እየተፈራረቁ በመግረፍ እንዲሁም የብረት መጥረቢያ፣ ሽጉጥና ጩቤ በማሳየት ልንገድልህ ነው እያሉ ሲያስፈራሩት የነበሩ እና ተበዳይ የታገተበት ራጓ የተባለው ቦታ በተከሳሾቹ አባሪዎች በጦር መሣሪያ የሚጠበቅ፣ በጣም ጠባብ ቦታ ላይ ከመቶ ሰዎች በላይ የሚቆዩበት፣ ሙቀቱ ከፍተኛ የሆነ፣ ሰው በሰው ላይ ተደራርቦ የሚተኛበት እንዲሁም በቂ ምግብና ውሃ በሌለበት ከ2 ወር በላይ አቆዩት::
በኋላም ሳዑዲ አረቢያ የሚኖር ዘመድ ስልክ ቁጥር ባለማግኘቱ ምክንያት በአማራጭ ኢትዮጵያ የሚኖር የቤተሰብ ስልክ ስጠን ሲሉት የወንድሙን ስልክ ሲሰጣቸው ተከሳሾቹም ደውለውለት ወንድምህን አግተነዋል 35 ሺህ ብር ካላስገባህ በሕይወት አታገኘውም እያሉ ሶስቱም ተከሳሾች በተራ እያስጠነቀቁ የነገሩት እና ኢትዮጵያ ውስጥ የሚኖር ሰው አካውንት የሰጡት ሲሆን በአንድ ግለሰብ በተከፈተ የባንክ ሂሳብ ቂጥር 30 ሺህ ብር አስገብቷል:: በመሐል የግል ተበዳይ በሳዑዲ ፖሊሶች በቁጥጥር ስር ውሎ ለ11 ወራት ያህል ከታሰረ በኋላ ወደ መጣበት ሀገር እንዲመለስ ተደርጎ ወደ ኢትዮጵያ የገባ በመሆኑ ተከሳሾች በዋና ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ በመሆን በፈፀሙት በሰው የመነገድ ድርጊት ወንጀል ተከሰዋል::
2ኛ፣ 3ኛ እና 4ኛ ክስ በሶስቱም ተከሳሾች ላይ ሲሆን ተከሳሾች ካልተያዙት ግብረ-አበሮቻቸው ጋር በመሆን ከኢትዮጵያ ክልል ውጪ ሳዑዲ ዓረቢያ ድንበር ራጓ ተብሎ ከሚጠራው ቦታ ላይ በሕገ-ወጥ መንገድ ሰዎችን ለማዘዋወር በማሰብ ሻምበል ሁሴን፣ ሁሴን ኢብራሂምና መሀመድ ሁሴን የተባሉ የግል ተበዳዮችን ውጭ ሀገር ሄዶ ሠርቶ ለመለወጥ ካላቸው ፍላጎት የተነሳ ለጊዜው ካልተያዘው ጀማል ሰኢድ የሚባል ደላላ ጋር ሲነጋገሩ ወደ ሳዑዲ ዓረቢያ ለሥራ እልካለሁ በአፋር በኩል በየመን በማቋረጥ ሳዑዲ አስገባችኋለሁ በማለት በማሳመን ተበዳዮች ሳዑዲ ዓረቢያ ለመሄድ በታህሳስ ወር 2012 ዓ.ም ከሚኖሩበት አካባቢ አማራ ክልል ደቡብ ወሎ ዞን በመነሳት በኮምቦልቻ አድርገው አፋር ክልል ከዚያም በእግርና በመኪና ለ8 ቀን በመጓዝ የመን ከደረሱ በኋላ ለጊዜው ያልተያዙ አህመድ ሰይድ እና አንዋር በሚባሉ አጋቾች ታግተዋል::
በኋላም የግል ተበዳይ ሻምበል ሁሴንን 30 ሺ ብር አምጣ ብለው በመደብደብና ወደ አባቱ ስልክ በመደወል እኛ በምንሰጥህ የባንክ አካውንት 30 ሺህ ብር የማትልክ ከሆነ ልጅህን በሕይወት አታገኘውም ሲሉት ገንዘቡን በሂሳብ ቁጥሩ ለግብረ-አበሮቻቸው የላከ ሲሆን፣ በተመሳሳይ የግል ተበዳይ ሁሴን ኢብራሂምን እና መሀመድ ሁሴንን አግተው 25 ሺህ ብር እንዲያመጡ በማስገደድ እና በመደብደብ እና አግቶ በማቆየት በስተመጨረሻም ወደ አባቶቻቸው ስልክ በመደወል ብሩን አስልከዋል::
በኋላም ሌሎች ከታገቱ ሰዎች ጋር በመኪና ተጭነው ሳዑዲ ድንበር ራጓ የሚባል ቦታ ለተከሳሾች ተላልፈው ከተሰጡ በኋላ የግል ተበዳዮችን እያንዳንዳቸው 35 ሺህ ብር ቤተሰቦቻቸው እንዲከፍሉ በተከሳሾች ትዕዛዝ ሲሰጣቸው የመን ላይ ከፍለናል በማለታቸው አስገድደው በድጋሚ ለማስከፈል እጅና እግራቸውን በገመድ በማሰር በኤሌክትሪክ ገመድ፣ በዱላ እና በእርግጫ እየተፈራረቁ ደብድበው የቤተሰብ ስልክ ተቀብለው በመደወል ልጅህን አግተነዋል ልንገድለው ነው ብር ላክ በማለት በሂሳብ ቁጥርና በእጅ ገንዘብ እንዲሰጣቸው ያደረጉ እና ከላይ አንደኛ ተበዳይ በቆየበት ቦታ እና ሁኔታ ውስጥ ከቆዩ በኋላ ወደ ሀገራቸው የተመለሱ በመሆኑ ተከሳሾች በዋና ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ በመሆን በፈፀሙት በሰው የመነገድ ድርጊት ወንጀል ዐቃቤ ሕግ ክስ መስርቶባቸዋል::
ተከሳሾች የተከሰሱበት ክስ በችሎት ተነቦላቸው የወንጀል ድርጊቱን አልፈፀምንም ብለው ክደው በመከራከራቸው ዐቃቤ ሕግ ማስረጃዎቹን አቅርቦ አሰምቷል:: በዚህም መሠረት ፍርድ ቤቱ ተከሳሾች እንዲከላከሉ ብይን በሰጠው መሠረት ተከሳሾች የመከላከያ ማስረጃ አቅርበው ቢያሰሙም የዐቃቤ ሕግን ማስረጃ ያላስተባበሉ በመሆኑ በ4ቱም ክሶች ጥፋተኛ ናችሁ ብሏቸዋል::
ጉዳዩን የተመለከተው የፌዴራሉ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የልደታ ምድብ 14ኛ ወንጀል ችሎትም ግራ ቀኙን ተመልክቶ ሌሎች አጥፊዎችን ያርማል ያለውን ውሳኔ አስተላልፏል። 1ኛ ተከሳሽን በ20 ዓመት ጽኑ እስራትና በ160 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጣ የተወሰነ ሲሆን 2ኛና 3ኛ ተከሳሾች ደግሞ እያንዳንዳቸው በ18 ዓመት ጽኑ እስራትና በ130 ሺ ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጡ ሲል ወስኖባቸዋል፡፡
አስመረት ብስራት
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሚያዝያ 11 ቀን 2017 ዓ.ም